በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ እንድንኖር የሚሻ ፅንፈኛ ተቋም

                                                       
ራሱን “ሂዩማን ራይትስ ዎች” እያለ የሚጠራው ፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራል ተቋም ከሚያቀነቅነው የርዕዩተ-ዓለም ቀኖና በመነሳት የሀገራችንን ገፅታ ለማበላሸት ያልጣረው ነገር አለ ማለት አይቻልም። ተቋሙ ስለ ኢትዮጵያ አንዳች ጉዳይ ሲሰማ ጉዳዩን ይበልጥ በማስፋትና ውሸትን  በመቀመር ጭምር በሀገራችን ላይ የቅብብሎሽ ዘመቻ ይከፍታል። ከመሰንበቻውም በኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ ድርጊት በሐሰት ቀምሮ በማቅረብ “የኢትዮጵያ አጥኚ” በሚል ስያሜ በተሰኘው ባልደረባው ሚስተር ፍሊክስ ሆርን በተሰኙ ግለሰብ አማካኝነት ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ የተሳሳተ ማብራሪያ ሰጥቷል። በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት የኢሬቻውን ክስተትና ሌሎች በሀገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮችን በውጭ ገለልተኛ አካል እንዲመረመር ያደርግ ዘንድ አጋሩ የሆነው የአውሮፓ ህብረት ጫና እንዲያደርግ ጠይቋል። 
ፅንፈኛው ተቋም በተለይም በኢሬቻው በዓል ላይ የሞቱን ሰዎች ብዛት በሚያስገርም ሁኔታ “ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ፣ ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስና አስለቃሽ ጋዝ አማካኝነት ሞተዋል” በማለት ገልጿል። እንደሚታወቀው ይህ ፅንፈኛ ተቋም እዚህ ሀገር ውስጥ ምንም ዓይነት የስራ መዋቅር የለውም። ተግባሩን ለመከወን መረጃ የሚያጠናቅረው፤ አንድም ሀገራችን በአሸባሪነት ከፈረጀቻቸው ቡድኖች፣ ሁለትም ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ከሚያገኘው የስሚ ስሚ ወሬና አሉባልታ ነው። እናም ከእነዚህ አካላት የሚያገኘውን ቃርሚያ ወሬ በመሰብሰብ ለሪፖርትነት ያውላል፤ በል ሲለውም የራሱን የ“ቢሆን” መላ ምት በመጨመር ልቦለዳዊ ድርሰት ያንበለብላል።
ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው በኢሬቻ በዓል ላይ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 55 ብቻ ናቸው። ይህ የሟቾቹ ቁጥርም ከቢሾፍቱ ሆስፒታል ተረጋግጧል። ሰዎቹ የሞቱትም ፀረ-ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ በመረጋገጣቸውና በናዳ ምክንያት መሆኑንን እንዲሁም ምንም ዓይነት በጥይት ተመትቶ የሞተ ሰው እንደሌለ የሆስፒታሉ ማስረጃ ያስረዳል። እርግጥ የሟቾቹ ቁጥር ቀላል ነው እያልኩ አይደለም። የአንድም ሰው ህይወት ቢሆን ያለአግባብ መጥፋት የለበትም። ያም ሆኖ በወቅቱ እንደ ኢሳት ያሉና በሀገራችን በአሸባሪነት የተፈረጁት ቡድኖች ልሳኖች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቁጥሩን በማጋነን ሲገለፅ ነበር። ፅንፈኛው ተቋምም እንደለመደው የወሰደው ይህንኑ የሽብር ቡድኖችንና የማህበራዊ ሚዲያዎችን ያልተረጋገጠ አሉባልታዊ ወሬ ነው—ለዚህም ነው በሚያስገርም ሁኔታ “የፀጥታ ኃይሎች በተኮሱት ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል” በማለት ለአውሮፓ ህብረት የተሳሳተ ማብራሪያ የሰጠው።
እንደ እውነቱ ከሆነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች”ም ሆነ እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዓይነት አንዳንድ በሰብዓዊ መብት ስም ተጠልለው የስሶተኛው ዓለም ሀገራትን መንግስታት ስምና ዝና ለማጠልሸት ገንዘብ መድበው፣ ‘አጥኚ’ ቀጥረው የሚራኮቱ ተቋማት ድብቅ አጀንዳ ምን እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል። ተቋማቱ በክቡሩ ሰብዓዊ መብት ስም የሚነግዱ የኒዩ- ሊበራሊዝም ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ህልመኞች ናቸው። ድሃ ሀገራት እነሱ በሚፈልጉት መስመር ለመጠምዘዝ ፈቃደኛ መሆን ካልቻሉ፤ ያለ የሌለን የፈጠራ ዘገባ በማጠናቀር ከለጋሽ ሀገራት ጋር ለማላተም ተግተው የሚሰሩ የበጋ ገበሬዎች ናቸው።   
ዳሩ ግን የሚገርመው ነገር እነዚህ ፅንፈኛ ተቋማት በተለያዩ ወቅቶች የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚያደርግ ይግለፁ እንጂ፤ የሚያነሷቸው ጉዳዩች እንዴት እንደተፈጠሩ እንኳን በቅጡ የሚያውቁት ነገር የለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሚያውቁት ነገር፤ ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችንና ሚዲያዎቻቸውን ከፍ ሲልም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ ሀገራትን ትረካ ብሎም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተብዬዎችን ቃርሚያ አሉባልታዎችን ብቻ ነው። 
ያም ሆነ ይህ ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ምንም እንኳን ለአውሮፓ ህብረት የቀረበው የፅንፈኛው ቡድን ማብራሪያ ልብ- ወለዳዊ ትረካ ቢሆንም ቅሉ፤ የተባለውን ጉዳይ አስመልክቶ በተጨባጭ ማሳያዎች ማስደገፍ በተገባው ነበር። ሆኖም ተቋሙ ከልምድ እንደሚታወቀው የመረጃ ምንጮቹን የመጥቀስ ዝንባሌም ይሁን ፍላጎት የለውም። እንዲያው በደፈናው “በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችን ጠይቄ ያገኘሁት ነው አሊያም በስደት ከሚኖሩ የጉዳዩ ሰለባዎች ያጠናቀርኩት ነው” የሚል ፈፅሞ ተዓማኒነት የሌለውን የመረጃ ምንጮቹን ያቀርባል። ይህ ደግሞ በሚጠየቁት ግለሰቦች ፍላጎትና የፖለቲካ አቋም ዝማሜ የሚወሰን መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። በኢሬቻው በዓል ላይ የሞቱን ሰዎች ቁጥር አስመልክቶም “መንግስት ከገለፀው ቁጥር በላይ እንደሞቱ ይገመታል” ከማለት በስተቀር የቢሾፍቱ ሆስፒታል የገለፀውን ቁጥር እንኳን ለመጥቀስ አልፈለገም። ይህም ፅንፈኛው ተቋም ዓላማው ኢትዮጵያን ማጥቃት እንጂ በትክክል የሞቱን ሰዎች ቁጥር ከማወቅ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ያስረዳል።
እርግጥ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሃይቅ ላይ የተፈጠረውን ሁከት ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች አሉ። በእነዚህ ምስሎች ላይ የሚታየው ነገር በወቅቱ በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የተከሰተው መረጋገጥና በመሬት ናዳ ምክንያት ሰዎች ሲሰርጉ ነው። የአየር ኃይል ሄሊኮፍተሮች “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክትን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን ሲበትኑ እንጂ፤ የፀጥታ ፅንፈኛው ተቋም እንዳቀረበው የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በዓሉን ለማክበር በተገኘው ህዝብ ላይ መሳሪያ ሲተኩሱ አይደለም። እነዚህ ሃቆች ለ“ሂዩማን ራይትስ ዎች” ምንም ማለት አይደሉም፤ ሊሰማቸው እንኳን አይፈልግም። ለዚህም ነው—ፅንፈኛው ቡድን በደፈናው በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ግድያ እንደፈፀሙ አድርጎ የሚያወራው።
የፅንፈኛው ተቋም ኢትዮጵያን የመፈረጅ አባዜ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም። ተቋሙ “በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ 80 አካባቢዎች ከመቶ በላይ የሚሆኑ በርካታ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ አድርጌ የኢትዮጵያ መንግስት የፀጥታ ሃይሎች በትንሹ 500 የሚሆኑ ሰልፈኞችን መግደሉንና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩትን ማሰሩን አረጋግጫለሁ” በማለትም ለአውሮፓ ህብረት ገልጿል። እንግዲህ አንድ ዘገባ ልቦለድም ቢሆን እንኳን “መቼት” (መቼ እና የት) ያስፈልገዋል። ሆኖም የተቋሙ ገለፃ መቼና የት እንዲሁም በምን ዓይነት የመገናኛ መንገድ ኢትዮጵያዊያንን እንዳናገረ አይገልፅም። “80 አካባቢዎች” ብሎ የጠቀሳቸውን ቦታዎችንም አይገልፅም። የመረጃውን ትክክለኛነት በምን ዓይነት መንገድ እንዳጣራው ያለው ነገር የለም። 
እርግጥ እንዲህ ዓይነት ጥናት በየትኛውም ዓለም የለም፤ ሊኖርም አይችልም። የተቋሙ “የኢትዮጵያ አጥኚ” ተብለው የተጠቀሱት ግለሰብ በማብራሪያቸው ላይ ይህን መረጃና ማስረጃ ከየትም ሊያመጡት ስለማይችሉ ያሉት ነገር የለም። ይህም “ሂዩማን ራይተስ ዎች” ሀገራችን ላይ ካለው ጥላቻ በመነሳት የሚያቀርበው የልቦለድ ትረካ እንጂ “ጥናት” ሊባል የሚችል አለመሆኑን ያሳያል—እንዲያውም በእኔ እምነት ከሩቅ ሆኖ በነሲብ አንድን ጉዳይ በመግለፅ ሌላን ሀገር ማጥላላት እንጂ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይመስለኝም።  
እርግጥ ፅንፈኛው ተቋም ያሻውን ቢልም ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ፍላጎቱ መጋለጡ የሚቀር አይመስለኝም። በመሰረቱ የአውሮፓ ህብረትም ይሁን ሌሎች የሀገራችን ለጋሽ ተቋማት እጃቸውን ለኢትዮጵያ የዘረጉት በምክናታዊነት መሆኑ ግልፅ ነው። ይህን ሃቅ ራሱ ፅንፈኛው ቡድንም ቢሆን ኢትዮጵያ በሚገባ የሚያውቀው ይመስለኛል። እርግጥ ሀገራችን ድጋፍ  እንደሚያስፈልጋትና እንደሚገባት የዕርዳታ ተቋማት የወሰኑት፤ ተቀማቱ ገንዘባቸውን የትም ለመበተን የሚፈልጉ ስለሆኑ አይመስለኝም— በሀገራችን እየተስተዋለ ባለው ፈርጀ ብዙ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በሚገባ ስለሚያውቁ  እንጂ። 
ሀገራችን ከለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ጋር አብራ የምትሰራው ሀገራቱ ኃላፊነት የሚሰማው ህዝብና መንግስት መኖሩን በወሬ ሳይሆን በተጨባጭ በማረጋገጣቸውም ጭምር መሆኑ አይታበይም። ሀገራችን ከለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርገው ግንኙነት በሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና ተስፋ ያላት መሆኗን ስለሚገነዘቡ ነው። 
እርግጥ ይህ አባባሌ ኢትዮጵያዊያንን የሚያግባባ ሃቅ እንደሚሆን እገምታለሁ። ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን የኢትዮጵያ ወዳጆችና እውነትን መካድ የሚጎረብጣቸው ሁሉ፤ ነገ የተሻለች ሀገር እንደምትኖረን በሚገባ ያውቃሉ። ይህ ብቻም አይደለም። የአውሮፓ ህብትን ጨምሮ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ የተባባሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ …ወዘተ. የመሳሰሉት መንግስታትና ተቋማት፤ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ነን ባዮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራግቡት አሉባልታዊ ወሬ ከእውነት የራቀና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን ስለሚያውቁ እስከዛሬም ቢሆን ከሀገራችን ጋር የሚያደርጉትን የትብብር ስራዎች አላቋረጡም። 
ይህ ዕውነታ ደግሞ የሀገራችን መንግስትና ህዝብ በኃላፊነት ስሜት እየሰሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ የፅንፈኛውን ተቋም ባዶ ማብራሪያ ትክክለኛነትን የሚያሳይ አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአውሮፓ ህብረት የቀረበው ይህ የፅንፈኛው ተቋም አሉባልታ፤ “ሂዩማን ራይትስ ዎች” ዛሬም እንደ ትናንቱ የሁከት ፈጣሪዎች ደቀ-መዝሙርና የእነርሱ ፈጠራ ወሬ አራማጅ ሆኖ፤ ሀገራችን ሰርክ በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ ሆና እንድትኖር የሚሻ መሆኑን ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያረጋገጠ ይመስለኛል።