ሀገራችንና የሶማሊያን ሰላም የማስጠበቅ ሚናዋ

                                             
የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች የዕድገት ተስፋ ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ሂደት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግም የክፍለ-አህጉሩን ህዝቦች ለዘመናት አንገት ሲያስደፋ የኖረውን ድህነት ድል ለመንሳት የቀጣናው ሀገራት ከምንጊዜውም በላይ በጋራ ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ—አካባቢውን ለማመስ ቆርጦ ከተነሳው የኤርትራ መንግስት በስተቀር። እርግጥ የቀጣናውን ያለመረጋጋት ችግር ለመቅረፍና ሰላምን በክፍለ-አህጉሩ ለማስፈን በአካባቢው የሚታየውን የሽብርተኝነት አደጋ ማስወገድ ይገባል። ይህ አደጋ ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ-አህጉሩ አካባቢ ለሚገኙ እንዲሁም ለሌሎች ሰላም ሀገራት ጭምር ምን ያህል አስጊና አስከፊ እንደሆነ በተጨባጭ በዓይናችን እያየን ያለነው ዕውነታ ይመስለኛል። 
ታዲያ እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ የአካባቢያችን ሁኔታ ምን ጊዜም በትኩረት በመከታተል በአንድ በኩል በጎ ተጽዕኖዎችን ለማስፋፋትና ለማጎልበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረቡ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ መሆኑ አያጠያይቅም። በቀጣናችን ካሉት ሀገሮች መካከል ጎረቤት ሀገር የሆነችው ሶማሊያ፤ የአክራሪዎችና የአሸባሪዎች መፍለቂያና መናኸሪያ በመሆን ለአካባቢው ሀገራት በተለይም ለሀገራችን ስጋት ሆና መቆየቷ ከማንም የተሰወረ አይመስለኝም።
ከዚያድባሬ መንግስት ውድቀት በኋላ መንግስት አልባ በነበረችው በያኔዋ ሶማሊያ የመሸጉ የተለያዩ የጦር አበጋዞችና አሸባሪ አክራሪ ቡድኖች፤ የገዛ ሀገራቸውን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ከመንሳት አልፈው፤ የቀጣናውን ሀገራት በሽብር የማመስ ዓላማን አንግበው ሲሯሯጡ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችንና በጎረቤት ሀገሮች ያደረሷቸው የሽብር ጥቃቶች ከበቂ በላይ ማሳያዎች ይመስሉኛል። በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የጅሃድ ጦርነት እስከማወጅ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው—ራሳቸውን “እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” በማለት ሲጠሩ በነበሩ የአክራሪዎች ስብስብና ኋላ ላይም ይህ አክራሪ ኃይል በ1999 ዓ.ም በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ተመትቶ ሲበታተን ርዝራዡን ይዞ በተቋቋመውና ራሱን “ሃረካት አልሸባብ አልኢስላሚያ” ወይም በአጭር መጠሪያው “አልሸባብ” በተሰኘው የሽርብ ቡድን አማካኝነት።   
እርግጥ እዚህ ላይ በማንኛውም ወገን በኩል፤ ‘ሀገራችን በሶማሊያ የመሸጉትን አክራሪ ሃይሎችንና አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት የምትታገለው ለምንድነው?፣ ሰራዊታችንስ “በሶማሊያ አፍሪካ ህብረት ተልዕኮ” (AMISOM) ጥላ ስር ሆኖ እንዲሁም ከሰላም ማስከበር ተልዕኮው ውጪ በድጋፍ ሰጪነት ተሰማርቶ ምን ዓይነት ተግባራትን እያከናወነ ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለነገሩ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ከመከላከያ ሰራዊታችን ህዝባዊ ባህሪ አኳያ ለሀገሪቱና ወንድም ለሆነው ለዚያች ሀገር ህዝብ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለመገንዘብ ያግዛል። ከዚህ ጎን ለጎንም በተለያዮ ወገኖች ሆን ተብለው ወይም ባለማወቅ እየተሰነዘሩት ያሉትን አፍራሽና ከተጨባጭ ዕውነታው ጋር የሚጣረሱ ሃቆችን ለማረም ያስችላል ብዬ አምናለሁ። 
በእኔ እምነት ሀገራችን በሶማሊያ የመሸጉ አክራሪዎችንና አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት የምትታገልበት ምክንያቶች ሁለት ይመስሉኛል። አንደኛው የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለው ሰላምንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገው የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግም ወንድም ከሆነው ከዚያች ሀገር ህዝብ ጋር ያለን በደም የተሳሰረ የማይሻር ግንኙነት ነው። 
ከቀዳሚው ምክንያት ብንነሳ፤ በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በገፅ 83 ላይ ሀገራችን ሶማሊያን አስመልክቶ የምትከተለውን ፖሊሲ አስመልክቶ “…ከሶማሊያ ጋር ያለን ጉርብትና ለልማታችን የተሻለ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችለው በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው። ብጥብጥን፣ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን በመዋጋት በአካባቢያችን ሰላም ሊኖር የሚችለው በዚሁ መስክ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በአጋርነት የሚሰለፍ መንግስት በሶማሊያ ሲቋቋም ነው።…” የሚል የሁለቱን ሀገራት የግንኙት መስመር የሚያሳይ ጉዳይ በግልፅ ተቀምጧል። 
እርግጥም ፖሊሲው እንዳለው፤ ሶማሊያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ከተቻለ የሀገራችን ውሰጥ የተጀመሩት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዳዩች ሳይስተጓጎሉ በሚፈለገው ፍጥነት ሊተገበሩ ይችላሉ። በሌላ አገላለፅ የሶማሊያ ሰላም መሆን ሀገራችን የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድና በስተመጨረሻም ዕውን እንዲሆን ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ይህም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን ለእኛ ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን ፋይዳ በሚገባ የሚያሳይ ይመስለኛል። ለዚህም ነው— ‘የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን የእኛ ሰላም መሆን ነው’ በማለት በተደጋጋሚ የሚገለፀው። እናም ሀገራችን በሶማሊያም ይሁን በማንኛውም ጎረቤት ሀገር ውስጥ የመሸጉ አክራሪዎችንና አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት የምትታገለው ለዚሁ ነው—ጉዳዩ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ ነውና። 
ሀገራችን አክራሪዎችንና አሸባሪዎችን በሶማሊያ ልሳነ-ምድር ላይ በፅናት የምትታገልበትን  ሌላኛውን ምክንያት ስንመለከተውም፤ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ህዝቦች የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነት ያላቸው ከመሆናቸው በላይ፣ እነዚህ ህዝቦች በደም፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሃይማኖት የተሳሰሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። እንደ እውነቱ ከሆነ አንዱ ህዝብ በሌላኛው ውስጥ የህይወት ቁርኝትን ፈጥሯል። ይህ ስር የሰደደ የግንኙነታቸው ትስስርም በየትኛውም ኃይል ሊበጣጠስ የማይችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራቱ ያላቸው የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የሚጋሩት እስከ 1600 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ረጅም ድንበር ለንግድ ግንኙነታቸው አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። ቀደም ባሉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት አልባ በነበረችው በያኔዋ ሶማሊያ፤ ህዝቦቿ በአክራሪ አሸባሪ ቡድኖች ሰላምና መረጋጋት ሲያጡ ከለላቸውና መከታቸው አድርገው የሚመርጧት ኢትዮጵያ መሆኗም የሀገራቱን ጥብቅ የህዝብ-ለህዝብ ቁርኝትን የሚያሳይ ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። 
አዎ! በወቅቱ እንደተመለከትነው ወንድም የሆነው የሶማሊያ ህዝብ በአሸባሪዎች እንግልት ሲደርስበት ሁለተኛው ሀገሩ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ከመሰደድ ውጭ አማራጭ አልነበረውም። ዛሬም ቢሆን አሸባሪው አልሸባብ በተቆጣጣራቸው ጥቂት ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ የዚያች ሀገር ህዝቦች ሀገራችንን እንደ ሌላኛው ሀገራቸው በመቁጠር በስደተኝነት እየተጠለሉባት ነው።ለነገሩ ሁለቱ ህዝቦች የተጋመዱበት ረጅም የወንድማማችነትና የህትማማችነት ሰንሰለት ሁሉን አቀፍ በመሆኑ፤ የትስስራቸውን ደርዝ በዚህ አጭር ፅሑፍ ልዘረዝረው አልችልም—አንዱን ጥሎ ሌላውን ማውሳት የዕውነታውን ፍካት ማደብዘዝ ይሆንብኛልና። ያም ሆኖ ግን ሀገራችን ከምትከተለው የሰላምና በጋራ የመጠቀም ፖሊሲ በተጨማሪ፣ ይህ ጠንካራና ለረጅም ጊዜ የኖረ የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነትም ኢትዮጵያ በሶማሊያ በመሸጉ አክራሪዎችና አሸባሪዎች ላይ ለምትወስደው እርምጃ ተደማሪ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል።
ታዲያ እነዚህን ሀገራዊና ህዝባዊ ምክንያቶችን አንግቦ ወደ ሶማሊያ ያቀናው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከብዙ ትዕግስት በኋላ በ1999 ዓ.ም ወደዚያች ሀገር በማቅናት እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ በነበረው ቆይታ በሀገራችን ላይ ጅሃድ አውጆ የነበረውንና ራሱን “የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” እያለ ይጠራ የነበረውን አክራሪ ቡድንን በሀገሪቱ ህዝብ እየታገዘ በታትኖታል። ከዚያም በኋላ በሀገራችን ላይ ጅሃድን በማወጅ ተጨባጭ አደጋን ደቅኖብን የነበረውን አልሸባብ በማዳከም ዛሬ ለደረሰበት የኪሳራ ደረጃ አብቅቶታል። 
እርግጥ አልሸባብ “ከፍርድ ቤቱ” መበተን በኋላ በዚያች ሀገር የተፈጠረውን የሽግግር መንግስት ለማዳከም መጣሩ አይካድም። ሆኖም የሶማሊያ ሽግግር መንግሰት የኢፌዴሪ መንግስት ዕገዛ እንዲያደርግለት ባደረገው ጥሪ መሰረት፤ መከላከያ ሠራዊታችን ዳግም በ2003 ዓ.ም ወደ ሶማሊያ በመዝለቅ ጅሃድ ያወጀብንን አልሸባብን በማዳከም የሽብር ቡድኑ ራሱን በጥቂት ቦታዎች ውስጥ ብቻ እንዲወስንና በቀቢፀ-ተስፋ የአጥፍቶ መጥፋት ተግባር እንዲወራጭ አድርጎታል። በወቅቱም በሶማሊያ ህዝብ እየታገዘ የሽብር ቡድኑን ለማዳከምና ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ በአንፃራዊ ሰላም እንዲኖር ለሁለት ዓመታት ባደረገው ቆይታ በሶማሊያ ብሎም በቀጣናው ላይ አንዣቦ የነበረውን የስጋት ደመና መግፈፍ ችሏል።
በወርሃ ታህሳስ 2006 ዓ.ም ሰራዊታችን ከሶማሊያ አፍሪካ ህብረት ተልዕኮን (AMISOM) እንዲቀላቀል በቀረበለት ጥሪ መሰረት ከ4400 በላይ የሚሆኑ የሰላም አስከባሪ አባላት ወደ ስፍራው አምርተዋል። እነዚህ ሰላም አስከባሪዎች ከሌሎች የተልዕኮው አባል ሀገራት ሰራዊቶች ጋር በመሆን የተሰጣቸውን ግዳጅ በህዝባዊ መንፈስና በጀግንነት እየተወጡ  ይገኛሉ። በሰላም ማስከበር ተልዕኮው ውስጥ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የሚገኘውና ከባይደዋ እስከ ገርበሃሬ አካባቢ ያለውን ቦታ የሚሸፍነውን ቀጣና-ሶስት (Sector-3) የተሰኘውን እንዲሁም ምስራቅ ሶማሊያንና አካባቢውን የሚያካልለውንና ከበለደወይኒ እስከ ጎራኤ ድረስ ያለውን ቀጣና-አራት (Sector-4) የሚባለውን ስፍራ ይቆጣጠራሉ። በዚህ ተልዕኳቸውም የሰላም ማስከበር ሰራዊቱ አባላት በተረከቧቸው ቀጣናዎች ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር አድርገዋል። ከአሚሶም እና በእርሱ ሰር ካሉ የሠላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር በመጣመር በሶማሊያ የመሸጉ ሽብርተኞችን መደምሰስና ማጥፋት እንዲሁም ከህዝቡ ጋር በመሆን የተረጋጋ የመስተዳድር መዋቅሮችን እንዲፈጠሩ በፅናት ሰርተዋል። በመስራት ላይም ይገኛሉ። በሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ አብዛኛውን ህዝብ ያካተተ ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ምቹ መደላድሎችን በመፍጠር ላይ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡ ራሱን የሚያስተዳድርበትንና የፀጥታ መዋቅሩን በባለቤትነት የሚመራበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማቀላጠፍና በዚህም ለዕርዳታ ሰጪዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የዕለት ደራሽም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ ተግባሮች በተገቢው ሁኔታ እንዲደርሱ የማድረግ ስራዎችን ገቢራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በሶማሊያ ውስጥ ያለው የሀገራችን ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል በሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት አማካኝነት ለሀገራችን በተደረገው ጥሪ መሰረት፤ የዚያችን ሀገር መንግስት የፀጥታ ኃይል የተሻለ ብቃት እንዲኖረው ለማድረግ የማሰልጠን፣ የማደራጀትና የራሱንም አቅም እንዲገነባ የሚያስችሉ ተግባራትን የሚያከናውን ከ“አሚሶም” ውጪ የሆነ ድጋፍ ሰጪ ሰራዊት በዚያች ሀገር ውስጥ ይገኛል—መረጃዎች እንደሚያመለክቱት። ሰራዊቱ መንግስታችን በሚደግፈው ውስን ሀብት እየታገዘ ጉልበቱንና ዕውቀቱን በማስተባበር አንዳንድ ማህበራዊ ተቋማትን ለአካባቢውን ህብረተሰብ የመገንባት ተልዕኮን ጭምር ያነገበ ነው። ይህ ሰራዊት በሶማሊያ ከተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ እጅግ አነስተኛ ነው። ዓላማው የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግስት ሰራዊት አቅም መገንባት በመሆኑም የቁጥሩ ጉዳይ ከግምት ውስጥ የማይገባና የፌዴራላዊ መንግሰቱ ሰራዊት አቅሙን በተሻለ ሁኔታ መገንባቱን ሲያረጋግጥ ወደ ሀገሩ የሚመለስ መሆኑ ይታወቃል። 
ሆኖም አንዳንድ ኃይሎች የአልሸባብን ጊዜያዊ እንቅስቃሴ እያዩ ‘የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሶማሊያ እየወጣ ነው’ በማለት ሲገልፁ ይደመጣል። ይሁንና እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። እርሱም ከሶማሊያ የወጣው ኃይል “በአሚሶም” ስር ያለው የሰላም አስከባሪ ሳይሆን፤ ምናልባትም ሊሆን የሚችለው ቀደም ሲል የጠቀስኩትን የአቅም ግንባታ ስራ ለማከናወን በሀገሪቱ የተገኘው አነስተኛ ቁጥር ሰራዊት ነው—ምክንያቱም እስካሁን ድረስ ተግባሩን እያከነወነ በመሆኑ ነው። ይህ ሰራዊት ወትሮም ቢሆን በጊዜያዊነት አቅምን ለመገንባት እንጂ የሶማሊያን የሰላም ማስከበር ስራ ለማከናወን የተሰለፈ ባለመሆኑ ምናልባት በአንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ከቦታው ወጥቶ ከሆነ ምንም የሚደንቅ ነገር ያለው ይመስለኝም—ሲጀመርም ቦታው ላይ የተገኘው ለተለየ ስራ ነውና።
ያም ሆነ ይህ ግን በእኔ እምነት ቀደም ሲል በጠቀስኳቸውና የኢፌዴሪ መንግስት በሶማሊያም ይሁን በቀጣናው ሀገራት ውስጥ አክራሪዎችንና አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት የሚታገልበት ምክንያት የጠራ ፖሊሲና ህዝባዊ መስመርን ስለሚከተል ነው። ከዚህ በመነሳትም በቀጣናው ውስጥ ያለውን ሰላምን የማስጠበቅ ስራ ለአፍታም ቢሆን የሚተወው ጉዳይ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በአሁኑ ወቅትም ቀጣናዊ ሰላምን ዕውን ለማደረግ ሶማሊያ ውስጥ ካሰማራው ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በተጨማሪ፤ በዳርፉር፣ በአብዬና በቅርቡም በጁባ በርካታ ሰላም አስከባሪ ኃይል አሰልፏል። 
ይህ ይህ የሀገራችን ቀጣናዊ የሰላም ማስከበር ሚናም መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። እናም በሶማሊያም የሚያከናውነው ይህንኑ ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። መከላከያ ሰራዊታችንም በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ በፅናት የሚተገብረውን ህዝባዊነቱን ሰንቆ የሚጓዝ ኃይል በመሆኑ፤ የሶማሊያንም ይሁን የሌላ ሀገር ህዝብን የሰላም ፍላጎት ለአክራሪዎችና ለአሸባሪዎች ኢ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤ የመተው ፍላጎትም ሆነ እምነት የለውም። በመሆኑም በየትኛውም ሚዛን ቢሰፈር የሀገራችንና የሰራዊቷ ሰልፍ ከሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።