በወንጭፍ የሚካሄድ የዘረኝነትና የአክራሪ ሃይማኖተኝነት ፖለቲካ…

ሶሪያ በአለማችን  የጥንት ስልጣኔ  ባለቤት ናቸው ከሚባሉ ጥቂት አገራት መካከል የምትጠቀስ  ናት። ይሁንና ጥንታዊነቷ  ከውድመትና ከምፈራረስ አላዳናትም።  ደማስቆ የአገሪቱ ዋና ከተማ ትሁን እንጂ  አሌፖም ከሶርያ ታላላቅ ከተሞች  መካከል  ከቀዳሚዎቹ ተርታ  የሚታወቅ ነበረች።  ዛሬ ሶሪያ  የውጭ ሃይሎች  መፋለሚያ ለመሆን በቅታለች።   ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወድማለች።  
አማጽያኑ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ አገርን እንታደጋለን፤ የሶሪ መንግስት በስልጣኑ ባልጓል፣  የህዝብ ሮሮ አልተሰማም ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን  በማንሳት ነበር።  በወቅቱም በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችለው ነበር። በአጭር ጊዜም በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠር ችለው ነበር። ይሁንና ነገሮች በታሰቡበት መንገድ መጓዝ አልቻሉም። የህዝቦች ጥያቄ ደም በጠማው ጽንፈኛ ሃይሎች ተነጠቀ። ራሱን አይ ኤስ  የሚጣው ጽንፈኛ የአልቃይዳ ክንፍ አገሪቱን ወደ ደም መራጫናት ቀየራት። አመጻና ሁከት ይህን ያመጣል።   
በአፍሪካም የታጠቁ ጽንፈኛ ሃይሎች ያደረሱት ውድመት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።  የማሊው አንሳርዲን ያደረሰው ጥፋት፣ የናይጄሪያው ቦኮሃራም የፈጸመው በደል እንዲሁም የሶማሊያው አልሸባብ ያደረሰው ውድመትና እልቂት መቼም የሚዘነጋ አይደለም። አንሳርዲን፣ ቦኮሃራምና  አልሸባብ በተከተሉት የተሳሳተ የስልጣን ፍለጋ መንገድ አገራቸውንና ህዝባቸውን ለውድመት ዳርገዋል። በእነዚህ የስልጣን ሱሰኞች    እርምጃ በሺዎች  የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞትና ለአካል መጉደል እንዲሁም በሚሊዮኖች   ለሚቆጠሩ ዜጎቻቸው  ደግሞ ለስደት ዳርገዋቸዋል፡፡  
አንሳርዲን  ለዘብተኛ የመሰሉትን የሃይማኖት  ተከታዮች ጨፍጭፏል፣ የሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ የሆነውና ጥንታዊ የቲንቡክቱ ሥልጣኔን የሚያሳዩ ቅርሶችን እንዳልነበሩ ሆነው አውድሟል፤ ቦኮሃራም ንጹሃንን በቦንብ አጋይቷል፣ በወጣት ልጃገረዶች ይጫወታል፤  አልሸባብ የራሱን ዜጎች እንደእንሰሳ እያጋደመ ያርዳል።   
በሁከትና ብጥብጥ የሚታወቀው አይ ኤስ በሰሜናዊቷ ሀገር ሊቢያም በቀጠለ ፍጅት ትሪፖሊ፣ ቤንጋዚ፣ቱርቡክ እና ሲርትን የመሳሰሉ  ታላላቅ ከተሞች ዘግናኝ ውድመት እያደረሰ ነው፡፡ አማጽያኑ ቆመንለታል የሚሉትን  ህዝብ ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡  በእነዚህ አገሮች ሁሉ የተመለከትነው ስልጣን የጠማው  ቡድን  መቼም ቢሆን ለህዝብና ለአገር ቆሜአለሁ ብሎ መናገር አይችልም፡፡ በየመንም እያየን ያለነው ወድመት ተመሳሳይ ነው። የውጭ ጣልቃ ገብነት በየትኛውም መስፈርት ሰላምና ልማት ሲያመጣ አልተመለከትንም። ግብጽ በኦነግ ተሸፍና በውስጥ ጉዳያችን ሰተት ብላ የገባችው ለኦሮሞና አማራ ህዝቦች አዝና እንዳልሆነ መቼም ኦነግና ግንቦት ሰባት ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም።   
ሶሪያና ማሊ ለዘመናት የገነቡት ብርቅዬ ቅርሶቻቸቸውና  ባህል ወጋቸው በጽንፈኞች ወድሟል። ጥንታዊቷ  አሌፖ ዜጎቿ ከውብ ህንጻዎቿ ጋር ተቀብረዋል፤ ቲምቡክቱ  ጥንታዊ የመቃብር ስፍራዎቿ ወድመዋል።  ዛሬ አለም ጆሮውን እንጂ እጁን አልዘረጋላቸውም።    
የአገራችንንም ሁኔታ አንዳንድ  ነገሮች ማንሳት ፈለግኩ። ግንባታና ልማት እንጂ  ማፍረስና ማውደም ቀላል ነገሮች ናቸው።  የሀገራችን ጥቂት አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች በተቀሰቀሱ አመጾች ዜጎች ለሞት እና ለእንግልት እንዲሀመ ንብረት ውድመት ተዳርጓል፡፡ 
በባሕርዳር እና በጎንደር ብዙ ሺህ ሰዎች የሚተዳደሩባቸው ፋብሪካዎች   ወድመዋል፡፡ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች  በተለይ በፊንፊኔ ዙሪያ  በሰበታ እና በምዕራብ አርሲ አካባቢዎች ትላልቅ ኢንቨስትመንቶችን ጨምሮ  የግለሰቦች እና አነስተኛ ነጋዴዎች ንብረት ወድመዋል፡፡  የሚገርመው  አውዳሚው አካል በባህር ዳርም  ሆነ አርሲ ኔጌሌ ለህዝቡ የውሃ  አገልግሎት የሚሰጥ  ተቋምን ጭምር እንዲወድም አድርጓል፡፡ ስልጣን ናፋቂው አካል  እየተከተለ ያለው የትግል መስመር ውድመት መሆኑን  ይህ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ ነው የኦነግና የግንቦት ሰባት  ህዝባዊነት።  
በሰበታ ከተማ ዙርያ ብቻ በደረሰ ውድመት 40 ሺህ ያህል ሠራተኞች ያስተዳድሩ የነበሩ ፋብሪካዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንዶቹ ላይ የከፋ ጉዳት ደርሷል፡፡ ለወንጂ  ስኳር ፋብሪካ  ሸንኮራ በማቅረብ የሚተዳደሩ የደሃ ገበሬዎች ንብረት የሆነ  በርካታ ሔክታር የደረሰ ሸንኮራ አገዳ በአዋኪዎቹ ተቃጥሏል፡፡  ይህ ሁሉ ውድመት እንግዲህ  ኢህአዴግን ለመጣል ወይም  መንግስትን  ለመቀየር መሆኑ ሲታሰብ እነዚህ ሰዎች ስልጣን ቢይዙ  የትኛውን አገርና የትኛውን ህዝብ ይሆን የሚመሩት። የደሃ አርሶ አደርን ሸንኮራ እንዲቃጠል የሚያደርግ ፖለቲከኛ አገር ለመምራት ያስባል።  
እንዲህ ያለ የህዝብ እልቂትና የንብረት ወድመት   ያስከተለው  ጃዋር  ትግሉ  ውጤታማ እንደሆነ በይፋ ሲናገር  ይደመጣል።  ጃዋር ኦሮሚያን የሚያስተዳድርበትን ቻርተር አርቅቆ አጠናቋል።  ጃዋር በሃሳቡ የኢፌዴሪን መንግስትን አፍርሶታል፣ ኦሮሚያን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ነጥሎታል፣ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ አስቁሞታል። የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጥሎታል። 
ኦነግ ከግብጾች  የተሰጠውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልእኮ አልሳካ አለው እንጂ  የአገራችን ንብረት እንዲወድም፣ የንጹሃን ህይወት እንዲጠፋ፣ የንጹሃን ደም እንዲፈስ፣ የመንግስትና የግለሰብ ንብረት እንዲወድም። የኦሮሞን ሕዝብ በመግደል፣ ንብረቱን በማውደም፣ የስራ እድሉን በማሳጣት፣ መሰረተ ልማቱን በማፈራረስ ለኦሮሞ ህዝብ ቆሜአለሁ ማለት አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ አማራን እየገደሉ ንብረቱን እየዘረፉና እያወደሙ   ለአማራ ህዝብ መቆም አይቻልም፡፡  ለኦሮሞ ሕዝብ የቆመ አካል የኦሮሞን በህልና ወግ ያከብራል እንጂ በክብረ በዓል ላይ የኦሮሞን ህይወት አያጠፋም። ኦነግ ግን በተግባር ያሳየው ይህን አሰቃቂ ድርጊት ነው። የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት በአመታዊ ክብረበዓል ላይ ህይወታቸው አልፏል። 
እነጃዋር  በሚያራምዱት  የዘርና የሃይማኖት   ፖለቲካ  አገር ሊገነባ አይችልም። ህዝቡን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍለውታል። አቶ ጃዋር ከዚህ ቀደም  የሃይማኖት ፖለቲከኛ ነበሩ።  ይህን ሃቅ አቶ ጃዋር ራሳቸው የሚክዱት አይደለም።   ጽንፈኛ የሃይማኖት  ፖለቲካ አራማጀ የሆኑት  አቶ ጃዋር በምን ስሌት አስልተውት ይሁን በማይታወቅ ጥናታቸው በአንድ መድረክ ላይ እንዳሉት “ከኦሮሚያ ህዝብ 90 በመቶው ሙስሊም ነው፤ በመሆኑም ኦሮሚያ ውስጥ እስልምናን እቃወማለሁ ያለ በሙሉ በሜንጫ አንገቱን እንለዋለን” እያለ በአደባባይ ሲፎክር ነበር። በእርግጥም በአገራችን  የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ አቶ ጃዋር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።   
አቶ ጃዋር አሁን የሃይማኖት ፖለቲከኝነታቸው አልሰምር ሲላቸው  በፍጥነት መሪያቸውን ጠምዝዘው  የአክራሪ ብሄርተኝነት የፖለቲካ ካባቸውን ደርበዋል። ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ በመሆኗ ሌላው ይውጣ፣ ባለፉት ስርዓቶች የኦሮሞ  ህዝብ ከሌላው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተለየ መልኩ ጫና ተደርጎበታል በመሆኑም ከግዛቲቱ (ኢትዮጵያ) መገንጠል አለበት፣  ሌላው የህዝብ በኦሮሚያ ሃብት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው፣ ወዘተ በማለት  የተሳሳተ መርዘኛ የዘር ፖለቲካቸውን በመርጨት አንዳንድ  ወጣቶችን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲጨብጡ አድርገዋል። 
አቶ ጃዋር አሜሪካ ተቀምጠው አገር ቤት  ለሚያልሙት ስልጣን የደሃው ልጅ  ህይወት እንዲያጠፋና  ንብረት እንዲያወድም በአጠቃላይ  ከህግ በላይ እንዲሆን መርዘኛ የዘርና የሃይማኖት ፖለቲካቸውን በመርጨት ላይ ይገኛሉ። በደሃ የኦሮሞ  ልጆች ደም መነገድ ማለት ይህ ነው። የኢፌዴሪዋ ኦሮሚያ መገለጫ ግን ይህ አይደለም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ  የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር፣ ባህሉን ወጉን ጠብቆ የሚኖርባት፣   ማንነቱ  የተከበረባት፣  ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመፈቃቀድ አብሮ  የሚኖርባት፣ በየዘርፉ  ፈጣን ልማት በማስመዝገብ ላይ የሚገኝባት አገር ናት። አቶ ጃዋር እውነት ይህ ትግል ትክክለኛ መስመር የያዘ  ትግል ከሆነ   ለምን እርሶ በአካል እዚህ ትግል ውስጥ አልተካፈሉም? 
አቶ ጃዋርና የጥፋት ተከታዮችህ ያሰባችሁት የአቋራጭ የስልጣን መንገድ  ዝግ ነው።  ስህተትን አምኖ መቀበል ብልህነት ነውና  ወደቀልባችሁ ተመለሱ። የሶሪያው  አይኤስ፣ የማሊው አንሳርዲን፣ የናይጄሪያው ቦኮሃራመና ከሶማሊያው አልሸባብ ሲጀምራቸው ልክ እንደእርሶ ህዝባዊ ድጋፍ እንዳላቸው አድርገው ሲደሰኩሩ ነበር።  የኋላ ኋላ  ህዝባቸውንና  አገራቸውን  አውድመዋል። ከእነርሱ  አቋም  በተቃራኒ የቆመ ወይም ያራመደ  የመሰላቸውን  ዜጎቻቸውን ሁሉ  ምህረት የለሽ እርምጃ በጠራራ ጸሃይ ወስደዋል። 
በጥፋት መንገድ የተሰለፋችሁ ከያዛችሁት እኩይ ተግባር የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነውና እጃችሁን ከመሰብሰቡ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖራችሁም፡፡ አማራጩ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ የያዛችሁትን የጥፋት መንገድ ትታችሁ ካሻችሁ የሰላማዊ ትግል ሜዳውን መቀላቀል የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ በወንጭፍ  የሚካሄድ የዘረኝነትና የአክራሪ ሃይማኖተኝነት ፖለቲካ  ለአገርም ለህዝብም አይበጅም።