ኦነግ እና የኩርፊያ ፖለቲካ

ወደ ዋናው የመጣጥፌ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ ከማለፌ በፊት አንድ መንደርደሪያ የሚሆነኝን ሰሞነኛ ክስተት አንስቼ ለኔ ሃተታ ማዳበሪያ ይሆናሉ የምላቸውን ጥቂት ተያያዥ ነጥቦችን ላስታውስ፡፡ ስለዚህም፤ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም የኦሮሞ ህዝብ ያከበረውን የኢሬቻ ዓመታዊ በዓል ተከትሎ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ስለተከሰተው የሁከትና ግርግር ተግባር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ወቅታዊ ማብራሪያ ሲሰጡ የሰማሁዋቸው ሁለት የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ምን ብለው እንደነበረ ነው የማስታውሳችሁ፡፡ 
    ወቅታዊውን ችግር በተመለከተ ለ98.1 ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣያ ማብራሪያ ሲሰጡ የሰማሁዋቸው የመንግስት አካላት፤ ኮማንደር የማነ ገሰሰው የተባሉ የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊና እንዲሁም ደግሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ የሆኑ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው፡፡ እናም ሁለቱ ሰዎች የየራሳቸውን የስራ ሃላፊነት ወክለው በቀረቤበት የፋና ብሮድካስቲንግ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ የቀጥታ ስርጭት ውይይታቸው ላይ ከተናገሩት መካከል የኔ መጣጥፍ ዋነኛ ትኩረት ለሆነው፤ ኦ.ነ.ግ.ን የሚመለከት መሰረተ ሃሳብ ማዳበሪያነት የፈለኩት አንድ ነጥብ ቢኖር፤ በተለይም “… የጥፋት ሃይሎቹ ይህንን ያህል መጠነ ሰፊ የሁከትና ግርግር እንቅስቃሴ አድርገው በርካታ  ፋብሪካዎችን እስከማቃጠል የደረሰ ሀገር አውዳሚ ጥቃት ለመፈፀም በሚያስችል መልኩ የተደራጁበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ግምት አልነበረንም” ሲሉ ሁለቱም በየተራ የሰነዘሩት አስተያየት ነው ማለት ይቻላል፡፡ 
    ይልቁንም ደግሞ ጋዜጠኛው “እንዴት ግን የሁከት ግርግሩ መሪ ተዋናይ ሆነው የሚንቀሳቀሱት ሃይሎች ይህን ያህል የህዝብ ሀብት ንብረት ለማውደም የሚያስችላቸውን ሰፊ አካባቢ የሚሸፍን እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲዘጋጁ እንኳን መንግስት ስለጉዳዩ የሚያውቅበት መረጃ አላገኘም?” ሲል ለጥቆ ላቀረበላቸው ተጨማሪ ጥያቄ የስራ ኃላፊዎቹ የየራሳቸውን ምላሽ ሲሰጡ የተደመጡበት አግባ ነበር እኔን ወደ 1980ዎቹ ግማሽ ዓመታት በትዝታ ፈረስ ተጉዤ ኦ.ነ.ግ ያኔም ልክ እንዲህ  እንደ አሁኑ ያልታሰበ ዱብዕዳውን በሽግግር መንግስቱ ሂደት ላይ የጋረጠበትን አግባብ ለማስታወስ የተገደድኩት፡፡ ስለዚህ በተለይ የፌዴራል ፖሊሱ ኮማንደር ለዚህየፋናው ጋዜጠኛ ጥያቄ ከሰጡት ምላሽ ላይ ጥቂት ነጥችን ለአብነት ያህል ጠቅሸ በማስታወቂያው ሃሳባቸውን ከኔ መጣጥፍ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ስለሚያስተሳስረው ታሪካዊ ምክንያት ማተቴን እቀጥላለሁ፡፡ 
    “በእርግጥ ህዘቡ ውስጥ የተሰገሰገው የጥፋት ሃይሎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ያለመ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚስተዋሉበት አዝማሚያ እንዳለ የሚያመለክት መረጃ እንደነበረን የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ህብረተሰቡ መሀል የነ ኦ.ነ.ግ.ንና የነግንት ሰባትን የሽብር ቡድኖች ጭምር አስርጎ በማስገባት የህዝቡን ሰላዊ ኑሮ የሚያናጋ የሁከትና ግርግር ተግባርን የመቀስቀስ ሙከራ የሚደረግበት ሁኔታ በኦሮሚያ ብቻም ሳይሆን፤ አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ጨምሮ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም የሚታይበት አዝማሚያ እንደነበር በደንብ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራሉ መንግስት በክልላዊ መስተዳድሮቹ የውስጥ ጉዳይ ፈጥኖ መግባት ምናልባትም ህዝብ ላይ ቅሬታ ሊፈጥርና አችግሩንም ሊያባብሰው ይችላል ከሚል ቅንነት በመነጨ ሆደ ሰፊነት መታገስን መርጦ በመቆየቱ ምክያት እኛ እንደፌዴራል ፖሊስ የጥፋት ቡድኖቹን እንቅስቃሴ የሚገታ ትርጉም ያለው ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሞከርንበት አጋጣሚ የለም…” ነው ያሉት ኮማንደር ጥያቄውን ሲመልሱ፡፡ 
    እንግዲያውስ ይህ መሰረተ ሃሳብ እኔን ወደ 1984/85 ዓ.ም ወስዶ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” እያለ የሚወራው ኦ.ነ.ግ በኢህአዴግ መራሹ የሽግግር መንግስት ጅምር ጥረቶች ላይ ያልተጠበቀ ዓይነት የቅልበሳ አደጋ ሲጋረጥበት የተስተዋለውን ሌላ ተመሳሳይ ክስተት እንዳስታውስ ያደረገኝም ያለምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቁንስ፤ ለያኔውም ሆነ ለአሁኑ ኦ.ነ.ግ ሰራሽ አደጋ እንደ ዱብ ዕዳ መቆጠር ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው ጉዳይ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት “ከመጠን ያለፈ ሆደ ሰፊነት” የመሆኑን ያህል፤ በዚያው ልክም ኦ.ነ.ጎቹ “ታሪክ ራሱን ደገመ” የሚያሰኝ ፖለቲካዊ ደባ መፈፀምና ከማስፈፀም አለመቦዘኑን የሚያመለክት ተመሳሳይ ገፅታ የተላበሰ ሆኖ ስለተሰማኝ ነው ሰሞነኛው የኦሮሚያ ክልል ዱብ ዕዳ፡፡ እስቲ ኦ.ነ.ግ ከኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቆና ትግል ጋር በመራራና በከረረ መልኩ መኳረፉን ስለገፀበት የመጀመሪያ እርምጃው እኔ ከማስታውሰው የታሪክ ሀቅ ውስጥ አንዳንድ አንኳር ነጥቦችን ነቅሼ እያወጣሁ ለማውሳት ልሞክር…
    መቸስ የደርግ ስርዓት መወገዱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ካስተዋወቅን የዚህች አገር ፖለቲካ ፈርጀ ብዙ ገፅታ መገለጫ እውነታዎች መካከል አንበሳውን ድርሻ ይዞ የሰነበተው “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” እያለ ራሱን የሚጠራው ኦ.ነ.ግ ያኔ የኢትዮጵያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፃኢ ዕጣፈንታ የሚወስን የሽግግር መንግስት በመመስረት ሂደት ውስጥ ከኢህአዴግ ቀጥሎ ሰፊ ሚና እንደነበረው ይታወሳል፡፡ እንዲያውም የሽግግር መንግስቱ ፓርላማ ወንበሮቹ በኢህአዴግና በኦ.ነ.ግ ታጋዮች የተያዙ ይመስል እንደነበር ነው ለኔ ትዝ የሚለኝ፡፡ 
    በርካታ የኦ.ነ.ግ መሪዎች ከምክልት ፕሬዚዳንትነት ጀምሮ የሚኒስቴርነትና ሌላምከፍተኛ የሚባል የሀገሪቷ መንግስታዊ የስልጣን ዕርከን ላይ ተመድበው ከኢህአዴጎቹ እንብዛም በማይተናነስ መልኩ ሃላፊነታቸውን የመወጣት ጥረት ሲያደርጉ አይተን “ጎሽ እንኳን ይልመድባችሁ!” ያልንበት የታሪክ አጋጣሚ እንደነበረም ማስታወስ ይጠበቅብናል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ያን ዓይነቱ በጎ ጅምር ረጅም ርቀት ሳይጓዝ ነበር ኦ.ነ.ጎቹ ወደ መረረና ወደ ከረረ የኩርፊያ የፖለቲካቸው ፊታቸውን አዙረው በኢህአዴግ ታጋዮች ላይ ቃታ ለመሳብ ያለመ ሴራ ሲዶልቱ የተገኙት፡፡ ጉዳዩን እጅግ በጣ አስተዛዛቢም፤ አወዛጋቢም አድራጎት የነበረው ደግሞ፤ በተለይም የኦ.ነ.ግ አመራር አካላት የ “ስልጣን የነበረው ደግሞ፤ በተለይም የኦ.ነ.ግ አመራር አካላት የ “ስልጣን አነሰን” ቅሬታቸውን ወደ መራራና ወደ ከረረ ኩርፊያ ቀይረው በኢህአዴግ ታጋዮች ላይ ቃታ ለመሳብ ሲጣደፉ የተስተዋሉበት አግባብ ፖለቲካዊ ብልህነት የጎደለው ችኩል እርምጃ መሆኑ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ አቋሜ እንደመነሻ ምክንያት አድርጌ የምወስደው አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥብም፤ በአቶ ሌንጮ ለታ ሊቀመንበርነት ይመራ የነበረው ኦ.ነ.ግ ኦሮምኛ ተናጋሪ የቀድሞው ጦር አባላትንና (የደርግ ወታደሮችን) ከያሉበት አፈላጎ እያሰባሰበ ነፍጥ ማስታጠቅና “በሉ እንግዲህ እዚያ ሰሜን ኢትዮጵያ አገራቸው ላይ ተዋግተው ያሸነፉዋችሁን የትግራይ ሰዎች አሁን እናንተም በራሳችሁ አገር በኦሮሚያ ምድር መሽጋችሁ ተፋለሟቸውና ቂማችሁን ተወጡ፡፡ እኛ የኦሮሞ ልጆች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን ነፀነታችንን መቀዳጀት ስላብን በቃ ወያኔዎቹን ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማስገደድ ይኖርብናል” ወዘተ እያለ በመደለል ስድሳ ሺህ ሰራዊት እስከማሰለፍ የደረሰበትን እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡ 
    ኦ.ነ.ግ እንዲህ ዓይነት አፍራሽ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ገና የደርግን ውድቀት የሚያበስረው የግንቦት 20 ድል ዜና ከተሰማበት ቀን ማግስት አንስቶ እንደነበርና በተለይም ምስራቅ ኦሮሚያን እንደዋነኛ የፀረ ኢህአዴግ ጦርነቱ ቀጠና አድርጎ የወሰደበት እውነታ እንደነበርምንው እኔ እንደ አንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚየውቅ የዓይን ምስክር እማኝነቴን የምሰጠው፡፡ ከዚያን ጊዜው የኦ.ነ.ግ ታጣቂዎች አጉል ትንኮሳና የጠብ አጫሪነት ተግባር ጋር በተያያዘ ምክንያት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰራዊት ውስጥ ለአንድ ሰሞን የተጧጧፈ ውዝግብ ተቀስቅሶ እንደ ነበረና ይልቁንም ደግሞ እኔ ራሴ የነበርኩበት የህወሐት 2ኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ሰራዊት አባላትን ጉዳይ ምን ያህል እንዳከራከረን ማስታወስ ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ለዚያን ጊዜው የኢህአዴግ ሰራዊትን ያወዛገበ ብርቱ ክርክር ስለተከሰተበት ምክንያትና አጠቃላይ የውዝግቡ ገፅታ ለአንባቢያን ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ነጥቦችን በቅደም ተከተል አንስቼ ለማስታወስ እችል ዘንድ እነሆ ወደ 1984/85 ዓ.ም ትዝታዬ አመራለሁ፡፡ እንግዲህ የወቅት የደርግ ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት ወደ ስርሰ መቃብሩ የመውረዱ ጉዳይ ተረጋግጦ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መከፈቱን የሚያመለክቱ የብሩህ ተስፋ ፍንጣቂዎች በመላው የሀገራችን ህዝቦች ልብ ውስት ማቆጥቆጥ የጀመሩበት ዘመን እንደበር የሚጣከራክር አይደለም፡፡ እናም ከወደ ሰሞኑ ጫፍ ተለኩሶ በደም አፋሳሹ የትጥቅ ትግል ሂደት ወደ መሀል አገርና እንዲሁም ወደ አራቱም ማዕዘን የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት አድማሱን እያሰፉ የቀጠለውን ኢህአዴግ መራሽ የፀረ ብሔራዊና ወደባዊ ጭቆና ንቅናቄ ተቀላቅለው ብረት ያነገቡ እጅግ በርካታ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ወጣት ታጋዮች የተሸነፈው ወታደራዊ መንግስት ጦር ሰራዊት የሚለቃቸውን ጠረፋማ አካባዎች መቆጣጠርና የሀገሪቷን ዳርድንበር ማስከበር ይጠበቅባቸው እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ 
    ከዚህ የተነሳም፤ እኔ ራሴ አባል የነበርኩበትን ሁለተኛው ሜካናይዝድ ዲቪዥንን ጨምሮ ሶስት የህወሐት እግረኛ ክፍለ ሰራዊቶችና እንዲሁም ደግሞ አንድ የብአዴን እግረኛ ክፍለ ሰራዊት በቀጥታ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰው የአካባቢውን ህዝቦች የማረጋጋት ተግባር እንዲያከናውኑ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ገና እኛ ምስራቅ ኢትዮጵያን ደርሰን ተልዕኳችንን የመወጣት እንቅስቃሴ ከመጀመራችን፤ ኦ.ነ.ግ እያስታጠበ በአካባው ያሰማራቸው ቡድኖች ድንገት ሳይታሰብ ከየጢሻው እየወጡና በየጉድባው አድፍጠው እጠየበቁ ጥይት ሩምታቸውን ያዘንቡብን ያዙ፡፡ እናም ይህ ያልተጠበቀ ዱብዕዳ ክስተት፤ በርካታ እንደወርቅ በእሳት እየተፈተኑ የመጡ የትጥቅ ትግሉ ዘመን ክዋክብት ታጋዮችን ሲቀጥፍብን ተመለከትን፡፡ በሁኔታው የተደናገጡ ጓዶች የኦ.ነ.ግ ታጣቂዎች ላይ የአፀፋ ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎም፤ጉዳዩ እዚህ አዲስ አበባ ይገኝ የነበረው የሁለቱም ግንባዎች ከፍተኛ የአመራር አካል ዘንድ ይደርስና እነ አቶ ሌንጮ ለታ ተሽቀዳድመው ኢህአዴግን በጠብ አጫሪነት የሚፈረጅ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ 
    ስለሆነም የኢህአዴግ ከፍተኛው የአመራር አካል፣ በተለይም በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ይንቀሳቀሱ ስለነበሩት ክፍለ ሰራዊቶች “ከዚህ በሁዋላ የኦ.ነ.ግ ታጣቂዎች ለሚሰነዝሩባቸው ጥቃት ምንም ዓይነት አፀፋዊ ምላሽ ከመስጠት ተቆጠቡ፡፡ ይህን የምናደርገው ደግሞ ኦ.ነ.ግ በባህሪው የዴሞክራሲ እንጥፍጣፊ ያልፈጠረበት ጠባብ ብሔርተኛ ድርጅት እንደሆነ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ትግላችን መነሻም፤ መድረሻም በመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክረሲያዊ የሀገር አንድነትን ለመፍጠር ያለመ እንደመሆኑ መጠን፤ እየሞትን የኦሮሞ ሰፊ ህዝብ እውነቱን እንዲረዳልን ማድረግ ስለሚጠበቅብን እንጂ …” የሚል ጠብቅ መመሪያ አስተላለፈ፡፡ 
    እንግዲያውስ ይህ ድርጅታዊ መመሪያ እንቀበል ወይስ አንቀበል በሚል ምክንያት የተፈጠረ ውዝግብ ነበር ያኔ ምስራቅ ኢትዮጵያ የነበርነውን ኢህአዴግ ሰራዊት አባላት ለሳምንታት ያወዛገበንና መጨረሻ ላይ የጦፈ ክርክር በተስተዋለበት ሰፊ ውይይት ወደ አንዱ ዓይነት የጋራ መግባባት የተደረሰበት፡፡ የጋራ መግባባቱ ደግሞ “በህወሐት/ኢህአዴግ የሚመራውን ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ድል ለማቀዳጀት ሲባል የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ምን ያህል ለማመን እንኳን የሚያዳግት ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት እንደ ከፈለ ከኛ ወዲያ የዓይን ምስክር አይኖርም፡፡ ስለሆነም የትግሉን መሰረታዊ ዓላማዎች ለማሳካት ይቻል ዘንድ ህዝባችን ያሳየውን ፅናትና የከፈለውን ዋጋ ግምት ውስት አስገብቶ ጉዳዩን ማጤን ካለብን ይህ አሁን የድርጅታችን ከፍተኛ አመራር ያስተላለፈው ጥብቅ መመሪያ ተገቢ ነው በሚል ልንቀበለው ግድ ይላል…” ይል እንደነበር ነው ለኔ ትዝ የሚለኝ፡፡ 
    ይህ ማለትም ደግሞ ያኔ በአብዛኛው የምስራቅ ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢዎች፤ እንዲሁም በአርሲና በባሌ ኦ.ነ.ግ አስታጥቆ ያሰማራቸው ስድሳ ሺህ የተሸናፊው የደርግ መንግስት ወታደሮችን ጨምሮ፤ ሌሎች የግንባሩ ነባር አባላት በተቀናጀ የዘረኝነት ፕሮፖጋንዳቸው እየታገዙ የኢህአዴግ ሰራዊትን ከኦሮሚያ ምድር ለማስወጣት ይሞክሩ ለነበረበት መጠነ-ሰፊ ትንኮሳቸው የአፀፋ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፤ የህይወት መስዋዕትነትን እስከ መክፈል በሚደርስ ሆደ ሰፊነት ታግሰን እያለፍን የትግሉን መሰረታዊ ዓላማ የሚያሳካ ተልዕኮ ልንፈፅም ተስማማን ማለት ነው፡፡ ደግነቱ ግን ኦ.ነ.ግ ራሱ ብዙም ሳይቆይ ነበር የኦሮሞ ህዝብ ትክክለኛ ማንነቱን እንዲያውቅበትና አንቅሮ እንዲተፋው ያደረገውን ዕኩይ ተግባር መፈፀም የጀመረው፡፡ 
    ምክንያቱ ደግሞ “መጤ ሰዎችን ሁሉ ከኦሮሚያ መሬት የማስወገድ ስትራቴጂ” በተሰኘ የዘረኝነት እንቅስቃሴው ሰላማዊ ህዝብ ላይ የለየለት ሽብርተኛ ቡድን ተደርጎ እንዲቆጠር ያስገደደ አረመኔያዊ የጅምላ ግድያ የመፈፀም ተግባርን ይሆነኝ ብሎ ስለተያያዘው እንኳንስ ሌላው ኦሮሞ አርሶ አደሮችም ጭምር ግፈኛነቱን ይመሰክሩበት ጀመሩ፡፡ ኦ.ነ.ግ ትክክለኛው ማንነቱ እንዲጋለጥ ካደረገባቸው የዚያን ጊዜ ዕኩይ ተግባራቱ መካከል፤ በተለይም ጋራ ሙለታ አካባቢ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን “እንቁፍቱ” እየተባለ ከሚወራው በጣም አስፈሪ ገደል ውስጥ እየተወረወሩ አይሞቱ አሟሟት እንዲሞቱ ያደረገበት ጅምላዊ የግፍ ግድያ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡
    በሌሎቹ የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች ይህን መሰሉን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅምና ሲያስፈፅም ከተስተዋለ በሁዋላም ነበር ህዝቡ ራሱ ወደ ኢህአዴግ ታጋዮች እየቀረበ “እንዴ እነዚህ ሰዎች ምን እንዲያደርጉን ነው የምትጠብቁት? ተግባራቸው ሁሉኮ የኦሮሞ ህብረተሰብ ከሚታወቅበት ባህልና ወግ በእጅጉ ያፈነገጠ ሆነብን፡፡ እረ እባካችሁ እናተ እንኳን ስርዓት አስይዙልን…!” እስከ ማት የደረሰው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ይሄው ዛሬ ድረስ ኦ.ነ.ግ እና የኩርፊያ ፖለቲካው እንድትሆን ሲያደርጓት የሚስተዋሉበት አሳዛኝ እውነታ እየታዘብን እንገኛለን፡፡ 
እኔ በግሌ ይህ የኦ.ነ.ግ ፖለቲካዊ ነገረ ስራ ሳስበው “አኩራፊ እረኛ ምሳው እራቱ ይሆናል” የሚል የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጎምቱ ተረት ነው ትዝ የሚለኝ፡፡ ምክንያም ደግሞ እንዲህ እንደ ኦ.ነ.ግ መሪዎች ጠዋት እንዲበላ የቀረበለትን ማዕድ በኩርፊያ ስሜት ገፍቶ የመውጣት ክፉ አመል የተጠናወተው ከብት እረኛ ቀኑን ሙሉ ረሃብ ሲቆጋው ውሎ ማታ ላይ ሲመለስ ለእራትነት የሚጠብቀው ምግብ ያው ማለዳ ንቆ የተወው እንጂ ሌላ የተለየ ነገር ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል፡፡ 
እናም ክፉ አመል ሆኖበት ጠዋት አጉል ሲነጫነጭ አራክሶት የሄደውን ምግብ ምሽት ላይ ያለ አንዳች ማቅማማት ጥርቅም አድርጎ ሲበላ የሚመለከት ቤተሰብ “አይ ያንተ ነገር አሁን እስቲ ፆምህን ውለህ የገዛ ራስህን ከምትጎዳ ምሳህን ስናቀርብልህ መመገብ ብትችል አይሻልም ነበርን?” እያለ ይስቅበታል፡፡ ክፋቱ ግን የኦ.ነ.ግ መሪዎች እንደ ፈሊጥ የያዙት የኩርፊያ ፖለቲካ የሚያስከትለው ከንቱ ጉዳት ከእነርሱ ይልቅ ጉዳዩ እንብዛም ያልገባቸውን እና የማይመለከታቸውን የኦሮሚያ ክልል ለጋ ወጣቶች ሰለባ እያደረገ መሆኑን ማስተባል አለመቻሉ ነው፡፡ ለማንኛውም እኔ ሀተታዬን እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡ 
መዓ ሰላማት!