የሰላምን ዋጋ ዘንድሮ ተገነዘብን

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ትግባራዊ በሁኑባቸው ቀናት ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ሆኖ ባከናወነው ስራ ሀገሪቱ የልማት እድገቷን ሊያስቀጥል ወደሚያስችል ቀደሞ ወደነበረ ሰላም እና መረጋጋት እየተመለሰች መሆኑን አረጋግጠዋል። በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ያለው የሰዎች ዝውውርና የገበያና ማህበራዊ እንቅስቃሴውም ይህንኑ ያረጋግጣል። አሁን በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ ቢሆንም ይህን ሰላምና መረጋጋት አስጠብቆ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ አሁንም ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል። አሁን የተመለሰውን ሰላምና መረጋጋት ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት ወደኋላ ሄጄ ያለፍንበትን ላስታውስ፤ የሰላምን ዋጋና የሁከትን አደገኛነት ያሳየናል።
የተረጋጋ ሃገራዊ ድባብ ሸሽቶን ሁከትና ግርግር ካጠላብን አንድ ዓመት ሊሞላን ነው። ባለፈው ዓመት ህዳር ነበር በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ሁከትና ረብሻ ያጠላብን የጀመረው። ሁከቱ የተጀመረው እንደዋዛ ነበር። በምእራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ የትምህርት ቤት ቅጥር ውስጥ የሚገኝ መሬት በከተማው አስተዳደር ለባለሃብት ሊሰጥ መመተር ሲጀምር ይህን በመቃወም ነበር ሁከት ‘ሀ’ ብሎ የጀመረው። ሁከቱ ግን በዚህ አልቆመም። “ሆድ ለባሰው . . .” እንዲሉ በመልካም አስተዳደር እጦት የተማረሩና በስራ አጥነት ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች እየተቀባበሉ አዛመቱት። በመጀመሪያ ኮሽታ ተሰምቶባቸው የማያውቅ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች፤ ቶሌ ወረዳ፣ አስጎሪና ቱሉ ቦሎ ከተማዎችን ጨምሮ እስከወሊሶ ደረስ በጎዳና ላይ ተቃውሞ መታመስ ጀመሩ። ተቃውሞው ዘሎ ወደምእራብ ወለጋ፣ ተመለሶ ወደምስራቅ ወለጋ፣ ባሌ፣ የሃረርጌ ዞኖች . . . እያለ 2008 ዓ/ም አጋማሽ ላይ አብዛኞቹን የኦሮሚያ ከተሞች አዳረሰ። 
ሁከቱን በቀላሉ መበመቀባበል ማዛመት ያስቻለው በመጀመሪያ ከዚያ ቀደም ከዓመት በፊት 2006 ዓ/ም ማገባደጃ ገደማ ተነስቶ እልባት ሳይበጅለት የቆየው የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞንና የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማሰተር ፕላን ነበር። ይህንኑ በማስታከክ በተለይ በፊንፊኔ ውስጥና በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ለልማት የተነሱ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ የአርሶ አደሮቹን ዘላቂ ኖሮ ታሳቢ ያላደረገና ለችግር የዳረገ መሆኑ መቃወሚያ አጀንዳ ሆኖ ወጣ። ከዚያ በኋላ ነገሩ ተደበላላቀ የስራ አጥነት ችግር፣ የመልካም አስተዳዳር እጦት፣ የልማት ጥያቄ . . . ተቃውሞውን አጋጋለው። በአጠቃላይ በኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ መነሻ ምክንያት  የልማት ፍላጎት፣ የመልካም አስተዳደር መጓደል ወዘተ የቀሰቀሰውና ተገቢ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ታዲያ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ በውጭ ሃገራት የተጠጉና ህግመንግስታዊ ስርአቱን በተለያየ ስልት ለመናድ ሲሞክሩ የቆዩና አልሳካ ብሏቸው ተስፋ የቆረጡ የተለያዩ የኦነግ ቡድኖች አይናቸውን እየጠራረጉ ካንቀላፉበት ተነሰተው በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ሁከት ለራሳቸው ዓላማ ለመጠቀም ተራወጡ። ኦሮሞዎች በፌደራላዊ ስርአቱ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት እያገኙ፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማሩ፣ ባህላቸውን እያጎለበቱና እያስተዋወቁ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ከሌሎች ያሀገሪቱ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጋር መኖራቸው የብብት ውስጥ እሳት ሆኖ ያንገበገባቸው የአሃዳዊ ስርአት ተስፈኞች ሳይቀሩ የኦሮሞዎች ተቆርቋሪ ሆነው ብቅ አሉ። የኦሮሚያ ሁከት የተቀሰቀሰ ሰሞን የተረሱ መኢሶንን የመሳሰሉ የፖለቲካ ቡድኖች ሳይቀሩ ከተቀበሩበት አፈራቸውን እያራገፉ ተነስተው ከአጋጣሚው ለማትረፍ ከጅለዋል።
እነዚህው እርስ በርሱ የሚቃረን ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ለራሳቸው ዓላማ የኦሮሚያ የወጣቶች ተቃውሞ ውስጥ እጃቸውን ማስገባት ሲጀምሩ ተቃውሞው መልኩን መቀየር ጀመረ። በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ሸዋ አዋሳኝ አካባቢ (አመያ) ለብዙ ዓመታት የኖሩ ከ4 መቶ በላይ የሌላ ብሄር ተወላጆች ላይ የተፈጸመው መኖሪያ ቤትን የማቃጠል፣ በምእራብ አርሲ ዞን በተመሳሳይ በሌሎች ብሄር አባላት ላይ እንዲሁም በቤተክርስቲያንና በክርስቲያን ተራድኦ ድርጅቶች፣ በጤና ተቋማት . . . ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በጸጥታ አስከባሪ አባላት ላይ የተፈጸመ እስከግድያ የዘለቀ ጥቃት፣ ከጸጥታ አስከባሪዎችና ከአካባቢ ሚሊሻዎች ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ የሚደረጉ ሙከራዎችም ተቃውሞው መልኩን እየቀየረ ለመምጣቱ ማሳያዎች ነበሩ። በዚህ መሃከል ከሁከቱ ተሳታፊዎችም ከጸጥታ አስከባሪዎችም ወገን የርካቶች ህይወጥ ጠፋ፣ አካል ጎደለ። 
ይህ በዜጎቸ ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ውጭ ሃገር ለሚኖሩት ተቃዋሚዎች ሲሳይ ሆነ።  የኦሮሞ አክቲቪስት ነኝ ባዩ ጃዋር መሃመድ የሚመራው ኦ ኤም ኤን እና የኤርትራ መንግስት የሚመራው ኢሳት የተሰኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በአሜሪካ መንግስት በጀት የሚንቀሳቀሰውና ከእስልምና አክራሪ ጀምሮ ማንኛውም የኢትዮጵያን ህገመንግስታዊ ስርአት ለመናድ የወጠነ አካል ዓላማውን የሚያራምድበት የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ሬዲዮ (ቪኦኤ) ሁከቱን አራገቡት። እጅግ የተጋነነ የሟቾች ቁጥር እየጠቀሱ፣ በጸጥታ ሃይል የሚወሰዱ ሰላም የማስከበርን እርምጃዎች በተዛባ ሁኔታ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመ አስመስሎ በማቀረብ አጋጣሚውን ኢተዮጵያን የማተራመስ ዓላማቸው ማሳኪያ ድግስ አደረጉት። 
በዚህ አኳኋን በኦሮሚያ በወጣቶች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ  የኢትዮጵያን መፍረስ የሚመኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ሲፈነጩበት ከርመው በተለይ የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር በመወያየት ሁኔታውን ለማርገብ በወሰደው እርምጃና በተለይ የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞንና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቀናጀ ማስተር ፕላን ረቂቅ በህዝቡ ተቀባይነት በማጣቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መወሰኑና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ በክልሉ መንግስት ቃል መገባቱ፣ በተለይ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመፈታት ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸው ሁከቱን አበረደው።
ይሁን እንጂ አጋጣሚው ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ኦሮሚያን ለመገንጠል ያስችላል ብለው ቋምጠው የነበሩ ቡድኖች ሃገሪቱን የማተራመስ ቅስቀሳቸውን በቀላሉ ሊተዉ አልቻሉም። በተለይ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሳ ማንኛውም ቡድን፤ ሃይማኖታዊ አክራሪ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ ብሄረተኛ፣ እንደሁኔታው ሰላማዊና ሰላማዊ ያልሆነ ስልትን እያጣቀሱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ወዘተ የውዥንብርና የሁከት ዓላማቸውን የሚያራምዱበት ቪኦኤ ከኦሮሚያ ላይ አልወርድ አለ።
የኦሮሚያው ሁኔታ እየበረደ ሃገርን ለማተራመስ ዓላማ ማስፈጸሚያነት የማይውልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ሁሉም ወደአማራ ክልል ዞሩ። በመጀመሪያ የቅማንት የማንነት ጥያቄ በኋላም የወልቃይትን መነሻ በማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን መጋለብ ጀመሩ። የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ የማንሳት ህገመንግስታዊ መብት ቢኖረውም ጥያቄውን ለማንም ሊገባ በማይችል ሁኔታ ወዲህና ወዲያ በመጎተት ወደመፍትሄ ከመውሰድ ይልቅ ሃገር ለማተራመስ ዓላማ የማዋል አካሄድን ታዝበናል። ይህ ሁኔታ በሌሎች በክለሉ ውስጥ ያሉ ተገቢ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ የመሆንና የልማት ጥያቄዎች የፈጠሩትን ቅሬታ መነሻ ባደረገ ተቃውሞ ተደግፎ በተለይ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ከምስራቅ ጎጃም ደብረማርቆስንና አንዳንድ የምእራብ ጎጃም ከተሞች መረን የወጣ አውዳሚ ሁከት ተቀሰቀሰ። ኢሳትና ቪኦኤ አጋጣሚውን ሰርግና ምላሽ አደረጉት።
በአማራ ክልል በተቀሰቀሰውና በአካባቢው በርካታ መሳሪያ የታጠቀ ህዝብ በመኖሩ በቀላሉ አይበርድም ብለው ያሰቡት ሁከት ብቻውን ሃገር ማፍረስ እንደማይችል የተረዱት ከኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ጋር ያበሩ የማይታረቅ ልዩነት ያላቸው ትምክህተኞችና ኦሮሚያን የመገንጠል ህልም ያላቸው ጠባብ ብሄረተኞች የስትራቴጂ ሳይሆን የትርምስ ስልት ስምምነት ተዋዋሉ። ኢሳትና ቪኦኤም ኢትዮጵያውያን እና ኦሮሞዎች ግንባር ፈጠሩ፣ ኢትዮጵያውያንና ኦሮሞዎች በምንትስ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ ወዘተ የሚል ዜናቸውን ያናፍሱ ጀመር። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በኢፌዴሪ ህገመንግስት ብሄራዊ መብትና ነጻነታቸው የተረጋገጠላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነታችንን አይወክልም ብለው ይህን የሚወክል አርማ ያኖሩበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ትተው የቀድሞውን አሃዳዊ ስርአት የሚያስታውስ ሰንደቃላማና የኦነግን አርማ የያዙ “ኢትዮጵያውያንና ኦሮሞዎች” ሰልፎችን ፎቶግራፎች መመልከት የተለመደ ሆነ። 
በሃገር ውስጥ ያሉት ኦሮሞዎች ኢትዮጵያውያን ሆነው ሳለ፣ ከዚህ በተለየ ሁኔታ በውጭ ሃገራት ኦሮሞዎችና ኢትዮጵያውያን እየተባለ የሚነዛ ወሬ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭና አሳዛኝ ነበር። ያም ሆነ ይህ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን በትርምስ የታክቲክ ስምምነት ሰሞነኛ ጋብቻ በፈጸሙ ትምክህተኞችና ጠባብ ብሄረተኞች ለሁከት እንዲነሱ በማህበራዊ ሚዲያ ተቀሰቀሱ። በዚህም በተለያዩ የክልሎቹ አካባቢዎች አውዳሚና ገዳይ ሁከቶች ተቀሰቀሰሱ። የአማራም ሆነ የኦሮሚያ ህዝብ በደረሰው ውድመት ስላዘነ ሁከቱ ጉልበት አግኝቶ የማህበራዊ ሚዲያ አዝማቾቹ ባሰቡት ልክ  ሃገር ማተራመስ የመቻል አቅም አጠረው። ሁኔታዎች በዚህ እንዳሉ የቢሾፍቱ ሆራ አር ሰዲ የኤሬቻ በአል በተለይ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የኦሮሚያ ወጣቶችን አስቆጥቶ ከዳር እሰከዳር ለሁከት እንዲነሱ ለማድረግ መጠቀሚያነት ለማዋል ተሞከረ። ይህ የሰሞኑ ትውስታችን ስለሆነ ሰፋ አድርጌ አላነሳውም። ያም ሆነ ግብጽና ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ከጀርባ ሆነው የሚደግፉት በጃዋርና ግብጽ በተጠጋው የዳዉድ ኢብሳ ኦነግ አዝማችነት የተመራ ሁከት  በተለያዩ ወረዳዎች ከፍተኛ የሃብት ውድመት አስከትሏል።
ይህ ውጭ ባሉ ቡድኖችና ግለሰቦች አዝማችነት የሚመራ ሁከት በዚህ አኳኋን መቀጠሉ ከሚያስከትለው የሃብት ውድመትና የሃብት ውድመቱ በዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ ላይ ከሚያሳደረው ጫና በተጨማሪ፣ ሃገሪቱን ወደማዳከም የሚያመራ ሆኖ ተገኘ። ሁኔታው በቁጥጥር ስር ካልዋለ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለአደጋ አጋልጦ ሃገሪቱን በታሪክ ብቻ የምትታወስ ሆና እንድትቀር ወደማድረግ ሊሸጋጋር የሚችል ሆኖ ተገኘ። በመሆኑም የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅን አስፈላጊ አደረገው። በዚህ መሰረት መስከረም 28፣ 2009 ዓ/ም ለስድስት ወራት ስራ ላይ የሚውል እንደሁኔታው ሊራዘምም ሊያጥርም የሚችል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል። አሁን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ እንገኛለን።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ አስጊ ሁከት ተቀስቅሶባቸው የነበሩ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ሰላምና መረጋጋት ቀድሞ ወደነበረበት እየተመለሰ ይገኛል። በኦሮሚያ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ጨፌ አባላት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት በአከባቢያቸው ባለፉት ጥቂት ወራት በሁከቱ ምክንያት ስጋት ተፈጥሮ እንደነበር፣ ሁከቱ ከፈጠረው ስጋት በተጨማሪ የህዝብና የመንግስት ንብረቶችን ጨምሮ የጋራ መገልገያ ተቋማት ላይም ጉዳቶች ሲደርሱ እንደነበር አስታውሰው፣ ይሁን እንጂ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣና ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን አረጋግጠዋል። ከሐረርጌ፣ ወለጋ፣ ጉጂና ፊንፊኔ ዙሪያ ዞኖች የተወከሉ የጨፌው አባላት ሲፈጠሩ የነበሩት ሁከቶች እና ንብረት የማውደም ተግባር ሙሉ በሙሉ መቆሙን አረጋግጠዋል።
በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስ አስችሎ የወከላቸው ነዋሪ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው መመለሱን የጨፌው አባላት መስክረዋል። የጨፌው ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር  የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አመልክተው፣ ሰላም የማስከበር ስራው በኮማንድ ፖስት የሚመራ ቢሆንም የህዝቡና የጨፌው አባላት ትብብር ሲታከል የታለመለትን ዓላማ በሚገባ ማሳካት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
አውዳሚ ሁከቶች ተቀስቅሰውባቸው በነበሩ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ ተሰብስቦ በማህበራዊ ሚዲያ በሚታዘዙ የግብጽን ኢትዮጵያን የማውደም ተልዕኮ አስፈፃሚዎች በህዝብና በግለሰብ ንብረት ላይ በደረሰው ዜጎችን ለስራ አጥነት አደጋ ያጋለጠ ሁኔታ አውግዘዋል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትንና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቡት ፋሲሊቲዎች የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎት መሰጫዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ኮንነው  በውጭ ጠላቶች ሴራ ተደናግረው በልጆቻቸው የወደሙ እነዚህን ተቋማት ገንዘብ እያዋጡ መልሰው መገንባት ጀመረዋል። ተቋማቱንና ንብረቶቹን ያወደሙ ወጣቶችም በድርጊታቸው ተጸጽተው ህዝቡን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በመልሶ ግንባታ ስራ ላይ መሳተፍ የጀመሩባቸው አካባቢዎችም አሉ።
በአጠቃላይ በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ ያለው የህዝቡ ስሜት ሁከቱን የተጠየፈ መሆኑንና ይህ አውዳሚ ሁኔታ ዳግም እንዳይከሰት ነቅቶ ለመጠበቅ የቆረጠ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ለክለሉ እና በአጠቃላይም ለሃገሪቱ ዘላቂ የሰላምና መረጋጋት ዋስትና የሚሰጥ አስተማማኝ ሁኔታ መኖሩን ያመለክታል።
ከዚህ በተጓዳኝ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት የመመለስ ተግባር የማስፈጸም ሃላፊነት የተሰጠው ኮማንድ ፖስት የእስከዛሬ ክንውንም አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም የሚፈጠርበትን ሁኔታ እያመቻቻ ነው። በጽሁፌ መግቢያ ላይ እንደጠቀስኩት አሁን በመላ ሃገሪቱ ሰላም ሰፍኖ የተለመደው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ መቀጠሉን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አሳውቀዋል። 
ከዚህ በተጨማሪ ኮማንድ ፖስቱ ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ የሰፈሩ ጉዳዮችም ሰላምና መረጋጋት የማስፈኑ ተግባር በምን አኳኋን እየተካሄደ እንዳለ ያመለክታል።  ኮማንድ ፖስቱ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፤ ጎንደር ከተማና አከባቢው ሸፍተው ጫካ የገቡና ከአሸባሪ ሀይሎችና ታጣቂዎች ጋር ሲገናኙ ከነበሩት ውስጥ በአከባቢው ህዝብ ድጋፍ እና ትብብር 93 ሰዎች ለፀጥታ ሀይል እጃቸውን ሰጥተው መግባታቸውን፤ ከእነዚህ ውስጥ 45 ከነሙሉ ትጥቃቸው፣  38ቱ ደግሞ ያለ ትጥቅ የገቡ መሆናቸውን አስታውቋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 4 ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍም በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 13 የሚሆኑ ነጋዴዎች፣ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ውስጥ ውስጡን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከትምህርት ገበታ ሆን ብለው በመቅረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሞከሩ ሶስት አስተማሪዎች ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ መግለጫው አመልክቷል። በተመሳሳይ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ እና ህዝቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 35 ነጋዴዎች መካከል ስድስቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ ሲለቀቁ የቀሩት 29 የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም አሳውቋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ቄሌም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማና ሶዶ ወረዳ ዙሪያ ከተለያዩ ቦታዎች ተዘርፈው የተወሰዱ በቁጥር 70 የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎች በራሳቸው በዘራፊዎቹ እና በህብረተሰቡ ጥቆማ ለፀጥታ ሀይሎች አስረክበዋል። በዚሁ በቄሌም ወለጋ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ከነበሩ ግለሰቦች መሃከል በአከባቢው ህዝብ የማጋለጥና የመጠቆም እንቅስቃሴ 110 ሁከተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ተደብቀው የቀሩትን የሁከት ተሳታፊዎች ለመያዝ የክትትል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በምእራብ አርሲ ዞን በተፈጠረው ሁከትና በህዝብ ንብረትና የልማት ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በህዝቡ ትብብርና ጥቆማ በሻሸመኔ ከተማ 450 እና በምእራብ አርሲ ወረዳዎች 670 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው መጣራት ጀምሯል። በዚሁ ዞን ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ከተዘረፈው 162 የጦር መሳሪያዎች ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች ጥረትና በዘራፊዎቹ ፈቃድ 88 ያህሉ ተመልሷል። የቀረውን የጦር መሳሪያ እንዲሁም ከመንግስት፣ ከግልና ከልማት ተቋማት የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ ጥረቱ ቀጥሏል።
በምእራብ ጉጂ ዞን ከተዘረፉት የጦር መሳሪያዎችና ከህዝብ ተቋማት የተወሰዱ ቁሳቁሶች መካከል 32 ክላሺንኮቭ ጠመንጃዎች ተመልሰዋል። ቀሪዎቹን የማስመለስ ስራ እየተካሄደ ይገኛል። በዚሁ ዞን የተፈጠሩ ሁከቶችን በማስተባበር ግንባር ቀደም ከነበሩት መካከል በአከባቢው ህዝብ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ 302 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል።
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት  አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ደግሞ በአሰቸኳይ ግዜ አዋጁ የተቀመጠው የ10 ቀናት የግዜ ገደብ ከማለቁ በፊት ከ400 በላይ ሰዎች እጃቸውን መስጠታቸውን አሰታውቀዋል። በአጠቃላይ የተሰበሰበው የጦር መሳሪያ ቁጥርም 1500 መድረሱን አስታውቀዋል።
አሁን ሁከትና ትርምስ ያለው ቪኦኤና ኢሳት ጋር ነው። አሁን ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው የሚለው እምነት ያለው ኢትዮጵያን በመበታተን ፍላጎት የሰከሩ ትምክህተኞችና ጠባብ ብሄረተኞች ዘንድ ብቻ ነው። አንዳቸው ገንጥለው የሚገዙትን ሃገር ለማየት፣ ሌለኞቹ ደግሞ ሁሉም ብሄራዊ ማንነቶች ቀልጠው አንድ ማንነት ያላት ሃገር ለመመስረት በየበኩላቸው ሃገር የማፍረስ ቻርተርና የሽግግር መንግስት የመመስረት ወሬ የሚናፈሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም። ይህን ወሬ የሚያወሩት ቡድኖች ሃገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማያውቁና ራሳቸው በቪኦኤና ኢሳት አማካኘነት የሚነዙትን የትርምስና ሃገር የማፍረስ ወሬ መልሰው አዳምጠው በራሳቸው ወሬ የሰከሩ ናቸው። ልትፈርስ የተቃረበችው ኢትዮጵያ በሰከረው አእምሯቸው ውስጥ እንጂ በነባራዊነት የለችም። እናም ሃገር ቤት የምንኖርና ሌላ ሃገር የሌለን ከሃገሪቱ ሰላም ቀዳሚዎቹ ተጠቃሚዎች፣ በሰላም እጦትም ቀዳሚዎቹ ተጎጂዎች የሆንን ዜጎች ኢሳትና ቪኦኤ በፈጠሯት የተተረማመሰች ኢትዮጵያ የቅዥት ወሬ አትደናገሩ። መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ አጢኑ።
በአጠቃላይ አሁን በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል። የህዝቡም ሰላሙን የማስጠበቅ ተነሳሽነት፣ በደረሰው ውድመት የተሰማው ቅሬታ፣ እንዲሁም በሁከቱ በመሳተፍ ንብረት ባወደሙ ተግባር እጃቸው የነበረበት ወጣቶች  ውስጥ የተፈጠረው ቁጭትና ጸጸት ከመንግስት ሰላምን የማስከበር አቅም ጋር ተዳምሮ የሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም መረጋገጡ አስተማማኝ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ሁከት ተፈጥሩ በነበረባቸው አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ አፍ ሰላም ከሁሉም እንደሚበልጥ ዘንድሮ አየን እያሉ ነው።