የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከህገ መንግስቱ አኳያ  

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ልዮ ትኩረት ከሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው። በህገ መንግስቱ “የሴቶች መብት” አንቀፅ 35 ስር በተዘረዘሩ በዘጠኝ ንዑሳን አንቀፆች አማካኝነት እነዚህ የሴቶች ልዩ ትኩረትና ተጠቃሚነት ተገልፀዋል። በተለይም በንዑስ አንቀፅ ሶስት ላይ፤ “ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግስትና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” በሚል ሴቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩባቸው የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በበታችነትነና በተጨቋኝነት መንፈስ ያሳልፉ የነበረው ሁኔታ በህገ መንግስቱ ፍፁም መሻሩና የቀረ መሆኑ ተመልክቷል።
ይህ ብቻ አይደለም። በዚሁ አንቀዕ ንዑስ አንቀፅ ስድስትና ሰባት ላይ፤ ሴቶች በብሔራዊ ልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በፕሮጀክቶች ዕቅድና አፈፃፀም፣ በተለይም የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሃሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ እንዲሁም ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት ያላቸው መሆኑን፤ በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ብሎም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል። ከሴቶች መብቶች ጋር በተያያዘ የተገለፁት ሌሎች አንቀፆችም ቢሆኑ፤ ሴቶች በህብረተሰቡ የህይወት መዘውር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በህግ የተደረገላቸውን ልዮ ትኩረትና ጥበቃ የሚተነትኑ ናቸው። 
ታዲያ እዚህ ላይ ‘ህገ መንግስቱ ለሴቶች ልዩ ትኩረትና ጥበቃ ካደረገላቸው ዘንዳ፣ ህገ መንግስቱን በስራ በመተርጎምና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ምን ተከናውኗል?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ ከህገ መንግስቱ አኳያ ሴቶች ምን ያህል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሆኑ እንዲሁም በዚህ ሂደት የተከሰቱትን ተግዳሮቶች ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህም የኢፌዴሪ መንግስት ልዩ የትኩረት ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች እያደረገ ያለውን ጥረትና የሚፈጠሩ ችግሮችን በምን መንገድ እየፈታ እንደመጣ ሁነኛ ማሳያ ይሆናል በዬ አስባለሁ።
የኢፌዴሪ መንግስት ህገ መንግስቱን ተከትሎ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች እና እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል—በሽግግር መንግስቱ ቻርተርና ኋላ ላይም ህገ መንግሰቱ በስራ በዋለባቸው 22 ተከታታይ ዓመታት። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከተሳትፎ አኳያ የሴቶች አጀንዳዎች በሁሉም ዘርፎች እንዲካተቱና ተጠያቂነትን በሚያጎሉ መንገድ ክትትል የማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ገቢራዊ ሆኗል። በመሆኑም ሴቶች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደረጃጀታቸው የአባላት ብዛትና በአመራር ሰጪነት ብቃት እንዲሁም በፖለቲካው መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ ስራዎች ዕውን ሆነዋል።
የፖለቲካውን ዘርፍ ስንመለከት፤ በዘርፉ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ውሳኔ ሰጪነታቸው ትልቅ እመርታን አስመዝግቧል። በዚህም በህግ አውጪው (በፓርላማ) ያላቸው ተሳትፎ በፌዴራል ደረጃ 38 ነጥብ ስምንት በመቶ፣ በክልል እስከ 48 በመቶ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ እስከ 50 በመቶ ደርሷል። በህግ ተርጓሚው ውስጥም ተሳትፏቸው 20 ነጥብ ስድስት በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በህግ አስፈፃሚው ውስጥ ደግሞ 13 ነጥብ 72 በመቶ ያህል የሚሆኑት በከፍተኛ አመራርነት፣ 34 ነጥብ 12 የሚሆኑት ደግሞ በመካከለኛ አመራርነት ተሳታፊ ሆነዋል። 
ከምጣኔ ሃብት ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያም፤ በመንግስት ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ሴቶች በተለያዩ ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም ሴቶች መሬት፣ ብድርና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ሃብቶችን የመጠቀምና የመቆጣጠር መብት እንዲጐናፀፉ ተደርጓል—ባለፉት ዓመታት። 
በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል። በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስም ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶችን የአማራጭ ኢነርጂና የተለያዩ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም የሴቶችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴም ተከናውኗል። 
በህገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም የመሬት ተጠቃሚነት የባለቤትነት መብታቸውን አረጋግጧል። ይህም የባለቤትነት ስሜቱን ይበልጥ በማረጋገጥ በተዘረጋው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። 
የሴቶችን እኩል የመሬት ተጠቃሚነትን መብት ለማረጋገጥ የክልል መንግስታት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በአባወራዎችና በእማወራዎች ስም በጥምር የመመዝገብ እርምጃ በመውሰዳቸውም፤ ሁለት ሚሊዮን እማወራና ዘጠኝ ነጥብ 11 ሚሊዮን እማወራና አባወራ በጥምረት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።
በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፍ ውስጥም ቢሆን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በስልጠና፣ በመስሪያና በመሸጫ ቦታ እንዲሁም በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በግንባታ፣ በንግድና በከተማ ግብርና በመደራጀትም ተጠቃሚነታቸውን ከፍ አድርገዋል። በከተማ በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች የቤት ባለቤት የመሆን፣ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር ህገ መንግስታዊ መብታቸው ዕውንና ተፈፃሚ ሆኗል። 
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሴት አንቀሳቃሾች ብድር እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን፤ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩበት አቅጣጫ ተቀምጦም ተግባራዊ እንዲሆን በመደረጉ በመስኩ ያላቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን ችሏል።
በዚህ ረገድ ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መስክ 50 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን በከተማ ልማት ፓኬጅ ግብ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ ግብ መነሻነትም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ካለው የስራ ዕድል 40 በመቶ የሚሆነው በሴቶች እንዲሸፈን ተደርጓል።
ባለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት ሴቶች በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የመሰረተ-ልማት አውታሮችም ተጠቃሚነታቸው እየጎላ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በገጠር 82 በመቶ፣ በከተማ 91 በመቶና በሀገር አቀፍ ደረጃ 84 በመቶ ሽፋን በመድረሱ፤ ውሃን በቀላሉ ማግኘት መቻሉ የሴቶችን ህይወት ይበልጥ ቀላል እንዲሆን አድርጎታል። ይህም ሴቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያባክነኑትን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ በምርት ተግባር ላይ እንዲያውሉ አድርጓቸዋል።  
በመንገድ መሰረተ-ልማትም በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ የተዘረጋው ጠቅላላ የመንገድ ርዝመት 110 ሺህ 414 ኪሎ ሜትር በመድረሱና ወደ 76 በመቶ የሚጠጉ የሀገራችን የገጠር ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ በሚያስኬዱ መንገዶች እንዲገናኙ በመደረጉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተችሏል። 
ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት በማሳየቱ፤ በርካታ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻለሉም በላይ፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን አድርጎታል። የአገልግሎቱ መስፋፋት ሴቶችን ወጪ፣ ጊዜና ማገዶ ቆጣቢ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል። 
በማህበራዊ መስክም ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል። በተለይ “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” የሚለውን ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት በመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የስርዓተ-ፆታ ልዩነትም እየጠበበ መጥቷል። 
በዚህም ሴቶች ተሳትፏቸው በሁለተኛ ደረጃ 41 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣ በመሰናዶ 30 በመቶ፣ በቴክኒክና ሙያ 51 ነጥብ ሁለት በመቶ እንዲሁም በዩኒቨርስቲ 32 በመቶ ሊደርስ ችሏል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ እየተደረገ ያለው የልዩ ድጋፍ እርምጃም (Affirmative Action) ተሳትፏቸው እንዲያድግ ሚናው የላቀ ነው። ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡም፤ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ስልጠና በመስጠትና ተጨማሪ የትምህርት ጊዜ በማመቻቸት ትምህርታቸውን በውጤታማነት እንዲፈፅሙ እየተደረገ ነው።  
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ ቢኖር፣ ሴቶች በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ያገኙት ከፍተኛ ተጠቃሚነነት ነው። በጤና የልማት ሰራዊት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ወደ 98 በመቶ አድጓል—በ38 ሺህ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ርብርብ። በዚህም የቤተሰብ ምጣኔ ወደ 42 በመቶ ከፍ ብሏል። 
እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ አማካኝነት የሚያገኙት የወሊድ አገልግሎትም ወደ 60 ነጥብ ሰባት በመቶ ማደግ ችሏል። የድህረ-ወሊድ አገልግሎትም ወደ 90 በመቶ ከፍ ብሏል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶችም የእናቶች ሞት ምጣኔ በ1982 ዓ.ም በመቶ ሺህዎች ውስጥ 1400 የነበረውን ጥምረት ወደ ከመቶ ሺህ ውስጥ 420 ዝቅ እንዲል አድርጓል። ይህ የእናቶች ሞት ምጣኔ መቀነስ ትርጉም ያለው ብቻ ሳይሆን፤ በጤናው ዘርፍ ያለውን እመርታ በጉልህ በማሳየት በህይወት የመኖር (Life Expectancy) ሁኔታን በመጨመር ሀገራችን በመስኩ ያስመዘገበችውን ድል ከፍ አድርጎ የሚናገር ይመስለኛል።  
ታዲያ ከላይ የጠቀስኳቸው ህገ መንግስቱንና እርሱን ተከትለው በወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች አማካኝነት የተከናወኑት እነዚህ ተግባራት ከሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያ ሲመዘኑ መልካም ሊባሉ የሚችሉ ቢሆንም፤ ምንም ዓይነት ችግሮች አልነበሩም ማለት አለመሆኑ ግን ግልፅ ይመስለኛል። እናም በየትኛውም የስራ መስክ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደማይሆነው ሁሉ፤ በዚህም ዘርፍ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። 
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ለሴቶች የሚሰጠው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ሽፋኑና ጥራቱ የሚፈለገውን ያህል ያለመሆን፣ የስራ ጫናን የሚያቃልሉና በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመቅረባቸው፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የእማወራዎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት የሚጋፉ ሁኔታዎች መኖራቸውና ለድሃ ሴቶች የሚሰጠው የብድር አገልግሎት አቅርቦት የሚፈለገውን ያህል አለመሆን በተግዳሮትነት የሚጠቀሱ ናቸው። 
ከዚህ በተጨማሪ የሴት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያላቸው ውጤት አጥጋቢ እንዲሁም ተቋማቱ በሚፈለገው መጠን ምቹ ያለመሆናቸውና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የሃይል ጥቃቶች በትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ተደማሪ ችግሮች ናቸው። 
በእኔ እምነት በሚቀጥሉት ጊዜያት እነዚህን ተግዳሮቶች በመፍታት የሴቶችን ህገ መንግስታዊ መብቶችን ይበልጥ ማጠንከር የሚገባ ይመስለኛል። በአጠቃላይ በሽግግር መንግስቱም ይሁን በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሙሉ ፈቃዳቸው ዕውን ባደረጉት ህገ መንግስት አማካኝነት ሴቶች ሁሉን አቀፍ መብቶቻቸው ተጠብቆላቸዋል። በተግባርም ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጦላቸዋል። በዚህም ጠንካራ ስራዎች ተከናውነዋል። 
ታዲያ ጠንካራዎቹን ይበልጥ በማጎልበትና የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በተገቢው ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። ያም ሆኖ የኢፌዴሪ መንግስት እንደ የወጣቶች የልማት ፓኬጅ ዓይነት አሰራሮች ውስጥ ሴቶችን በማሳተፍና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመው ዕቅድን በመሳሰሉ መስኮችን በማጠናከር በመስኩ የሚታዩ ችግሮችን እንደሚፈታ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።