ጠንካራ ስራዎች የሚጠብቁት አዲሱ ካቢኔ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በትናንትናው ዕለት የመንግስታቸውን 30 የካቢኔ አባላት ሹመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስፀድቀዋል። መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠትም ሞሽኑ በሙሉ ድምፅ እንዲፀድቅ አድርገዋል። በዕለቱ ለየካቢኔ አባላቱ የተሰጠው ሹመት፤ በያዙት የኃላፊነት ቦታ የሚቀጥሉ፣ ሽግሽግ የተደረገባቸውና አብዛኛዎቹ አዲሶችን ያካተተ ነው። የሹመቱ መስፈርትም ውጤታማነት፣ የህዝብ ውግንና እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል። 
በተለይም በካቢኔው የተካተቱት አዳዲስ ሚኒስትሮች በአብዛኛው የሀገራችን የዕድገት ደረጃ የሚጠይቀውን ዝንባሌ የያዘ፣ ዕውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ፣ ተሿሚዎቹ በፊት ሲሰሩባቸው በነበሩት የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት እንዲሁም በሙያቸውና በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ የነበሩ፣ በመልካም ስነ ምግባራቸው የታወቁ፣ በስራ ትጋትና ታታሪነታቸው የተመሰከረላቸውን በማፈላለግ የተከናወነ መሆኑም ተወስቷል። ያም ሆኖ ሹመቱ በቀጣይም በውጤት እየተመዘነ ማስተካከያዎች የሚደረጉበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ታዲያ ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው መስፈርቶች መሰረት የአዲሱ ካቢኔ አባላት በአፈፃፀም ረገድ ፊታቸው ላይ ጠንካራ ስራዎች ይጠብቋቸዋል። በተለይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ውስጥ የተጠቀሷቸውንና በትናንትናው ዕለትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማብራሪያ የሰጡባቸው ጉዳዩችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በመፈፀምና በማፈፀም ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው ይመስለኛል።
እርግጥም አዲሱ ካቢኔና አባላቱ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታና ዴሞክራሲን በማስፋት፣ አፍራሽ እንቅስቃሴን በመመከትና በሂደትም እንዲጠፋ በማድረግ፣ በሀገራችን ተከስቶ ለነበረው ሁከትና ብጥብጥ ሁነኛ ምክንያት የነበረውን መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ  ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ አኳያ የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ በማጎልበት፣ ዜጎች ተደራጅተው የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉበትንና መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የሚታገሉበትን የሲቪክ ማህበራት አደረጃጀት በማጠናከር ረገድ ካቢኔው ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ ላይ እንደተገለፀው፤ ሀገሪቱ ከምትከተለው የምርጫ ስርዓት አንፃር በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የህዝቦችን የተሻለና ተመጣጣኝ ውክልና ለማምጣት የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን የመተግበር ውሳኔ ላይ ተደርሷል። እንደሚታወቀው እስካሁን ድረስ በሀገራችን ሲሰራበት የነበረው ስልጣንን በምርጫ የመያዝ ሂደት በምርጫ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ የህዝብ አስፈፃሚውን አካል ያቋቁማል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አብላጫ ወንበር ያላገኙ ፓርቲዎች ድምፃቸው የሚሰማበት መድረክ ይኖር ዘንድ ሀገር ውስጥ በህጋዊነት ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ይካሄዳል። 
ይህ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓት መኖር የፖለቲካውን ምህዳር ይበልጥ የሚያሰፋው በመሆኑ ከሀገር ውስጥ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረገው ድርድር ካቢኔው ቁልፍ ሚና የሚኖረው ይመስለኛል። በመሆኑም ካቢኔውና አባላቱ በሀገራችን ውስጥ መንግስትና ህዝቡ የሚፈልጉትን ዓይነት የፖለቲካ ውክልና እንዲመጣ በግልም ይሁን በካቢኔ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። 
እርግጥ እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ሃቅን መገንዘብ ይገባል። ይኸውም ድርድሩ የሚካሄደው በሀገራችን ውስጥ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ በምርጫ ቦርድ መዝገብ ላይ ከሰፈሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንጂ፤ ህገ-መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል ከተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎችና ሽብርተኞች ጋር አለመሆኑን ነው። ምክንያቱም ሲጀመርም እነዚህ ኃይሎች በህገ መንግስቱ “የመደራጀት መብት”ን በሚገልፀው አንቀፅ 31 ላይ “…አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ” በሚል ክልከላ ውስጥ ያሉና መብትም የሌላቸው መሆኑ የተገለፀ ስለሆነ ነው። 
ታዲያ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረገው ድርድር የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም ህጎችን የማሻሻልና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የህገ መንግስት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ስራም ሊሰራ እንደሚችል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ላይ ተጠቁሟል። ምንም እንኳን ምርጫ በህዝቡ ፍላጎትና ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ መንግስትም በመሪነቱ የሀገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የማጎልበት ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ አዲሱ ካቢኔ ይህን በማስፈፀምና በመፈፀም የበኩሉን እገዛ ማድረግ ይኖርበታል።   
ዴሞክራሲን ከማስፋት ጋር ተያይዞ በፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ላይም ይሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳላኝ ማብራሪያ የተሰጠበት ሌላው ጉዳይ የማንነት ጥያቄን የተመለከተ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት 25 ዓመታት በሀገራችን የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ጥያቄ መመለስ የቻለ ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን መመለስ የግድ ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን አስመልክተው ከማንነት ጋር ተያይዞ ህጋዊና አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች መነሳታቸውን አስታውሰዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች በህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢና አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘታቸው ለግጭቶች መፈጠር መንስኤ መሆናቸውንም አብራርተዋል—በህዝብ ስም የሚነግዱ አካላትም በህዝቦች መካከል መቃቃር መፍጠራቸውን በመጠቆም። 
ታዲያ ይህን መሰሉን ችግር ለመፍታት መንግስት ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰራ ይታወቃል። አብዛኛዎቹ የካቢኔው አባላት ምሁራንና ለህዝብ ባላቸው ታማኝነት የተመረጡ በመሆናቸው ችግሩን ለማቃለልና በህዝቦች መካከል መቃቃር እንዳይፈጠር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ያለባቸው ይመስለኛል።    
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነገር መልካም አስተዳደርን የተመለከተ ነው። እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር ከከፍተኛው እስከ ዝቅተኛው የመንግስት የስራ ክፍሎች ውስጥ እውን መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከህዝቡና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚኖራቸው የግንኙነት መስተጋብር ህግና ስርዓት ተበጅቶለት በተጠያቂያዊ ሁኔታ እንዲከናወን በመንግስት በኩል ዕቅድ መያዙ ይታወቃል። 
በመሆኑም በየደረጃው የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ ከአዲሱ የካቢኔ አባላት ብዙ የሚጠበቅ ይመስለኛል—ራሳቸው በመፈፀምና እስከ ታችኛው የመዋቅር እርከን ድረስ በመውረድ በማስፈፀም። እርግጥ ይህን የካቢኔውን ስራ የሚቆጣጠረው ፓርላማው ቢሆንም፤ የአዲሱ ካቢኔ አባላት መልካም አስተዳደርን ዕውን በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ። ይህን ለመፈፀምም ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቃል የገቡት ተሿሚዎች፤ ህዝቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በሚፈለገው ጊዜና ፍጥነት በመስጠት ፋና ወጊዎች መሆን ያለባቸው ይመስለኛል። 
ምንም እንኳን መልካም አስተዳደር በሂደት እንጂ በአንድ ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ ሊሆን የማይችል ቢሆንም፤ መፈታት የሚችሉ የዘርፉን ችግሮች በመለየት ጊዜና አቅምን የሚጠይቁትን ደግሞ ከህዝቡ ጋር ፊት ለፊት በየጊዜው በግልፅ በመነጋገር የጠራ ግንዛቤ ማስያዝ ይገባል። በመሆኑም መንግስት መልካም አስተዳደርን በተቻለ መጠን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የካቢኔው አባላት ከህዝቡ ጋር በመሆን ውጤታማ ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። 
ከወጣቶችና ከሴቶች ጋር በተያያዘም በፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ላይ የተገለፁት የተጠቃሚነት ሁኔታዎችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ላይም ተነስተዋል። እንደሚታወቀው ላለፈው አንድ ዓመት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ ብቅ ጥልም እያለ ሲካሄድ የነበረው የሁከትና የብጥብጥ ድርጊት ላይ ዋነኛ ተሳታፊዎች ወጣቶች እንደነበሩ አይዘነጋም። ለወጣቶቹ በድርጊቱ መሳተፍ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ደግሞ ሁለት ናቸው። አንደኛው ወጣቶቹ በሀገራችን ከተገኘው ልማት በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሀገራችንን ዕድገት የማይሹ የውጭ ኃይሎች ገንዘብ በገፍ ያስታቀፏቸው የሀገራችን ፀረ ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች እንዲሁም ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ከውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመሆን በፈጠሩት ትስስር ወጣቶቹ ተታልለው የሁከቱ ተሳታፊ በመሆናቸው ነው። ታዲያ እነዚህን ምክንያቶች ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል— አንድም የውስጥ ተጋላጭነትን ለመፍታት ለወጣቱ ምቹ የስራ ሁኔታን በመፍጠር፤ ሁለትም ፀረ ሰላም ኃይሎችን የማጋለጥና የማዳከም ስራዎችን በማከናወን።
እናም በእኔ አምነት እነዚህን ሁለት ጉዳዩችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አዲሱ ካቢኔ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም እንደምናውቀው ወጣቱ በከፊል አሊያም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ የገጠሩን አካባቢ የለቀቀ ነው። በከተማ ውስጥ ደግሞ ለእርሱ የሚሆን ስራ በበቂ ሁኔታ አልተፈጠረለትም። ይህን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍም መንግስት አስር ቢሊየን ብር በመመደብ ፈንድ አቋቁሟል። ፈንዱ በዋነኛነት ወጣቶች ሊሰሩባቸው የሚችሉ ነገሮችን የመለየት፣ ወጣቶች በሚቀረፁ ፓኬጆች ባለቤት እንዲሆኑ የማድረግ፣ የወጣቶችን ቤተሰቦች ተሳታፊነት የማሳደግ ብሎም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በወጣቶች የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ትልሞችን ያነገበ ነው። ይህ የወጣቶች ተጠቃሚነት እዚያም እያለ ሴቶችን የሚጠቅም ነው—ምክንያቱም ከሀገራችን ወጣቶች ውስጥ ምናልባትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸውና።
እርግጥ ይህን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የሚደረገው ርብርብ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን አሊያም የሴቶችና ህፃናትን ሚኒስቴርን ብቻ የሚመለከት አይደለም። አዎ! ስራው የሁሉም አስፈፃሚ አካላት ይመስለኛል። እናም እነዚህ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ትግል ቁልፍ ተግባር አላቸው። በእኔ እምነት የወጣቶችንና የሴቶችን ችግር በመሰረታዊነት መፍታት ማለት የህብረተሰቡን ችግር ከሞላ ጎደል ማቃለል ነው። የህዝቡን ሰላምና ልማት በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጡም ማድረግ ነው። ይህ ሲሆንም መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያሰበውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በተሳካ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። ታዲያ እነዚህ ወሳኝ ሁኔታዎች የመፈፀምና የማስፈፀም ህዝባዊና ሀገራዊ አደራ የተጣለበት አዲሱ ካቢኔ፤ ከፊቱ የተደቀኑትን ጠንካራና ወሳኝ ስራዎችን በሚፈለገው የብቃት መጠንና በህዝባዊ ወገንተኝነት መወጣት ይጠበቅበታል።