የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ

በየአካባቢያችን እንደሚስተዋለው ወጣቱ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው እና በዚህም ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም መንግስት ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር ዳግም ስላለመጋለጧ ዋስትና የለም፤ በርግጥ ሁኔታውን በውል በመገንዘብ ወደ አዲስ አይነት አሰራርና መሰረታዊ ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቱን መንግስት ይፋ ማድረጉ የሚደነቅ ነው፡፡
በእርግጥ መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ቢቻልም ለዚህ ጽሁፍ አስረጅ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እና ማህበራቸውን መመልከት በቂ ነው፡፡ 
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ለበርካታ የወጣት ማህበራትና መሰል አደረጃጀቶች መመስረት መሰረት የጣለ፤ የከተማችን ወጣቶች በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ መሪ ተሳትፎአቸውን ያጐለበተ፤ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ፤ ስነ-ልባናዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን  በራሳቸው ጥረትና በባለድርሻ አካላት ድጋፍ መቅረፍ እንዲችሉ አደራጀቶ ያነቃነቀ አንጋፍና የብዙሃን ወጣቶች ማህበር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ማህበሩ ከተመሰረተባቸው አላማዎች መካከል የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑ የሚጠበቅና የማያከራክር ነው፡፡ በዚህ አግባብ በ2008 ዓ/ም ያከናወነውን ስንመለከት፤ በስራ እድል ፈጠራ ስራ አጥ የሆኑ 5113 አባላቱን በተለያዩ ቋሚና ጊዜአዊ የስራ አድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ከመቻሉም ባሻገር 11484 ብዙሃን ወጣቶችን የስራ ማማረጥና መናቅ አመለካከታቸውን መቅረፍ የሚችሉበትን ግንዛቤ በመፍጠር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የስራ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ ።   
በሁለንተናዊ ሃገራዊ ተሳትፎ ረገድም ከ138 ሺህ በላይ ወጣቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማነቃነቅ በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቱን የሚያመለክቱት መረጃዎች በተለይ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተዘጋጀውን ህዳሴ ሎተሪ በልዩ ሁኔታ እንደ ከተማ  በማስተዋወቅና እንዲሸጥ የማድረግ ስራን ከህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ም/ቤት ፅ/ቤት ጋር በመተባበርና ራሱን በቻለ እቅድ በመምራት ከ109,000 ብር በላይ ሎተሪ መሸጥ መቻልንም ያመለክታሉ።ይልቁንም በማህበር ደረጃ በስጦታና በቦንድ ግዥ ከ203276 ብር በላይ አስተዋፅኦ ማበርከት መቻሉ ከተንቀሳቀሰ የወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ መሆን የሚያስችል ጉልበትና አቅም ያለው መሆኑን ያመላክታል ፡፡
ከተሳትፎዎቹ ጥቂቶቹን ስንመለከትም በ98 ወረዳዎች 20,600 ወጣቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፋ የአካባቢ ፅዳት ዘመቻዎችን በማካሄድ 1444.7 ሜትር ኪዮብ ቆሻሻን በማስወገድ 918,239 ብር የሚገመት ወጪ አድኗል፤ ከሰብአዊነት ተግባር አንጻርም ከ546 በላይ የሚሆኑ የማህበሩ አባላትና ሌሎች ወጣቶች ደም እንዲለግሱ አድርጓል ፡፡
‹‹የአዲስ አበባ ወጣቶች የተሳትፎ የመደራጀትና የተጠቃሚነት የ1 ክፍለ ዘመን ታሪክ›› በሚል ርእስ በነባርና መስራች አባላት አማካኝነት የመወያያ ሰነድ እንዲዘጋጅ በማድረግ መላው አባላትና ብዙሃን የከተማው ወጣቶች በክ/ከተማ፤ በከተማና በወረዳ ደረጃ በድምሩ በ113 የፓናል ውይይት መድረኮች ከ50,800 በላይ ወጣቶች እንዲሳተፉና እንዲወያዩ በማድረግ ወጣቶች ስለስራ ፈጠራና ስለሰላም ግንዛቤ እንዲያገኙም መደረጉን የተመለከተው መረጃ ስለጉዳያችን ሁነኛ አስረጅ ነው፡፡
በተመሳሳይ መላው የማህበሩ አባላት በመንደርና ቀጠናዎች በህዝብ አቅም በሚከናወኑ የአካባቢ ልማት ስራዎች በኮሚቴ አበልነት ፤በጉልበት፤በፋይናንስ ፤በማቴሪያልና በእውቀት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ በተደረገጥረት 28,987 አባላትን ታሳታፊ ማድረግ የቻለው ማህበር የማህበሩ አላማዎች እንዲሳኩ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራቱንም ያመላክታሉ ፡፡
ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚህ ላይ በመመሰረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን በቶሎ ተገንዝቦ ተመጣጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤
ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና የተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአድልአዊ እና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት መደነቃቀፉ የፈጠረው የተስፋ ቢስነት ስሜት ቀደም ብለን ላየናቸውና ዋጋ ለከፈልንባቸው የግጭትና የትርምስ አደጋዎች የሚያጋልጥ መሆኑ ስለማያጠያይቅ ከዚህ የበለጠ መስራት አስፈላጊነቱ አያከራክርም፡፡ 
በመንግስት በኩል ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች ራሱን ወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል የሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰውም ለዚህ መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡
በዚሁ መሰረት መንግስት ከያዘው  የወጣቶች የማንቀሳቀሽ ፈንድ  ወጣቶች የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይ ማህበራት ልዩ ዝግጅትና የማንቀሳቀሻ ፈንዱን የሚመጥን አደረጃጀትና አሰራር ከወዲሁ መዘርጋት ያሻቸዋል ። ለዚሁ የማነቀሳቀሻ ፈንድ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ስነ ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከላይ የተመለከቱ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የ2009 ዓ.ም የመንግስት ትኩረት የአገሪቱን ወጣቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑም በንግግራቸው ተመልክቷል፡፡
ፈንዱ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆን መንግስት የገባው ቃል በብልሹ አሰራሮች እና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ተጠልፎ ወደባሰ ቀውስ እንዳይወስደን ደግሞ ወጣቱና ልማታዊው ሁሉ በአይነ ቁራኛ ተሳትፎ ማድረግና ሃብትና ንብረቱን ሊጠብቅ ይገባል። የሥራ ፈጠራው በሚያተኩርባቸው መስኮችም ላይ ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ይጠበቃል ። 
የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድን ተግባራዊ ለማድረግ የተያዘው እቅድ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የስራ እድል ፈጠራና የመልካም አስተዳደር ችግሮችኘ ለማስወገድ የሚያግዝ መሆኑም ይታወቃል። በመንግስት በኩል የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች በወጣቱ ዘንድ እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግና ማሳተፍም ለማንቀሳቀሻ ፈንዱ ስኬት አስፈላጊ ይሆናል።
በተጨማሪም መንግስት ወጣቱ ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ተከታታይነት ያላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም። የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በየደረጃው የሚገኙ ፈጻሚ አካላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከትም ይጠበቅባቸዋል።ከሁሉም የሚልቀው ግን በራሱ በወጣቱ በኩል የሚጠበቀው ነው።ከወጣቶች ተጠቃሚነት አኳያ ከላይ እንደማሳያነት ወስደን በመጠኑ የተመለከትነው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የአንድ አመት አፈጻጸም የሚያሳየውም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የወጣት ማህበራት አባሎቻቸውን የማንቀሳቀሻ ፈንዱ ተጠቃሚ ማድረግ ይችሉ ዘንድ ከወዲሁ መስራት ያለባቸው በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ መሆኑን ነው።
በየትኛው አግባብ ስለወጣቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የተቋቋሙ ማህበራት  አላማቸውን በላቀ ደረጃ ማሳካት የሚችሉት ከላይ እስከ ታች በየእለቱ  የሚያከናውኗቸው ተግባራት ዓላማዎቻቸው ላይ ብቻ ያተኮሩ ሲሆኑና ፣ በተለይም የብዙሃን ወጣቶች ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅሞችን በላቀ ድርሻ የሚያረጋግጡ ሲሆኑ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ  በተለይ አመራሩ ስለአባሎቹ ጥቅም በዚህ አግባብ ብቻ  መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡
የባከኑ አመታትን ለማካከስ ሰፋፊ እቅዶችን ወጥኖ በግዜ የለንም መንፈስ ያለ እረፍት መረባረብና የሙሉ ጊዜ ስራቸው የሆኑ አመራሮች ማፍራትና መመደብም የማንቀሳቀሻ ፈንዱን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል፡፡
መዋቅራዊ ጥንካሬን ማጎልበት ፤ አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ላይ በመመስረት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር፣ የምልመላ ስራዎችን ማጠናከር፤ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በሚማሩባቸው፣ በሚሰሩባቸው፣ በሚውሉባቸውና በሚያዘወትሩባቸው ሁሉም አካባዎች ላይ መዋቅር በመፍጠር በማስፋትና በማጠናከር  በርግጥም ማህበራቱ የብዙሃን ወጣቶች ማህበር መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራርን በማስፈን ይልቁንም አመነታን በማስገኘት የወጣቱን ተሳትፎ እና በተሳትፎው ልክ ጠቀሜታውንም የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
የአመራርና የአባል ወጣቶችን የመምራት፤የማቀድ የማሰማራትና አደራጅቶ የማነቃነቅ አቅምን ለመገንባት ተግባርን ማእከል ያደረገ የአመራር አቅም ግንባታ ስራዎችም ስለማንቀሳቀሻ ፈንዱ ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት የሚያሻው ይሆናል፡፡ በገቢ አቅም ማጐልበት ረገድ ወጣቱ የሚገኝበትን የገቢ አቅም መሰረት በማድረግ ሰፍፊ ተግባራትን ማሳካት በሚያስችል መልኩ አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመቀየስና ወጣት ተኮር ፕሮጀክቶችን ማበልፀግ የማንቀሳቀሻ ፈንዱንም ሆነ የባለድርሻ አካላትን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ያስችላል፡፡
አጠቃላይ ስራዎች የሚሳኩት  ማህበራቱ በዘረጉት በታችኛው መዋቅራቸው ጥንካሬ ልክ መሆኑን በመገንዘብ በብዙሃን ወጣትና በመላው ነዋሪዎች ዘንድ አስተማማኝ እግር መትከል አስፈላጊነቱ አያከራክርምና በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮቻቸውን ሁለንተናዊ አቅም መገንባት፣  በሰው ሃይልና ግብአት ማሟላትም ስለማንቀሳቀሻ ፈንዱ ተጠቃሚነት ትኩረት ከሚሹና ከወዲሁ ዝግጅት ሊደረግባቸው ከሚገቡ ቁም ነገሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡