ተጋላጭነትን መቅረፍና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር— ጥቃትን ለመመከት 

                                                       
ዛሬ አፍሪካውያን ከገቡበት የድህነት አረንቋ መላቀቂያ መንገዱን በግልፅ የተገነዘቡበት፣ ለተግባራዊነቱም እጅ ለእጅ ተያይዘው መንቀሳቀስ የጀመሩበት ወርቃማ ዘመን ላይ ደርሰዋል ማለት ያስደፍራል፡፡ ምክንያቱም ግጭቶችን የመፍታት ጥረታቸው በስኬት ታጅቦ የራስን ችግር የመፍታት አቅማቸው እያደገና እየጎለበተ ለፍሬ የበቃበት እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ድጋፍ ናፋቂነት አመለካከትም የከሰመበት ሁኔታ በመፈጠሩ አፍሪካዊው ትብብርና ትስስር ዋነኛ ትኩረትና የመፍትሄ አቅጣጫ በመሆን ላይ ስለሆነ ነው፡፡ 
እርግጥ አፍሪካውያን በጀመሩት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ አቋም እያደገ ከመምጣቱም በላይ፤ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመመስረት የትብብር መድረካቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መካከል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አንዱ ነው፡፡ 
እንደሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የኋላ ታሪክ በድህነት፣ በኋላ ቀርነትና ከከፋ የግጭት መድረክነት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይሁንና የእነዚህ ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው ‘ማንነታቸው’ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ተሻሽሏል። እናም ዛሬ ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝባቸውን ከችግር ማላቀቅ በሚገባቸው ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት መንገዶችን የመጠቀም አስፈላጊነትን ተገንዝበዋል፡፡ እነርሱም ውስጣዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የልማት ትልምን መከተል እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተቋማትን የማስፋፋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ 
ታዲያ እነዚህ አቅጣጫዎች በዋነኛነት የፀረ- ድህነት ትግሉን ከዳር የማድረስ ዓላማና ግብ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአንድ በኩል ሀገሮቹ በነፃነትና በሉዓላዊነት መርህ ላይ ተመስርተው ዕድገታቸውን የሚያፋጥኑበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጥሯዊ የጋራ ሃብታቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ተቀናጅተውና ተባብረው ለመስራት ምቹ ዕድል ይፈጥሩላቸዋል—“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው፡፡ 
እስቲ እነዚህን አቅጣጫዎች ተመርኩዘን የሀገራችንን ዕውነታ በመጠኑም ቢሆን እንዳስስ።…እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በመንግስትነት ከተመሰረተበት ከዛሬ 22 ዓመት ጀምሮ ሀገሪቱ በምትከተለው በመልካም ጉርብትና እና በጋራ አብሮ የመኖር ብሎም የማደግ መርህ ምክንያት ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ዝምድና መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህ መልካም ዝምድና እና ጉርብትና ከፖለቲካዊ ትስስሩ ባሻገር፤ በኢኮኖሚ ዘርፍ በኩልም በመሰረተ ልማትና የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራ የመጠቀምና ተያይዞ የመበልፀግ ተነሳሽነታቸውን እያጠናከረው መጥቷል፡፡
ታዲያ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የዜጎቹን እኩል ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ ዋነኛ ጠላት በሆነው ድህነትን የመቅረፍ ስራ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል ውስጣዊ ችግሮች ላይ በማተኮርና አቅም በፈቀደ መጠን እልባት በመስጠት ተግባር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት የማስፋፋት ስራን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 
የሀገራችን የፀረ- ድህነት ትግል በህዝቦች ሰፊ ተሳትፎ ታጅቦ በመጓዙና ችግሮቹን በመፈተሽ እንደ ክብደታቸው በቅደም ተከተል ለመቅረፍ በተከናወነው ብልህነት የተሞላበት መንግስታዊ አካሄድ ሀገሪቱንና የህዝቦቿን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ ብሎም ሀገራችንን ከአስሩ የዓለማችን የፈጣን ዕድገት ባለቤቶች ጎራ እንድትመደብ ያደረገ ነው፡፡ እርግጥ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዓይነተኛው ምክንያት መንግስት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየትና እልባት ለመስጠት ያከናወነው ጥረት መሆኑን መገንዘብ አዳጋች የሚሆን አይመስለኝም፡፡ 
እርግጥ ባለፉት 13 የዕድገት ዓመታት የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በተለይም የዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምላሽ መስጠቱ እንዲሁም የትምህርት፣ ጤና፣ የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማት ተቋማት እንዲስፋፉ ማድረጉ፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትህን የማግኘት ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን እንዲከናወኑ ባደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ላይ ዋነኛ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ የቆየችና የህዝቦቿን የልማት ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ መንቀሳቀሷን የሚያመላክት ሃቅ ነው፡፡ 
ያም ሆኖ ግን የውስጥ ተጋላጭነታችን አሁንም በሚፈለገው መጠን ተቀርፏል ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምንም እንኳን ሀገራችን ውስጥ የተገኘው ዕድገት ከህዝቡ ቁጥር መጨመርና በዚህ ሳቢያ በሚፈለገው መጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታም የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይመኙ እንደ ግብፅ መንግስት ዓይነት የውጭ ኃይሎች ከፀረ-ሰላምና ከሽብር ኃይሎች ብሎም ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ቤንዚንና እሳት አስታጥቀው በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ የውስጥ ተጋላጭነትን አቅም በፈቀደ መጠን መቅረፍ ይገባል፡፡ 
የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቅረፍ ባልቻልን ቁጥር ለውስጥና ለውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች ይበልጡኑ የሚጋለጠው ከሀገራችን የህዝብ ብዛት ውሰጥ እስከ 70 በመቶ ድረስ  የሚደርሰው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ኃይል ትኩስና ያለበት የዕድሜ ደረጃ በበቂ ሁኔታ ለማመዛዘንና ለስሜታዊነት ቅርብ የሚያደርገው በመሆኑ በቀላሉ ለእነዚህ ሃይሎች የውሸት ስብከትና አሉባልታ የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ወቅት በሚነሱ ውዥንብሮች ውስጥ ባለማወቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ከዚህ አኳያ ለወጣቱ በበቂ ሁኔታ ስራ በመፍጠርና ድጋፍ በማድረግ በዚህ ረገድ ሊፈጠሩ የሚችል ተጋላጭነትን መፍታት የግድ ይላል፡፡ 
እርግጥ መንግስት በወጣቶች ፓኬጅ ላይ የተጠቀሰውን ‘የወጣቶች ፈንድ’ በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገባ አስር ቢሊዩን ብር መድቦ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል፡፡ ይህ አንድ በጎ ጅምር ነው። ሆኖም ጅምሩ በተጠናከረ መንገድና ሁሉንም ወጣቶች ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል ደረጃ ይበልጥ መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። አዎ! ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቀነስ ከተቻለ፤ በየትኛውም አካል ሊሰነዘርብን የሚችለውን የጣልቃ ገብነት ጥቃት መመከት መቻላችን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡  
ከዚህ ጎን ለጎንም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን አግባብ ባለው መልኩ ምላሽ መስጠት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያስቀራል፤ ይመክታል፡፡ በተለይም በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እስታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ዘልቆ መፍታት ተገቢ ነው፡፡ 
እርግጥ መንግስት ችግሩን በጥልቀት ካስጠና በኋላ በየደረጃው የመፍትሔ ሃሳቦችን አስቀምጧል፤ የእርምት እርምጃዎችንም ወስዷል። ከህብረተሰቡ ጋርም በጥልቀት እየተወያየ መፍትሔዎችን እየሰጠ ነው። ይህም ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት ቀዳዳ ባለመተው የተጀመረውን የህዝብና የመንግስት ውይይትና መግባባት ይበልጥ ማጠናከርና ወደቸሬት አውርዶም አመኔታ መፍጠር የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ከሆነ የውጭ ጣልቃ ገቢዎችም ይሁኑ ተላላኪዎቻቸው ምንም ዓይነት አጀንዳ ሊኖራቸው አይችሉም፤ ብሶትን የሚያራግቡበት ቀዳዳም አያገኙም። 
በተፈጥሮ ሃብት ከቀጣናው ሀገሮች ጋር ፍትሐዊ በሆነና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መንገድን ተከትሎ መጓዝም ትስስርን ከማጠናከር ባሻገር፤ በሀገራቱ መካከል የእኔነትን ስሜት የሚፈጥር በመሆኑ የውጭ ጣልቃ ገብነትንና ጥቃትን የሚመክት ሌላኛው አካሄድ ነው።  
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ኢትዮጵያ ከማንኛውም የጎረቤት ሀገር ጋር የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን በቅንጅት ለመስራት ያሳየቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው—ላለፉት 25 ዓመታት፡፡ ሀገራችን ባደረገቻቸው በዚህ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሁለትዮሽ ስምምነት፤ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ የመንገድ፣ የኤሌትሪክና የንግድ ትስስር መፍጠር ችላለች፡፡ 
ዛሬ የሱዳንና የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የኢትዮጵያ እንዲሁም የጅቡቲና የኢትዮጵያ ህዝቦች የእኛ የሚሉት የጋራ የሃይል አቅርቦት አላቸው፡፡ የእርስ በርስ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶችን የማሳደግ ሚና ባለው ሁኔታም በመንገድ መሰረተ- ልማት ተሳስረው የጋራ ተጠቃሚነታቸውንም በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ እርግጥ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ከሚያጋሯቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዓባይ ወንዝ መሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድም ሀገራችን ምንም እንኳን ዓባይ አንጡራ ሃብቷ ቢሆንም፣ ከወንዙ ጋር ተያይዞ በጋራ ተጠቃሚነት የሚያስተሳስር መርህን ተከትላ ዛሬ ላይ ደርሳለች። 
ይህ መርህዋም በአንድ በኩል ሃገራዊ ልማትን የማሳደግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለጎረቤት ሀገሮች የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት አሰራር ነው። በዚህ ረገድ ለጎረቤት ሀገሮች ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ሃይል ሊሰጥ የሚችለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማስተዋወቅ ጭምር በትብብር የመስራት ፍላጎቷን አረጋግጣለች፡፡ በዚህም የግድቡ ፕሮጀክት የትብብርና የጠንካራ ትስስር መፍጠሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ቁርጠኝነቷን አሳይታለች፡፡ 
በመሰረቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሁለት አባይት ዓላማዎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያ የሀገራችን የዕድገት ማነቆ የሆነውን የሃይል አቅርቦት እጥረት በመፍታት ሀገራዊ ልማቱን የማሳደግ ዓላማን ያነገበ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደግሞ፤ የጎረቤት ሀገሮች ከዚህ ግድብ ከሚመነጨው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ነው፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራትም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ግድቡ የአፍሪካ ህብረት ያሰቀመጠውን በሃገራት መካከል ጠንካራ ትስስር የመፍጠር ራዕይን የሚያሳካ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የትብብር ፕሮጀክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እናም ይህን ቀጣናዊ ትስስር በሁለንተናዊ መልኩ አጠናክሮ መቀጠል ከውጭ ጥቃት ተጋላጭነት ይታደገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እናም በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ካለው የትስስር ድር በላይ ጠንክሮ መስራት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን የፕሮጀክቱን ጠቀሜታና ዓላማ የተገነዘቡ ጎረቤት ሀገሮች አዎንታዊ ምላሻቸውን በግልጽ አራምደዋል፡፡ በተለይ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኡጋንዳና ሱዳን፣ ፕሮጀክቱ የማንንም ጥቅም የማይነካ እንደሆነና ለስኬታማነቱም ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን  እንደሚቆሙ አቋማቸውን በተለያዩ ጊዜያት በይፋ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቱን በበጎ ዓይን ያልተመለከቱና “የያዙኝ ልቀቁኝ” ጩኸታቸውን ማሰማት የጀመሩ እንዲሁም የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚያስችሉ እኩይ ሴራዎችን ቀይሰው ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ኃላፊነት የጎደላቸው እንደ ኦነግና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የጨለማው ዘመን የሽብር አቀንቃኞች አልታጡም—የኢትዮጵያን ህዝቦች ንብረት በተላላኪነት የማደናቀፍ ልፋታቸው የቀን ቅዥት እንደሚሆን ቢታወቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በአንዳንድ በግብፅ ተቋማት ላኪነትና በሀገራችን ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች እንዲሁም በፅንፈኛ ዲያስፖራዎች አማካኝነት የህዳሴውንም ግድብም ይሁን በማናቸውም የሀገራችን የውስጥ ጉዳዩች ላይ ጣልቃ በመግባት የሚሰነዘሩ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት፤ የውስጥ ተጋላጭነታችንን በተገቢው መንገድ መቅረፍና ቀጣናዊ የምጣኔ ሃብት ትስስርን ይበልጥ ማጠናከር ፍቱን መድኃኒት ይመስለኛል፡፡