ሰላም፤ ሰላም ለኢትዮጵያ

                                                                                 
ለአንድ ሀገር ልማትና እድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ አለው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ የሀገርም የህብረተሰብም የቤተሰብም፡፡ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ አይሰላም፤ ተመንም ሆነ መስፈሪያ የለውም፡፡ ከግለሰብ የነገ የማደግና መለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም አይነት ራእይና ተስፋዎችን ማሳካት አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው የሀገር በሰላም ውሎ ማደር የህዝቦችዋ ሰላም የሚሆነው፡፡ ስለሆነም ሰላማችን ይበዛ ዘንድ ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም ዘብ መቆም አለብን የሚባለው፡፡ 
የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ግዴታና ሀላፊነት የህዝብ ነው፡፡ ህዝቡ በያለበት ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጠው የትኛውም ሀይል ሀሳቡን ማሳካት አይችልም፡፡ ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም አይነት ንብረቶች የግለሰቦችን ሀብት ለማውደም አይበቃም፤ ይጠብቃቸዋል እንጂ በምንም አይነት መንገድ እንዲወድሙ አይፈቅድም፡፡
ህዝብ ገሳጭ ነው፤ በዚህ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩትንም ሆነ ሊሰማሩ የተዘጋጁትን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያደርጋል፡፡ እውነታው ይሄ ስለመሆኑ ደግሞ ሰሞኑን ከሰፈነው ሰላምና መረጋጋት አንጻር በተግባር እያየን ነው፡፡ ህዝቡ ሰላሙንና መረጋጋቱን አጥብቆና አጠንክሮ መጠበቅም ይገባዋል፡፡ ከመንግስትም በላይ የሰላሙ ባለቤት፣ ዋናው ተጠቃሚና ሊንከባከበውም የሚገባው ህዝብ ነውና ይህ ሊሆን የግድ ነው፡፡ 
በህዝብ ውስጥ የተፈጠረውን ቅሬታ የመልካም አስተዳደር፤ የፍትህ እጦት፤ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት፤ የመንግስትን ስልጣን ያለአግባብ የመጠቀምና ለግል ፍላጎት መጠቀሚያ የማድረግ ችግሮች  በራሱ በገዢው ፓርቲ ግምገማ የተደረገባቸውና ጥልቅ ተሀድሶ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም የተያዘባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ ችግሮቹ ሊፈቱ የሚችሉት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመስራት መተማመኑ እየጎለበተና እየዳበረ ሲሄድ ጭምር ነው፡፡
ከገዥው ፓርቲ ጠንካራ ጎኖች በተጓዳኝ በስራ ሂደቱ ውስጥ የተከሰቱ፣ በተጨባጭ የታዩ፣ ራሱም ያመነባቸው፣ ህዝቡም የገለጻቸው ደካማ ጎኖች አሉት፡፡ ይህንን ለማረም የሚቻለው ህዝቡም ሆነ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት በህጋዊና ሰላማዊ ማእቀፉ ውስጥ ሁነው ጫና በመፍጠር ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ የበኩላቸውን ሀላፊነት መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀድሞ ከነበረውና ትኩረት ሳይሰጠው ከቆየው ሁኔታ ውስጥ በመውጣት በጋራ  ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ተነጋግሮ የመስራቱ ባህል እየሰፋና እየጎለበተ መሄድ ይገባዋል፡፡ ህዝቡ ለመብቱ መከበር ያደረገውን ትግል ያሰማውን ተቃውሞ ተገቢነት ኢህአዴግ ተቀብሎ አክብሮቱን መግለጹ ተገቢ ቢሆንም፣ የዚያኑ ያህልም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን ችግሮቹ መፈታት ያለባቸው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ጽንፍ የወጣ መንገድ ለሀገርም ለህዝብም አይበጅም፡፡ የህዝቡን የመብቴ ይከበርልኝ ህጋዊ ጥያቄ በመጥለፍ ሊጠቀሙበት የሞከሩት ጽንፈኛ ተቃዋሚዎችና የውጭ ሀይሎች አጀንዳቸውን ለማሳካት በማቀድ የመንግሰትን፣ የህዝብንና የግለሰቦችን ንብረት ጭምር በጥላቻ ተሞልተው በእሳት አጋይተዋል፤ መሰረተ ልማቶችን አፈራርሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ በመሆኑ የተጎዳው ህዝብ ነው፡፡
ኦነግ፣ ግብጽና ሌሎችም ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ ሀይሎች ተቀናጅተው ወኪሎቻቸውን በማሰማራት በእርዳ ተራዳ ተሰልፈው የሀገሪቱም ሆነ የህብረተሰቡ ሰላምና መረጋጋት እንዲታወክ፣ ስርአተ አልበኛነት እንዲሰፍን፣ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል፤ በዚህም ተጎጂው ህዝብ ነው፡፡
እነዚሁ ሀይሎች በፈጠሩት ቀውስ ትርምስና ግጭት በርካታ ዜጎች ህይወታቸው አልፎአል፡፡ ከስራ፣ ከኑሮአቸውና ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሰላማቸው ደፍርሶ ጭንቀት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በአንድ ድሀና ታዳጊ የእድገትና የልማት አቅጣጫን ይዛ በመስራት በምትተጋ ሀገር ውስጥ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ንብረቶችን ማውደም ምን ያህል ጉዳት እንዳለው ምን ያህልስ ከነበርንበት የተሻለ ደረጃ መልሶ ወደኋላ እንደሚጎትተን ለማንም አይጠፋውም፤ በድርጊቱ ተጎጂዎች እንጂ ተጠቃሚዎች ልንሆንም አንችልም፡፡
ስንት የተለፋና የተደከመበትን የህዝብና የመንግስት ሀብት፣ የሰው ጉልበት የፈሰሰበትን ንብረት ማውደም ሀገሬን ወገኔን እወዳለሁ ከሚል ዜጋ ሊታሰብ አይችልም፡፡ ተልእኮው ሀገሪቱን ለማጥፋት የከፋ ጠላትነት ይዘው ወኪሎቻቸውን በማሰማራት የዘመቱት የውጭ ሀይሎች ለዚሁ ወንጀለኛ ድርጊታቸው ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ሰዎችን በመደለል የፈጸሙት እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ሰላሙን፣ ሀብትና ንብረቱን መጠበቅ፣ አገርን ከእንዲህ አይነቱ ጥፋት መከላከል ያለበት ህዝብ ነው፡፡ በጭፍን ተቃውሞ የሚነሱ በስሜታዊነት የተሞሉ ተቃውሞዎች በሀገርና በህዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከባድ ሲሆን ለትላንቱ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም እንዲህ አይነቱ ድርጊት እንዳይደገም ነቅቶ መከላከል የሚገባው ሁሉም ዜጋ በመረባረብ መሆን አለበት፡፡ ከሚለያዩን ይልቅ በጋራ የሚያቆሙን እጅግ የበዙ እሴቶች አሉን፡፡ የተሳሰረና ከቶውንም ሊያለያየን የማይችል እንደ አለት የጠጠረና የማይፈረካከስ ለዘመናት የዘለቀ የጸና በክፉውም በደጉም የሚያገናኘን የጋራ እኛነታችን የጎላና የደመቀ ነው፡፡ ማህበራዊ ትስስራችን፣ እድሮቻችን በሰርጉ፣ በሀዘኑ፣ በልደቱ፣ በእቁቡ፣ በአብሮአደጎች/ጓደኞች ማህበር፣ በጸበል ጻዲቅ፣ በጽዋው ማህበር፣ በአበልጅነቱ፣ በሽምግልናው ወዘተ እጅግ በበዙ ድሮች የተሳሰርን፣ የተቆራኘን፣ ጥንትም የነበርን፣ ዛሬም ያለን፣ ነገም  የምንኖር ህዝብ ነን፡፡
ችግሮችን በውይይት በሽምግልና በታላላቆች ፊት በሀገራዊ ባህላችን ወግና ልምድ መሰረት ስንፈታ፤ ጥፋተኛም ሲቀጣ ተመልሶም በሰላም ሲኖር ነው የማህበራዊ ህይወታችን መሰረቱ።  እነዚህን የመሳሰሉ እሴቶች ከእናት አባቶቻችን ወርሰን በተግባርም እያዋልን የኖርን ነን፡፡ ሰላማችንን በዚህ መልኩ የማስጠበቅ ወግና ባህሉ አለን፤ ልንጠብቀውም ይገባል፡፡
ከአብሮነታችን አልፈውና ገዝፈው ለመለያየት የሚያስችሉ መሰረቶች የሉም፡፡ ድህነትን መታገልና ማስወገድ በሀገሪቱ ጤናን ትምህርትን መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ስራአጥነትን ለመቅረፍ መታገል የጋራ የሆነውን የሀገር ሰላምና ደህንነት ከውጭ ሀይሎች መጠበቅ ከብዙው በጥቂቱ በጋራ የሚያቆሙን ጉዳዮች ናቸው፡፡ በሀገር ሰላም መደፍረስ ህዝብ ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ምናልባት በዚህ እንጠቀማለን የሚል ቢኖር በሁከትና በብጥብጡ ዘርፌ ነጥቄ አገኛለሁ እከብራለሁ ብሎ የሚያስበው ወገን ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ህዝብ ሰላሙ እንዲታወክ አይፈቅድም፡፡ የታወከውን ሰላም መልሶ ያረጋጋውም ህዝቡ ነው፡፡ የወደሙትን ንብረቶች እንደገና ለመተካት ለመስራት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ ያለውም ህዝቡ ነው፡፡
በአንድ ከድህነት ለመውጣት ወሳኝ ትግል እያደረገች ባለች ሀገር ውስጥ የተገነባውን ማፍረስና ማውደም የለየለት የህዝብ ጠላትነት እንጂ ለህዝብ ማሰብ ሊሆን አይችልም፡፡ ህዝቡ የሚሰራበትን ድርጅት ፋብሪካ የእርሻ ቦታ የመንግስት ቢሮዎች አምቡላንስ ወዘተ ማንደድና ማጋየት ህዝቡን ወደ ስራ አጥነት፣ ወደ ድህነት ከመክተት ሌላ አላማ የለውም፡፡ ይህ ደግሞ የአክራሪና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ዋና አጀንዳ ሲሆን የሚመራውም በኦነግ፣ በእስላማዊ አክራሪው የጀዋር መሀመድ ቡድንና በግብጽ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ፡፡ 
ከእንግዲህ ኦነግም ሆነ ጀዋር መሀመድ፣ ግብጽም ሆነች ኤርትራ ሌሎችንም ጨምሮ እንዳሻቸው የሚፈነጩበት መሬት የሚያሰማሩት ተላላኪና ወኪል በኢትዮጵያ ውስጥ ለመፈንጨት የሚችልበት ቦታ አይኖረውም፡፡ ስለሀገር አንድነትና ስለህዝብ ሰላም ሲባል  እጃቸው ይቆረጥ ዘንድ የግድ ነው፡፡ በእንዲህ አይነቱ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት ትግሉ የሀገሪቱን ህልውና፣ ሉአላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ጉዳይ ስለሆነ በይቅርታ የሚታለፍ አንድም ነገር አይኖርም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡
መንግስት አምኖ የተቀበለው የህዝቡ ችግር የሚፈታው ሀገር በማውደም በማጋየት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይህንን የህዝቡን ቅሬታና ተቃውሞ በመጠቀም ቀዳዳውን በማስፋት ሀገሪቱን ወደከፋ ሁከት ውስጥ ለመክተት ህገወጥነትና ስርአተ አልበኝነት እንዲሰፍን ለማድረግ ሲራወጡ የነበሩት የግብጽ ቡችሎችም ሆኑ የቀለም አብዮት ናፋቂዎች ኢትዮጵያን እንደሊቢያ እንደ ሶርያ እንደ የመንና ሌሎችም መበታተን ማጥፋት ማውደም እንደማይችሉ ለዚህ የሚሆን እድል እንደሌለ በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
ከግብጽም ሆነ ከሻእቢያ ጋር የተሰለፈ ማንኛውም ሀይል ጸረ ኢትዮጵያ መሆኑ በተጨባጭ የታየበት የተረጋገጠበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ይሄንን እንደ መልካም ትምህርትና ልምድ የተገኘበት አጋጣሚ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ቀደም ሲልም እነዚህ ሀይሎች ለኢትዮጵያ ተኝተው አያውቁም፡፡ ዛሬ አይደለም ወደፊትም አይተኙም፡፡ የሚጠበቀው የእርስ በእርስ መናቆሩንና መባላቱን አስወግደን ስግብግብና የማይጠግቡ ለህዝብ ምሬትና መከፋት ብስጭት ምክንያት የሆኑትን ሙሰኞች ኪራይ ሰብሳቢዎች የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጠንቆችን በህግ ተጠያቂ በማድረግ ተጠያቂነት ያለው ህጋዊ አሰራር በማስፈን የህዝቡን ችግር በመፍታት በጋራ ለሀገሩ ለሰላሙ እንዲቆም ማድረግ ብቻ ነው፡፡
ይህ ችግር ሊፈታ ካልቻለ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ አይነት ሁኖ ለግዜው ዝምታን ቢፈጥርም ተመልሶ የባሰ ችግር እንዳይወልድ መጠንቀቁም ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ህዝቡ የሚታይና የሚጨበጥ ጥልቀት ያለው ተሀድሶና እርምጃ ከመንግስት ይጠብቃል፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ የግለሰቦች ሹም ሽር ብቻ እንዲሆን ህዝቡ አይፈልግም፡፡ አንዱን አንስቶ ሌላውን መተካት ወይንም ከታች አንስቶ እላይ ማውጣት ብቻውን መፍትሄ መሆን አይችልም፡፡
በራሱ በመንግስት ሲነገር የነበረው ከህግና ከስርአት ውጪ በጥቅም ግንኙነት በየደረጃው የተዘረጋውና ለአመታት የዘለቀው የዘረፋና የነጠቃ መረብ እስካልተበጣጠሰ ድረስ ለትንሽ ግዜ የተሻለ መስሎ ቢቆይም ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም እንደሚባለው አዲሶቹን ተሿሚዎች በተለመደው መረባቸው ጠልፈው እንደማያስገቡዋቸው ምንም መተማመኛ አይኖርም፡፡
የክትትልና ቁጥጥር ስርአቱ በነማን ይመራል? የሚለውም የተለየ ትኩረትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ የተካኑትን ሰርቶ ሳይሆን ዘርፎ አደሮች ሙሉ በሙሉ ከየትኛውም መንግስታዊ ሀላፊነትና መዋቅር ውስጥ ማራቅ ካልተቻለ አሁንም ችግሮቹ በባሰና በከፋ ሁኔታ ሊከሰቱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ከጀርባ ሁነውም ረዥሙን እጃቸውን መልሰው ከመስደድ እንደማይቆጠቡ ህዝቡ በተደጋጋሚ ካሳለፈው ተሞክሮ በሚገባ ያውቃል፡፡ ለህዝብና ለሀገር ሰላም ሲባል የዘረፉትን ሀብትና ንብረት በህግ ተጠይቀው ሊመልሱ ይገባል፡፡
ይህ ካልሆነ ዛሬ የሚሾሙትም ሆነ ነገ የሚመጡት ትላንት የዘረፉት መቼ ተጠያቂ ሆኑና ነው እኛንስ ማን ይነካናል የሚል መጥፎ ምሳሌ እንዳይፈጥር ማሰብም ተገቢ ነው፡፡ በሀገራችን ለተከሰተው የሰላም መደፍረስ የመጀመሪያው ዋነኛ ምክንያት ህዝቡን ያስመረረውና ያንገፈገፈው ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል በፍትህ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በመሬት ቅርምትና ዘረፋ ላይ የፈጸመው ግፍና በደል ነው፡፡
ይሄው ሀይል በህግ ተጠያቂነት እንደሚመጣ ሲያምን በዘረፋ ያካበተውን ገንዘብ እየረጨ በዘረጋው መረብ አማካኝነት በተለይ በኦሮሚያ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶአል፡፡ የህዝቡ ህጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሁከቱን ማጋጋምና እንዲባባስ ማድረግ በመንግስት ደረጃ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረውን ትግልና መሪ አጀንዳ ማደብዘዝ ይቻላል በሚል ያደረጉት ነው፡፡ በትክክልም ተሳክቶቸዋል፡፡ አጀንዳውን አስቀይረውታል፡፡
ሁከቱና ብጥብጡ መልኩን ቀይሮ በየቦታው እየተዛመተ ሲመጣ ብሄራዊ አጀንዳው ሰላምና መረጋጋት በነበረበት ቦታ መመለስ ሆነ፡፡ በዚህ ቀዳዳ በመጠቀም ኦነግና ግብጽ ሻእቢያም ሌሎችም ተቀናጅተው ሀገሪቱን የማፈራረስ አላማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቀሱ፤ በዚህ አጋጣሚም በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር ተከሰተ፡፡
አሁንም በሰላምና በውይይት ሊፈታ የሚችለውን የህዝቡን ጥያቄ ለመጥለፍ ጽንፈኛውና አክራሪው ተቃዋሚ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ እኔ ነኝ የመራሁት የለም እኔ  ነኝ የሚል እሰጥ አገባ ውስጥ ገባ፡፡ ህዝቡ እጃችሁን ከእኔ ላይ አንሱ በስሜም አትነግዱ አላቸው፡፡ በመሰረቱ ተቃውሞውን ተቃዋሚዎች አልመሩትም፡፡ አላደራጁትም፡፡ ለመጥለፍ ነው የሞከሩት፡፡
በዚህ ሁሉ ትርምስና ሁከት ግጭት መሀል የተጎዳው፣ ንብረቱ፣ ሀብቱ የወደመውና ልጆቹን የተነጠቀው ህዝቡ ነው፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራው አካባቢ የወደመው ሀብትና ንብረት ድርጅቶች፣ እርሻዎች በህዝቡ የተደረጉ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄንን እኩይ ተግባር ለመፈጸም በውጭ ሀይሎች ተመልምለው የተሰማሩ ግለሰቦች ሁኔታውን ወደከፋ ደረጃ ለማድረስ በማሰብ የፈጸሙት ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር ወንጀለኛ ድርጊት ሲሆን ልንታገለውም ግድ ነው፡፡