የአዲሱ ካቢኔ መነሻም  ሆነ መድረሻ የሕዝብ እርካታን መፍጠር ነው!

በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛው ዙር ምርጫ በተወዳደረባቸው አራት ክልሎች ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ መንግሥት የመሰረተው ኢህአዴግ አዲሱን የስልጣን ዘመን ሲጀምር ብዙዎች በተለይ ራሱን ሊያርም ይችላል በሚል ተስፋ የመረጡት ዜጎች አዲስ ነገር ጠብቀው ነበር። ኢህአዴግ ስልጣን በተረከበበት ዋዜማ ባካሄደው 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ስር እየሰደደ መሆኑን አምኖበት ችግሮቹን መፍታት ካልቻለ ህልውናው እንደሚያከትም አሳውቆ ስለነበረ ብዙዎች አዲስ ነገር እንዲጠብቁ ያደረጋቸው፤ 
ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ስራ በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁሉም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገኙበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት ስብሰባ ላይ ቀርቦ የነበረው በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የተመለከተ በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ የተደረገው ውይይት የመልካም አስተዳዳርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከአገራችን ተጠራርጎ ሊወጣ ነው የሚል ተስፋ ፈጥሮ ነበር። በጥናታዊ ጽሁፉ ላይ ውይይት የተደረገበት መድረክ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ሕዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጠያ መሆኑ ተነግሮ ነበር። ከዚያ በኋላም በየደረጃው ተመሳሳይ የሕዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጣያ መድረኮች ይካሄዳሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክለሎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከት የተባለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ውል አሳጣው። በአገሪቱ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ጢም ብሎ ሞልቶ ስለነበረ፤ በድንገት ገንፍሎ በተለይ ወጣቱ ችግሩን ለመፍታት ታጥቄአለሁ የሚለውን መንግሥት ተናነቀ። እርግጥ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልም ያላቸው ቡድኖችና የአገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ሁከቱን አፍራሽ በሆነ አኳኋን እንዲባባስ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው መሆኑ አይካድም።
ያም ሆነ ይህ፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ 2008 ጥቅምት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረው ካቢኔ አምስቱን የመንግስት የስልጣን ዘመን መዝለቅ አልቻለም። የካቢኔ አባል መሆን ብዙም እውቀት አያስፈልገውም፣ ፖሊሲ የማስፈጸም ስራ እውቀት ሳይሆን መሰጠት ነው የሚያስፈልገው ብለው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም፤ ይህን ተናግረው አንድ ዓመት እንኳን ሳይደፍኑ ብቃት የሌለው አስፈጻሚ የአገሪቱን ችግሮች ፈትቶ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት አይችልም ብለው መጡ። እናም ሰሞኑን ልክ እንደአዲስ መንግሥት ምስረታ ዘመን አዲስ ካቢኔ አዋቅረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቅላቸው ይዘው ቀረቡ። እርግጥ በተጨባጭ ያለውን እውነታ ተረድቶ አቋምን በይፋ ማስተካከል በራሱ የአዋቂነት መገለጫ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከተሉት አካሄድ የሚያስመሰግናቸው ነው።
አሁን ልክ አዲስ የስልጣን ዘመን የተጀመረ ያህል አዲስ ካቢኔ ተዋቅሯል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ባለፈው ዓመት አገሪቱ ከገጠማት ሥርዓቱን ለአደጋ ያጋለጠ ፈተና ለመውጣት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የነበረውን የድርጅቱንና የመንግሥትን አሰራር ገምግሞ በድርጅቱና በመንግሥት ውስጥ የአመራር ችግር መኖሩን መለየቱን አስታውቋል። ይህንንም ችግር የአመራር ብቃትና ብልሽት ችግር መሆኑንም ነግሮናል። የብቃት ማነስ፤ የቴክኒክ እውቀትና ብቃትን የሚመለከት ሲሆን፤ ብልሽቱ ደግሞ የመንግሥትን ስልጣን ሕዝብን ለማገልገል ከማዋል ይልቅ ለግል መጠቀሚያ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ችግር መሆኑ ነው የተነገረን፤ ከዚህ ሕዝቡን ማርካት ከተሳነው የአመራር ብቃት ጉድለትና ብልሽት ለመውጣት ጥልቅ ተሃድሶ ማካሄድ ያስፈልገኛል ብሏል።
ይህ ጥልቅ ተሃድሶ በቅድሚያ ብቃት ያላቸውን የመንግሥት ኃላፊዎች መመደብን ያመለከታል። የብቃት ችግሩ ቀደም ሲል የመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ከቴክኒካል እውቀት ብቃት ይልቅ የፓርቲውን ፖሊሲ በማወቅና በመቀበል፤ ለማስፈጸም ባለ ቁርጠኝነት መመዘኛነት ላይ በመመስረት የሚሰጥ በመሆኑ ተፈጥሯል የሚል እምነት መኖሩን ድርጅቱ ገልጿል። በዚህ ሁኔታ የተፈጠረውን የአመራር ብቃት ክፍተት ለመሙላት ሕዝብን የማገልገል ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን ግን የድርጅቱ አባል ያልሆኑ ዜጎች ከየትኛውም ቦታ በማምጣት የመሾም አማራጭ ተቀምጧል። የጥልቀት ተሃድሶው ሌላኛው እርምጃ ከሕዝባዊ አገልጋይነት ዝንባሌ መጥፋት የተፈጠረውን የአመራር ብልሽት ማስተካከል ነው። ይህም በተመሳሳይ ሁኔታ ከድርጅትም ሆነ ከየትኛውም ቦታ የሚገኝ ብቃትና የሕዝብ አገልጋይነት ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በመመደብ የሚከናወን መሆኑ ተነግሮናል።
እንግዲህ ይህን በጥልቀት የመታደስ እሳቤ በቅድሚያ በተገለጸው አኳኋን አመራር በመሾም የተገበረው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፓርቲው አባላት ያልሆኑና በፓርቲው ውስጥ ተራ አባል የሆኑትን ብቃትና የህዝብ አገልጋይነት ዝንባሌ አላቸው ብሎ ያመነባቸውን አስሰፈፃሚዎች ሾሟል፤ ከአንድ ሳምንት በፊት። በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ጥቅምት 22፣ 2009 ዓ/ም ደርሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርታም ደሳለኝ ብቃትና ይህዝብ አገልጋይነት ፍላጎትን አጣምረው የያዙ ያሏቸውን የካቢኔ አባሎቻቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስጸድቀዋል።
ይህ በጥልቀት የመታደስ ቀዳሚ ርምጃ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ብሄራዊ ድርጅቶች በሚመሯቸው የአማራ፤ የትግራይና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታትም የቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ የየክልሉ መንግስትና ገዢ ፓርቲዎች ባካሄዱት ግምገማ የብቃትም ሆነ የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ጉድለት ያለባቸው ሳያገኙ ቀረተው ሊሆን ይችል ይሆናል። በአጠቃላይ የብቃትም ሆነ የህዝብ አገልጋይነት ፍላጎት እጦት በክልልና በፌደራል ከፍተኛ አመራር ደረጃ ብቻ ሳየሆን እሰከቀበሌ ባለ የመንግስት መዋቅር ውስጥና በየደረጃው ባለ አመራር ዘንድም ያለ በመሆኑ በጥልቀት መታደሱ እዚያ ድረስ መዝለቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ በጥልቀት የመታደሱ ነገር ከሚዲያ ወሬ ያለፈ ፍሬ ማፍራት አይችልም። ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግም አይቻልም፤ ህዝቡ መንግስት ላይ እንዳይቆጣ ማድረግም አይቻልም።
እንግዲህ በጥልቀት የመታደሱ መድረሻ የከፍተኛ አመራር ለውጥና ሽግሽግ ማድረግ አይደለም። ይህ መነሻ ነው። መድረሻው ሕዝብን በተገቢው መንገድ በማገለገል እርካታ መፍጠር ነው። በአመራር ደረጃ ስላለው መታደስ ይህን ያህል ብዬ የታደሱ አስፈጻሚዎች እንዲያከናውኗቸው ከሚጠበቁ ተግባራት የተወሰኑትን ልመልከት፤ በተለይ ቀጣዩን የመንግሥት አፈጻጸም በተመለከተ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ያቀረቡትን ንግግር መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች በተወሰኑት ላይ አተኩራለሁ። እነዚህም የወጣቶችን ተጠቃሚነት፤ መልካም አስተዳደር ማስፈንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን የሚመለከቱ ናቸው።
ወጣቶች ከአገሪቱ ልማት በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉበት ሁኔታ የአገሪቱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ ወጥቷል። በተለይ የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር ወጣቱን ተስፋ በማስቆረጥ በመንግሥት ላይ እንዲቆጣ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። ይህ ተስፋ ቆርጦ የተቆጣ ወጣት ደግሞ አገሪቱን ማፈራረስ ለሚፈልጉ ቡድኖችና የኢትዮጵያ ጠላቶች  የተመቸ ሁኔታ ፈጥሮ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ አገሪቱን ለትርምስ በማጋለጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ጥሏል። በዚህ የተነሳ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን አስመልክቶ  ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የወጣቶችን  ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋናው የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል። ለዚህም ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ያለውን የፋይናንስ ችግር ለማቃለል በመደበኛነት ለወጣቶች ተጠቃሚነት ከተያዘው ፋይናንስ በተጨማሪ መንግስት 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ ፈንድ ማቋቋሙን አረጋግጠዋል። ወጣቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉትን ሥራዎች መለየት፤ ወጣቶች በሚቀረጹ ፓኬጆች ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ፤ የወጣቶችን ቤተሰቦች ተሳታፊነት ማሳደግ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በወጣቶች ልማት ጉዳይ ውስጥ ማሳተፍ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተብለው መለየታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ሌላው ሕዝብን አስቆጥቶ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ ያጋለጠው ጉዳይ የመልካም አስተዳደር መጓደል ነው። የመልካም አስተዳደር መጓደል አልፎ አልፎ የሚታይ ሳይሆን በሁሉም የመንግሥት ተቋማትና  የአስተዳደር መዋቅሮች ደረጃ በአዋጅ የተነገረ እስኪመስል የተንሰራፋ ነው። ይህ ሁኔታ ሕዝብ በመንግሥት ላይ የመረረ ቅሬታ እንዲያድርበት አድርጓል። በዚህ ዙሪያ ሊሰራ የታሰበውን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሕዝቡን መልካም አስተዳደር ጥያቄ በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ማለት ሕዝቡ ከመንግሥት የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በፍጥነት፤ በጥራት እና በቅንነት የማግኘት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። የፖለቲካ አመራሩም ይሁን በፐብሊክ ሰርቪስ የተሰየሙ አመራሮች እነዚህን ባሟላ መልኩ ሕዝቡን ማገልገል እንደሚገባቸው፤ ይህንን ለማድረግ ዋናው ሥራ አመለካካትን መቀየር በመሆኑ በዚህ ዙሪያም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ከዚህ ባሻገር ጊዜ እና ሀብት የሚጠይቁ የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች መኖራቸውን አንስተው፤ ከነዚህ ውስጥ የመሰረተ ልማት ጥያቄ አንዱ መሆኑን፤ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደግሞ ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው የምንችለውን በመስራት፤ አቅም የማይፈቅዳቸውን ደግሞ ከሕዝቡ ጋር ተነጋግሮ በመተማማን መሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በመጨረሻም በጥልቀት ከመታደስ ጋር በተያያዘ የማነሳው የአገሪቱን ዴሞክራሲ ጊዜው በሚጠይቀው ልክ ማጎልበትን የሚመለከት ነው። ኢትዮጵያ የብሄር፤ የፍላጎት፤ የአመለካከት . . . ብዝሃነት ያላት አገር ነች። በመሆኑም ብዝሃነት የሚስተናገድበት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። አገሪቱ ብዝሃነትን ማስተናገድ ባቃታት ቁጥር ትታመማለች፤ ትናጋለች። 
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዴሞክራሲን በሕገ መንግሥት አረጋግጣ መተግበር ጀምራለች። ይሁን እንጂ፤ ዴሞክራሲው ገና በመጎልበት ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ችግሮች አሉበት። በተለይ የአመለካከት ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ክፍተት ታይቷል። በምርጫ በሚገኝ ቀላል አብላጫ ድምጽ ስልጣን የሚያዝበት የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት በርካታ ደጋፊ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውክልና ማገኘት የማይችሉበትን የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ፈጥሯል። ባለፉት ሁለት ምርጫዎች የሆነውም ይህ ነው። ኢህአዴግና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ የምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፈው ሌሎች አናሳ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎች የደጋፊያቸውን ድምጽ ማሰማት የሚችሉበት እድል አጥተዋል። ይህ ሁኔታ እያደረ የመረረ ተቃውሞ ቀስቅሷል። በመሆኑም ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም በዚህ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደተለመደው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለአገሪቱ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህ ዙሪያ ቀዳሚው ተግባር የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት  መሆኑንም ገልጸዋል። የሕዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ማጎልበት፤ ዜጎች ተደራጅተው የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉበትንና መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የሚታገሉበትን የሲቪክ ማህበራት አደረጃጀት ማጠናከርም ቀጣይ የመንግሥት  ዋናው ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አገሪቱ ከምትከተለው የምርጫ ሥርዓት አንጻር በፓርላማው የሕዝቦችን የተሻለና ተመጣጣኝ ውክልና ለማምጣት የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን የመተግበር አስፈላጊነት ታምኖበት በዚህ ላይ ውሳኔ መተላለፉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ  በቀጣይነት ሕጋዊ ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አገሪቱ መከተል በሚገባት የምርጫ ሥርዓት ዙሪያ ድርድር እንደሚኖር አመልክተዋል። በድርድሩ ውጤት ላይ በመመስረት ሕጎችን የማሻሻልና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ሥራ የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ የገዢውን ፓርቲ በጥልቀት የመታደስ ውሳኔ ተከትሎ ብቃትንና የሕዝብ አገልጋይነትን ዝንባሌ መነሻ በማድረግ የተከናወነው የካቢኔ ሹመት በራሱ መድረሻ አለመሆኑ መታወስ አለበት። መድረሻው ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት እርካታ መፍጠር ነው። እርግጥ አዲሱ የካቢኔ ሹመት ወደዚህ ለመሄድ መነሻ ሊሆን ይችላል። ተሿሚዎቹ በተለይ በሕዝብ ላይ ወደተቃውሞ ያደገ ቅሬታ የፈጠሩ የወጣቶች የልማት ተጠቃሚ ያለመሆን ችግሮችን መፍታት፤ የከፋ የመልካም አስተዳደር እጦትን ማሻሻል፤ በተለይ የአመለካካት ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ክፍተት የታየበትን የአገሪቱን የዴሞክራሲ ጉድለት ማጎልበት የሚጠበቅባቸው መሆኑን በጽኑ ሊገነዘቡ ይገባል። አዲሱ ካቢኔ የሕዝብ እርካታ መፍጠር ተስኖት ከርሞም ሌላ ጥልቅ ተሃድሶ እንዳያስፈልግ በርትቶ መሥራት ይኖርበታል። የአዲሱ ካቢኔ መድረሻ የሕዝብን ጥያቄ በመመለስ  እርካታ መፍጠር ብቻ ነው።