ዛሬም እጃችን በማንም አይጠመዘዝም!

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ነኝ የሚለው ድርጅት በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ የውንጀላ ዘመቻውን አሁንም ቀጥሎበታል። ይህ ድርጅት የሚከተለው ስትራቴጂ ጠንካራ ልማታዊ መንግሥት በአገራችን እንዳይኖር በማድረግ መንግስት በልማት የሚያስተዳድራቸውን ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙ ሴከተሮችን ለምዕራባዊያን ባለሃብቶች ማስተላለፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ለአብነት ያህል በአገራችን ያሉ ጠንካራና ትርፋማ የሆኑ የፋይናንስ ተቋማትና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ያሉ ድርጅቶችን ከመንግሥት እጅ በማስወጣት ለምዕራባዊያን ከበርቴዎች ለማሸጥ ነው። ይህ የሆነበትም ምክንያት ባለፉት 13 ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ የሚገኝ በመሆኑ እነዚህ ተቋማት እጅግ ትርፋማ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው። 

ሂዩማን ራይትስ ዎች  አገራችንን በተመለከተ ያላቀረበው ውንጀላ የለም። ዜጎች በግዳጅ ተፈናቀሉ፣ የእምነት መብት ተጣሰ፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት በዜጎች ላይ ተፈጽሟል ወዘተ የሚሉ አዛኝ ቂቤ አንጓች እንዲሉ የኢትዮጵያን መንግሥትና ህዝብ ለማቃቃር ያመቸኛል ያለውን የተለያዩ መንገዶች ሁሉ ከመተግበር ወደኋላ አላለም። ይኸው ድርጅት በቅርቡ ደግሞ ሌላ የውንጀላ መንገድ ተከትሏል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ያስከትላል በሚል በገና ለገና ላይ የተመሠረተ ውንጀላ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አለም አቀፍ አሠራር ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዴሞክራሲ ተምሣሌት ተደርገው የሚወሰዱት በምዕራባዊያን አገሮች ሳይቀር የተለመደ አሠራር ሆኖ ሳለ ለእኛ አገር ሲሆን ክፋቱ እምኑ ላይ ይሆን? ሂዩማን ራይትስ ዎች ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያን መንግሥትን  ምክንያት ፈልጎ  መወንጀል  የሚቀናው ድርጅት በመሆኑ  አሁንም እንደቀድሞው  ጊዜ ሰሚ ጆሮ አያገኝም።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሃብታም አገራት ቀውስ ማስወገጃ ዜጎቻቸውን ከከፋ ጉዳት መታደጊያ  ተደርጎ ሲወሰድ ለደሃ አገር ደግሞ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት  ተደርጎ መወሰዱ አግባብነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው።  

በሁሉም አገሮች በህገ መንግሥት ወይም በሌላ የህግ ሰነድ መሠረት አድርገው   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይደነግጋሉ። ለአብነት  በዩ ኤስ አሜሪካ በ 2016 በተለያዩ ግዛቶች በጥቁሮችና በፖሊሶች መካከል በተደረገ ግጭት ሠላም የደፈረሰባቸው አንዳንድ ግዛቶች  እንደነሉዚያየና፣ ባልቲሞር፣ ደቡብ ኪሮሊና የአስቸኳይ ጊዜ ታውጇል። በቅርቡም   ከባድ  ማዕበል በመታቸው የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል፡፡   በፈረንሣይና ቱርክም አሁን ድርስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በመተግበር ላይ ይገኛል።  በአገራችንም በደርግ ጊዜ 17 ዓመት ሙሉ ሀገሪቷ በአስቸኳይ ጊዜ አገዛዝ ውስጥ ነበረች፡፡ በመሆኑም በመላ አገሪቱ ሰዓት እላፊ ታውጆ የዜጎች የመንቀሳቀስ እንዲሁም ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በቋሚነት ተገድበው እንደ አሠራር የሥርዓቱ ባህርይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኢፌዴሪ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ25 ዓመታት ታሪክ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አለም አቀፋዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው አሠራር ነው።  ማንኛውም የአለም አገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነገገው በአገር ውስጥ ሰፋ ያሉ አካባቢዎችን የሚሸፍንና ከመደበኛ የህግ ማስከበሪያ ዘዴ አቅም በላይ የሆኑ  ሁከት ሲፈጠር፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በአገር ደህንነት ላይ የታጠቀ ኃይል ወረራ ወይም ረብሻ ሲነሳ ከባድ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም/ ጎርፍ፣ ሰደድ እሣት፣ አውሎ ንፋስ፣ የመሬት መንሸራተት ወይም መደርመስ፣ ድርቅ በአጠቃላይ በአገራዊ ወይም በህዝቦች ደህንነት ላይ ከባድና ያልተጠበቀ  ሰው ሰራሽ ወይም የተፈጠሮ አደጋ ሥጋት ሲያጋጥመው በህዝብና በአገር ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል  የሚተገበር አሠራር ነው። ኢትዮጵያ ያወጣችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ምንነቱን፣ አስፈላጊነቱን፣  ህገ መንግሥታዊና አለም አቀፋዊ መርሆዎችን መሠረት በማድረግ  ነው።

 

 

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚተገበርበት ወቅት የፀጥታ ኃቀይሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅሞ ሥልጣኑን ካለአግባብ እንዳይፈጽም ህግ አውጪው አካል በቅርብ መቆጣጠር የሚያስችለውን አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገሪቷን ህገ መንግሥት መርሆዎችና ድንጋጌዎች በአለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት መፈፀሙን የመመርመር ኃላፊነት ሊኖረው ይችላል፡፡ በዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ፓርላማ የተወከለ ተቆጣጣሪ አካል ተቋቁሟል። ይህ አካል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  አተገባበር በመደበኛ የመመርመርና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው አዋጁን እስከመሰረዝ  የማድረግ ሥልጣን አለው። 

ይኸው አካል ሰዎች በህግ ፊት እኩል ፍርድ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅ የማድረግ፣ እንዳይጣሱ የተከለከሉ መብቶች  በአስፈፃሚ አካል ተጥሰው ሲገኙም የመመርመርና የማስተካከያ ሥራዎች ይከውናል። እንዲሁም ይህን ተግባር በፈጸሙ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል። 

የሲቪል ማኅበረሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ የመተባበር፣ ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የመሥራት፣ የዜጎች ተሳትፎ የማሳደግ ሚና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የአለማቀፉ ማኅበረሰብና  የዲኘሎማቲክ አካሉ አዋጁ ከአገሪቱ ጋር ያለውንና የሚኖረውን ግንኙነት የሚያሳድረው አሉታዊም ሆነ የተለየ ሁኔታ የመከታተል፣ የመመርመርና በቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ  ግንኙነት የማድረግ ወዘተ…ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህገ መንግሥታዊ መነሻና የህግ አውጭው ድጋፍ ሊኖረው ይገባል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በውጤታማነት ለመፈፀም የሚያስችል ራሱን የቻለ አደረጃጀት / በእኛ ሁኔታ ኮማንድ ፖስት/ እና እቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ አንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ ሊያሟላቸው  የሚገባቸው  ነጥቦችን የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ  አፈጻጸሙ አለም አቀፍ መሥፈርቶችን ያሟላ ነው። ለአብነት ያህል በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች ከዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት ብቻ የሚፈጸሙ ናቸው እንጂ እንዲያው በግብታዊነት  የተጣሉ አይደለም፡፡

የህግ የበላይነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትም በጥብቅ የሚከበሩ ናቸው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ወቅቶች  የማይጣሱና የማይገሰሱ ወይም ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች፤ ጭካኔ የተሞላበት አያያዘ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት፣ በግዴታ በሰው የመነገድ ተግባር፣ በኃይል አስገድዶ ሥራ ማሰራት የተከለከለ ነው፡፡ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ የማግኘት፣ በዘር፣ በብሄር፣ በብሄረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ከእነዚህ አለም አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ረገድ በአገራችን የታወጀውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲወጣ ያስገደዱ ምክንያቶች ተጨባጭ፣ ወቅታዊና በማኅበረሰቡ ደህንነትና ጥቅም  ላይ ከባድና ተጨባጭ ሥጋት ሲሆንና  በመደበኛው የህግ አካሄድ ለመቆጣጠር የሚከብዱ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። ይህ በአገራችን በተጨባጭ የታየ ጉዳይ ነበር። ይህም አዋጅ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች  የአዋጁ ይዘት እና ሥራ ላይ የሚውልበት ጊዜ በግልጽ መቀመጥ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ  መደረግ አለበት፡፡ ይህንንም መንግሥት  በወቅቱ  ተግባራዊ ተደርጓል።  ይህ በሚደረግበት ወቅት ዜጎች ስለአዋጁ በቂ ግንዛቤ ስለሚኖራቸው አዋጁ  ዓላማውን ሊያሳካ ከማስቻሉም ባሻገር ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል፡፡  ሌላውና ዋንኛው  የዜጎች መብቶች ከህግ አግባብ ውጪ ጫና እንዳይደርስባቸው የሚቆጣጠር አካል ማቋቋም ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉ  ግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሠራር ሊሰፍን ይገባል፡፡  የኢትዮጵያ መንግሥትም በህግ አውጪው አካል የተቋቋመ ተቆጣጣሪ አካል ተቋቁሞ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ላይ ነው።

ሌላው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ገደብ የሚደረግባቸው መብቶችና ነፃነቶች ለኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እንዲያውቁት በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይካሂድ ተደርጓል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን አድርጎታል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የጸጥታ ኃይሉ የሚወስደው እርምጃ   የተመጣጠን መሆን ይኖርበታል፡፡

 

በኢፌዴሪ  ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  የታወጀው አሁን በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጨባጭ አደጋ ሲያጋጥምና  አደጋውን ለመቀልበስ ተብሎ ብቻ በተወሰነ ወቅት የሚታወጅ ነው፡፡

አዋጁ የሚገደቡና የማይገደቡ መብቶች ምንድን ናቸው? በአስቸኳይ ጊዜ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት የሚያስገድዱ ጉዳዬች በአንቀጽ 93 ሥር ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት አራት ጉዳዬች ሲያጋጥሙ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅና ተግባራዊ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 /1//ሀ/እና /ለ/ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ለሚከተሉት አካላት ሰጥቷል። እነርሱም የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና  የክልል መሰተዳድሮች ናቸው፡፡