የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው!

ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ህጻናትና ወጣቶች ቁጥር 27 ሚሊዮን ገደማ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉት ወጣቶች ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ይደርሳሉ። መቶ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ከሚጠበቀው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ፤ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደጠቀሱት ደግሞ 70 በመቶ ገደማ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው። ማለትም አገሪቱ ከ50 እስከ 70 ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ ወጣቶች ናቸው። ይህም አገሪቱ የወጣቶች አገር መሆኗን ያመለክታል። ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ብቻ አይደለችም፤ ይልቁንም የተማረና ወላጆቹ ይኖሩ ከነበሩት የተሻለ ህይወት የመኖር ፍላጎት ያለው ወጣት አገር ነች። አሁን የአርሶ አደሩ ልጆች እየተማሩ ነው። ቀጣዩ የአርሶ አደር ልጆች ትውልድ በገጠር በአነስተኛ ማሳ ላይ በበሬ እያረሰ የመኖር ፍላጎት የለውም።

ይህ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ መንግሥት ከአሁን ጀምሮ ለተማረውና ሥራ ለሚፈልገው፤ የተሻለ ህይወት መኖር የሚፈልገውን፤ በእያንዳንዱ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ የያገባኛል ስሜት ያለውንና ጠያቂ የሆነ ወጣት ማህበረሰብ ማስተናገድ የሚችል ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ ማደላደል ያለበት መሆኑን ያመለክታል።

የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋጋጥ በቅድሚያ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የተመዘገበውን ተከታታይ ባለሁለት አሀዝ  የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ማረጋገጥ ይጠይቃል። በየኢኮኖሚ ዘርፉ የሚመዘገበው እድገት፤ በሁሉም የትምህርት ደረጃ የሚገኘውን የወጣት ጉልበት በግብአትነት ስለሚጠቀም የማያቋርጥ የሥራ እድል ይፈጥራል። ይህ ብቻ ግን ለሥራ እድል ፈጠራ በቂ አይደለም። በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ለራሳቸው የገቢ ማስገኛ ፈጥረው የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ማገዝ የሚችሉበት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል። ይህ ሥርዓት ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ፤ የማምረቻ ዎርክ ሾፕና የምርት ማሳያ ቦታ፤ የአገር ውስጥና የውጭ የገበያ ትስስር፤ የሞያና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ማመቻቸት ጭምር ይፈልጋል።

በዚህ ረገድ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማደራጀትና የብድር አቅርቦት በማመቻቻት፤ የሞያ ስልጠና በመስጠት፤ የመስሪያ ዳስ በማዘጋጀት ወዘተ. የታለፈበት ሂደት እንደመነሻ ጥሩ ልምድ ሊቀመርበት ይችላል። የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ1998 ዓ.ም.  በኋላ ተግባራዊ በተደረገው የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚዎች መሆናቸውም ይታወቃል። በእነዚህ ዓመታት ምን ያህል ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው ራሳቸውን እንደቻሉ፤ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ በማበርከት በተለይ ወደኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋጋር የሚደረገውን መዋቅራዊ ለውጥ በምን ያህል መጠን እንደደገፉ የሚያመለክት የነጠረ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን መሆናቸው ግን እርግጥ ነው። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በእቅድ ትግበራው አምስት ዓመታት ውስጥ 8 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸው ለዚህ አመላካችነት ሊጠቀስ ይችላል።

መሬት ላይ ግን  ከዚህም የተለየ እውነታ እናገኛለን። በርካታ ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የተደራጁ ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ለዚህ ምክንያቶቹ ደግሞ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ላይ የተሟላ የቴክኒክና የገበያ አዋጭነት ቅድመ ፕሮጀክት ጥናት አለማከናወን፤ የገንዘብ አያያዝና የገበያ አመራር ክህሎት ማነስ፤ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ማጣት፤ የገበያ ትስስር እጥረት. . . ናቸው። የስልጠና እድል ያገኙትም ቢሆኑ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና እንዳላገኙ ነው የሚናገሩት፤ “ስልጠና ሰጥተናል” ከሚል የሪፖርት ማሳመሪያነት የዘለለ እንዳልሆነ ባለጉዳዮቹ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ጋር በተያያዘ በአስፈፃሚውም በተጠቃሚዎችም በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ነበሩ። በርካታ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በተሰጣቸው የማምረቻ፤ የመነገጃ ወይም አገልግሎት መስጫ ቦታ ከመጠቀም ይልቅ ያከራዩበት ወይም ገንዘብ ተቀብለው አሳልፈው ለሌሎች የሰጡበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል፤ ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የተዘጋጁ ማምረቻ ሼዶችና ማሳያ ሱቆች አገልግሎት ሳይሰጡ ለዓመታት ታሽገው የተቀመጡበትም ሁኔታ አለ።

ያም ሆነ ይህ፤ በመላ አገሪቱ በገጠር የስምንተኛና የአስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ለሥራ ፍለጋ በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ከተሞች ፈልሰዋል። ከሙያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋማት፤ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ላይ ያሉ የአርሶ አደር ልጆች ቁጥርም ቀላል አይደለም። እነዚህ የገጠር ወጣቶች አባቶቻቸው ተሰማርተውበት በነበረው የግብርና ሥራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት የላቸውም። ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ቤተሰቦቻቸው መስራት የሚችሉበትን መሬት ሊሰጧቸው አይችሉም።  እዚሀ ላይ የአገሪቱ የቤተሰብ አማካይ የመሬት ይዞታ መጠን አንድ ሄክታር ገደማ መሆኑን ልብ በሉ። አርሶ አደሩ ከዚች  ኩርማን መሬት ላይ ቆረሶ ለልጁ መስጠት አይችልም።

እርግጥ ነው፤ በተለይ በተፋሰስ ልማት የተከለሉ ጥብቅ መሬቶችን ንብ ለማነብና እንስሳ ለማደለብን ለመሳሰሉ ሥራዎች የሚውል ተጨማሪ መሬት ማግኘት የቻሉበት ሁኔታ አለ። ይህም ቢሆን ግን በገጠር ካለው መሬት አልባ አርሶ አደርና ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በከተማ ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። በከተሞች በተለይ በትላልቅና በመካከለኛ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በላይ የተማሩና በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ናቸው። ይሁን እንጂ፤ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ጨምሮ በከተሞች የሚፈጠረው እድል እነዚህን ሥራ ፈላጊዎች ለማሰማራት በቂ አይደለም። ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው ከሚወጡ ተማሪዎች መካከል የሥራ እድል የሚያገኙት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ መልኩ የተመራቂ ሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በየዓመቱ እየተከማቸ ከገጠር ሥራ ፍለጋ ወደከተማ ከሚጎርፉት ጋር ተዳምሮ ከተሞችን የሥራ አጥ መናኸሪያ አድርጓቸዋል። ይህ አሁን በአገራችን ከተሞች የሚስተዋል ነባራዊ ሁኔታ ነው። በየዓመቱ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከመቃለል ይልቅ ባለበት መዝለቁ በርካቶችን ተስፋ አስቆርጧል። ተስፋ የቆረጡት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የሥራ ፈላጊዎችን ጎራ የተቀላቀሉት ብቻ ሳይሆኑ በመማር ላይ ያሉት ጭምር ናቸው። ወላጆችም ልጆቻቻው የትምህርት እድል ማግኘታቸውና በከፍተኛ ደረጃ ተምረው መመረቃቸው ቢያሰደስታቸውም ሥራ አጥ መሆናቸው ግን አሳዝኗቸዋል።

ይህ ሁኔታ የሥራ እድል ይፈጠር የሚለው ጥያቄ የአጠቃላይ የሕዝቡ ጥያቄ እንዲሆን አድርጓል። ባለፉት ዓመታትም ይህ የሥራ እድል ይፈጠር የሚለው ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱ የፈጠረው ቅሬታ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተቀሰቀሰው ሁከት አንዱ መንስኤ መሆኑ ይታወቃል። የልማት ኃይል ሆኖ ራሱንና አገሩን መጥቀም ያልቻለና ወደተስፋ መቁረጥ የተሸጋገረ ወጣት የሁከት ኃይል መሆኑ አይቀሬ መሆኑ መታወስ አለበት።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግሥት የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር አሳሳቢና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ተገንዝቧል። እናም ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር የልማት ኃይል እንዲሆኑ ማድረግ ለሚያስችል ተግባር ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። መንግሥት በያዝነው ዓመት ይህን የወጣቶች ፍትሃዊ ጥያቄ የሚፈቱ እርምጃዎችን እንደሚወስድ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በሁለተኛ ዓመት የመንግሥት የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የጋራ ስብሰባ ባደረጉት ንግግራቸው አንስተዋል። ይህም በዋናነት የወጣቱን የኢኮኖሚ ፍላጎት ማርካት ላይ የሚያተኩር ነው። በዚህ መሰረት በመላው አገሪቱ በሁሉም ወረዳዎች ቀደም ሲል ከነበረው የወጣቶች ተጠቃሚነት መደበኛ ፋይናንስ በተጨማሪ ለወጣቶች የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚነት ብቻ የሚውል የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንደተያዘ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በተለይ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ወጣቶች የሚያስፈልጋቸውን ማሺነሪ ማግኘት የሚችሉበት የሊዝ ፋይናኒስንግ ሥርዓት ተዘርግቷል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን የካፒታል እቃዎችን ለ3ሺህ አምራች እንተርፕራይዞች ማቅረብ የሚያስችል 42  ቢሊዮን ብር  አዘጋጅቷል ። ይህ ገንዘብ በተለይ ለወጣቶች ብቻ የተያዘ ባይሆንም፤ ባንኩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት  በአገሪቱ  የተደራጁ ወጣቶች  በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሊዝ ፋይናንሲንግ ድጋፍ  እንደሚደረግላቸው  መረጃው ያመለክታል። የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማትም ወጣቶች እንዲደራጁ   በማድረግና  ሥልጠና በመሥጠት፤ ወደ ኢትዮጵያ  ልማት ባንክ እየላከ መሆኑንና  ባንኩ በሊዝ  ፋይናንስ  ሥርዓቱ  የማምረቻ  ካፒታል  እቃዎች በማቅረብ  ለወጣቶች  ሰፊ  የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ጥረት  እያደረገ  መሆኑንም አስታውቋል። የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓቱን በመላ አገሪቱ  ለማስፈጸም 75 አዳዲስ  ቅርንጫፎች  መከፈታቸውንም ባንኩ ሰሞኑን አስታውቋል። ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ  550  ሚሊዮን ብር  የሚያወጡ  የካፒታል  እቃዎች  ለ88  ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት ማቅረቡንም ልማት ባንክ አስታውቋል።

እነዚህ ከላይ የተመለከቱት የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ የሥራ መነሻ ፈንድና 42 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናኒሲንግ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋለ፤ ወጣቶችን በሥራ እድል ፈጠራና በሥራ ውጤታማነት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ፤ በዚህ ገንዘብ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የተሟላ መልካም አስተዳደርና ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ የመንግሥት አፈጻጸም እንደሚሻ ግን መታወቅ አለበት። ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጁ ሥርዓቶች በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋሉ የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል ጋር ተዳምሮ አሁን ያለውን የከፋ ሊባል የሚችል የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር በጉልህ ማቃለል ይቻላል።

የወጣቶች ችግር ኢኮኖሚያዊ ብቻ እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት። ፖለቲካዊ ጥያቄዎችም አላቸው። የኢትዮጵያ ወጣቶች የተማሩና በአገሪቱ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋምና አመለካከት ያላቸው ናቸው። በመሆኑም ይህ አቋማቸውና አመለካከታቸው በክልላዊም ይሁን በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ውክልና እንዲኖረው ይፈልጋሉ። አሁን ባለው አንድ ፓርቲ (ኢህአዴግ) አውራ ሆኖ በወጣበት ሁኔታ አቋምና አመለካከታቸው ሊደመጥ የሚችልበት እድል ጠብቧል። እናም ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል ይፈልጋሉ። አመለካከቱ ይፋ የሚወጣበት መንገድ ያጣ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ድምጹን ለማሰማት አመቺ ሆኖ ያገኘውን ማንኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይል መታወቅ አለበት። በመሆኑም የኢትዮጵያ ወጣቶች አመለካከታቸውና አቋማቸው ሊደመጥ የሚችለበትን ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው።

መንግሥት በሚቀጥለው ምርጫ ሁሉም አመለካከቶች ከፍተኛ የሥልጣን አካል በሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው በሚያስችል አኳኋን የምርጫ ሕጉን እንደሚያስተካክል ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ  በፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል። በዚህ ማሻሻያ በሚፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የወጣቶችም አመለካከት የሚወከልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል።

በአጠቃላይ ወጣቶችን በሥራ አጥነትና በመንግሥት ውስጥ ውክልና በማጣት ከገቡበት የተስፋ መቁረጥና የመገፋት ስሜት በማውጣት በልማት ኃይልነት በዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መቀጠል ወይም አለመቀጠል ጉዳይ ነው። ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተቀስቅሰው የነበሩ ሁከቶች ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እናም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ