አዲስ ካቢኔ፤አዲስ ተስፋ…

የምክር ቤት አባላት ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ዲፕሎማቶች፣የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በተዘጋጀላቸው ቦታ ተቀምጠዋል፡፡ የዓመቱ ወሳኝ ጉዳይ ሊጀመር ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ በጉጉት የሚጠበቀው የአዲሱ ካቢኔ ሹመት ይፋ ሊሆን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲሱን ካቢኔያቸውን ሊያስተዋውቁ በምክር ቤት ተገኙ፡፡ የሁሉም ልብ ምት ጨምሯል፡፡ ‹‹እነማን በአዲሱ የካቢኔ ሹመት ውስጥ ተካተዋል;›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስማት፡፡ በአፈ ጉባዔው ጋባዥነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ካቢኔ እንዲያስተዋውቁ መድረኩ ተለቀቀላቸው፡፡

የካቢኔ ሹመቱ ሶስት ሂደቶችን የተከተለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡ ይህንንም አብራሩ፡፡ በሥራቸው ውጤታማ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ሚኒስትሮች በያዙት የሚኒስትርነት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ መደረጉን ተናገሩ፡፡ በዚህም ዘጠኝ ያህል ሚኒስትሮች ቀድሞ በነበሩበት መቀጠላቸው ተሰማ፡፡

ሌሎች ደግሞ በፊት ከያዙት ዘርፍ ወደ ሌላ ዘርፍ ተቀይረው በሚኒስትርነት ቢሰሩ የተሻለ መሆኑ ተገምግሞ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቆሙ፡፡ በመሆኑም የሽግሽግ ሥራ ተከናወነ፡፡ ቀድሞ ከነበሩበት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወደ ሌላ ሚኒስትር መስሪያ ቤት እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል፡፡

አብዛኛው ታዲያ አዲስ ሹመት ነው፡፡ አዲሶቹን የካኔ አባላት ለመመልመል ጊዜ ተወስዶ፣ ጥንቃቄ ተደርጎ ከፍተኛ ሥራ መሰራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረዱ፡፡ በተለይም የአገሪቱ ዕድገት የሚጠይቀውን ዝንባሌ የተከተለ፤ ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድን መሰረት ያደረገ ሹመት መሆኑ ተብራርቷል፡፡

አዲሶቹ ተሿሚዎች ረጅም ጊዜያቸውን በምርምርና ጥናት ያሳለፉ፤በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በብቃትና ጥራት ያገለገሉ፤ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ማህበራዊ ተግባራትን በስፋት ማናወናቸው ተመልክቷል፡፡

በሙያቸውና በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ የምርምር ሥራዎቻቸውን በተለያዩ መድረኮች ላይ በማቅረብ ለህዝብና አገር እንዲጠቅሙ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ የጥናት ውጤታቸውን በዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በመልካም ስነ ምግባር የታወቁና ታታሪ መሆናቸውም ተመስክሮላቸዋል፡፡

ይህን ሂደት ተከትሎ የተመለመሉት የካቢኔ አባላት ዝርዝር ለምክር ቤቱ ቀረበ፡፡የትምህርት ዝግጅታቸውና የሥራ ልምዳቸው ተገለፀ፡፡ የኋላ ታሪካቸው፣ የምርምርና የጥናት ሥራዎቻቸው ተዘረዘረ፡፡ የምክር ቤት አባላት አስተያየት እንዲሰጡ ተጋበዙ፡፡

የካቢኔው ሹመት ይበል የሚያሰኝና ታሪካዊ መሆኑን ተናገሩ፡፡ ውጤታማነት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድና ብቃት ያለው አፈፃፀምን የተከተለ መስፈርት መሆኑን አደነቁ፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስና የአገሪቷን ዕድገት ለማፋጠን፤ የተያዘውን የሕዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ተስፋ የሚጣልባቸው ሚኒስትሮች እንደሚሆኑም የምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡፡

ሹመት ያዳብር፣ ለህዝባችሁና ለአገራችሁ ልማትና ብልፅግና የተሻለ ሥራ የምትሰሩበት ዘመን ያድርግላችሁ ተባሉ፡፡ ተሿሚዎችም ህገ መንግስቱን አክብረው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት ለመወጣት ቃለ መሀላ ፈፀሙ፡፡

የሹመት ሥርዓት መፈፀሙን ተከትሎ አዳዲሶቹ ተሿሚዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የተረከቡት አገራዊ ኃላፊነት ከባድና ጥልቅ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግስት የተያያዘውን መልካም አስተዳደርን የማስፈንና የህዝብ እርካታን የማረጋገጥ ሥራ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

ዋልታ ካነጋገራቸው አዲስ ተሿሚዎች መካከል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም፣የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ፣ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ኃላፊነቱ ህዝብና አገርን በታማኝነት ለማገልገል የተሰጠ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

የተረከቡትን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት በመወጣት ህዝብን በሀቀኝነትና በታማኝነት ለማገልገል ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡ በየተመደቡበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚተጉ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ካቢኔ አዲስ ኃላፊነትና ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ቀደም ሲል በቆዩባቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያካበቱትን ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ በመጠቀም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአገሪቷን ዕድገት ለማፋጠን እንደሚሰሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በተለይም የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የመልካም አስተዳደር እጥረትን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይታገላሉ፡፡

ለማሳያነት እነዚህን ጠቀስን እንጂ ሌሎቹም የካቢኔ አባላት የተረከቡትን ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት ለህዝብና ለአገር ልማት ለማዋል ታጥቀው መነሳታቸውን ነው የገለፁት፡፡ የሥልጣን ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ የሚኒስትሮቹ አገልጋይነትም ለህዝብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕዝባዊ አደራውን ለመወጣት ቃል መግባታቸው፡፡

ከአዲሱ የካቢኔ ሹመት ጎን ለጎን ሌሎች መዋቅራዊ ማሻሻያዎችም ተደርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪ የነበሩት ሹመቶች እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡ አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ መኖሩ በቂና ህገ መንግስታዊ ድንጋጌን የተከተለ አካሄድ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ ሁሉም ሚኒስትሮች ራሳቸውን ችለው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት እንዲወጡ ያስችላል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የጠቅላይ ሚነስትሩ አማካሪ ሲባሉ የነበሩ ቦታዎችም ሙሉ በሙሉ እንዲተው ተደርጓል፡፡ በዚህ ፈንታ ራሱን የቻለ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሟል፡፡ ይህም በተደራጀ መልኩ የተጠናከረ ሥራ ይሰራል፡፡ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡

በተለይም የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ለማፋጠን የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ደግሞ ሴቶች በአስተባባሪነትና በዳይሬክተርነት በብዛት እንደሚመደቡ ነው የተገለፀው፡፡

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ አማራጮች እንደሚተገበሩም ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክርና ውይይት ይደረጋል፡፡ የምርጫ ህጉን እስከ ማሻሻል የሚደርስ እርምጃም ሊወሰድ ይችላል፡፡

ዲሞክራሲን ማስፈን ልማትን ከማረጋገጥና ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ጎን ለጎን የሚሰራ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ መንግስትም ለዚህ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ የሞት ሽረት ትግሉ ተጧጡፏል፡፡ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በብዛት፣ በጥራት፣ በፍትሃዊነትና በተደራሽነት ማረጋገጥ፡፡

መልካም አስተዳደርን የማስፈኑ ትግል ከተጀማመረ ሰነባብቷል፡፡ መንግስትም ራሱን በመፈተሽ የለውጥ ጉዞውን ማፋጠኑን ተያይዞታል፡፡ ገዥው ፓርቲ ራሱን በመገምገም የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡

ጥልቅ ተሀድሶ በማካሄድ የመፍትሔ ሃሳቦችን የማስቀመጥ፣ የመቀመርና የመተግበር ጉዞውን ጀምሯል፡፡ ገዥውን ፓርቲ የመሰረቱት ብሔራዊ ድርጅቶችም ግምገማ በማካሄድ ራሳቸውን በመፈተሽ የለውጡን ሀዲድ ተያይዘውታል፡፡

መንግስት ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊቱ ተደቅነዋል፡፡ እነዚህን መስራትና ለውጤታማነት ማብቃት ደግሞ በየደረጃው የተቀመጡ ባለሥልጣናት፣አመራሮች፣ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይም አመራሩ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት፣በጥራት፣በፍጥነት፣በፍትሃዊነትና በታማኝነት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

አገሪቱ የተያያያችውን የህዳሴ ጉዞ ዕውን ለማድረግ የአመራሩ ሚና እጅጉን የላቀ ነው፡፡ አመራሩ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ አርዓያ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ ችግሮችን ወደ ሌላ የሚገፋ ሳይሆን የሚፈታ፣ ቅሬታዎችን ለማዳመጥ ጆሮውን የሚሰጥ፣ ከሚመራው መስሪያ ቤት ባለሙያዎችና ሠራተኞች ጋር ተቀራርቦና ተመካክሮ የሚሰራ ጠንካራ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡

አመራርነት የቅንነትና የታማኝነትን ካባ ሊጎናፀፍ ይገባል፡፡ ማንኛውም ጥያቄም ሆነ ቅሬታ ሲሰነዘር ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ህዝብን በቅንነት የማገልገል መልካም ባህርይን መላበስ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡

ሁሉንም አካላት በፍትሃዊነት ማገልገልም ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጥሩ ሰብዓዊነት መገለጫም ነው፡፡ ከህሊና ተጠያቂነት የሚታደግ ሥራን መስራት ከጥሩ አመራር የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

አመራሩ ለህገ መንግስቱ ታማኝ የሚሆነውን ያህል ሥራውን በታማኝነት ይወጠዋል ብሎ ላስረከበው አካልም ታማኝነቱን በጥሩ ውጤት ማስመስከር አለበት፡፡ ህዝብና መንግስት ያስረከቡትን ሥልጣን በሀቀኝነት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት አስመዘግባለሁ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳካት አመራሩ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ግድ ይለዋል፡፡

በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ቢደረስባቸው የተባሉ ዕቅዶች ዕውን እንዲሆኑ ትግሉ ከባድ ነው፡፡ የዚህ ፊታውራሪ የሆነው ከፍተኛ አመራር የቤት ሥራ በአግባቡ በመወጣት ማንነቱን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ የአማራርነት ሚናውን በደንብ በመወጣት በመስሪያ ቤቱና በተጠሪ መስሪያ ቤቶቹ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችና መሻሻሎችን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

የሥልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥና የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ ችግሮችን በመጠቆምና በመታገል የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ በእኔነት ስሜት መታገል ያስፈልጋል፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም ልማትን ማፋጠንና ማረጋገጥ የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ ነውና ርብርቡ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል፡፡

ታሪካዊ የተባለውን ካቢኔ ለተቀላቀሉ ሚኒስትሮች ደግሞ ኃላፊነቱ ብዙ የቤት ሥራዎችን አብሮ የሰጠ ነው፡፡ ለዚህም ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ህዝቡ አዲሱ የካቢኔ አባላትን ሹመት ወዶታል፤ አድንቆታል፤ አሞግሶታል፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ የተባለና የተሞገሰ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ከነበረው ሹመት ወጣ ያለና ውጤታማነትና ብቃትን መሰረት ያደረገ መስፈርትን የተከተለ መሆኑ እንጂ፡፡

ህዝቡ ‹‹ከታሪካዊው የካቢኔ ሹመት ብዙ ውጤት እንጠብቃለን›› ሲል ተደምጧል፡፡ ለዚህም ነው ኃላፊነቱ ከባድ ነው መባሉ፡፡ የካቢኔ አባላቱም ለህዝቡና ለአገር ጠቃሚ ተግባራትን ለማከናወን ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

እናም ተሿሚዎች ያሰቡትን እንዲያሳኩ፣ ህዝቡም የሚፈልገውን እንዲመለከት፣ መንግስትም ዕቅዱ ዕውን እንዲሆን የጋራ ጥረትና ርብርቡ በተግባር ሊታይ ይገባል፡፡ አዲስ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ካቢኔ የአመራርነት  ኃላፊነቱን  በብቃትና  በጥራት  ለመወጣት  የገባውን  ቃል  ለማሳካት  የሁሉም  ድጋፍና ትብብር ወሳኝ ነው፡፡