ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመቸች ሃገር

ላለፉት 25 ዓመታት የመንግስትን ስልጣን ይዞ ሃገሪቱን እየመራ የሚገኘው ገዢ ፓርቲ የሚከተለውን ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና እንደ ሃገሪቱ ተጨባጭ የኢኮኖሚና ፓለቲካዊ ሁኔታዎች እያደሰ በመሄድ ይታወቃል፡፡ በተለይ ባሳለፍናቸው 15 ዓመታት ውስጥ ለተገኘውና ተከታታይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት ገዢ ሥርዓቱ የተከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተአለማዊ ፍልስፍና ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ብዙዎቹ የምጣኔ ሃብታዊና የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች ይመሰክራሉ፡፡
 
ማንኛውም ለልማት የቆመ መንግስት ሁሉ ልማታዊ መንግስት ነው ማለት ቢቻልም በኢኮኖሚ ልማት ንድፈ ሃሳባዊ ማዕቀፍ ልማታዊ መንግስት (Developmental State) በሚባል የሚታወቀው አስተሳሰብ ግን የራሱ ታሪካዊ አመጣጥ ያለው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ንድፈ ሃሳብ ከላይ እንደወረደ ሲታይ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሰረት ከሆነው የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የሚጣረስ መምሰሉን መነሻ በማድረግ ልማታዊ መንግስት ሆኖ ዴሞክራሲያዊ መሆን አይቻልም በማለት የሀገራችንን ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግስት ከመነሻው ብልሹና የማይሆን በማለት ብዞዎች ለተቃውሞአቸው በምክንያትነት የሚጠቀሙበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን ልማታዊ መንግስትና የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚጣጣሙበትን መንገድ መሻትና ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ አንጽሮ ጥቅም ላይ የማዋል ጉዳይ በሳል ከሆኑ መንግስታት የሚጠበቅና የሌሎችን ጽዋ ያለምክንያት ከማይጎነጩት የሚጠበቅ መሆኑን ጥቂት ማሳያዎች በማንሳት የሃገራችንን ቁመና ማሄስ ይቻላል፡፡

ሃገራችን በአፍሪካ የንግድ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏት እድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ብዙዎች እያመኑ እና ማመናቸውንም በይፋ እየተናገሩ መምጣታቸው ልማታዊውም ዴሞክራሲያዊም ሃገር እየተገነባ ለመሆኑ አንደኛው ማሳያ ነው። ይህም እምነት  የማኑፋክቸሪንግ ግንባታ እየተስፋፋ መሆኑን የተመለከተ እና  የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በሃገሪቱ ለሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ስራ የሃገሪቱ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን  የተመለከቱ  እና ዴሞክራሲያዊም ልማታዊም ከመሆናችን ጋር የተያያዙ ናቸው። እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለባለሃብቶችም መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ የሚገኘው ልማታዊም ዴሞክራሲያዊም መሆን ስለተቻለ ነው። ከዚህም በላይ በሁለተኛው ዙር የእቅድ ዘመን ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈሩ ምክር ቤቱ ስራውን በይፋ በጀመረበት ስነስርአትና በጠቅላይ ሚንስትሩ የሞሽን ማብራሪያ ግልጽ መደረጉም ስለአጀንዳችን ሊታወስ የሚገባው አስረጅ ነው።
ሌሎቹን ለጊዜው አቆይተን ሰሞንኛ ከሆኑቱ ጥቂቶቹን ስናይ ሳንሼንግ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ በ85 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው የመድኃኒት ፋብሪካ ለመንግስት ቁርጠኝነት አንደኛው ማሳያችን ይሆናል። ፋብሪካው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በርካታና የተለያዩ መድኃኒቶችን ማምረት የሚችልና ለ300 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማእከል ነው።
በኢትዮጵያ የመጣው ይህ እድገት በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ በውጭና በመንግሥት በኩል በተከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና እንደምትቀጥልና ከስድስት በመቶ በላይ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧንም እንደምትገፋበት የሚያመላክቱት መረጃዎች ከመንግስት ብቻ የተገኙ ሳይሆን አለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት አመታዊ ሪፖርትም ጭምር ያረጋገጠው ነው። 
በሃገሪቱ እየታየ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዕድገት የተለያዩ የውጭ ባለሃብቶችን ትኩረት እንዲስብ ያስቻሉ በርካታ ምክንያቶች ሲኖሩ ከነዚህም ምክንያቶች ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ውጤት በሆነው መሰረተ ልማትና በቀጠናው የተረጋጋች ሃገር ሆና መገኘቷ ነው። 

በቅርቡ የተጠናቀቀው የኢትዮ ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ባቡር ይፋ ከሆነ ወዲህ እንኳ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን “ኢትዮጵያ ወደፊት የአፍሪካ የገበያ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏትን እድሎች እያሰፋች ነው” የሚል ይዘት ያሏቸው ሐሳቦችን በዘገባዎቻቸው ማመላከታቸው አንዱ ማሳያ ነው።

በመሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሃገሪቱ እየታየ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ መሆኑ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሃገሪቱ መንግሥት ለውጭ ባለሃብቶች እየፈጠረ ያለው ምቹ ሁኔታ ወደፊት ሃገሪቱን ሰፊ የገበያ መዳረሻ ያደርጋታል። ሌላውና ለሃገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለው መነቃቃትና ፈጣን መሻሻል ነው። ያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ያለው የሆቴል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ሲሆን የዚህን ዘርፍ እድገት ከፍ ለማድረግም በሃገሪቱ ያለው ጠንካራ የሆነ የአየር ትራንስፖርት እና አዲስ አበባ ከዓለማችን ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ ከተማ መሆኗ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። 
 
ሌላም የሃገሪቱን የወጪ ንግድና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት የሚያስችል ግን ደግሞ  በጥረት፣ በውጤት  እና በትጋት የተገኘ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይኸውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ አባል ሆና መመረጧ ነው። የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጆርጅ ኦቲኖ፣ “ኢትዮጵያ አባል ሆና መመረጧ በፍጥነት በማደግ ላይ በሚገኘው ምጣኔ ሀብቷ ላይ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት እንዲፋጠን ይረዳል” ሲሉ መግለጻቸውም ከላይ ለተመለከተው አመክንዮ ሁነኛ አስረጅ ነው። 
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ አባል መሆኗ የጎረቤት ሃገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እንደ ልባቸው ኢንቨስትመንት ማካሄድ እንዲችሉ እድል ስለሚፈጥር ለስራ አጥ ወጣቶች በተመሳሳይም እድሎች ይሰፋሉ። ኤጀንሲው ይህንን መፍቀዱ ሀገሪቷ በቀጣናው የተረጋጋች መሆኗን የሚያመላክትና በጊዚያዊ ግርግሮች እንደማትደናቀፍ ያመላከተ ነው። የአፍሪካ ልማት ባንክ ሂደቱን በገንዘብ መደገፉም ስለዚሁ ምክንያት ነው።  

በጥቅሉ የልማታዊ መንግስት ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና እንደው በደፈናው ሃገራችን የተከተለችው መንገድ ሳይሆን በርካታና በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሃገራት በተግባር ላይ አውለው ውጤት ያገኙበት ሁለት ምክንያቶች ስላሉት ነው፡፡ የልማታዊ መንግስት ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና የመጀመሪያውና ምናልባትም ዋናኛው ተልዕኮ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት የሰፈነበትን ሁኔታ ደረጃ በደረጃ የመቀየር እና ከላይ በተመለከተው አግባብ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ሰፋፊ የስራ እድሎችን መፍጠር ሲሆን፤ ሁለተኛውደግሞ ለልማት ማነቆ የሚሆኑ የገበያ ጉድለቶችን በተመረጡና ውጤታማ አኳኋን ጣልቃ በመግባት ማስወገድ ነው፡፡