ሁላችንም የየድርሻችንን

ለአንድ ሀገርም ሆነ ህዝብ ሀገራዊውን ወቅታዊ ሁኔታ በውል መረዳት በአህጉርም ሆነ  በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እድገቶች እየመዘኑ ከተጨባጩ እውነት ጋር በማጣመር ሊራመዱ የሚችሉ ለውጦችን ማምጣት መንግስትንም ህዝቡንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የትላንትን ስኬት ብቻ በማሞካሸትና በማድነቅ የተጠመደ አመራር አዲስና ወቅቱ የሚፈልጋቸውን ተጨባጭ ውጤቶች ለማስመዝገብ ይሳነዋል፡፡ ትላንት ትላንት እንጂ ዛሬ መሆን አይችልም፡፡ ትላንት የተሰራው ታላላቅ ስራ ተሰርቶአል፡፡ ትኩረት መሰጠት ያለበት ዛሬና ነገ ወደፊት ስለሚሰራው የበለጠ ስራ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለዚህም ሁሉም የየድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

በአስተሳሰብ በአመለካከት ከህዝቡ ወደኃላ የቀረ አመራር መሳቂያና መሳለቂያ ነው የሚሆነው፡፡ ከህዝቡ ጋር ለመናበብ ያዳግተዋል፡፡ ችግሮቹም እየሰፉ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው ሀገርና ህዝብ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ መኖርና ማለፍ ያለባቸው፡፡ ለአዲስ ለውጥና ስኬት የሚደረጉ ተነሳሽነቶች ጎልብተው መቀጠል አለባቸው፡፡ በቁርጠኝነት ለበለጠና ቀድሞ ያልነበረ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ካልተደረገ ስርነቀል የሆነ የአሰራርና የአመራር ለውጥ ማድረግ ካልተቻለ የተቸከለ አሰራርና አመለካከት ከነገሰ ምንም የሚጠበቅ የሚመጣም ለውጥ የለም፡፡

በአመራርና በአሰራር ለውጥ ማድረግ የተሻሉና ብቁ የሆኑ ዘዴዎችን መንገዶችን በመከተል ተግባራዊ ለውጦችን ለማምጣት ይረዳል፡፡ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግሮች ለይቶ ማወቅ መረዳት በጋራ ግንዛቤ የሚፈቱበትን መፍትሄ ማስገኘት በቅርበትም ከህዝቡ ጋር እየተገናኙ መስራት ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ሁሉንም ነገር በመንግስት ተሿሚዎች ላይ ብቻ እንደ እዳ መጣል ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋም ሆነ ህብረተሰቡ የየድርሻውን ዜግነታዊና ሀገራዊ ሀላፊነት ለመወጣት መብቃት አለበት፡፡

አዲሶቹን ተሿሚዎች በተመለከተ በአንድ ግዜ ተአምራዊ ለውጥ የሚፈጠር አይነት አድርገው የሚያስቡ ክፍሎች አሉ፡፡ ይሄ ስህተትና የተዛባ አመለካካት ነው፡፡ በአብዛኛው ህይወታቸውን ያሳለፉት በአካዳሚክ ምርምርና ጥናት  በመምህርነት በተለያዩ ሀላፊነቶችም ነው፡፡

 

እንደሌላው ሀገር ሁሉ ምሁራኑ ሀሳብ አፍላቂዎች፣ የአዲስ ቀመር ስሌት አስሊዎች ናቸው፡፡ ረዥሙን ህይወታቸውንና ስራቸውን ስንመለከት በጥናትና በምርምሩ ውስጥ የዘለቁ፤ የተቆጠበ ትኩረትና ጥልቀት የሚፈልጉ ስራዎችን ከብዙ ነገር ተገልለው ስኬታማ ለመሆን ሲሰሩ፣ ሲመራመሩ ሲጽፉ፣ አዲስ ሀሳብ ሲያመነጩ፣ ያ አዲስ ግኝት ወይም ሀሳብ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ምሁራዊ/ምክንያታዊ ክርክር ሲያደርጉ በዚህ መልኩ የኖሩ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የላቀ የእውቀት አድማስ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምሁራን በውስብስቡና ጥልፍልፉ ቢሮክራሲ ውስጥ አልኖሩም፡፡ አያውቁትም ማለት ይቻላል፡፡ የእነሱ ህይወት የጥናትና የምርምር አለም ነው፡፡ አሁን የተሰጣቸው ሀገራዊ ሀላፊነት በሰፊው ከህዝብ ጋር የሚያገናኝ የስራውንም ሆነ የህዝቡን ችግር ከመፍታት አኳያ ሰፊ ትኩረትና ግንኙነት ማድረግን የሚጠይቅ በመሆኑ ለስራቸው መቃናት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቅን እገዛና ትብብር ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡

የመጡት ወደአልነበሩበት አዲስ አለም ነው፡፡ ፈጣን ውሳኔ መስጠትን በየእለቱ ይፈልጋል፡፡ ምሁራን ውሳኔ ላይ የመዘግየት ነገሮችን ረጋ ብሎ የማየትና በማስረጃ የማስደገፍ ተጠያቂነት እንዳያመጣ ብለው የመጨነቅ ባህርይ ድሮም ዛሬም አላቸው፡፡ ይሄም መልካምና ተፈላጊ ነገር ነው፡፡ የአንድ መሪ ዋናው ሚና የተሻለ አቅጣጫ ማሳየት፣ በብቃትና በተምሳሌነት መምራት ጉዳዮችን ከሁሉም አቅጣጫ በትኖ አበጥሮ መመልከት፣ ሀገራዊ ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን በመጨረሻም መወሰን ነው፡፡

የመሪ ዋነኛው ተግባሩ ግልጽና ቁርጠኛ ውሳኔ መስጠት ይሄንኑም በብቃት ወደታች አውርዶ ማስፈጸም ነው፡፡ መሪነት እውቀት ብቻ ሳይሆን ልምድን ተግባራዊ የህይወት ተሞክሮን በፈታኝ የአመራር ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍንም ይጠይቃል፡፡ ብዙዎቹ በታሪክ ውስጥ ገዝፈው የወጡ መሪዎች ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣  ባለሁለትና ሶስት ማስትሬት ዲግሪ ባለቤቶች አይደሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ የእኛንም ሆነ የሌሎች ሀገርን ልምድና ተሞክሮዎች ማየት ይቻላል፡፡

ህብረተሰቡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ በጉጉት እየጠበቀ ያለው ለውጥ ምንድነው? ቢባል ለተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞና ቀውስ ምክንያት የሆኑትን መንግስትና ህዝብ አምኖ የሰጣቸውን ሀላፊነት ወደጎን በመጣል በብልሹ አሰራር ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ ያደረጉትን በህግ ተጠያቂ ሁነው ማየት ይፈልጋል፡፡ ህዝቡ በስልጣናቸው ተጠቅመው የመዘበሩትን፣ የዘረፉትን፣ መሬት የተቀራመቱትን ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ሙሰኞች፣ የፍትህ ስርአቱን በአድልዎና መድልዎ የበከሉና የህዝብን መብት የገፈፉትን ህጉ ሊያልፋቸው አይገባም እያለ ነው፡፡

መልካም ነው፣ አዲስ ካቢኔ አዲስ አመራር ተሾመ፤ ምሁራን ናቸው፤ይሄም የሚደገፍ ነው፡፡ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት አንጻር በመርህ ደረጃ ህዝብ የማወቅ መብት ስላለው መንግስት ይህን ለማድረግ የተነሳበትን የህዝብ ተቃውሞና ጥያቄ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለህዝብ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ የተፈጠረውን የተዛባ አመለካከት ለማጥራት ይረዳል፡፡ ከሃላፊነት የተነሳው የተቀየረው ሁሉ ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከመልካም አስተዳደር ችግር ከመሬት ቅርምት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው የሚሉ የተሰሳቱ ግንዛቤዎችን ለማረም ይረዳል፡፡ በአዲስ መንፈስ አዲስ አሰራር ይዞ ለመቀጠል ሰዎች ከነበሩበት ቦታ እንዲነሱ፣ እንዲለወጡ፣ ወደሌላ ቦታም እንዲዛወሩ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ይህም ተደርጎም ያውቃልና አዲስ ነገር አይደለም።

በእርግጥም መንግስታዊ ሀላፊነትና ሹመት የበለጠ ለሀገርና ለህዝብ በቅንነት በታማኝነት እንዲሰሩ የሚያተጋ እንጂ የሚኩራሩበት የሚመጻደቁበት ወንበራቸውን ተጠቅመው የመሰላቸውን የሚጠቅሙበት የጠሉትን የሚጎዱበት ለግል ጥቅማቸውም ሲሉ ዘረፋና ምዝበራ ውስጥ የሚዘፈቁበት አይደለም፡፡ ጎሳና ጎጥ እየመረጡ የሚጠቃቀሙበትም ሊሆን አይገባውም፡፡ አንዱም በህዝቡ ውስጥ ትልቅ መከፋት ቅሬታና ቁጣ ያስከተለው ከሌላው በተጨማሪ ይሄው ገዝፎ የሚታይና አይን ያወጣ ችግር ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የተሾሙት ባለስልጣናት አገልጋይነታቸው ለመላው ህዝብ ነው ሲሉ የተናገሩት፡፡ ያለልዩነት ከዚህ ብሄረሰብ ከዚያ ሳይባል ህዝቡንና ሀገሪቱን ማእከል አድርገው መስራት የነበረባቸው ሹሞች በመንደር አስተሳሰብ እየተዋጡ ህዝብ በይፋ እስኪታዘብ ድረስ ምን እንደሰሩ፣ ሲሰሩ እንደኖሩ ይታወቃል፡፡

ከዚህ የመንደር፣ የወንዝ ጠባብ አስተሳሰብ በሽታ መውጣትና ስለሰፊዋ ሀገር ስለሰፊው ህዝብ ማሰብ፣ መስራትና መጨነቅ ነው ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችለው፡፡ የጠባብ አስተሳሰብም ሆነ የትምክህት ጎራው እሳቤ ለሀገርና ለህዝብ ውድቀት ታላቅ በር ከመክፈት ውጪ የሚፈይዱት አንዳችም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም በዚህ በሽታ የተለከፉና የተመረዙ ሰዎች ለዛሬውም ሆነ ለነገው ትውልድ የማይበጁ ስለሆነ አስተሳሰባቸው ተቀባይነት እንደሌለው ባለፈው ከተነሳው ቀውስ በግልጽ ሊማሩበት ይገባል የሚሉ ሰፊ የህዝብ አስተያየቶች አሉ፡፡ መንግስት የመዋቅር ለውጥ ማምጣቱ በተጨባጭ የሚታየው እስከታችኛው ደረጃ ድረስ ወርዶ ሙሉ በሙሉ አሰራሩን መቀየር ሲችል ብቻ ነው፡፡

መንግስት ከመሾም ውጪ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን ተጠያቂ አላደረገም፡፡ ጉዳዩ በሽፍንፍን እንዲታለፍና እንዲረሳሳ የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ እየታየ ሲሆን ይህ ደግሞ ዝርፊያንና ምዝበራን የማበረታታና የመሸለም ያህል ይቆጠራል፡፡ በዚህ መልኩ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚሉም የህዝብ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡  ቀደም ሲል የነበረው የህዝብ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ኢህአዴግ ችግሩን ከለየ በኋላ ፈጥኖ እርምጃ ለመውሰድ ባለመቻሉ ነው፡፡ አሁንም ግዜ ለመግዛት፣ ለማስተንፈስ የሚደረግ ጥረት ካልሆነ በስተቀር ምሁራኑ ወሳኝ ውሳኔዎችን የመስጠት ሙሉ መብት ከሌላቸው እነሱ በወንበሩ ላይ ተቀምጠው እያሉ ከጀርባ እየታዘዙ ይሄን አድርግ አታድርግ ተብለው በማያምኑበት የሚታዘዙ ከሆነ የተፈለገውን ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚሉ የህዝብ አስተያየቶችም በሰፊው ይደመጣሉ፡፡

እንዲህ አይነቱ ጫናና ጣልቃ ገብነት ከበረታ ምሁራኑ የማያውቁት ህይወት ስለሆነ ቀድሞ ወደነበርንበት ስራችን ማስተማርና ምርምሩ እንመለስ ወይንም በፈቃደኝነት ስራዬን ለቅቄአለሁ የሚሉበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችልም ስጋታቸውን የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ክላስተር፣ ልዩ አማካሪ በሚል ብዙ ሚኒስትሮች ከአንድ በላይ ምክትል ጠ/ሚ/ሮች የነበሩበት ሁኔታ መታረሙ ተገቢ ነው፤ የሴቶች ቁጥር በመንግስታዊው ከፍተኛ የአመራር ቦታም ቀንሶና አንሶ መገኘቱ ሊስተካክል ይገባዋል፡፡

በሀገሪቱ 70 በመቶ የደረሰውን ወጣት እንዴትና በምን መልኩ ወደ ስራ እናሰማራው? ምን እንፍጠርለት? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ በፍጥነት የሚመለስበት ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ አዲሱ አመራር የተቻለውን ያህል ርብርብ አድርጎ በቅድሚያ መስራት ያለበት በህዝቡ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ነው፡፡ ህዝቡ እንዲማረር እንዲከፋ ከመንገድ እንዲወጣ ታላቁን ሚና የተጫወቱት የራሱ የኢህአዴግ አባላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሄንን ቀዳዳና ክፍተት ለመጠቀም ኦነግ፣ ግብጽና ሌሎችም በሰፊው ጥረት አድርገዋል፡፡

ሕዝቡ የተሸረሸረው እምነቱ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ለማድረግ የሚቻለው በተግባር የሚታዩ ተጨባጭ ምላሾችን በመስጠት ብቻ ነው፡፡ በድሮ በሬ ያረሰ የለም እንዲሉ ዛሬም ግትርና የተቸከለ አስተሳሰብ የሚያመነዥጉ፣ የጠባብነትና የትምክህት እሳቤን እንደትልቅነት የሚቆጥሩ ካሉ ከስህተታቸው ካልታረሙ ህዝቡን በትክክል አላወቁትም ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ መሄድ ዳግም ሀገራዊ ቀውስ ከመፍጠር ውጪ የሚያመጣው ፋይዳ እንደሌለ መታወቅ አለበት፡፡