ህብረ-ብሄራዊነታችን የአንድነታችን ማሰሪያ ገመድ ነው

ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአገራችን የብዝሃነት አንዱ መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የውበታችንና የጥንካሬያችን ምንጭ ጭምር ናቸው። በኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 39 ላይ “ብሔር፣ ብሔረሰብ” የሚለውን ቃል ሲያብራራው ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ልምዶች፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልከዓ ምድር የሚኖሩ  ህዝቦች ናቸው ይላቸዋል።

 

ህገ-መንግሥታችን የአገራችንን ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በተመለከተ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የተዛነፉ አስተሳሰቦችን ያስተካከለ፣ በአገሪቱ ይታይ የነበረውን የሠላም እጦትን እልባት እንዲያገኝ ያደረገ  ሰነድ ነው።  ህገ መንግሥታችን የቡድንና የግለሰብን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያስከብር፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህሎችንና ኃይማኖቶችን  እኩልነት  ያረጋገጠ የአዲሲቷ  ኢትዮጵያ የህልውና መሠረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁባት አገር ናት። በመሆኑም በ1983 ዓ.ም አገራችን የነበሯት አማራጮች ሁለት ነበሩ። የመጀመሪያው የህዝቦቿን ህብረ ብሔራዊነት ተቀብላ ማስተናገድ አሊያም በነውጥና ሁከት በመቀጠል ወደማይቀረው መበታተን መግፋት ነበር። በመሆኑም አገራችን ትክክለኛውን የህዝቦቿን ፍላጎት መሠረት ያደረገውን  መንገድ መከተል በመቻሏ ህዝቦቿ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት በመመሥረት ተከባብረውና ተደጋግፈው አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት  የሚረባረቡባት አገር ለመሆን በቅታለች።

 

የህብረ-ብሄራዊነት ዋነኛ መገለጫዎች ከሆኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል የብሄር፤ የቋንቋ፤ የኃይማኖት እና የባህል ብዝሃነት ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ብዝሃነት በህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚኖር ትልቅ አሴት ነው። ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ ነው። ልዩነቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ  የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር በመሆን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነትን የሚያጠናክር የአንድነት ማሰሪያ ገመድ በመሆን ያገለግላል። 

 

ህብረ ብሄራዊነትንም ማስተናገድ እንዲቻል ህገ መንግሥታችን አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በሀገራችን ብዝሃነትን እውን ለማድረግ ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል የፌዴራል ሥርዓቱ አንዱና ዋነኛው ነው። የፌዴራል ሥርዓታችን ብዝሃነትን ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ የአገሪቱ ሠላም በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል። ብዘሃነትን ማስተናገድ ማለት በአብሮነትና በመቻቻል፣ ልዩነቶችን በማጣጣም አብሮ መኖር ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ በኃይማኖቶች፣ በብሄሮች፣ ብሄረሰሰቦችና ህዝቦች፣ በጾታ ወዘተ…መካከል ያለውን ግንኙነት በመቻቻል፣ በመከባበርና በመረዳዳት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ህብረት እንዲሆን ለማድረግ በሚፈጠረው መልካም ግንኙነትን የሚረጋገጥ የአብሮነት ውጤት ነው፡፡

 

ብዙሃነት በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት የውበትና የጥንካሬ ምንጭ ለማድረግና ለማጎልበት በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል። እንዲሁም ብዝሃነት ማለት መቻቻል ማለት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶቻችንን በፈጠሩት እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶቻችን ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ (መረዳዳትን) መፍጠር ነው፡፡ መቻቻል ለአብሮነት የሚያስፈልግ የጋራ እሴት ቢሆንም ተቻችሎ ለመኖር ግን አንዱ የሌላውን እምነት፣ ምንነትና ማንነት በጥልቀት ማወቅ ጠቃሚ ነው። ከእነዚህ መተዋወቂያ መንገዶች ውስጥ አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ቀን ነው።  

 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል ለህዝቦች የእርስ በርስ ትውውቅ እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው ሦስተኛ የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ህገ መንግሥቱ የፀደቀበትን ቀን ተንተርሶ በየዓመቱ ህዳር 29 የኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር ወስኗል። በዚህም መሠረት  ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በጥንታዊቷ የታሪክና የንግድ መናኸሪያ በሆነችው የምሥራቁ የአገራችን ክፍል በሐረር ይከበራል።

 

ኢትዮዽያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አገር በመሆኗ ይህ ቀን እንዲከበር መወሰኑ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ህዳር 29 ቀን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ቀን በሚል እንዲከበር በዋነኛነት የተወሰነው የአገራችን ህዝቦች ተመካክረውና ፈቅደው ያፀደቁት ህገ-መንግሥት ያስገኙላቸውን ጥቅሞች እንዲያስቧቸው ለማድረግና በቀጣይ ማከናወን የሚገባቸውን ተግባሮችም ለመምከር እንዲችሉ ጭምር ነው። ከሀገሪቱ ህገ-መንግሥት መሠረታዊ መብቶች መካካል ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ባህል ቋንቋን  ማሳደግ፣ ልማትን ማፋጠን፣ ከልማት እኩል ተጠቃሚ መሆን ወዘተ…ናቸው፡፡ የዘንድሮውም ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም  በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በሐረር ከተማ ለ11ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል።

 

የዘንድሮውን ጨምሮ እስካሁን ለ11ኛ ጊዜ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ተከብሯል። የመጀመሪያው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም “ህገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው” የሚል ነበር። ሁለተኛው በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልል አስተናጋጅነት በሀዋሣ ከተማ በ2000 ዓ.ም በድምቀት ሲከበር መሪ ቃሉም “ልዩነታችን ውበታችን፤ ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን ነው” የሚል ነበር።

 

ሦስተኛው ደግሞ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት በአዲስ አባባ በ2001 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም “ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥናለን” የሚል ነበር። አራተኛው በምሥራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች አዘጋጅነት ማለትም ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በጋራ በድሬዳዋ ከተማ በ2002 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም “መቻቻል ለዴሞክራሲያዊ አንድነትና ልማት” የሚል ነበር ።

 

አምስተኛው በአዲስ አበባ በ2003 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም “የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘን የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ እናደርሳለን” የሚል ነበር። ስድስተኛው ደግሞ በ2004 ዓ.ም በትግራይ ብሄራዊ ክልል አስተናጋጅነት በመቀሌ ሲከበር መሪ ቃሉ “ህገ መንግሥታችን ለብዝሀነታችን ለአንድነታችንና ለህዳሴያችን” የሚል ነበር።

 

ሰባተኛው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ባህር ዳር በ2005 ዓ.ም ተከብሯል።  መሪ ቃሉም “ብዙም አንድም ሆነን በመለስ ራዕይ በህገ መንግሥታችን ለህዳሴያችን” የሚል ነበር።  ስምንተኛው ደግሞ  በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ሲከበር መሪ ቃሉም “ህገ መንግሥታችን ለህዳሴያችን” የሚል ነበር።

 

ዘጠነኛው የታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚከናወንበት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት በአሶሳ “በህገ መንግሥታችን የደመቀው ኢትዮጵያዊነታችን ለህዳሴያችን”  በሚል መሪ ቃል ተከል። አሥረኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን  በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በጋምቤላ ከተማ በ2009 ዓ.ም ሲከበር የነበረው መሪ ቃልም “በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ የላቀ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” በሚል ነበር።

 

ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ "ህገ መንግሥታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው በምሥራቅ የአገራችን ክፍል በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በሐረር ከተማ ነው። ከተማዋም የአካባቢውን ነዋሪዎችና እንግዶቿን ለመቀበል ሽር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች። በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ብዝሃነት እንዲጎለብት ሲደረግ በሥርዓቱ ውስጥ በተሻለ ደረጃ ግልጽነትን ስለሚፈጥር ለኪራይ ሰብሳቢነት፤ ለጥበትና ትምክህት እንዲሁም ለፀረ ሠላም ኃይሎች የመደበቂያ ዋሻን ለመናድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር እድሉ ትልቅ ነው፡፡ እንዲሁም ብዝሃነት ለኃይማኖትና ለብሄር ማክረርም ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም።

ኢትዮጵያ የብዙ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁባት አገር ናት። አገራችን ይህን ብዘሃነቷን ማስተናገድ የማይቻላት ከሆነ የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ የሚወድቅበት ሁኔታ እንደሚፈጠር መገመት የሚከብድ አይደለም። የባለፉት ሥርዓቶች የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መብት በመደፍጠጥ ወጥ ባህልና ወግ ለመፍጠር ካደረጉት ሙከራና ከደረሰው ውድቀት ልንማር ይገባል። Top of Form

Bottom of Form