የግብርና ማቀነባባሪያ፤ ባለተስፋው የልማት ዘርፍ

የኢፌዴሪ መንግስት በሚቀጥለው ዓመት ወደሥራ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ አራት የግብርና ማቀነባበሪያ (agroprocessing) ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስገንባት ማቀዱን አስታውቋል። መንግስት በአጠቃላይ 17 የግብርና ማቀነባባሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ነው እቅድ የያዘው፤ ከእነዚህ መካከል ዘንድሮ ግንባታቸው ይጀመራል ተብለው የሚጠበቁት ለናሙናነት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና ትግራይ ክልሎች የሚገነቡት ናቸው።

የግብርና ማቀነባበሪ ፋብሪካ ምን ማለት ነው? የግብርና ማቀነባባሪያ ወይም አግሮ ፕሮሰሲንግ የተለመደ ፍቺው ከግብርና የተገኘን ምርት በጥሬ እቃነት ወይም በመካከለኛ ደረጃ በተዘጋጀ ግብአትነት በመጠቀም የሚከናወን የማምረት ሥራ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ከእርሻ (ከሰብል ምርት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከቃጫና መሰል ተክል፣ ቡና . . .) ከደን፣ ከአሳ ማስገር፣ ከንብ ማነብ፣ ከእንስሳ እርባታና ማደለብ፣ ከቆዳ፣ ወዘተ. የተገኙ ምርቶችን በግብአትነት በመጠቀም በማምረት ሂደት ፍጆታ ላይ ወደሚውል ወይም በበለጠ እሴት ጭመራ ወደ ሌላ ምርትነት የሚለወጥ ምርት ማምረት ማለት ነው።

የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በተለይ በግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ያላቸውን አገራት ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር በእጅ ያለ ተጨባጭ አቅም ነው። የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የአርሶ አደሩን ምርቶች በግብአትነት ስለሚጠቀሙ፣ አርሶ አደሩ ለማምረቻ ኢንዱስትሪ ግብአት ሊሆን የሚችሉ የገበያ ምርቶችን እንዲያመርት ይበረታታል። ከዚህ በተጨማሪ አግሮ ኢንዱስትሪ በበቂ ሁኔታ ሲሰፋፋ አርሶ አደሩ በቂ ገበያ ስለሚያገኝ ምርታማነቱን ለማሳደግ ይበረታታል። የምርት ጥራቱንም ያሻሽላል።

የግብርና ማቀነባባሪያ ፋብሪካዎች የግብርና ምርቶችን የፋብሪካ ግብአት ሊሆኑ በሚችሉበት የጥራት ደረጃ ለማቅረብ፤ የማጠብ፣ የማድረቅ፣ የማጥራት፣ . . . ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ የቅድመ ምርት ስራዎችን ስለሚሻ ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል። በጥሬው ወደውጭ ሲላኩ በነበሩ ምርቶች ላይ በተለያየ ደረጃ እሴት መጨመር  ስለሚያስችል ለሰለጠነ የሰው ኃይል የስራ እድል ይፈጥራል። እሴት በመጨመር ወደውጭ ከሚላክ ምርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ  ማግኘት ያስችላል።

አሁን በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ፋይዳ ያሏቸውን ፋብሪካዎች ለማቋቋም ነው የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የተወሰነው፤ በጽሁፉ መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡበና በትግራይ ክልሎች የሚገነቡት የኢንደስትሪ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የዲዛይን ሥራ በታህሳስ ወር እንደሚጠናቀቅ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የፋብሪካዎቹ ግንባታም በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የግብርና ማቀነባባሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከ250 እስከ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፉ ናቸው። እያንዳንዳቸው ከ100 እስከ 300 ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ይይዛሉ።

የግብርና ማቀነባባሪያ ኢነዱስትሪ ፓርኮቹ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገቡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማፋጠን ረገድ የጎላ ሚና ይኖራቸዋል። ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያም አራቱ ፓርኮች እያንዳንዳቸው ለ200 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገነቡት ፋብሪካዎች ለግል ባለሃብቶች ይሰጣሉ። ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በፓርኩ ውስጥ የሚገነቡትን ፋብሪካዎች ከሚይዙት ባለሃብቶች መካከልም 80 በመቶ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሆኑ ይደረጋል።

ፋብሪካዎቹ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለኢንዱስትሪ እንዲያቀርብ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻል በተጨማሪ፤ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ወጣቶችን በማደራጀት በግብርና ምርቶች ላይ የተወሰነ እሴት በመጨመር ለፓርኮቹ ግብዐት ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ይህም በተለይ ለበርካታ የገጠር ሥራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የጠበቃል።

የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ለመገንባት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ30  ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስፈልጋል። የፓርኮቹ ግንባታ መንግሥት ለዚሁ ተግባር ከመደበው በጀት በተጨማሪ ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ)፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፤ ከአውሮፓ ኅብረት የኢንቨስትመንት ባንክ፤ ከእንግሊዝ የልማት ኤጀንሲ፤ ከኮሜሳ የንግድና ኢንቨስትመንት ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል። ከልማት ባንክ የሚገኝ ብድር፤ ክልሎች የሚመድቡት በጀት፤ እንዲሁም የተባባሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስፈጸም አገሪቱ የምትመድበው በጀትም ለዚሁ ዓላማ እንደሚውል ታውቋል። የልማት ባንክ በማኑፋክቸሪንግና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ለማሽነሪ መግዣ ብድር የመደበው 41 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ ገንዘብ በፓርኮቹ ውስጥ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች እንደሚሰጥ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከዚህ ባሻገር ለፓርኮቹ ግንባታ የጣሊያን መንግስት 110 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ፤ ደቡበ ኮሪያ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ቃል መግባቷን ተከትሎ የ268 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ፕሮጀክት እንደቀረበላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሁኑ ግዜ የኮርፖሬሽኖች ሞዴል ደንብ፤ መዋቅር፤ የሥራ ኃላፊዎች የሥራ ዝርዝር የተዘጋጀ ሲሆን፤ ፓርኮቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም ተቋቁሟል።

በአጠቃለይ፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡት የግብርና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አገሪቱ ያላትን የግብርና ምርት በግብአትነት በመጠቀም እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ማሳደግ ያስችሏታል። ከግብርና ወደኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግርም ያግዛል። የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከዝቅተኛ እስከከፍተኛ የሞያ ደረጃ ያለው በርካታ የሰው ኃይል ስለሚጠቀሙም አሁን በአገሪቱ ጎልቶ የሚታየውን የወጣት ሥራ አጦች ቁጥር በመቀነስ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል።