ዓለምን አንገት ያስደፋው ሕገ-ወጥ ስደት

 

 

እያንዳንዱ ዘመን ራሱን የሚገልፅበት መንፈስ እንዳለው ይታመናል፡፡ እናም ይህን መሰረተ ሀሳብ መነሻ አድርገን አሁን ላይ የሚስተዋለውን ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ እውነታ ለመገምገም ብንሞክር በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የዘመናችን መንፈስ መገለጫ ክስተት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሕገ ወጥ መንገድ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያስደነግጥ መልኩ እየጨመረ እንደመጣና ይልቁንም ደግሞ ወደ ባለፀጋው የአውሮፓ አህጉር ለመሻገር ሲሞክሩ የተሳፈሩበት ጀልባ አደጋ እያጋጠመው ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ የሚሰጥሙ አፍሪካውያን ወጣቶች ጉዳይ መላውን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አንገት የሚያስደፋ የዕለት ተዕለት መጥፎ ዜና እንደሆነ ከተረዳን ሰነባብቷልና ነው፡፡

በጎርጎሪሳውያኑ የዘመን ቀመር ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ ይበልጥ እየተባባሰ የመጣው ስደት ወይም የሰዎች ፍልሰት ጉዳይ ለመላው አውሮፓ እንደዋነኛ ችግር በመሆኑ፤ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራትን የሚመሩ መንግስታት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጀንዳዎቻቸውን ቅኝት ከዚሁ የዘመናችን ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢ ክስተት ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመቃኘት መገደዳቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሰሞኑ በተካሔደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን እንዲያሸንፉ ያደረጋቸው አንዱ አጀንዳም፤ ሰውየው ሕገወጥ ስደት የሽብርተኝነት ምንጭ ስለሆነ እርሱን የሚያስቀር ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፌ አሜሪካንና አሜሪካውያን ላይ የሚፈፀመውን የሽብር ጥቃት አስቆማለሁ የሚል መሰረተ ሀሳብ የያዘ መሆኑን ማስታወስ ይቻላል፡፡

በተለይም ደግሞ ጉዳዩን ወደራሳችን ስናመጣው፤ ኢትዮጵያን ከሕገ-ወጥ ስደት ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሳ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ሆና እናገኛታለን። ካለፈው የጋራ ታሪካችን የወረስናቸው የፈርጀ ብዙው ድህነታችን መገለጫዎች ሁሉ፤ በሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅእኖ ገፋፊነት አሁንም ድረስ አገር ወገናቸውን ጥለው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በባሌም፣ በሞያሌም መሰደድን የሚመርጡ ወጣት ዜጎቻችን ቁጥራቸው ጥቂት እንዳልሆነ ይታመናልና ነው፡፤

ይህን ስልም ደግሞ፤ በተለይ ወደ አረብ አገራት ለመሔድ ሲባል የሚደረገውን የባህር ላይ አደገኛ ጉዞ ጨምሮ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካና በሰሜን አፍሪካ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚደረገውን ሕገ-ወጥ ስደት ለማመልከት እንጂ ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው ባሻቸው ጊዜ ወደፈለጉት የዓለማችን ክፍል የመንቀሳቀስ መብት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከአገር ሲወጡና ሲገቡ የሚስተዋሉበትን አግባብ ለመንቀፍ እየቃጣኝ አይደለም፡፡ እናም ሕገ ወጡን መንገድ ተከትለው ወደተለያዩ አገራት የመሰደድ ፍላጎት እያደረባቸው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሞክሩ ውጤቱ እነርሱ ከገመቱት ፈፅሞ የሚቃረን እየሆነባቸው ላልተጠበቀ አደጋ ሲጋለጡ በሚስተዋሉት ወገኖቻችን ላይ ስለሚደርሰው አሰቃቂ ጉዳት በሰማን ቁጥር ልባችን ክፉኛ ይደማል።

ለዚህ እንደ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለውም በ2006 ዓ.ም የሳውዲ አረቢያ መንግስት ሕገ ወጥ ስደተኞችን ከአገሩ እንዲወጡ በማድረጉ ምክንያት፤ የእርምጃው ግንባር ቀደም ኢላማ የመሆን እጣ በገጠማቸው ብዙ ሺህ ዜጎቻችን ላይ የደረሰው እንግልት የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግስት ክፉኛ ቅር ያሰኘ ክስተት ሆኖ ማለፉን ጨምሮ፤ ሌሎች ከዚያ ወዲህ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቻችን ለአሰቃቂ ጥቃት የተጋለጡባቸውን ተመሳሳይ ክስተቶች በሰማን ጊዜ እንደ ህብረተሰብ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶን የታየበት እውነታ ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ በ2007 ዓ.ም ሊቢያ ውስጥ በሚገኝ በረሃማ ስፍራ አይ.ኤስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን ከሰላሳ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በስለት እየቀላ ሲገድላቸው የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል የለቀቀበት ሰይጣናዊ ድርጊት፤ መላውን የአገራችን ሕዝቦችና መንግስትንም ጭምር ከመጠን በላይ ያስደነገጠ የጭካኔ ተግባር እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዚያው ሰሞን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተቀሰቀሰ የአገሬው ሰዎች ፀረ ስደተኛ ተቃውሞ ምክንያት የጥቃቱ ሰለባ በሆኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት ሰምቶ ያልተንገበገበ ዜጋ እንዳልነበረም ይታወሳል፡፡

ሕገ ወጥ ስደትን ከድህነት ማምለጫ መንገድ አስመስለው የሚተርኩ ህሊና ቢስ ደላላዎች በሚያማልል ባዶ ተስፋ አነሁልለው ለአደጋ ያጋልጧቸውን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከዚህ አኳያ የተሻለ ማሳያ ይሆናል የምለው፤ የሶማሊያን ወደቦች እንደ ጥሩ መረማመጃ በመጠቀም ወደ የመን ለመሻገርና ከዚያም ወደ ሳውዲ አረቢያ ዘልቀው ለመግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሳፈሩበት የሶማሌዎች ጀልባ እየተበላሸ ህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ሰጥመው ሲቀሩ የሚስተዋሉበት ተደጋጋሚ ክስተት ነው፡፡ እንዲያውም እውነቱን መነጋገር ካለብን፤ በሶማሊያ በኩል ወደ አረብ አገራት ለመሻገር ሲሞክሩ በሚያጋጥማቸው የባህር ላይ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡት ዜጎቻችን፤ እንዲሁም፤ ሌሎችም ተመሳሳይ ገፅታ ያላቸው ተግባራት ከዚያ ወዲህ ተከስተው እንደህብረተሰብ ያዘንንበትን እውነታ ማስከተላቸው አይዘነጋም፡፡

እንግዲያውስ እኔም፤ ለመሆኑ ከዚሁ የዘመናችንን ዓለም አንገት እያስደፋ ካለው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ መልኩ በአገራችን ወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት የሚያስቀር ዘለቄታዊ መፍትሔ ስለማፈላለግ ጉዳይ የኢፌዲሪ መንግስት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ መንግስት ወጣቶችን በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፓኬጆችን እንደቀረፀ፤ ለዚሁ ዕቅድ ማስፈፀሚያም የሚሆን የአስር ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበም ጭምር መግለፃቸውን እንደ መልካም ዜና ይወሰዳል። በዚህ ረገድ ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ ከዋለ ብዙ ቀዳዳዎችን መድፈን የማይችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደማይኖር ያለኝን እምነትና ዕቅዱ ወደ ተግባር ተቀይሮ ከላይ የተወሱትንና ሌሎች ያልተጠቀሱ የወጣት ዜጎቻችን አሳሳቢ ችግሮች የሚያቃልል መፍትሔ ሲያመጣ የምናይበት ቀን ሩቅ እንደማሆን ያለኝን ተስፋም እንገልፃለሁ፡፡

በተረፈ ግን የአገራችን ወጣቶች ጥሮ ግሮ የማትረፍ ብሩህ ተስፋ ሰንቀው ለኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ መሳካት የሚተጉ የልማት አርበኞች እንዲሆኑ ማድረግ እየተቻለ ከዚህ በተቃራኒ ተሰልፈው የጥፋት ኃይሎችን ዕኩይ ተልዕኮ ለመፈፀምና ለማስፈፀም ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አግባብ መኖር የለበት ባይ ነኝ፡፡ በግልፅ አነጋገር፣ መንግስት አሁን ለነደፋቸው ተጨማሪ የወጣቶች ልማት ፓኬጆች የመደበውን አስር ቢሊዮን ብር በአግባቡ ለታለመለት ግብ መዋል አለመዋሉን ተከታትሎ ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተፅእኖ እንዲያሳድርና ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የአገራዊ ዕድገቱ ተቋዳሽ ነኝ ብሎ እንዲያምን ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ይጠበቅበታል! የሚል አቋም አለኝ፡፡ መዓ ሰላማት!