አክራሪነትን ወይም ጽንፈኝነትን በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ለመረዳት መሞከር ለጋራ የመግባባት ድምዳሜ በመጠኑም ቢሆን ያስቸግር ይሆናል። በተለይ አክራሪነት ከአጥባቂነት ጋር ያለውን ልዩነት ለመገንዘብም እንዲሁ ሳያስቸግር አይቀርም የሚል እምነት አለኝ። አንዱን ከአንዱ እየደበላለቅንና እንዳሻን ትርጓሜ ስንሰጥ ስለሚስተዋል የአክራሪነትና የአጥባቂነት ተግባራትን እንደየገጽታቸውና እንደየባህሪያቸው ለያይቶ ማየቱ በሁለቱ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት እንድንረዳ ያስችለናልና በጥቂቱ ዳሰስ አድርገን እንየው።
እንዲሁ በደምሳሳው አጥባቂነት ሠላማዊ ተግባር ሲሆን አክራሪነት ግን ፀረ ሠላም ተግባር ነው ማለት ይቻላል። አጥባቂነት በራስ ዙሪያ የታጠረ ሲሆን አክራሪነት ግን የሌሎች ህይወትና መብት የሚነካ እንቅስቃሴ ጭምር ነው።
አክራሪነትን ይበልጥ ለመገንዘብ ደግሞ በተለያዩ አገራት የተፈፀሙና የበርካታ ንጹኃንን ህይወት የቀጩ ድርጊቶችን መለስ ብሎ ማየት ጠቃሚ ይሆናል። በታላቋ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ ወደ አፍሪካም ስንዘልቅ በኬንያ፣ በዑጋንዳ፣ በሶማሊያና በናይጄሪያ የተፈፀሙ የአሸባሪዎች እኩይ ተግባራትን በመመርመር አክራሪነትና ሽብርተኝነት ምን ያህል አስከፊ ገጽታ እንዳላቸው ለመገንዘብ አያዳግትም።
አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነት ከአንድ ኃይማኖት ወይም ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር የሚያያዝ እሴት እንዳልሆነ በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች የሚያካሂዱ ምሁራን ያስረዳሉ። የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ምንጩ የተለያየ የተዛባ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ባህሪ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ብዝኃነትንና ልዩነትን የማይቀብል ስብዕና ባላቸው ሰዎች ዘንድ የሚከወን እንደሆነም ለመረዳት ብዙ አያዳግትም።
ሌሎችን በማንነታቸው ለመቀበል ያልተዘጋጁና ማንነታቸውን ጥለው እነሱን እንዲመስሉ የሚሹ ሰዎች ናቸው አክራሪነትን፣ ጽንፈኝነትንና ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉት። መቻቻል የሚባል ነገር አይዋጥላቸውም። በእነሱ አስተሳሰብ የበላይነት መረጋገጥ ብቻ የሚያመልኩ ሌላውንም በዚህ ደረጃ የሚለኩ ሰዎችና እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያዘለና ከእኔ ሌላ ላሳር የሚል እምነት የያዙ ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚያራምዱት ተግባር ነው አክራሪነት የሚባለው።
ይህ ደግሞ ሠላምን ለማረጋገጥና የህዝቦችን እኩልነት ለማስፈን የማያስችል ጉዳይ ነው። ወደ አገራችን ተመልሰን ያለውን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን ስናይ ከላይ ከተተነተነው የተለየ ነገር አይኖረውም።
የኢትዮጵያን ሠላም የማይመኙና የያዘችውን የልማት ጎዳና ማደናቀፍ ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ለሚተጉ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነት የተደፈቀው አስከፊ ሥርዓት ናፋቂና፣ የከሰረ ፖለቲካቸውን ለማራመድ ሲሉ ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በኃይማኖት ሽፋን በአክራሪነትና በፅንፈኝነት ጎዳና ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴያቸውም በማናቸውም መሥፈርት ቢለካ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንደሆነ ለማወቅ እምብዛም አያስቸግርም።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 11 መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ኃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በማለት በማያሻማና ግልፅ በሆነ መልኩ አስቀምጦታል፡፡ አክራሪዎች ግን ይህንን መብት ለመሸርሸር የማያደርጉት ነገር የለም።
መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለት መንግሥት የህዝቦችን ሠላም አይጠብቅም፤ ሕግንና ደንብን አያስከብርም ማለት አይደለም – ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ይህንኑ ሲጠቀሙ ተስተውለዋልና።
ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ እያደረጉና ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጩ መንግሥት በዝምታ እንዲመለከታቸው ይሻሉ። የአገሪቱን ሠላም ሲያደፈርሱ መንግሥት በታዛቢነት እንዲያይ መፈለጋቸው የመንግሥት ተግባርና ኃላፊነት ጠፍቷቸው ሳይሆን ኅብተሰቡን ለማደናገር ነው። ስለሆነም በየትኛውም መንገድ መንግሥታዊ ኃይማኖት ለመመሥረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ህገ መንግሥታችንን ለመናድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ማናችንም ብንሆን ብዥታ ሊኖረን አይገባም።
መንግሥታዊ ኃይማኖት በመደንገግ ወይም ኃይማኖታዊ መንግሥት በመፍጠር ሌሎች ኃይማኖቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመደፍጠጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት የሌለውና ኢ ሕገ መንግሥታዊ የሆነ አፍራሽ አስተሳሰብ /ተግባር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል።
አክራሪው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው አኳኋን ውጭ በድርድርም ይሁን ህገ መንግሥቱን በመጣስ መንግሥታዊ ሥልጣን መያዝ እንደማይችል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ኃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የጎዳና ላይ ነውጥ እና ትርምስ መፍጠር በህጋዊ መንገድ ያጡትን ሥልጣን በአቋራጭ በግርግር ለመቆናጠጥ የመቧዘኑ ምስጢር ኃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደሆነ በግልፅ ይታወቃል።
የአክራሪው ኃይል አማኞችም ሆነ ቅዠት የተለያዩ የማደናገሪያና የፈጠራ ወሬዎችን በማዘጋጀት የምዕመናኑን አስተሳሰብ በመስለብና በማታለል የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያስችለው አፍራሽ ድርጊት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰንበትበት ብሏል።
ይህ አክራሪው ኃይል በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎች የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም። ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚተላለፍ ድርጊት ነው፡፡
ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም በግል ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተግበር ወይም የመግለፅ መብትንም የማያከብር በመሆኑ በሕዝቦች ዘንድም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።
የአክራሪነትና የፅንፈኝነት ጫፍ የንፁኃን ዜጎችን አስተሳሰብና አመለካከት በጫና የመቀየር አካሄዱ ካልተሳካ ወደ ጅምላ ግድያ የሚሸጋገር ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ በማንኛውም መሥፈርት ኃይማኖታዊ ተልዕኮ የሌለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ዜጎችን በመረጡትና በያዙት ኃይማኖት ምክንያት ለማሸማቀቅ መሞከር በኃይል ኃይማኖታቸውንና እምነታቸውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ የሚሸከም ኅብረተሰብ በአገሪቱ እንደሌለም መገንዘብ የግድ ይላል።
የእኔን ኃይማኖት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም አሊያም ከሃዲ ነህ በማለት ማሸበርም ሆነ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈፀም የእምነት ተቋማትን ማፍረስና መካነ መቃብሮችን ማውደም በእውነት በፀረ ሠላም ኃይሎች የተጠነሰሰ ሴራ በመሆኑና የሌሎችን ነጻነት በማፈን ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የተያዘ እንቅስቃሴ እንደሆነ ከማንም የሚደበቅ አይደለም።
እነዚህ ድርጊቶች የአክራሪነትና ፅንፈኝነት መገለጫዎች ናቸው። በአገራችን እየተፈፀመ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንደዚህ ዓይነቱ ሽብርተኝነት ፀረ ልማት በመሆኑ ይህንን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንጂ ለመንግሥት ወይም ለሌላ ወገን የሚተው አይደለም፡፡
የኃይማኖት አክራሪነት በጥቅሉ የዜጎችን የኃይማኖትና እምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ እንደሆነ ለማየት ይቻላል። የኃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስም ሌላው ተግባራቸው ነው። መንግሥታዊ ኃይማኖትን ለመመሥረት የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ በመሆኑ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥርዓቱን ለመቀልበስና ሕገ መንግሥቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚጠነጠን ድርጊት እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የአገሪቱን ልማት የሚቃወሙና ለልማቷ መደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎችም የቻሉትን ያህል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ላይ የሚቃጣውን ማንኛውም አፍራሽ ነገር በመቋቋምና ልማቱንና ሠላሙን አጠናክሮ በመያዝ ከራሱ አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ተምሣሌት መሆን ብቻ ሳይሆን በተግባር እያገዘ ይገኛል።
ይህ ደግሞ ለቀጠናው ሠላምና ልማት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል። አገሪቱ ሠላምና ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂ በመከተል የተለያዩ ተግባራትን እየፈፀመች ትገኛለች። ይህ ተግባሯ ደግሞ ድጋፍ ያሻዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማትም ይህንኑ ለማጠናከር ነው ቃል የገቡት።