ጠንካራ ትብብርና መደጋገፍ፤ እየተገነባ ባለው የፌዴራል ሥርዓት

አገራችን ዴሞክራሲ በትግል እውን ከሆነ በኋላ የዜጎችና የማህበረሰቦች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተከብረዋል፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን መብት ድረስ ያሉ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው የህግ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በህገ መንግስታችን ሃሳብን የመግለፅ፣ የመቃወምም ሆነ የመደገፍ፣ የመደራጀት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ በህይወት የመኖር፣ ከአካላዊ ጉዳት የመጠበቅ ወዘተ… ግለሰባዊ መብቶች ተከብረዋል፡፡ ይህ ቀጣይነት እንዲኖረውና ያለአንዳች መሸራረፍ ጎልብቶ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚቻለው አገሪቱን ለዘመናት ሲሻቸው ተቀራምተው፤ ሲያሻቸው ደግሞ ለቤተሰባቸው አካፍለውና አውርሰው ሲገዙ የነበሩ ገዥዎች በተከተሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የአገዛዝ ሥርዓት ዜጎችም ሆነ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው በስቃይና እንግልት ይኖሩ የነበረ መሆኑን ከማመንና ከመቀበል መነሳት ተገቢ ነው፡፡ ያለፈውን ጉዳትና ጥቅም ያለወቀ ትውልድ ተመልሶ እዚያው ውስጥ ስላለመዘፈቁ ምንም ዋስትና ስለማይኖር፤ 

ስለሆነም፤ ያለፈውን ገዢ መደብና ጨቋኝ ሥርዓቶች ማንሳት ነገን ለማደላደል የማያከራክር ፋይዳ አለውና ይህንኑ ለማውሳት ደግሞ በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን ከሚከበረው የብሄረሰቦች ቀን የበለጠ ምቹ አጋጣሚ ስለማይኖር ዛሬም ይህንኑ እያስታወስን፤ ዛሬንም እያነሳን ነገን ለማሰማመር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በዚህ ተረክ በመጠኑ እንዳስስ፤

ነገሩን የበለጠ ለማቅረብ ከደርግ ጊዜ መነሳት ሳይሻል አይቀርምና ከዚያው እንነሳ፤ ደርግ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ጊዜያቱ የእስትንፋሱ ማስቀጠያ አጀንዳ አድርጎት የነበረው “የኢትዮጵያ አንድነት” ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል። ከደርግ ውድቀት በኋላም የአፈና አንድነትን ማስቀጠል መሰብሰቢያ አድርገው በፖለቲካ ፓርቲና በነጻ ፕሬስ ስም የተካሄዱትን እርኩቻዎች በአንድ ወገን፤ በተመሳሳይም አንዲትም ቀን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ላለመሰለፍ የተሰባሰቡት ደግሞ በሌላ ወገን አገሪቱን ከውድቀት አፋፍ ላይ ጥለዋት የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወስና የማይዘነጋ ነው፡፡ ሁለቱ ጥጎች የመጨረሻውን ጫፍ ይዘው ሊሰነዝሩ የተዘጋጁት መባላትም ብዙዎች የኢትዮጵያ እጣ ዩጎዝላቪያን ያጋጠማት እልቂትና መበታተን እንደሚሆን አስገምቷቸው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወስና የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡  ይህ  ግምታቸው  ደግሞ ክፉ ምኞት ወይም ሟርት ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔም የነበረ ለመሆኑ ብዙ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

የወቅቱ የኃይል አሰላለፍ ዓይነተኛ መለያ የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጥያቄ ሌላ መፋለሚያ ነበር፡፡ በተለይ የእስከ መገንጠል መብት ዓይነተኛ የፍልሚያ ርዕስ የነበረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊነት ፈቅደውና ወድደው የሚጎናፀፉት፤ የኢትዮጵያ አንድነትም በሕዝቦቿ መፈቃቀድ ላይ የሚመሰረት እንጂ፤ በኃይልና በግዴታ የሚጫን መሆን የለበትም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ወጥቷል፡፡ 

“የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተራዘመ ትግል ዕውን ባደረጉት ዴሞክራሲያዊ መድረክ እየተረቀቀ ያለውን ሕገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን የራሳቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ለማንም የሚተው ጉዳይ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ የበላይነትን መያዙም በግዴታ ተጭኖ የነበረው አንድነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገርሰሱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ “ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስራ ለዳኞች መተው አለበት” ብለው ቢሞግቱም ጥያቄው የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የአትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አብረው ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን፣ እምነትና ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆኑ ይህ አቋም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ችሏል፡፡

በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በአገራቸው ዘላቂ ሰላም፤ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፤ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋልና በየዓመቱ ሊታወስና አጋጣሚውንም ልምድና ተሞክሮ ለማስፋፋት መጠቀም ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የአገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋገጡ በመላ አገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት ጥሏል፡፡

በሰፈነው ዴሞክራሲያዊ መብትና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቅስቀሳቸውን ለዴሞክራሲያዊ ፕሬስ ቦታ እስኪጠብብ ድረስ ያጧጧፉትና መድረኩን በጩኸት የሞሉት የደርግ ፀሃፌ ትዕዛዞችና ትምክህተኞች፤ የቱንም ያህል ዕሪታ ቢያቀልጡ  ሰሚ ጆሮ ግን አላገኙም፡፡ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 የተደነገገውን የፕሬስ ነፃነት ተጠቅመው የአፈና ሥርዓታቸውን ለመመለስ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመዋል፡፡ በወቅቱ የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከ1984 ዓ.ም  ጀምሮ /ከሽግግሩ ጀምሮ ማለት ነው/ በአገሪቱ እንደ አሸን ከፈሉት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አብዛኛዎቹ የደርግ የፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች በነበሩ የኢሰፓ አባላትና ወታደራዊ መኮንኖች ባለቤትነት፤ ያለበለዚያም በትምክህት ኃይሎች ቀጥታ ፋይናንስ የሚደረጉ ነበሩ፡፡ ይሁንና መሰረታዊ መብቶቹ በተረጋጡለት ሕዝብ መሃል ምንም መፍጠር አልቻሉም፡፡

በቡድን መልክ የሚገለፁ ማህበረሰቦችም የተሟላ እኩልነት ተጎናፅፈዋል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉ ማህበረሰቦች የቡድን መብቶቻቸውን የተጎናጸፉ መሆኑም እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ህልውናዋ ተረጋግጦ ልትቀጥል የምትችለው ዜጎቿንና ሕዝቦቿን አክብራ ስትይዝ ብቻ እንደሆነ በማመን ተግባራዊ የተደረገው ዴሞክራሲ አገሪቱን ለፅኑ ሕዝባዊ አንድነት አብቅቷታል፡፡ስለሆነም በሃይማኖትም ሆነ በብሔር፣ በፆታም ሆነ በሌላ መልክ የሚካሄዱ ጭቆናዎች የተወገዱበት እና ፅኑ መሰረት የተጣለበት ቀን የሚከበረው ስለዚህ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ሕዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ አርግቦታል፡፡ መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በተግባር ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ሕዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፤ ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ አዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት መከበር የጀመረውን መብት ተከትሎ በርከት ላሉ ዓመታት ጥቂት በማይባሉ የህብረተሰብ ልሂቃን ዘንድ ሰፍኖ የቆየውን “መበታተን አይቀሬ ይሆናል” የሚል ጥርጣሬ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማስወገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፤ አሁንም መፍጨርጨሮች የቀጠሉ መሆኑና በፌደራላዊ ሥርአቱ ላይ የሚወረወሩት ሟርቶች የቀጠሉ መሆኑ ቀኑን ለበለጠ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዋል ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በአገራችን እየተገነባ ያለው ፌዴራለዝም በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ስርአት ነው። ኢህአዴግ የሕዝብን ጥያቄዎች ከመሰረቱ ለመመለስ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትን ማረጋገጥ ቢሆንም፤ ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህም አዲሲቷንና በሕዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት አገር የመገንባት ራእይ ተቀርፆ እየተሰራ ነው። 

በአገራችን እየተገነባ ባለው የፌዴራል ሥርአት በክልሎች መካከል መነጣጠልና መለያየት ሳይሆን ጠንካራ ትብብርና መደጋገፍ ከመቼውም ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል።  በየዓመቱ የሚከበሩት የብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀናትም ቀድሞ የነበረውና በሕዝቦች መካከል የተረጨው በመጠራጠርና ቁርሾ ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ተወግዶ፤ በየአካባቢው የተፈፀሙ ምርጥ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን የሚለዋወጡባቸው የትምህርት መቅሰሚያ መድረኮች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ።