ሠላም ይብዛ !!

የሠላምና መረጋጋት መሠረቱ የሚያፀናው ሆነ የሚጠብቀው ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ የአገሩ ባለቤት የሠላሙም ዋነኛ ባለድርሻ ነው፡፡ በአገራችን የተለያዩ ዘመናት የታዩትና የተከሰቱት ሁኔታዎችም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ የትኛውም ዓይነት አለመረጋጋት ሲፈጠር ወይም ሲከሰት ሁኔታዎችን ተቆጣጥሮ ወደነበሩበት ሠላምና መረጋጋት የሚመልሳቸው፣ ሠላሙን የሚጠብቀው፣ የሚያስከብረው፣ ያደፈረሱትንም ተቆጣጥሮ ለህግና ለፍትህ የሚያቀርባቸው ወይንም መክሮና ገስጾ የሚመልሳቸው ህዝቡ ነው፡፡

በጥንት የአገራችን ታሪክ መደበኛ ሠራዊትና ፖሊስ ባልነበረበት ዘመን ህዝቡ በያለበት አጥቢያና ቀበሌ አለቆችን እየመረጠ ሠላሙንና ፀጥታውን ሲያስከብር፣ ቀማኞችና ሽፍቶችን ሲቆጣጠር ለአካባቢው ዳኞችና ሽማግሌዎች ሲያስረክብ የኖረበት በድንበር አካባቢም ህዝቡ ራሱ ሠላሙንና ፀጥታውን ሲጠብቅ ከውጭ ሰርጎ ገቦችና ወራሪዎች ሲፋለም አገርና ድንበሩንም ሲከላከል የኖረበት ሰፊ ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡

በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሠላም መደፍረስ ሁኔታው በቁጥጥር ሥር እንዲውል የነበረው ሠላምና መረጋጋት ተመልሶ እንዲሰፍን የህዝቡም ሠላማዊ ህይወት እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ትልቁን ድርሻ የተወጣው ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ እርስ በእርሱ ስለሚተዋወቅ ፀጉረ ልውጦችንም ለይቶ ስለሚያውቅ የራሱም ልጆች አላስፈላጊ የሆነ ጥፋት ውስጥ ተደልለው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንዳይገቡ በመምከር እየመለሰ የየአካባቢውን ሠላም ማረጋጋት ችሏል፡፡ ለአገርም ለህዝብም ወሣኙ ሠላምና ሠላም ብቻ ነውና፡፡

የሠላሙ ባለቤትና በሠላሙም ተጠቃሚው ራሱ ህዝቡ ነው፡፡ በሠላም መታጣትና መደፍረስ የሚታወከውና የሚጎዳው፣ የቤተሰቡ ልጆቹ ሀብቱና ንብረቱ አደጋ ላይ የሚወድቀው ከማንም በላይ የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው ህዝቡን ስለሆነ ነው ህዝብ ቅድሚያ ለሠላም የሚሰጠው፡፡ ሠላሙን ለማደፍረስ የሚራወጡ ኃይሎች በሚፈጥሩት ትርምስና ሁከት የችግሩ ሰለባና ቀጥተኛ ተጠቂ እንደሚሆን ስለሚያውቅ በሠላም ጉዳይ አይደራደርም፡፡

ከአቅሙ በላይ የሆነ ሁኔታ ሲፈጠር የፀጥታ አስከባሪዎች በሥፍራው ተገኝተው ጥፋትን የመከላከልና ሠላሙን የማስከበር ሥራ ይሰራሉ፡፡ ይህም ስኬታማ የሚሆነው በህዝብ አጋርነትና ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጨ አይታሰብም፡፡ ውጤት ሊያመጣም ሆነ ሊያስገኝ አይችልም፡፡

በግብጽ የበላይ መሪነት፣ አደራጅነትና አቅጣጫ ሰጪነት በኦነግና በነጃዋር መሐመድ አስተባባሪነትና አጋፋሪነት በሌሎችም ጽንፈኛና አክራሪ ተቃዋሚ ድርጅቶች ተሳታፊነት በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ተቃጥቶ የነበረው አገር የማፍረስና የማውደም ሴራ የተወሰነ ርቀት በመሄድ ታላቅ ጥፋት ቢያደርስም ቀጣዩን አደገኛ አካሄድ በፍጥነት ለመረዳት የቻለው ህዝብ ነው  እኩይ ሴራቸውን ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን ያመከነው፡፡

በርካታ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ ውድ የሆኑ የመንግሥት፣ የግለሰቦችና የኢንቨስተሮች ሀብትና ንብረት በእሣት እንዲወድም አድርገዋል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች የቱንም ያህል ለመሰወር ጥረት ቢያደርጉም ከህዝቡ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ለህዝብ አስባለሁ፣ እቆረቆራለሁ የሚል የፖለቲካ ተቃዋሚ የአገርና የህዝብ መጠቀሚያ መገልገያ ሰርቶም የሚያገኝበትን ድርጅት ተቋም ንብረት በእሣት አያጋይም፤ አያወድምም፡፡

ህዝብ የሚታከምበትን ክሊኒክና ለህመምተኞች፣ ለወላድ እናቶች አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶችን አያቃጥልም፡፡ ብዙ ሺህ ዜጎች የሚሰሩበትን፣ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ገንዘብ አግኝተው የሚያስተዳድሩበትን ድርጅት፣ የእርሻ ቦታ፣ የመንግሥት ቢሮ ወዘተ… አያጋይም፡፡ ነገም ከነገ ወዲያም እንደሚጠቅማቸው ያውቃሉና፡

ተቃውሟቸው መንግሥትን ከሆነ መንግሥት ቢቀየርም እንኳን ያ ሀብትና ንብረት ድርጅት ተሽከርካሪዎች መልሰው የሚጠቅሙት የሚያገለግሉት ህዝቡን እንጂ ሌላ ማንንም  አይደለም፡፡ እስከዚህ ድረስ የዘቀጠ አስተሳሰብ አመለካከት ያላቸውን ቅጥረኛ ተላላኪዎችን  አይተናል፡፡ ህዝቡም ማንነታቸውን በውል ለይቶ ለማወቅ ችሏል፡፡

በዚህ የጥፋት እንቅስቃሴ ፈጻሚዎች ላይ ሠላምና መረጋጋቱን ለማስከበር የአገርና የህዝብን ሀብትና ንብረት ህይወት ጭምር ከጥፋት ለመታደግ እርምጃ መውሰድ ተገቢና ትክክለኛም ነው፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች መሠረታዊ ተልዕኮም የአገርን፣ የህዝብን፣ የኅብረተሰብን ሠላም ከማንኛውም ዓይነት ጥፋት የመከላከልና የመጠበቅ ሥራ ቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡ በሌላውም አገር ከዚህ የተለየ ሥራ የላቸውም፡፡

አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ወይንም አፍሪካ ሠላምን መጠበቅና ከህዝቡ ጋር የማስጠበቅ ግዳጅ ነው ተልዕኳቸው፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት አንዣቦ የነበረውን በውጭ ጠላቶቻችን መሪነትና አዝማችነት በነኦነግና በነጃዋር መሐመድ ግንባር ቀደም ተባባሪነትና አደራጅነት በኦሮሚያ ክልል የከፈቱት የጥፋት አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ የነበረው አደጋ ተቀልብሷል፡፡ አሁንም እንደማይተኙ ይታወቃል፡፡

በአገርና በህዝብ ሠላምና መረጋጋት ላይ ምንም ዓይነት መደራደርና ትዕግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ ሰይፍ ይዞ የመጣውን በሰይፍ  ሠላምን ላለ በሠላም እንዲሉ፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ሠላም ወሣኝ የሚሆንበት በርካታ ምክንያቶች አሉት፡፡ የተጀመረውን አገራዊ ልማትና የዕድገት ጉዞ አስቀጥሎ ከድህነት ጋር የሚደረገውን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት፤ መሠረተ ልማቱን በአገር ደረጃ ክልሎችንም ጨምሮ በስኬታማ ደረጃ ከግብ ለማድረስ፤ ፈርጀ ብዙ የሆነውን የሁለተኛውን ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሳይዘገይና ሳይስተጓጎል ፍጥነቱን ጠብቆ ለስኬት እንዲበቃ ለማድረግ አገራችን የተረጋጋ ሠላም ሊኖራት  ይገባል፡፡ ሠላሟ ዘለቄታዊና የማይደናቀፍ መሆን አለበት፡፡

ሠላም ከሌለ አገራዊ እድገትን ማምጣት አይቻልም፡፡ የአገሪቷ ጠላቶች የሚፈልጉት ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ ሲሆን ይህንን ፀንቶ የመጠበቁ ኃላፊነት የፀጥታ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ ቀዳሚና መደበኛ ተግባርም ነው፡፡ በሠላም አለመኖርና መታጣት ዋናው ተጎጂ ህዝቡ ነውና፡፡

በሠላም አለመኖርና መጥፋት በርካታ ጥንታዊ ሥልጣኔ የነበራቸው አገራት በዚህ ባለንበት ዘመን በርስ በርስ ጦርነት እየታመሱ የውጭ ኃይሎችም እጅ ተጨምሮበት ዘግናኝ በሆነ ደረጃ ህዝብ ሲያልቅ ህጻናትና ሴቶች፣ አዛውንትና አሮጊቶች በአየር ድብደባና በፈንጂ በጥይት ሲረግፉ እያየን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ሶሪያ ዐቢይ ምሣሌ ናት፡፡

የቀደሙ ሥልጣኔዎች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ሐውልቶች ስንትና ስንት ሚሊዮን ቢሊዮን የአገር ሀብት ወጥቶባቸው የተገነቡ ለህዝቡ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ መሠረተ ልማቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ሰፋፊ የህዝብ መኖሪያ የነበሩ ህንጻዎች፣ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ከተሞች ሁሉ በተቀናቃኝ ኃይሎች የእልህ ጦርነት እነሱን በሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ድጋፍ እንዳልነበሩ ሆነው ሲጠፉና ሲወድሙ ወደፍርስራሽ አቧራነት ሲለወጡ እኛም ዓለምም በጋራ እያየን እንገኛለን፡፡ አገራቸውን ቆመው እየቀበሩ ነው፡፡

በአንድ የታሪክ ዘመን ገናና የነበሩ አገራትና ህዝቦች በአሣዛኝ ሊጠፉ እየተቃረቡ ይገኛሉ፡፡ መንግሥታትና ተቃዋሚዎቹ የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ በሠላምና በውይይት መፍታት ተስኗቸው በግትርና ጽንፈኛ አቋም ተገፍተው በራሳቸው እጅ የየራሳቸውን አገር እንዳልነበረ አድርገው አውድመውታል፡፡ ለዚህ ዐቢይ ምሣሌዋ ዛሬ ድረስ ያልተቋጨው የሶሪያ ሰቅጣጭና ዘግናኝ የእለት ተእለት ጦርነት ቀጥሎ መገኘቱ ነው፡፡

የመጀመሪያው የአክራሪ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቋም በሽር አልአሣድን ከሥልጣን ለማውረድ በተከታታይ ያካሄዱት የመንገድ ላይ ምድር አንቀጥቅጥ ሰልፍ እንዳለ ሆኖ በወቅቱ የተሻለ ማሰብ ቢችሉ ኖሮ ሁለቱም ወገን ተነጋግሮና ተደራድሮ አገራቸውንና ህዝባቸውን ከጥፋት ለመታደግ በቅተው ያየነው ዘግናኝ ጥፋትና ውድመት አይከሰትም ነበር፡፡

አክራሪው ተቃዋሚ በምዕራባውያን የሎጂስቲክስና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ሲታገዝ በሽር አልአሣድ ደግሞ በሩሲያና በኢራን በመረዳት ሲዋጉ ቆይተው በመጨረሻም አይሲስ የተባለው እስላሚክ ሌባንት ፍጹም አክራሪና አሸባሪ ቡድን በተፈጠረው ክፍተት መሀል ዘው ብሎ በመግባት ከሶሪያና ከኢራቅ ግዛት ሰፊ የመሬት ይዞታ በመያዝ በወታደራዊ አቅሙና ብቃቱም እየጎለበተ በመሄዱ ይኸው ትንቅንቅና ጦርነት እየገፋ ሄዶ ሶሪያን ዳግም ለማንሰራራት በማትችልበት ደረጃ እንድትወድም አድርጓታል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የነበሩ ከተሞች ሁሉ በአየር ድብደባና በከባድ መሣሪያ ውርጅብኝ እንዳልነበሩ ሆነው ወድመዋል፡፡ ዛሬም ውጊያው እንደቀጠለ ነው፡፡ ከዜጎቿ ሌላ የውጭ ኃይሎች እጅ በሰፊው ገብቶበት ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት ቀርባለች፡፡ ይኼን ሁሉ መዓትና መቅሰፍት በገዛ አገራቸውና ህዝባቸው ላይ ያመጡት የራሷ ዜጎች ለአገራቸውና ለህዝባቸው ፀንተው መቆም ለውጭ ኃይሎችም በር መዝጋትና መከላከል ባለመቻላቸው ነው፡፡ የተጎዱት፣ ያለቁት፣ የተሰደዱት አገራቸው የወደመችውና የጠፋችው ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆኖ ወደ አቧራነት የተለወጠው በእነሱውና በእነሱው ብቻ ነው፡፡

በዚህ ሊያዝኑ ሊፀፀቱ ይገባቸዋል፡፡ ሌላው ዓለም ደግሞ ከበቂ በላይ የሆነ ትምህርት ወስዶበታል፡፡ አገሩንና ሠላሙን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ተምሯል፡፡ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ሴራ፣ ቅጥረኛ ከሆኑ ለህዝብ እናስባለን ዴሞክራሲ ሰብዓዊ መብትና ወዘተ…በሚል ጭንብል ተጠልለው የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ የሚያራምዱ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ኃይሎችን በምንም መንገድ እድል እንደማይሰጣቸው በተግባር እየታየነ ነው፡፡ አገር እየገደሉ ወደ መቃብር እያስገቧት ለአገር እናስባለን ማለት የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ኦነግ ጃዋር መሐመድ ኦብነግ ግንቦት ሰባት ዓይነቶቹን ማለት ነው፡፡

እነዚህ ኃይሎች በቀጥታ በግብጽ በሻዕቢያና በሌሎችም የኢትዮጵያን ሠላምና እድገት በማይፈልጉ አገራት የሚረዱና የሚታገዙ መሆናቸውን ህዝቡ የበለጠ ያወቀበት የተረዳበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለአገሩ ሠላምና ደህንነት ለሊት ከቀን ፀንቶ የቆመውም ለዚህ ነው፡፡

በውስጥ ያሉ የመልካም አስተዳደር የፍትህ ማጣት የሙስና ችግሮች የሚፈቱት ህዝብና መንግሥት በጋራ ሆነው በሚያደርጉት ትግል ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሰበብ በመንተራስ አገርን የማጥፋትና የማውደም አጀንዳቸውን ለማሳካት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት የሚያደርጉት ያላሰለሰ ዘመቻ ብዙ ርቀት እንደማይሄድ የተረዱት ይመስላል፡፡