አዋጪው የመስኖ ልማት !!

በዘንድሮው ዓመት የመኽር ወቅት ከአምናው እጅግ የላቀ ምርት እንደሚገኝ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ከእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተገኘው የሰሞኑ መረጃ እንደሚገልፀው 320 ሚሊዮን ኩንታል ያህል የሰብል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አምና ኤልኒኖ ባስከተለው ድርቅ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለከፋ ችግር ተዳርገው የነበረ ቢሆንም መንግሥት አስቀድሞ በዘረጋው የአስቸኳይ ጊዜ ድርቅና አደጋን ለመከላከል በሚያስችለው ከፌዴራል እስከ ክልሎች፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በተዘረጋው መዋቅር ተጎጂ ለሆኑ ዜጎችና አካባቢዎች ፈጥኖ መድረስ ችሏል፡፡

ከውጭ እርዳታ ሳይጠብቅ በራስ አቅም ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ ያስከተለውን አደጋ ለመከላከል በተደረገው ርብርብ አስከፊ ችግር ከመፍጠሩ በፊት ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ የዘንድሮው ውጤት በተመሳሳይ ወይንም በበለጠ መልኩ እንዲደገም መሥራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በድርቅ የተጎዱ ወይንም ሊጎዱ የሚችሉ አካባቢዎች መኖራቸው አይቀሬ መሆኑን በማመን ብሄራዊ የምግብ እህል መጠባበቂያ አቅምን በላቀ ሁኔታ ማሳደግና ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

በሰብል ምርት ውጤታማነትም ሆነ ድርቅን በመከላከል ረገድ ቀድሞ ሲሰራባቸው ከነበሩት ሌላ አዳዲስ ሥልቶችንና ዘዴዎችን መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ ለበለጠ ውጤት ያበቃል፡፡ ድርቅን የመሰለ ተፈጥሯዊ ክስተት ከሰው ልጅ አቅም ውጪ የሚፈጠር ነው፡፡

አገራችንን በተደጋጋሚ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬም የሚያጠቃት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከምንከተለው ባህላዊ የእርሻ ዘዴ ዝናብን ብቻ ጠብቆ በዓመት ከመዝራት በመላቀቅ የመስኖ ግብርናን ማበረታታትና ማስፋፋት ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ ባህል እየሆነ እንዲመጣ ቢደረግ ድርቁንም  ሆነ የዝናብ እጥረቱ የሚያስከትለውን ችግር ለመመከት ያስችለናል፡፡   

በእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰመድ አብዲ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት በ2008/09 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ  በሰብል ተሸፍኗል። 320 ሚሊዮን  ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚሰበሰብ መገመቱን ገልፀዋል፡፡ ይኼ ውጤት መገኘቱ የበለጠ ያበረታታል፡፡ ቀጣይነት እንዲኖረው በተለየ ትኩረት ቢሰራ ከአሁኑም የበለጠ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡

አምና ኤልኒኖ በሚል ሥያሜ የሚጠራው ድርቅ ያስከተለውን አደጋ በተመለከተ  ኢትዮጵያ በታሪኳ ከዚህ በፊት ካየቻቸው ድርቆች ሁሉ የከፋውና አደገኛ የሆነው ነው የገጠማት ሲሉ ፍራንስ ኢንተርናሽናል፣ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ አሦስየትድ ፕሬስ፣ ዶቼቬሌና ሌሎችም ዘግበውት ነበር፡፡ ሆኖም ግን መንግሥት ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ አደገኛ የተባለውን የድርቅ አደጋ በራስ አቅም በመረባረብ ተጎጂ ለሆኑት አካባቢዎችና ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ የእርዳታ እህል እንዲሰራጭና ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ በእንስሳት ላይ የተጋረጠውንም ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ለመከላከል ተችሏል፡፡

ድርቁ ከከፋበት ሥፍራ ወደሌሎች አካባቢዎች የማዛወር ሥራም ተሰርቷል፤ በኤልኒኖ ምክንያት የተፈጠረውን የምርት ጉድለት ለማካካስ  ምርታማነትን ለማሳደግ  ለአርሶ አደሩ የተለያዩ  ድጋፎች ሲደረጉ መቆየታቸውን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

አምና በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች ለእርሻው ተስማሚ የሆነ የዝናብ ሥርጭት የነበረ ሲሆን ለአርሶ አደሩ የተሰጡት ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችና ክትትል የታቀደውን ምርት በማስገኘት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይታመናል፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባውም ይኼው ነው፡፡

በመኸር ወቅት በመላው አገሪቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ከ275 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መቅረቡ ብሎም ልዩ ልዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ መዋላቸው የታቀደውን ምርት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የጎላ ድርሻ እንደነበረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

በሰብል ምርት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮችንና የዋግ በሽታን በቅድሚያ ለመከላከል 264 ሺህ 599 ሊትር የፀረ ዋግ ኬሚካልን በመኸር ወቅት በማሰራጨት የበሽታ መከላከል እርምጃዎችን ለማጠናከር መቻሉንም ሚኒስቴሩ አስምሮበታል፡፡

በተለይ በአገሪቱ ቆላማና የወይና አደጋ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የደረሱ ሰብሎች በብዛት እየተሰበሰቡ መሆኑን  የደረሰው ሰብል በድንገተኛ ዝናብ እንዳይበላሽ በማሰብ ከብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባባር ለአርሶ አደሩ  መረጃዎች  በፍጥነት እንዲደርሰው እየተደረገ ነው፡፡

የአገራችን ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ሲሆን ከጥንት ጀምሮ በነበረን ባህል ገበሬው ወደ እርሻ የሚሰማራው በዓመት ውስጥ የሚመጣውን የክረምት የዝናብ ወራት ብቻ ጠብቆ ነበር፡፡ እርሻችን በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለድርቅ ለረሀብ ለምርት እጥረት የመጋለጥ ተጠቂ የመሆን ከፍተኛ አገራዊ ችግርና አደጋ ሲፈጥርብን ኖሯል፡፡

ዛሬ ትግል እየተደረገ ያለው ከዚህ ዓይነቱ ከዘመኑ የራቀና የተለያየ አካሄድ በመውጣት ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ በመለወጥ ዝናብ በሌለበት የበጋው ወራት የመስኖ ልማትን በመጠቀም ገበሬው ዓመት ሙሉ ሥራ ሳይፈታ አምራች እንዲሆን ለማስቻል የተደረገው ጥረት ደረጃ በደረጃ ውጤታማ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ በዓመት የሚመጣውን ዝናብ ብቻ ከመጠበቅ እየተላቀቀ ይገኛል፡፡

ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣበት አንዳንድ ዘመን ደግሞ የማይመጣበት የማይዘንብበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ ይኼ ሁኔታ ሲከሰት የእኛ ሰው ቦና ነው፤ ዝናብ አልዘነበም፤ ሰብል ምርት የለም፤ ከብቶች የግጦሽ ሣር የላቸውም፤ ምንጮች ደርቀዋል በአጠቃላይ ድርቅ ገብቷል የሚለው፡፡

ዘመናዊ የግብርና አሠራር ትምህርት በሰፊው ለገበሬው በማስተማር የመስኖ ውኃ ልማትን በመጠቀም በጋ ከክረምት ከጓሮ የተለያዩ አትክልቶች እስከ እርሻ ድረስ በሰፊው እያለማ ተጠቃሚ መሆን የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለእርሻ የዝናብ ውኃን ብቻ መጠበቅ ካልተገኘም በገበሬውም ሆነ በቤተሰቡ በከብቶችና እንስሳትም ላይ ከፍተኛ ችግርና ውድቀት የሚያስከትል መሆኑ በተደጋጋሚ የታየ በመሆኑ ገበሬው ፊቱን ሙሉ በሙሉ አዋጪ ወደሆነው የመስኖ ልማት አዙሯል፡፡

በመስኖ ልማት ግብርና አሠራር በመጠቀም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በደቡብ ክልሎች ጭምር እጅግ ከፍተኛ ተጠቃሚ አምራች ለመሆን በቅተዋል፡፡ ትልቁ ድርቅ በተለምዶ ይከሰት የነበረው በበጋው ወራት ነበር፡፡

ገበሬው የመስኖ ልማትን በመጠቀም በበጋውም ወራት  አትክልቶች ያለማል፤ ይዘራል፤ ያጭዳል፤ ለገበያ ያወጣል፡፡ ከፍተኛ ገቢም ያገኛል፡፡ የራሱንና የቤተሰቡን ህይወት መለወጥ ችሏል፡፡ አንዱ ትልቁ በመንግሥት ደረጃ እየተደረገ ያለው ጥረት የግብርናውን ኢኮኖሚ ከኢንዱስትሪው ጋር ተመጋጋቢ በማድረግ አግሮ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋና እንዲያድግ ማድረግ ነው፡፡

ከፍተኛ የሰብል ምርት ባለባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ፋብሪካዎችን ማቋቋም ይቻላል፡፡ ለአብነት የስንዴ፣ የገብስ፣ የሩዝ፣  የጤፍ ወዘተ…ፋብሪካዎችን በመመሥረት ገበሬው ምርቱን በተሻለ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን ሲያስችለው በሌላም ጎኑ በሚቋቋመው ፋብሪካ ውስጥ የአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ከሌሎች ከባድ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተዳምሮ በዚህም መስክ አገሪቱን ደረጃ በደረጃ ወደ አደገ ኢኮኖሚ ሊያሸጋግራት የሚችል ነው፡፡

በቅርቡ ይሰበሰባል ተብሎ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ሰብል የምርት መትረፍረፍ ቢያጋጥም የገበያው ዋጋ ከተጠበቀው በላይ እንዳያሽቆለቁልና በገበሬው ሥነ ልቦና ላይ ጫና እንዳያደርስ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን ተጠባባቂ ክምችት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ ሌሎች አገሮችም ይህን ዘዴ ይጠቀሙበታል፡፡ የከፋ ድርቅ በአንዱ አካባቢ ቢከሰት ፈጥኖ ከተጠባባቂው ክምችት በማውጣት ለተጎጂዎች  ለመድረስ ያስችላል፡፡ የመስኖ ልማቱ አዋጪነት ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባዋል፡፡