ስለሚዲያና (መገናኛ ብዙኃን) ንድፈ ሀሳብ በፖለቲከኞችና በሙያው አንጋፋ ምሁራን ብዙ ሲባልለት ኖሯል፡፡ ዋነኛው የሜኒስትሪም ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ እንዲሁም ትራዲሽናል ሚዲያ (ባህላዊው ሚዲያ) የህትመት ፕሬሱ የዛሬው ዘመን ኦን ላይን ሚዲያ ከመምጣቱ በፊት በዘመናቸው እውነተኛ፣ ትክክለኛ፣ ተጨባጭ የዜና ምንጮች ተደርገው ስለሚወሰዱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተአማኒነትና ተደማጭነት እንዲሁም ከበሬታ ነበራቸው፡፡
የቀደመው ትውልድ ይህን እምነቱን ይዞ ወደቀጣዩና ተተኪው እያሸጋገረ ብዙ መቶ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ሚዛናዊ የሆኑ፣ አድሎአዊነት የሌላቸው ዜናዎችን ታሪኮችን በማቅረብ የኅብረተሰቡን ቀልብና ልቦና በመሳብ ተነባቢነትንና ቤተሰብነትን አትርፈው ተወደው ተናፍቀው ምን ጻፉ ምን አሉ ተብለው ኖረዋል፡፡
የዓለም ኅብረተሰብ ታሪክ አካል ሆነው አገራዊና ዓለም አቀፍ ክስተቶችን እየዘገቡ ቀርፀውም ሆነ በጽሁፍ በጋዜጣ ላይ አስፍረውት አልፈዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን በህትመቱም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ቁልፉን ሚና የሚጫወቱት መሪ ተዋናዮች ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ጋዜጠኝነት ከፍተኛ ልምድን እውቀትን የሞራል ብርታትና ጥንካሬን የሚጠይቅ በየእለቱ በአዳዲስ ፈተናዎች የተሞላ የሙያ መስክ ነው፡፡
የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ተጠንቅቆ መሥራትን የሚጠይቅ ሁለት ተጻራሪ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ሚዲያውን ወይም ጋዜጠኛውን ወደየራሳቸው ወገን እንደ ገመድ ጉተታ ሊስቡት ኃያል ትግል ወሣኝ ትንቅንቅ የሚያደርጉበት መስክ ስለሆነ ከዚህ መሀል ፈልቅቆ የሚወጣ መሀል ላይ ሆኖ ሁለቱንም ወገኖች በእኩል ሚዛን የሚያስተናግድ ሚዲያ ብቻ ነው በኅብረተሰቡ ውስጥ ታማኝ የመሆን ክብርን የሚያገኘው፡፡
በዚህ ሙያዊ ልቀት ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ሽልማትና ክብር የበቁ ጋዜጠኞች በዓለማችን ታይተዋል፡፡ የሚሰሩበትን ሚዲያም ሆነ ጋዜጠኝነትን አስከብረው አልፈዋል፡፡ በህይወት ያሉም አሉ፡፡ በአውሮፓ ውስጥ ጋዜጠኝነት ብዙ የተባለለት የተነገረለት የተወደሰ ሙያ ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ኖሯል፡፡
በአውሮፓ ከቅርብ አሥርት ዓመታት በፊት የሙያው ታማኝነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ የአፍሪካንና የሌሎቹን አገራት ለጊዜው እንተወው፡፡ የባሰና የከፋም ጭምር ስለሆነ፡፡ አውሮፓዎች ጋዜጠኝነትን የጀመርነው ያሳደግነው እዚህ ያደረስነው እኛ ነን ስለሚሉ በተለይም እንግሊዞችና አሜሪካኖች አሁን ገዝፎ የተፈጠረውም ችግር የተወለደው የታየው በእነሱው ደጅ መሆኑ የሙያውን ተአማኒነት አጠያያቂ አድርጎታል፡፡
በሚዲያው ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ ለማግኘት የማይቻልበት የፈጠራ ወሬዎችና ዜናዎች በሰፊው እውነተኛ እንዲመስሉ ተደርገው የሚሰራጩበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ ከሁሉም አሳዛኙ ይኸው ነው፡፡ በተለይም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የፈጠራቸው በኢንተርኔት የሚሰራጩት የተለያዩ ዓይነት ሚዲያዎች ዌብ ሣይቶች (ፌስ ቡክን የመሰሉ ሌሎችም የፈጠራ ዜናና ውሸት በብዛት የሚያሰራጩ መሆናቸውን የአሜሪካው ቴሌቪዥን ሲኤን ኤን በሰፊው ዘግቦታል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው ሲል ጠይቋል፡፡
ኅብረተሰቡ ጋዜጠኛውን ጨምሮ ያልተረዳው ውሸትን እውነት አድርገው የሚያሰራጩት ዌብ ሣይቶች ፌስ ቡክና ትዊት አድራጊዎች የኅብረተሰቡን ቀልብ ቶሎ ስለሚስቡ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበት ንግድ መሆኑን ነው፡፡ ኅብረተሰቡን ከፍተኛ ስህተት ላይ እንደጣሉት ሙያውም ጥያቄ ውስጥ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሙያውን ከዚህ ውድቀትና ጥፋት ሊታደጉት የሚችሉት ራሳቸው ጋዜጠኞች ብቻ መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡
በአሜሪካው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር አብዛኛው መረጃዎች ግለሰቦቹ ያላሉትን እንዳሉ ተደርጎ በዌብ ሣይቶች ይሰራጭ የነበረ የፈጠራ የውሸት ዜና መሆኑ ታውቋል፡፡ በመሠረቱ የትኛውም ሚዲያ ቢሆን ነጻ ነው ተብሎ የሚጠራ የለም፡፡
ነጮቹ ፍሪ ፕሬስ (ነጻ ፕሬስ) ሲሉ ከመንግሥት ውጭ ያለ በግል የሚሰራ ለማለት እንጂ በኅብረተሰቡ ውስጥ ካለው አገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ውጭ የሚሆን የህትመትም ሆነ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ሙያው ሚዛናዊነትን፣ ትክክለኛነትንና ጭብጥን የግድ ይጠይቃል፡፡
እያንዳንዱ የሚዲያ ባለቤት እንደ ማንኛውም ዜጋ በኅብረተሰቡ ውስጥ የራሱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ አመለካከት አለው፡፡ እንደ መንግሥት ሁሉ የግሉም ኢዲቶሪያል ፖሊሲ የሚመራው በባለቤቱ የፖለቲካ አመለካከትና አቋም ነው፡፡
በአመለካከትና በአስተሳሰብ የተለያዩ መሆን የብዝሀነትና የዴሞክራሲ መገለጫ ከመሆን ባለፈ በሰለጠነው ዓለም በጠላትነት የሚያፈራርጅ አይደለም፡፡ በዘንድሮው የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋና የተባሉት የአሜሪካ ሚዲያዎች በቅርቡ በተመረጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ ሰፊ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ሚዲያዎቹ የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግዙፍ የሚዲያ ኮርፖሬት ባለቤቶች የሆኑት የኒዮ ሊበራል ኃይሎች በባለቤትነት የሚመሯቸው ናቸው፡፡ እንደ ሩፐርት መድሮክ ዓይነት የሚዲያ ግዙፎች ንብረቶች ናቸው፡፡
ትራምፕ የራሳቸው ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ትራምፕ ሚዲያ የሚባል ያላቸው ሲሆን የመዝናኛ ፕሮግራሞችም ይቀርቡባቸዋል፡፡ ለምን ትላልቅና ግዙፍ የተባሉት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ጋዜጦችን ጨምሮ በዶናልድ ትራምፕ ላይ ስም የማጥፋት ሰፊ ዘመቻ አካሄዱ የሚለው ጥያቄ ሰፊ ጉዳዮችን የሚሸፍን ነው፡፡ የጥቅም ግጭት በሰፊው አለ፡፡ እውነት ያልሆኑ ዘገባዎች በስፋት መሰራጨታቸው የሚዲያውን ተዓማኒነት አውርዶታል፡፡ ትዝብት ላይም ወድቋል፡፡
ትራምፕ በሚዲያው ዓለም ከ30 ዓመት በላይ ቅርበት ያላቸውና የሚዲያውን አካሄድ ያለውንም ከባድ ዋጋና ምን ሊሰራበት እንደሚችልም ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው መሆናቸውን መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በሰለጠነው ዴሞክራሲና በአደገው ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉት ረዥም ታሪክ ያላቸው ቀደምት ነን ብለው የሚያምኑት ሚዲያዎች በዚህ ደረጃ ወርደው ከተገኙ የሐሰት ዘገባዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን ኦባማ እንዳሉት በማሰራጨት ከተጠመዱ ቀጣዩ የሚዲያው እጣ ፈንታ ወዴት ይሄዳል፤ የወደቀውን ስሙን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያጣውን ተአማኒነት እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል የሚለው ጉዳይ የሚዲያ አውታሮች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ዘመናዊ ሚዲያ ተብሎ የሚጠራው ሶሻል ሚዲያ ፌስ ቡክን ጨምሮ ሐሰተኛ ዜናዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት ረገድ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል፡፡ ሙያው ያለውን ተቀባይነትና ክብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓለም በገሀድ እየተመለከተው ይገኛል፡፡ ለአውሮፓ ሚዲያ ለትላልቆቹ የሚዲያ ኮርፖሬቶች ታላቅ ውድቀት ነው የሆነው፡፡
ሚዲያ መቼም ነጻ ሊሆን እንደማይችል የሚዲያው ባለቤቶች የየራሳቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ግብና የኢኮኖሚ ፍላጎት እንዳላቸው በተለይ በግልጽ አፍጥጦ የወጣው በዓረቡ ዓለም የማግሬቡ አብዮት ተብሎ በሚጠራው ንቅናቄ ውስጥ ነው፡፡
ህዝቡ ወደአደባባይ እንዲወጣ፣ አመጹ ይበልጥ እንዲቀጣጠል፣ ጦርነቱ እንዲፋፋም፣ እልቂትና ውድመት በየአገራቱ እንዲፈፀም፣ መረጃ በማቀበልና በማስተባበር በቀጥታ በቴሌቪዥኖቻቸው እያንዳንዱን ክስተት በመከታተልና በማሰራጨት የጦር አዝማችና መሪ ሆነው የዓረብ አገራትን ሊቢያን፣ ሶሪያን፣ ግብጽን፣ የመንን እና ሌሎችንም ወደማይመለሱበት አዘቅት የከተቱዋቸው ግዙፎቹ ታዋቂ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡
ግብጽ ከቀውሱ ተመንጭቃ ልትወጣ ብትችልም ዛሬም እነዚሁ ሚዲያዎች ሶሪያን ወደመቃብር እየወሰዷት ይገኛሉ፡፡ እነሱ ዜናውን በማሰራጨታቸው በብዙ ሺህ ዶላሮች ተከፋይ ናቸው፡፡ በደጋፊውም በተቀናቃኙም፡፡ ኦባማ በቅርቡ እንደገለጹት ህዝቡ እውነተኛውን ጉዳይ ከፕሮፓጋንዳ መለየት አለበት፡፡ አለበለዚያ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡
ለሠላም ለሰው ልጆች ፍቅርና አንድነት ለሰብዓዊነት መከበር ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ኃይማኖት ሳይለይ ለሁሉም መብትና እኩልነት መቆም መሥራት ማገልገል የሚገባው ያደገው ኅብረተሰብ ውጤት የሆነው የተለያየ ግዙፍ ሚዲያ በጥላቻ በዘር ልዩነት በኃይማኖት ጉዳይ ውስጥ እየተዘፈቀ የሚያሰራጨው አሉታዊ የፈጠራና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዓለማችንን የከፋ ታላቅ አውዳሚ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ከወዲሁ ያሰጋል፡፡ መመለሻውም ያጥራል፡፡
ዘመቻውን በትራንስ ናሽናልና ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች በጥቂት ቡድኖችና ቢሊዮነሮች ፍላጎት የሚመራ ሲሆን የራሳቸውን ዓለም አቀፍ ጥቅም በየትኛውም የዓለም ገጽ ገብተው በኃይልም ሆነ በፈለጉት መንገድ ለማስከበር ያለእረፍት የሚሰሩ ኃይሎችም ናቸው፡፡
የግል ንብረታቸው የሆኑት ታላላቅ የተባሉት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተሰጣቸው ርዕስ የሥነ ልቦና ጦርነት በመክፈት ያንን ግብ ለማሳካት የተሰለፉ የእነዚሁ የዓለማችን ጥቂት ቢሊዮነሮች የግል ሐብትና የጥቅማቸው ማስከበሪያ ትንፋሾችና እንደ ሠራዊትም ሁሉ ብርቱ ክንዶቻቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ነጻ የሚባል ሚዲያ በዓለም የሌለውና የማይኖረው፡፡
የግል ሚዲያ የባለቤቱን ፍላጎት ጥቅም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍልስፍናውን አቅጣጫ የሚያስጠብቅ ለዚህም ጥብቅና የሚቆምና የሚሞግት በጠላትነት የፈረጀውን ከስም ማጥፋት ጀምሮ ሰፊ የሥነ ልቦና ጦርነት የሚከፍትበት መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የዘንድሮው አነጋጋሪ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድርና ፉክክር አረጋግጧል፡፡ በሚዲያዎቹም ሆነ በሶሻል ሚዲያው ማንነት ላይ ያለውን ከጀርባ የተደበቀ ማንነት አጋልጦ በአደባባይ አሳይቷል፡፡
ባህላዊ ተደርጎ የሚወሰደው ሚዲያ ፕሬሱ (የህትመት ሚዲያው) ቀድሞ የነበረውን አንባቢና ቤተሰብ ተነጥቆ በሶሻል ሚዲያው በኤሌክትሮኒክስ ኦን ላይን ሚዲያው ተሸንፏል፡፡ ገበያውም ተወስዶበታል፡፡ ዓለምን በኢንተርኔት፣ በትዊተር፣ በፌስ ቡክ፣ በያሁና ጉግል በፍጥነት መሸፈንና ማዳረስ የሚችሉ ኅብረተሰብን የሚያነጋግሩ በአጭር መልዕክት የሚነበቡ በመሆናቸው የተነሳ ለበጎ ሥራ ሊውሉ የሚችሉትን ያህል ለከፋ የጥፋት ድርጊቶች የፈጠራ መልዕክት ማስተላለፊያና ፈጣን የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ለመሆን የበቁበት ዘመን ነው፡፡
ለድሮው የኒውዮርክ ጋዜጣ ወዳጅና አንባቢ ቤተሰብ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ የፈጣኑ አዲስ ሶሻል ሚዲያ ትዊተር መደበኛ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አጫጭር መልዕክቶቻቸውን ማስተላለፉን አሁንም ተያይዘውታል፡፡ ታላላቆቹና አንጋፋዎቹ ሚዲያዎች አዲሱን ሶሻል ሚዲያ በዋነኛነት ይዞ በስም ማጥፋት በሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች በዘረኝነት ላይ የተመረኮዙ ህዝብን ከፋፋይ ጥላቻን የሚያስፋፋ ዘገባ ላይ መጠመዳቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡