ሕገ ወጥ ስደት ያብቃ!!

በስደቱ ዓለም ሁለት ዓይነት ስደቶች ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደት፡፡ የፖለቲካው ስደት በየትኛውም አገር ውስጥ ያሉ በወቅቱ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ፖሊሲና አሠራር የሚቃወሙ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎች በአገሪቱ ውስጥ በሠላም መኖር አንችልም ለህይወታችን ያሰጋናል ብለው በገመቱበት ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሲወጡ  የፖለቲካ ስደት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የጎረቤት አገራትን ድንበር አቋርጠው በመውጣት በሌላ አገር ተገኝተው ጥገኝነት ሲጠይቁ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ተመዝግበው ሌላ ተቀባይ አገር እስኪገኝላቸው ድረስ በስደተኛ ካምፕ እንዲቆዩ ሲደረግ ወዘተ…ይኼ በፖለቲካ ስደተኞች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

የኢኮኖሚ ስደተኞች በአገር ውስጥ ሰርተን ለመኖር የሚያስችል ሰፊ የሥራ አድል የለም፤  ከአገር ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለን በመውጣት ጉልበታችንን ሸጠን ሰርተን የምንኖርበትና ገንዝብ የምናገኝበት አገር መድረስ ብቻ ነው የምንፈልገው በሚል ተነሳስተው በተገኘው አጋጣሚና ቀዳዳ ሁሉ በመጠቀም ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ብንሞትም እንሙት በሚል ወስነው ከአገር የሚወጡት ናቸው፡፡

ሥራ ፍለጋ ከአገራቸውና ከቤተሰባቸው ተለይተው በሀገ ወጥ የሰው ዝውውር ላይ በተሰማሩ ሰዎች አማካይነት የሌለ ገንዘባቸውን ከፍለው ከአገር የሚወጡት ዜጎች ነገን ተስፋ ከማድረግ ውጭ ምን ዓይነት ፈተናና መከራ እንደሚገጥማቸው እንኳን አያውቁም፡፡ የችግሩን መራራ ገፈት የሚቀምሱት ከአገራቸው ከወጡ በኋላ  ነው፡፡ ድንበሩን ለማቋረጥ  በአስፈሪ ገደላ ገደሎች ሸለቆዎች ወንዞች ሐይቆች  ጥቅጥቅ ደኖች በረሀዎች ውስጥ መጓዝ ግድ ይላቸዋል፡፡

በአውሬ ተበልተው የሚቀሩ በበረሀ ወባ ተይዘው የሚታመሙ ገደል ወንዝና ባህር ወስጥ ገብተው የሚሞቱ ወዘተ…ብዙዎች ናቸው፡፡ ድንበራቸውን አቋርጠው የሰው አገር ድንበርን በህገ ወጥነት ጥሰው ሲገቡ ከፍተኛ ወንጀል በመሆኑ ተይዘው እንዳይታሰሩ አካባቢውን በደንብ ያውቀዋል ተብሎ የሚገመተውን መንገድ መሪ በመከተል ያለምግብ ያለንጹህ ውኃ በጫካ ውስጥ ተሸሽገው መዋል ማደር ግዴታ እንደሆነ የስደቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ከተሳካላቸው አምልጠው ወደከተማ ይገባሉ፡፡ ተቀባዮቻቸው በስደተኞቹ ህይወት ላይ የመወሰን ሙሉ መብት አላቸው፡፡ ሴቶች ይደፈራሉ፡፡ ለወሲብ ንግድ ሊሸጡም ይችላሉ፡፡

ወደማያውቁት አገርና ዓለም የመሄድ እድልም ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ወንዶቹ ለጉልበት  ወይንም ለተለያየ የወንጀል ሥራ እንዲሰማሩ ይደረጋሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ወዘ ልውጥ ሰዎች አይተናል ብሎ ካመለከተ ደግሞ ተከበው በፖሊስ ይያዛሉ፡፡ ይታሰራሉ፡፡ አብዛኞቹ መታወቂያ የላቸውም፡፡ ከአገራቸው ቋንቋ ውጪም የሚናገሩት የለም፡፡ ፖሊስ በመልካቸው በመለየት አገራቸውን ብቻ እንዲናገሩ ያደርግና አስተርጓሚ በመፈለግ በአቅራቢያው ባለ ፍርድ ቤት ያቀርባቸዋል፡፡

የክሱ ወንጀል በህገ ወጥ መንገድ የሌላ ሀገር ድንበር ጥሰው በመግባት ይሆናል፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች ተፈርዶባቸው ለወራት በእሥር ቤት ያሳልፋሉ፡፡ ይኼ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሚያወጡት ዘገባ ነው፡፡ በየመንም ሆነ ወደ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ላምባዱሣ መለስተኛ በሆኑ የእቃ ጭነት መርከቦች ተጠቅጥቀው እየተጫኑ ሲጓዙ የመገልበጥ አደጋ እያጋጠማቸው ከሚሞቱትም መሀል በተደጋጋሚ የእኛም ወገኖች ተለይተው የተገኙበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡

የማያውቁት አገር በስደት ሄዶ  ገና ለገና ያልፍልኛል ብለው እያሰቡ ባህር ውስጥ ሰምጦ መሞት አሳዛኝ እድል ነው፡፡ ይኼ የኢኮኖሚ ስደት በመላው ዓለም የተንሰራፋ ሲሆን አብዛኛዎቹ ስደተኞች አፍሪካውያን ናቸው፡፡ ከእዚህ ውስጥ የእኛ ዜጎችም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሰደዱት ቁጥርም የገዘፈ በመሆኑ ነው የሰሞኑ አጥር ወይንም ግንብ እንገነባለን የሚለው የትራምፕ ንግግር ብዙ ቁጣን የቀሰቀሰው፡፡ በአሜሪካ አገር ብቻ በህገ ወጥ ስደተኝነት የገቡ ህጋዊ መታወቂያና መለያ የሌላቸው 12 ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ፡፡

በዓረቡ ዓለም በተከሰተው ጦርነትና ምስቅልቅል የተሰደዱት የሊቢያ፣ የሶሪያ፣ የየመን፣ የግብጽ እና የሌሎችም አገራት ስደተኞች በአውሮፓ መብዛትና መከማቸት ትልቅ ብሄራዊ የፀጥታና የኢኮኖሚ ችግርም ደቅኗል፡፡

ኢትዮጵያ በአቅምዋ በአፍሪካ ትልቁን የስደተኞች ቁጥር በማስተናገድ ላይ የምትገኝ አገር ሆናለች፡፡ በተለይም የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ደርሷል፡፡

አገራችን እያሳየችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የመሠረተ ልማትና የግንባታ፣ የዘመናዊ እርሻ፣ የውኃ ግድብና የኤሌክትሪክ መስመር በመላው አገሪቱ መትከልና ማስፋፋት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣፤የህንጻ፣ የከተሞችና የመንገድ ሥራ መስፋፋት፣ የኮሌጆች፣ የዩኒቨርስቲዎች፣ የጤና ተቋማት፣ አዳዲስ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መስፋፋትና ግንባታ በአዲስ አበባና ክልሎች በየወቅቱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ሥራዎች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች ግንባታዎችን ስናይ እጅግ በጣም ብዙ ለፍተው ደክመው ራሳቸውን መለወጥ ለሚፈልጉ ዜጎች ሰፋፊ የሥራ እድሎች ከትናንት በበለጠ ዛሬና ነገም አሉ፡፡

ይህ እድል በተለይ ተጠቃሚ የሚያደርገው አሁን በስደት እየፈለሰ በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣውን ወጣት የሥራ ባለቤት አድርጎ በአገሩ ላይ እየሰራ፣ አገሩንም እያለማ፣ እየገነባ፣ እያሳደገ፣ በሠላም ያለችግርና ያለመንከራተት ራሱንም ለስደት አደጋ አሳልፎ ሳይሰጥ እንዲኖር የሚያስችለው ነው፡፡ የአገሪቱ ትልቁ ሀብት የነገው አገር ተረካቢ የሆነው ወጣት ትውልድ ነው፡፡

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ ውስጥ የተሰማሩትን ሰዎች በተመለከተ በዜጎቻችን ህይወት እየነገዱ ምንም የማያውቁትን ወጣቶች በመደለል ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ለአደጋ አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ ቀድሞም በዚሁ ድርጊታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አታለው በባዶ ተስፋ ከአገር አስወጥተው ለአደጋ እንዲጋለጡ ያደረጉ በመሆናቸው የተነሳ በከፍተኛ የአገር ክህደትና ዜጎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር በማስኮብለል ወንጀል በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ከፍተኛ ፍርድም ይጠብቃቸዋል፡፡

ደላሎቹ በመላው አገሪቱ ውስጥ ተስፋፍተው በሥውር እንደሚሰሩ መንግሥት ያውቃል፡፡ አሁንም ከወንጀለኛ ድርጊታቸው እንዳልታቀቡም የሚገልጹ መረጃዎች አሉ፡፡

ከስህተታቸው እንዲማሩ፣ እጃቸውን እንዲሰበስቡና እንደማንኛውም ዜጋ በአቅማቸው ሰርተው እንዲኖሩ ቤተሰባቸውን እንዲያስተዳድሩ በቅንነትና በሰብዓዊነት የተሰጣቸውን መልካም እድል ለመጠቀም ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ቀረበም ራቀ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ የተወሰደም አለ፡፡ በሌሎቹም ላይ ይቀጥላል፡፡ ኅብረተሰቡ ራሱ እየጠቆመ ነው ለህግና ፍትህ የሚያቀርባቸው፡፡

የስደት ህይወት የፈተና የመከራ የችግር ሰለባ የሆነ ነጻነት አልባ ህይወት ነው፡፡ ስደት ብሄራዊ ክብርን ኩራትን የሚገፍ የበታችነት ስሜትን የሚያሳድር የሥነ ልቡና ቀውስ ውስጥ  የሚከት ፈታኝ አደጋ ነው፡፡ ከሰውነት በታች አንሶ የመገመት የመቆጠር አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ መደፈርን መናቅን በባርነት መንፈስ መታየትን ሁሉ ይወልዳል፡፡ ከዚህ ሁሉ ነጻነትንና ክብርን ጠብቆ በአገር መኖር በአገር ላይ መሥራት በአገር ላይ ማደግ ይቻላል፡፡

በሌላው የዓለም ክፍል ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ አገራት ዜጎች አገራቸውን ያሳደጉትና ያለሙት ተሰደው በመውጣት አይደለም፡፡ ዶክተሮችንና ፕሮፌሰሮችን የተለያዩ ተመራማሪዎችን ጨምሮ በአገራቸው ከተማና ገጠር የመጨረሻው ሩቅ የተባለ ሥፍራ ጭምር ሄደው በመሥራት በመኖር ምቾትና ድሎትን ሳይመርጡ ምግብና ልብስ ሳያማርጡ ለፍተው ደክመው ሰርተው ነው አገራቸውን ለትልቅነት ያበቁት፡፡ የእኛም ወጣት ትውልድ ከውጮቹ ልምድ መማር መቅሰም ያለበትም ትልቅ ጥንካሬ ይኼንኑ መሆን ያለበት፡፡

ደን፣ ጫካ፣  ወንዝ፣  ሸለቆና በረሀ ያለበት መብራት ውኃ የሌለበት ለሥራ የተመደቡበት የትም ሆነ የት አገራቸው እስከሆነ ድረስ ሄደው በመኖር በመሥራት ነው አገራቸውን ለትልቅ እድገትና ልማት ያበቁት፡፡ ያሳደጉት፡፡ ተቀምጠው ሥራ መርጠውም አይደለም፡፡ የአገር እናትነትና ውለታ የሚከፈለውም በዚህ መልኩ ብቻ ነው፡፡ ስደት ያበቃ ዘንድ እንትጋ፡፡