ከስህተታቸው የሚማሩ “ብፁዓን” ናቸው!

ለየትኛው አገር መንግስት በሚመራው ሕዝብ ዘንድ አመኔታን ከማጣት የከፋ ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህ አኳያ መንግስታት ሁሉ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አጀንዳቸውን፤ እንዲሁም የማህበራዊ ዕድገትና ብልፅግና ትልሞቻቸውን ቅኝት የሚመሩትን አገር ሕዝብ አመኔታ እንዲያስገኝላቸው አድርገው ሲቃኙት የሚስተዋሉበት አግባብ ያለምክንያት አለመሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ በሌላው ዓለም የሚስተዋለውን ተጨባጭ እውነታ መነሻ አድርገን ጉዳዩን ወደእኛ አገር ፖለቲካዊ ገፅታ ስናመጣው የመንግስትን ሸክም ይበልጥ የሚያከብዱ እክሎች ተበራክተው የሚገኙበት ነባራዊ ሀቅ ነው የሚታየው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አመለካከት አቀንቃኝ ተቃዋሚዎች መንግስትን በሚመራው ሕዝብ ዘንድ አመኔታ ለማሳጣት ሲሉ የማይፈፅሙት ደባ የለምና ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የራሱ የገዥው ፓርቲ አባላት ጭምር ለኢህአዴግ አገር የመምራትን ስልጣን በሰጠው ሕዝብ ላይ የሚፈፅሙት አስተዳደራዊ በደል ምን ያህል መንግስትን ከህብረተሰቡ ጋር ሆድና ጀርባ እያደረገው እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችሉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት አያዳግትም፡፡

በዚህ ረገድ ሥርዓቱን ክፉኛ የሚፈታተን ውስጣዊ ችግር ስለመኖሩ መንግስት ራሱም ሲናገር ከሰማንባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱን ብቻ እንደ ምሳሌ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ እናም ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ባሳለፍነው 2008 ዓ.ም በተለይም የኦሮሚያን ብሔራዊ ክልል ለማተራመስ ያለመ ሁከትና ብጥብጥ ተቀስቅሶ ስላስከተለው ጥፋት ይቅርታ በጠየቁበት የፌዴራል ፓርላማ መድረክ ላይ “ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሱ የመደባቸው የራሳችን አባላት በሚፈፅሙት ያልተገባ ተግባርና የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ከትግራይ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ ከሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተጣልተናል፡፡ ስለሆነም መንግስት ስህተቶቹን አርሞ ከመላው የአገራችን ሕዝቦች ጋር መታረቅ ነው እንጂ ያለበት ጣታችንን ወደሌሎች መቀሰሩ ተገቢ አይመስለኝም” ያሉትነ እጠቅሳለሁ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ የፓርላማ መድረክ ላይ የተናገሩትን ጨምሮ ሌሎችም የኢህአዴግና የኢፌዴሪ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተለያየ አጋጣሚ ለምልዓተ ሕዝቡ ቃል ሲገቡ በተደመጡት መሰረት የጥልቅ ተሃድሶ መርሐ ግብር ተዘርግቶ ደረጃ በደረጃ የግንባሩን ድርጅታዊ መዋቅር የማጥራት ስራ ከተጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡

ለመሆኑ ኢህአዴግና መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ እንደስሙ ጥልቅ ነው ወይ? ይህን ለማረጋጋጥስ መለኪያችን ምንድነው? እውን ሁሉም የኢህአዴግ አባልና አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች በዕኩል ጥልቀት እየታደሱ ናቸውን? ያን ማድረግ ሳይቻልስ እቺን ሀገር ከሚፈታተኗት ወቅታዊ ችግሮች ለመታደግና የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችለንን ሀገራዊ የጋራ መግባባት ማስፈን አያዳግትምን? ይህ ጉዳይ ምን ያህል ታስቦበታል…? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ለውይይት የሚጋብዝ ሃሳብ እስነዝር ዘንድ ወድጃለሁ፡፡

ስለዚህም እንደኔ እምነት ከሆነ፤ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው ስለመጀመሩ ለምልዓተ ሕዝቡ ይፋ የተደረገባቸው ጉልህ ተግባራትን እየታዘበን መሰንበታችን በራሱ የተሃድሶ ንቅናቄውን ስፋትና ጥልቀት የሚያመላክት ገፅታ ያለው ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ በተለይም ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን እንደ አዲስ ያዋቀሩበትን አግባብና እንዲሁም ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኦ.ህ.ዴ.ድ የከፍተኛ አመራር ለውጥ ሂደቱን በፋና ወጊነት ተግባራዊ አድርጎ ያሳየበት እርምጃ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስሜት እየተቀጣጠለ ነው ብለን እንድናምን የሚጋብዙ መልካም ጅምሮች ናቸው።

ሌሎቹን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተመለከተም እንዲሁ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ጀምሮ ወደ መካከለኛውና ወደ ዝቅተኛው የአመራር አካል ደረጃ በደረጃ እየቀጠለ ያለ ጥልቅ ዕርስ በርስ የመገማገም ትግል ሂደት ላይ ስለመሆናቸው በየእለቱ ከሚሰጡት መገለጫ እንገነዘባለን።

በስተምዕራቡ የአገራችን ክፍል የሚገኙትን ታዳጊ ክልሎች (ቤንሻንጉልንና ጋምቤላን) የመምራት ታሪካዊ ሃላፊነት የተሸከሙት የኢህአዴግ አጋር ድርጅችም ጭምር በጥልቀት የመታደሱን ወቅታዊ አጀንዳ አስፈላጊነት አምነው ስለመቀበላቸው ሰምተናል።

ጉዳዩን ለተራ የፕሮፖጋንዳዊ ፍጆታ ሲባል ብቻ ለአንድ ሰሞን የሚወራለት ሆይ – ሆይታ አስመስለው ሊያቀርቡት ሲሞክሩ የሚስተዋሉ ወገኖች መኖራቸው የሚካድ ባይሆንም፤ እኛ ከምናየውና ከምንሰማው ተጨባጭ እውነታ መገንዘብ የሚቻለው ጥሬ ሀቅ ግን፤ በእርግጥም የጥልቅ ተሃድሶን አስፈላጊነት አምኖ ከመቀበል የመነጨ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት ሀገር አቀፍ ድባብ መስፈኑን የሚያመለክት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በጥልቀት የመታደስ መርሐ-ግብሩን የማሳካት ንቅናቄው ስፋትና ጥልቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመሔድ ባህሪይ እንዳለውም በተለይም የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ከሰሞኑ ለፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት ከሰጡት ወቅታዊ ማብራሪያ አስረድተዋል።

ሌላው የወቅቱ አገር አቀፋዊ የጋራ አጀንዳ ስለሆነው በጥልቀት የመታደስ መርሐ-ግብር ራስን የመፈተሸና ድክምነትን የማረም በጎ ገፅታዎች ከወዲሁ ያየንበት ኢህአዴጋዊ የውስጥ ትግል መድረክ ነው ብዬ እንዳምን ያደረገኝ ምክንያት ደግሞ፤ ብ.አ.ዴ.ን የሚመራው የአማራ ክልላዊ መንግስት ህዳር 12 ቀን 2009 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ላይ የተንፀባረቀውን ከስህተት ለመማር የመፍቀድ አዝማሚያ መኖሩ ነው፡፡

በተለይ፤ ክቡር ርዕስ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳጋቸው የ2008ቱን ሁከትና ብጥብጥ አስመልክተው ሲናገሩ “የጥፋት ኃይሎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲፈፀም ማድረጋቸው የክልላችንን ሕዝብና መንግስት በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ስለነበር የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ወገኖች ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ብ.አ.ዴ.ን መራሹ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት  ባሳለፍነው የ2008 በጀት ዓመት የተስተዋሉት አሉታዊ ክስተቶችና ክስተቶቹ የተገለፁበት ኢሕገ-መንግስታዊ አግባብ ፈፅሞ መክፈል ያልነበረብንን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለን በቅጡ መርምሮ የጉዳቱ ግንባር ቀደም ሰለባ የነበሩት ወገኖች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ስለተፈፀመባቸው ጥቃት እንዲህ ይፋ በሆነ መግለጫው ሲያወግዝና ይቅርታ ሲጠይቅ መደመጡ መሰል ችሮች እንዳይደገሙ ከእስከ ዛሬው የተለየ ቁርጠኛ አቋም መፈጠሩን የሚያመለክት የጥልቅ ተሃድሶው አዎንታዊ ጅምር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡

ምንም እንኳን፤ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገራዊ የጋራ ህልውና እንደዋነኛ የደህንነት ስጋት ሊወሰድ የሚችለውን የትምክህት ወይም ደግሞ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ በማቀንቀን የሚታወቁት ፅንፈኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች የሚያቀነባብሩትን የአመፃ ተግባር ጨርሶ ለማስቀረት ከመግለጫ ያለፈ ብዙ የቤት ስራ መስራት እንደሚጠበቅብን ባያከራክርም፤ የአማራ ክልል መንግስት ይፋዊ የቅርታ “ከስህተታቸው ለመማር የፈቀዱ ብፁዓን ናቸው” የሚያሰኝ ሆኖ እንደተሰማኝ ግን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ መዓ ሰላማት!