ለተሃድሶው ስኬት የህዝብ ተሳትፎ ጉልህ ድርሻ አለው!

መንግስት ራሱን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ማስተካከል ያስችለኛል የሚላቸውን እርምጃዎች በቅደም ተከተል በመውሰድ ላይ ይገኛል። የጥልቅ ተሃድሶው መንገድ ተጀምሯል። እንደእኔ እንደኔ መንግስት የተሻለ አስፈጻሚ የሚላቸውን ወደ ከፍተኛ አስፈጻሚነት ማምጣቱ ወይም ፈጻሚዎችን ከአንድ ቦታ ወደሌላ የስራ ሃላፊነት ያሸጋሸገው ህዝቡ በሚፈልገው ፍጥነት ለውጥ ለማስመዝገብ ነው።  መንግስት አዳዲስ  አስፈጻሚዎችን  የወደ  ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ማምጣቱ የቀድሞዎቹ አስፈጻሚዎች ህዝብ በሚፈልገው መጠንና ፍጥነት ለውጥ አላመጡም በሚል እንጂ  እነዚህ  ግለሰቦች  ተጨባጭ ለውጦችን ማስገብ የቻሉ  እንደነበሩ  ማገናዘብ  የሚከብድ አይመስልኝም።

አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት በልማት ብቻ ሳይሆን  በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ተጨባጭ ለውጦችን ያመጣችው በቅርቡ ከሃላፊነታቸው በተነሱ አስፈጻሚዎች  ጭምር መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። በመሆኑም እነዚህ አካሎች  የአገራችን ባለውለተኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።  አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰበችና የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በተመለከተ የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች እጅግ የወረዱና ከመንገድ የወጡ ሆነው አገኝቼቸዋለሁ። ለማንኛውም የዛሬ አተያዬ የእነሱን የወረዱ አስተያየቶች ለመዳሰስ ባለመሆኑ ወደርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ።  

የአገራችን ህዝቦች ፍላጎት  እጅጉን አድጓል። መንግስት መብቱን ጠያቂ ህብረተሰብ መገንባት መቻሉ በራሱ አንድ ስኬት ነው።  ጠያቂ ህብረተሰብ የዴሞክራሲ ስርዓት ስለመኖሩ አንዱ መገለጫ ነው።  የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው የሚታወቀው መብቱን የሚጠይቅና መላሽ የሚሰጥ መንግስት መኖሩን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መኖሩን የሚያሳይ ነው። መንግስትን የሚመራው ኢህአዴግም በህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን  አምኖ ተቀብሎ ራሱን የማስተካከል እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋንኛው አስፈጻሚውን አካል እንደገና የማዋቀር ስራ በማካሄድ ላይ ነው።  ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ይህ ተግባር የባለፈው ካቢኔ ደካማና ምንም አልሰራም ማለት እንዳልሆነ መታሰብ ይኖርበታል።  

በአዲስ የተተኩት አስፈጻሚዎች አገራችን በአለም ፈጣን እድገት የሚባል ማስመዝገብ የቻሉ እንደሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።  አዲሶቹ ተሿሚዎች  የባለፈውን አስፈጻሚዎች መልካም ነገሮች በመውሰድ  ደካማ ጎኖችን  ደግሞ  በማረም አገራችንን ወደተሻለ ከፍታ ማውጣት ይኖርባቸዋል። የቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በማጣጣል አዳዲሶቹን አስፈጻሚዎች ደግሞ ተዓምራዊ ለውጥ እንደሚያመጡ አድርጎ  አስተያየት መሰንዘር በቀድሞዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በአዳዲሶቹ ላይ ስነልቦናዊ ጫና ያስከትላልና አግባብነት ከጎደለው አስተያየት ልንቆጠብ ይገባል።  

መንግስት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዝገቡ ይችላሉ የሚላቸውን  አስፈጻሚዎች   ይሾማል፣ ከቦታ ቦታ ያሸጋሸጋል እንዲሁም ተጠያቂ የሚሆኑ ካሉም በህግ አግባብ ተጠያቂ ያደርጋል። ይህ በኢህአዴግ ቤት አዲስ አሰራር አይደለም።  ከፍተኛ ባለስልጣኖችን ተጠያቂ በማድረግ እንደኢህአዴግ ያለ ፓርቲ   በአፍሪካ ያለ አይመስለኝም። ከአቶ ታምራት ላይኔ ጀምሮ የነበሩ ታላላቅ የኢህአዴግ አመራር የነበሩ ሚኒስትሮችን እስር ቤት የወረወረ  ፓርቲ ነው። ኢህአዴግ በርካታ የድርጅቱን መስራች የሆኑ አንጋፋ ታጋዮችን ሳይቀር ለጥፋቱ ተጠያቂ እንዲሆን የማድረግ ልምድ ያለው ፓርቲ በመሆኑ አሁንም ይህ አሰራር የነገሰበት ነው።

አንዳንዶች መንግስት በላይኛው አስፈጻሚ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ  ከህዝብ ጋር ቀን ከቀን የሚያገናኙ የታችኛው አስፈጻሚ ድረስ ሊያወርደው ይገባዋል ሲሉ እየሰጡ ያለው አስተያየት  ተገቢነት ያለው እውነታ ነው። መንግስት  ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም ብቻ ስለሚያስቀድሙ አንዳንድ የወረዳና የቀበሌ ፈጻሚዎች  ሁኔታ በአግባብ ሊያስብበት ይገባል። በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ሕዝባዊ ዓላማ የሌላቸው ራስ ወዳዶች፣ ሕዝብን በመከፋፈል፣ የህዝብን ጥቅም ችላ በማለት  በየቦታው ችግር ሲፈጥሩ የነበሩትን የበታች አስፈጻሚዎች በጥልቅ ተሃድሶው ተነቅሰው ሊወጡ ይገባል።   

በጥልቀት መታደስ ዋንኛ አላማ መነሻና መድረሻ የመንግስት ስልጣን ለህዝብ አገልግሎት ብቻ እንዲውል ማድረግ ነው። በጥልቀት መታደስ ስም  የሚካሄዱ  የግለሰቦች ለውጥ ለጥፋተኞችና  ለኪራይ ሰብሳቢዎች መደበቂያ ጉድጓድ መቆፈሪያ እንዲሁም መልካሞችን ማጥቂያ መሳሪያ እንዳይሆንም መንግስት መጠንቀቅ ይኖርበታል። በየመድረኩ ለህዝብ ጥቅም ዋስ ጠበቃ እንደሆኑ  ራሳቸውን ለመቅረብ የሚሞክሩ የመድረክ አንበሶችን አካሄድ መንግስትና ህዝብ ሊነቃባቸው ይገባል። ህብረተሰቡ በተለይ በቅርበት ያሚያውቃቸውን የታችኛው አስመሳይ ፈጻሚዎችንና አስፈጻሚዎችን በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት መለየት  ይኖርበታል።

በመንግስትን የጥልቀት የመታደስ መርህ ህብረተሰቡም በአግባብ ተረድቶት በባለቤትነት መንፈስ ቀጥታ ሊሳተፍበት ይገባል።  ይህ ካልሆነ የመንግሥት ጥረት ብቻ በጥልቀት የመታደስ ሂደት  ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። መንግስት ራሱን በቁርጠኝነት ውስጡን ለማፅዳት እንደተናሳ ሁሉ ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን መሰለፍ ይኖርበታል።  ህዝብና መንግስት  በቅርበት በመስራት በቅርቡ የታዩ ችግሮችን መቅረፍ ካልቻሉ  አገራችን  ዳግም ወደ ችግር  እንደምትገባ  እያጠራጥርም፡፡

የጥልቅ ተሃድሶው  የሕዝብ ቅሬታና ብሶት መነሻ ማድረጉ መልካም ጅምር ነው። በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የግለሰቦችን የጥቅም ግንኙነቶች በመበጣጠስ የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው በማድረግ ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ማንገስ ተገቢ ነው።  የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱና ወንኛው ደግሞ ሚዲያው ነው። የአገራችን ሚዲያዎችም በጥልቀት መታደስ ይኖርባቸዋል። ፐብሊክም ሆነ የግሉ ሚዲያ የህዝብንና የአገርን ጥቅም ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም ሚዲያዎች ከሚያራምዱት  ጽንፍ ከወጣ አዘጋገብ   ሊታረሙና ወደቀልባቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የሚያስፈልጉን ሚዲያዎች የመንግሥት ጠንካራ ጎኖች የበለጡ እንዲጎለብቱ  በማድረግ  እንዲሁም  ድክመቶቹንም በአግባብ በመተቸት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው በማድረግ  የአገራችንን የለውጥ ጉዞ ማፋጠን ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው በጥልቀት መታደስ እውን የሚሆነው፣ የህዝብ ተጠቃሚነትም የሚረጋገጠው። አገርም ወደፊት የምትራመደው።

መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲወገድ፣ ፍትሕ እንዲነግስና    የተጀመሩ  ልማት ስራዎች  እንዲፋጠኑና አገራችን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ መሸጋገር እንድትችል  ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ ሊወጣ ይገባል፡፡ መንግስት  ከላይ ወደታች እንዲሁም  ህብረተሰቡ  ከታች ወደላይ  በማረቅ ብልሹ አሰራርን  መዋጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ህዝብና መንግስት ተቀራርበው በመስራታቸው በአገራችን በየዘርፉ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ ተችሏል። ይህን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገገጥ አሁንም ህዝብና መህግስት የበለጠ ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል።

በመንግሥታዊ ተቋማት ለአብነት በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በትራንስፖርት፣ በግዥና ጨረታ፣ በፍትሕ ስርዓት፣ በትምህርትና ጤና ተቋማት፣ ኤሌክትሪክ፣ መብራት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በተለይ በቀበሌ፣ በወረዳና በክፍለ ከተሞች የሚሰጡት አገልግሎቶች ላይ መንግስት በተሀድሶው ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ሴክተሮች ናቸው።  እነዚህ ሴክተሮች ከህዝብ እለት ከለት አገልግሎት የሚያገኝባቸው  በመሆናቸው ትናንሽ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ህዝብን የሚያማርሩ በመሆናቸው ነው።

የአገራችን  የዴሞክራሲ ስርዓት  እንዲጎለብትና   መልካም አስተዳደር  እንዲሰፍን መንግስት አሁን የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ  ህብረተሰቡ እንዲያግዘውና  ቀጥታ ተሳታፊ  እንዲሆን ማድረግ  ይኖርበታል። ምክንያቱም የመንግስት ጥረት ብቻ ለውጥ ሊመጣ እይችልም፤ ለውጥ ቢመጣም ለውጡ ዜለቄታዊነት ሊኖረው አይችልም። መልካም አስተዳደርም የአንድ ወቅት ስራ ሊሆን አይችልም።  መልካም አስተዳደር ችግሮች ነገም ተነገወዲያም የሚነሳ ችግር እንደሚሆን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው። ዋናው ህዝብና መንግስት በቅርበት በመስራት ለችግሮች አፋጣኝ መልስ መስጠት መቻል ነው።