የመታደሱ ጥልቀት ምን ያህል ነው?

 

 

ማንኛውንም ዓይነት ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ችግር በትክክል መግለጽ መቻል፤ የመፍትሔው የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ አሊያም ዶክተር፤ የታማሚውን የበሽታ ዓይነት ለይቶ የሚያውቅበት ማረጋገጫ መንገድ ሳይኖረው መድሃኒት ሊያዝለትና በአግባቡ ተከታትሎ እንዲፈወስ ሊረዳው የማይችለውን ያህል፤ ለማንኛውም ችግር ትርጉም ያለው መፍትሔ ይገኝለት ዘንድ፤ በቅድሚያ የችግሩን መሰረታዊ ባህሪይ መርምሮ፤ የተሟላ ግንዛቤና መረጃ መጨበጥ እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም፡፡

ወደራሱ ውስጣዊ ድክመቶች የማመልከቻ ድርጅታዊ የተሀድሶ ንቅናቄዎችን ተግባራዊ የማድረግ የፖለቲካ ባህል እንዳለው የሚታወቀው ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት፤ አሁን የጀመሩትን በጥልቀት የመታደስ አገር አቀፋዊ አጀንዳ፤ ከእስከ ዛሬው ተመሳሳይ ጥረት በተለየ መልኩ ‹‹ጥልቀት››የሚያሰኙት ተጨባጭ መለኪያዎች ምን ምን እንደሆኑ በግልጽ ተብራርተው እስካልተቀመጡ፤ የአሁኑን የተሀድሶ ንቅናቄ ይዘት በእርግጥም የተለየ ግምት እንዲሰጠውና ትርጉም ባለው ጥልቀት ተግባራዊ መደረግ የሚኖርበት ነው ብሎ ማጠቃለል እንደሚቻል ባያከራክርም፤ ግን የጥልቀቱን ልክ ለማወቅ የሚረዳን ተጨባጭ መሰፈርት ቢቀመጥለት ውጤቱን በመገምገም ረገድ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚለው ነጥብ ይሰመርበት፡፡

በግልፅ አነጋገር፤ ማንኛውም የተሃድሶ መርሐ-ግብር ንቅናቄ ከአመራሩ መጀመር እንደሚጠበቅበት ባያጠያይቅም፤ የታለመለትን ግብ ሊመታ የሚችለው ግን በጥልቀት መታደስ አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገውን ድርጅታዊ፤ አሊያም ደግሞ መንግስታዊ አጀንዳ በማስፈፀም ረገድ የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት የሚኖርባቸው አካላት ሁሉ አምነው እንዲቀበሉትና አመራሩ በሚያስቀምጠው አዲስ አቅጣጫ የሚሰጠውን እያንዳንዱን ተልዕኮ ለማሳካት ዝግጁ ሆነው እንዲገኙ የሚያደርግ ትርጉም ያለው የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣትን ባካተተ መልኩ ተቃኝቶ ሲከናወን ብቻ ነው።

ምክንያቱም፤ በጥልቀት የመታደሱ መርሐ-ግብር  የፌደራሉ መንግስት ካቢኔ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የተደረገበትን ለኢህአዲግ አባል ድርጅቶች እንብዛም ያልተለመደ የሹመት አቀራረብ ጨምሮ፤ አንዳንድ እንደዚያ ዓይነት የከፍተኛውን አመራር አካል ፖለቲካዊ ስብዕና ፈትሾ መልክ የማስያዝ በጎ ጅምሮችን እያየንበት ባለነው የገዢው ፓርቲና እርሱ የሚመራቸው ክላላዊ መስተዳድሮች ባለስልጣናት የስራ ሃላፊዎች ላይ እየተወሰደ ነው ተብሎ በሚነገርለት መሰል የማስተካከያ እርምጃ ብቻ እንደማይሆን ተገቢ የጋራ ግንዛቤ ሊጨበጥበት ይገባል ማለቴ ነው፡፡

ምንም እንኳን እነዚህን የመሳሰሉ የግንባሩን አባል ድርጅቶች የአመራር አካላት ቁመና በቅጡ መፈተሻ የግምገማ መድረኮች በራሳቸው አጠቃላይ መዋቅሩን በማጥራት ረገድ የሚኖራቸው አወንታዊ ተጽእኖ ቀላል ግምት እንደማይሰጠው ቢገባኝም፤ በጥልቀት የመታደሱን መርሐ-ግብር እጅግ አስፈላጊ እንዲሆን ከሚያደርጉት የአገራችን ፈርጀ ብዙ ፈተናዎች አኳያ ሲታይ ተሃድሶው የችግሮቻችንን ስፋትና ጥልቀት ያገናዘበ ይዘት ያለው ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ ግን ልፋታችን ሁሉ ከንቱ ድካም የመሆን ዕድል አይገጥመውም ለማለት ያዳግታል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ተሀድሶው የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች በመባል የሚታወቁት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሯቸውን አምስት የክልል መስተዳድሮች መዋቅር ባካተተ መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ፤ እንዲሁም ሌሎች አገር አቀፋዊ ገጽታ እንዲላበስ የሚያደርጉ የሲቪክ ተቋማትን የሚያቅፍ እስካልሆነ ድረስ ልፋታችን ሁሉ በጥልቀት መታደስ ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጋር ሊፋለስ ይችላልና ከወዲህ ይታሰብበት እላለሁ፡፡

ኢህአዴግ በ1993 ዓ.ም ያካሔደው የተሃድሶ ንቅናቄ አገራችንን ካንዣበበባት የምጣኔ ሀብታዊ ድቀት አደጋ ወይም ናዳ የታደገና በምትኩም ዛሬ ላይ “የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ” እያልን ወደምንጠራው የዕድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር ያደረገ አመርቂ ውጤት ያመጣ እንደነበር አቶ በረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” በሚል ርዕስ የፃፉት መፀሐፋቸው ላይ ገልፀዋል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ከዚያን ጊዜው የተሃድሶ ንቅናቄ ተግባራዊ መሆን ጋር በተያያዘ መልኩ መንግስታዊው መዋቅራችን ላይ አንዳች በጎ ተፅእኖ ያሳደረ አዲስ ዓይነት የአሰራር ቅኝት (ዘይቤ) ባይፈጠር ኖሮ፤ ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት አገራችን ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ፈርጀ ብዙ ማህበራዊ ብልፅግና መቀዳጀት ባልተቻለን ነበር፡፡ ለነገሩ ባሳለፍነው 2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የድህረ 1993ቱ ተሃድሶ 15 ዓመታት ጉዟችን ምን ይመስል እንደነበር የገመገመው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና ምክር ቤቱ ጭምር የአቶ በረከት መፀሐፍ ላይ የሠፈረውን ሃተታ የሚያዳብር መግለጫ ነው የሰጠው ለማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ይህም ስለአንድ ጉዳይ ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የአሁኑን በጥልቀት የመታደስ መርሐ-ግብር ተፈፃሚ ማድረግ እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ እንዲገኝ ምክንያት ከሆኑት የአገራችን ወቅታዊ ፈተናዎች አኳያ ሲታይ፤ ንቅናቄው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ስፋትና ጥልቀትን በሚጠይቅ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ከወዲሁ መረዳት አይከብድምና ነው፡፡

ስለዚህም በእኔ እምነት፤ አሁን ላይ የኢፌዴሪ መንግስት የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ አገር አቀፋዊ ንቅናቄ፤ እስከ ወረዳና እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አስተዳደራዊ መዋቅር አውርዶ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረጉ ጥረት ሁሉ፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉትን ጥቃቅን ችግሮች ሳይቀር እያባባሱ ስርዓቱን ሕዝባዊ አመኔታ የማሳጣት ደባ መፈፀምን እንደ “አዋጭ የትግል ስልት” የቆጠሩት ፅንፈኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እየፈጠሩብን ያለውን አሉታዊ ጫና ለማስቀረት የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ ሆኖ እስካልተገኘ፤ በከዚህ ቀደሙ የትግሉ ታሪክ የተከፈለውን ዋጋ መና የሚያስቀር አደጋ ሊያጋጥመን እንደሚችል ነው ሊሰመርበት የሚገባው፡፡

የመታደሱን ጥልቀትም ሆነ ስፋት የምንለካበት ተጨባጭ መመዘኛችን ሊሆን የሚገባው፤ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ ባለመ ሴራ አሰፍስፈው የሚጠብቁትን የሁከትና የብጥብጥ ተግባር አራማጆች ለመመከት የሚስችል አስተማማኝ አቅም ፈጥረን ስንወጣ ብቻ ነው እንጂ፤ ከዚህ ያነሰ ውጤት ግን ዋጋ አይኖረውም ማለቴ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡

በጥልቀት የመታደሱን ጥልቀትና ልክ ማወቅ የሚቻው መርሃ-ግብሩ ወደ እያንዳንዱ ወረዳና ቀበሌ ወርዶ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚ እንዲሆን ሲደረግና ትርጉም ያለው አወንታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ተጨባጭ የአስተሳሰብ ለውጥን ማምጣቱ ሲረጋገጥ ነው። እንጂ፤ አሁን ላይ የሚስተዋሉ አበረታች ጅምሮች ላይ የሚወሰንና ተንጠልጥሎ የሚቀር አይደለም፡፡ በተረፈ ግን ከፌደራሉ መንግስት እስከ ክልላዊ መስተደደሮች ድረስ ያሉት  አካላት የየራሳቸውን የቤት ሥራ በአግባቡ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አያጠያይቅም፡፡ በጥልቀት የመታደሱ ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ የሚታየው ያኔ ነው፡፡መዓ ሰላማት!