የራዕይ ራዕዮች!!

 

                                                      

የገዢው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ልሣን የሆነችው አዲስ ራዕይ መጽሄት ጥልቀታዊውን ተሀድሶ በተመለከተ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄያችን አስፈላጊነት ይዘትና ፋይዳ በሚል ርዕስ ሰፊና መሠረታዊ የመለወጥና የመታደስን አስፈላጊነት ከህዝቡ ፍላጎትና ከወቅታዊነት አንጻር የሚያሳዩ ጭብጦችን አስነብባለች፡፡ የፀሐፊው ትኩረትም በዚሁ አቅጣጫ ያጠነጥናል፡፡

አዲስ ብሄራዊ ራዕይ የሚተለመውም ሆነ የሚሳካው ሁልጊዜም በየደረጃው በየተደረሰበት የዕድገት ጉዞና ምዕራፍ ቆም ብሎ ጊዜውንና ወቅቱን አንብቦና ፈትሾ ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ጥልቀታዊ ተሀድሶ ሲኖር ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ዓለም እለት በእለት በፈጣን የለውጥ ሂደት እየተምዘገዘገች በመሄድ ላይ ባለችበት በዚህ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመን ስለትናንት እያወሩ በአሠራርም ሆነ በአስተሳስብ ተቸክሎ አገር መምራትና ማስተዳደር አይቻልም፡፡ ጥልቀታዊ ተሀድሶ ያስፈለገበት አንዱም መሠረታዊ ምክንያት የመንግሥትንም የፓርቲውን የውስጥ አሠራርና አካሄድ ጠልቆ በመፈተሽ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ በመስጠት የተጀመረውን የልማትና የዕድገት ጉዞ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማስቀጠል ነው፡፡

አገራዊ ዕድገቱ ራሱ ይዞ የመጣቸው ታላላቅ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጦችም አሉ፡፡ ይህን አቅም የሚመጥን አስተሳሰብና አመራር ነው ኅብረተሰቡ የሚፈልገው፡፡ የአዲስ ራዕይ ጽሁፍ እስካሁን በጥቅሉ ሲባል ከነበረው ውጪ በዝርዝር የጥልቀታዊውን ተሀድሶ ምንነት እስከ የትና እስከ ምን ድረስ የሚለውን በግልጽ ያስቀመጠ ያሳየ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግ በዚህ ደረጃ ያለውን አገራዊ ወቅታዊ ተጨባጭ እውነት በግላጭ ተንትነው የሚያስቀምጡ ነባር አይዲኦሎጎቹ ቁጥራቸው ተመናምኖ በአዲስና ተተኪ በሆኑ ግን ደግሞ በቂ ዝግጅትና ብቃት የተፈተነ የተግባር እውቀት በሌላቸው በጥድፊያ የአካዳሚክ ወረቀት ብቻ በተሸከሙ ግለሰቦች ተሞልቷል የሚሉ ትችቶች በሰፊው ይሰነዘሩበታል፡፡

በሰው ድርቅ ተመቷል በሚል፡፡ መሪም ሆነ ሊቅ አንድም ይፈጠራል አሊያም ይወለዳል እንዲሉ፡፡ ወረቀት የተሸከመ ሁሉ ምሁር ሊባል አይችልምና፡፡

ጥልቅ ርዕዮተ ዓለማዊ የኃይል አሰላለፍና ሚዛን በመሬት ላይ የሚነበቡ ተጨባጭ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች ፈተናና ችግሮችን ለምን ብለው የሚተነትኑ መፍትሄዎችንም የሚያመነጩ ከፍተኛ የማንበብ ባህል ያላቸውና የጠለቀ እውቀት ባለቤት የሆኑ በስፋት ለመመልከት የሚችሉ ሰዎች የሉም ተብሎ በሚታመንበት በዚህ ልዩ ወቅት አዲስ ራዕይ ይዛ  የወጣችው እትም ተስፋ የሚያጭር ሆኗል፡፡

በዚህ ደረጃ ተጨባጩን እውነት ነባራዊውንና ስሜታዊውን ሁኔታ የሚተነትኑ ለምን ብለው የሚጠይቁ ችግሩን አበጥረው አሳይተው መፍትሄውንም የሚያስቀምጡ በነባሩ አጠራር የፓርቲው ቁንጮ ስትራቴጂስቶች (ቁልፍ ጭንቅላቶች) ርእዮተ ዓለማውያን ከሌሉ አንድ ፓርቲ ህያው ሆኖ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ዛሬ ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን ጥገኛነትን ከበላይ አለቆቻቸው ብቻ ሰምተው የሚደግሙ ግን ደግሞ ጽንሰ ሀሳቡ ምን ማለት እንደሆነ ከምን እንደተነሳ የማያውቁ የኢሕአዴግ አባላትን ማየትና መስማት በእጅጉ አነጋጋሪ የሆነበት ወቅትም ነው፡፡

እነዚህን ቃላት ኢሕአዴግ የፈጠራቸው አድርገው የሚወስዱ እንኳን ኅብረተሰቡን ሊያሳውቁና ሊያስረዱ ለራሳቸውም በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ኅብረተሰቡን ግራ ማጋባትና በሆነው ባልሆነው እየተነሱ ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ጥገኛ ነህ የሚሉ ጥራዝ ነጠቆችን ማየት የተለመደበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ስመ ብዙ ወረቀት የተሸከሙ ምሁራዊ አቅሙና ጥልቀቱ የሌላቸው ሰዎችን በየመስኩ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ከመጠምጠም መማር ወይም ማንበብ ይቅደም እንዲሉ፡፡

ድሮ ጥልቅ እውቀት ለመያዝ በጥልቀት ማንበብ መጽሀፍ እያጣቀሱ በምክንያት መከራከር መወያየት በሎጂክ መርታት ነበር የቀደመው ትውልድ መለያ፡፡ አንደበተ ርዕቱ ተጨልፎ የማያልቅ እውቀት ባለቤት መሆን ነበር የሚያኮራው፡፡ ዛሬ እሽቅድምድሙ ሦስት አራት ዓይነት የምረቃ ወረቀት መያዝ ሆኗል፡፡ ሁሉንም ባይመለከትም አብዛኛው በዚህ መንገድ እየተርመሰመሰ ነው፡፡ ትውልዱ ተላልፏል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱም በጥልቀታዊው ተሀድሶ ውስጥ በጥልቀት መፈተሸና አንዳች ዓይነት አገራዊ እልባት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ምሁራን ሆይ ምሁርነትስ የቀለም ቀንድነትስ ወደስተየት ናችሁ ተብሎ እስኪባል ድረስ አስደንጋጭ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ጥልቅ ምሁርነት አገርን ማገልገያ መገንቢያና ለአገር ችግርም መፍትሄ ማፍለቂያ ማስገኚያ ነው፡፡ ይህንን ደረቅ እውነት ወደፊት እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬው ጉዳያችን ወደሆነችው የአዲስ ራዕይ ጥልቅ ምሁራዊ ትንታኔዎች እንዝለቅ፡፡

በአዲስ ራዕይ ጥልቅ ትንተና ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶች፣ መፍትሄዎች፣ ለምንና እንዴት በምንስ ተከሰቱ እንዴትስ እንዋጣቸዋለን የሚሉት እውነቶች ሰንገው ይይዛሉ፡፡ ይህም ኢሕአዴግ በፓርቲ ወይንም በድርጅት አባልነት የሰው ቁጥር ከማብዛት ወጥቶ ጥራት ብቃት የህዝብ ታማኝነትና አገልጋይነት ስሜት ያላቸው ላይ ማተኮር እንዳለበት ሁኔታዎቹ ያረጋግጣሉ፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት ጥገኝነት የሚለውን ቃል ኢሕአዴግ አልፈጠረውም፡፡ ቃሎቹ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩ በእውቁ እንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት አዳም ስሚዝ የወጡ ናቸው፡፡ ሰርተው ለፍተው ከመጠቀም ይልቅ ባለፉበትና ባልደከሙበት የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ሹሞችን ተጠግተው ወይም የመንግሥት ሹም ቢሆኑም የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራና ኃላፊነት በመርገጥ በብልሹ አሠራር ውስጥ ተዘፍቀው ሀብትና ንብረት በህገ ወጥ መንገድ የሚዘርፉና የሚመዘብሩ በውጭ ካለው ደላላና አቀባባይ ከበርቴ ጋር በመሞዳሞድ መንግሥታዊ ቢሮክራሲውንና ቴክኖክራቶችን በመጠቀም በሚዘረጉት ህገ ወጥ የጥቅም አግበስባሽነት መረብ በመንግሥት ወንበር ማህተም ቢሮ በመጠቀም ወንጀል የሚፈጽሙት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ጥገኞች ፓራሳይቶችም ናቸው፡፡

ሰውነትን ተጠግቶ እንደሚመጠው ተውሳክ ሁሉ ጥገኞችም ባለሥልጣኖችንና ሹሞችን በመታከክ በእነሱም አማካይነት የአገርና የህዝብን ሀብት የሚዘርፉና የሚቦጠቡጡ የሰው ፓራሳይቶች ናቸው፡፡ አዲስ ራዕይ በትክክል እንዳስቀመጠችውም የሥልጣን ምንጩ ሥልጣንም የሚገኘው በምርጫ የመንግሥትነት ወንበር ከያዘው ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ባለሥልጣን መሆንም ሆነ ወደሥልጣን መብቃት አይታሰብም፡፡

ይህንን አድርባዮችና ኪራይ ሰብሳቢው ወይም ጥገኛ የሆኑ አካላት እንደተጠቀሙበት እንዴትስ ከህዝብ አገልጋይነት ወጥተው ራሳቸውን በሰፊው ወደማገልገልና መጠቀም እንደተሸጋገሩ በዚህ ሂደት ውስጥ ህዝብ ለመብቱ መከበር ባነሳው ጥያቄ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ የመፈጠሩ ማሣያ መሆኑን አመራሩ በየጊዜው ካለው ብሄራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ራሱን እያበቃ ሊሄድ ካልቻለ በተቸከለ አስተሳሰብ የትም መድረስ እንደማይችል ፈተናና ተግዳሮቶቹን አዲስ ራዕይ መጽሄት በተጨባጭ ተንትናለች፡፡ አሣማኝ ጭብጥ ነው፡፡

መጽሄቷ በድረ ገጽ በየወቅቱ ብትጫን ሰፊ ብሄራዊ ወይይቶችን በማጫር ምላሾችንም በማግኘት ለሌላ ሰፊ ጥናት መነሻም ይሆናታል፡፡ ከፓርቲ ልሣንነቷ ባሻገርም የአገራዊ ፖሊሲዎች ጥናትና ምርምር መድረክ በመሆን ልታገለግልም ትችላለች፡፡ ግብዋ የፓርቲ አባላትዋን በፓርቲው መስመርና እምነት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ መሥራት ቢሆንም ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ለኅብረተሰቡም ያላት ጠቀሜታ የላቀ ነው፡፡ ግብረ መልሱ ውይይቱና ክርክሩ ለአገርም ለህዝብም ለመንግሥትም ይረዳል፡፡ ይጠቅማል፡፡ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ይበል ይሁን የሚያሰኝም ነው፡፡

የቀደመው ትውልድ የማያቋርጥ የማንበብ ባህል ሁልጊዜም አገራዊ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የመተንተን አቅም በማዳበር አካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በፍጥነት የመረዳት ከአገራዊ ሁኔታ ጋር የማነጻፀር ለአገራችን የሚጠቅመው የትኛው መንገድ ነው፤ በየት መሄድ አለብን የዲፕሎማሲው አቅጣጫስ ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ሁኔታ ጋር በምን መንገድ መራመድ አለበት የሚለውን ጉዳይ በሰፊ መረጃዎች የመፈተሸ፣ የመገምገምና የመተንተን ብቃት የገነባና ያዳበረ ነበር፡፡ የአሁኑም ትውልድ ከዚህ ብዙ መማር ይጠበቅበታል፡፡

ዛሬም ሰፊ ጥናቶች በማድረግ ነገንና ከነገ ወዲያን ሀምሳና መቶ ዓመት አሻግሮ ከብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት አኳያ ለመገመትና ለማየት የሚያስችል የጠለቀ ምሁራዊ አቅም ለመገንባት ካልቻልን አሁንም ችግር ውስጥ መሆናችን መረሳት የለበትም፡፡ እንደ አገር እንደ ህዝብ ቀደምት ነንና መሆን የግድ አለበት፡፡ መሪ የዛሬን ሳይሆን የነገና የከነገ ወዲያ ግማሽና ሙሉ ምዕተ ዓመትን ወደፊት አስቀድሞ አሻግሮ አይቶ ለቀጣዩ ትውልድ ማስቀመጥ የሚችል ነው መሆን ያለበት፡፡

የሰለጠኑና የበለፀጉ አገራት ወደላቀው የዕድገታቸው ማማ ያወጣቸው ያስፈነጠራቸው በዚሁ ላይ ተመሥርተው ስለሚሰሩ ነው፡፡ ወደ አዲስ ራዕይ የጥልቀታዊው ተሀድሶ ትንተና ስንገባ የገዘፉ ብዙ እውነቶችን ታሳየናለች፡፡ የሚከተሉትን ለአብነት እንመልከት፡፡

በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ስለሆኑ ብቻ አይሾሙም ቅሬታ ትለናለች፡፡ እንደምንም ተሳክቶለት የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሊቀመጥ የቻለ ሰው በቀላሉ ከሚገኙ ጥቅማ ጥቅሞች ጀምሮ በአጭር ጊዜ ሰፊ ሀብት ለማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ እንደሚያሰፋ የተገነዘቡ ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም ዓይናቸውን የማያሹበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣንን መቋደስ ለዚህ ዓይነቱ እድል እንደሚያበቃ ግልጽ በሆነበት በዚህ ዘመን ዋናው የሥልጣን መንገድ የሚፈጠረው በድርጅታችን እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በልማዳዊ አሠራር የድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተሻለ ብቃት ባላቸው ሰዎች የተሞላ እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ የመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲያዙ ይደረግ ነበር፡፡ አሠራሩ በመቀጠሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ወደከፍተኛው አመራር የገቡ ሰዎች ሁሉ ብቃት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም  በሹመኝነት ትልልቅ ቦታዎችን እንዲይዙ ተደረገ፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትና ሚኒስትርነት የቢሮ ኃላፊነት የማይነጣጠሉ ተደርገው ተወሰዱ፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግሥት ሹመኛ መሆን የፈለጉ እንደምንም አንገታቸውን ወደ ፓርቲው አመራርነት ለማስገባት መረባረብ ጀመሩ፡፡

ድርጅታችንም የሥልጣን ብቻ ሳይሆን ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማረጋገጫ መሣሪያ ወደመሆን አምርቶ የድርጅታችን የአመራር ጥራት ለአደጋ መጋለጥ ጀመረ፡፡ አድርባዮችና የሥልጣን ጥመኞች ወደ ፓርቲው የኃላፊነት ቦታዎች በመግባት በቀላሉ ወደ መንግሥት ሥልጣን የሚሸጋገሩበት ሁኔታ እየሰፋ በመሄዱም ይዘነው የተነሳነው ልማታዊ መንግሥት የመገንባት ተልዕኮ ለአደጋ መጋለጥ ጀመረ፡፡

አንድ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግሥት ይህንን ለመሰለ የኪራይ ሰብሳቢነት  አዝማሚያ በመጋለጡ ምክንያት ተልዕኮውን ለመፈፀም እየተቸገረ መሄድ ሲጀምር ያነገባቸው መሠረታዊ ግቦች መደነቃቀፋቸው አይቀርም፡፡ መንግሥት አገር የመለወጫና የህዝብ ጥቅም ማረጋገጫ ከመሆን ይልቅ የግል ጥቅም ማስጠበቂያና የኑሮ መሠረት መሆን ሲጀምር የዕድገት ፍጥነት መቀነስና ከዚሁ በማይነጠል መልኩ ደግሞ በህዝብ ፍትኃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ተመሳሳይ ችግር መከሰት ይጀምራል፡፡ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እየተዳከመ የህዝብ ጉዳትና ቅሬታ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይኼ በአገራችን ሁኔታ በተጨባጭ መታየት የጀመረ ዝንባሌ መሆኑ ከዚህ የተነሳ ነው፡፡

በአገራችን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን አስፈላጊ ካደረጉት ጉዳዮች ሌላው መሠረታዊ ምክንያት ይህ ነው፡፡ በጥልቀት መታደሱ አስፈላጊ የሆነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን ድርጅታችንንም ጭምር ይህን ከመሰለው አደጋ ለመጠበቅና በአገራችን የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ በታለመለት አቅጣጫ ተጉዞ ተፈላጊው የዕድገት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ነው በማለት አዲስ ራዕይ መጽሄት ሰፊና ጥልቅ ትንተና ሰጥታለች፡፡

አዲስ ራዕይ መጽሄት የመንግሥትና የድርጅቱ ጤንነት ለማነው የሚተወው? ድርጅቱ ለምንድነው የመንግሥት ሥልጣን የሚይዘው? በድርጅቱ የታዩ ባዕድ ዝንባሌዎች የትኞቹ ናቸው? ማህበራዊ ድረ ገጾች የነበራቸውን ሚና እንዴት ያዩታል? በሚሉት ንዑስ ርዕሶች ሥር ከፍተኛ አገራዊ ህዝባዊ መንግሥታዊ ቁም ነገሮችን በተጨባጭ ፈትሻለች፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ ለመንግሥትም ለድርጅቱም ለምን አስፈላጊ ሆነ የሚለውን ምክንያታዊነት በስፋት አስረድታለች፡፡ በቀጣዩ ሣምንት  ጽሁፍ ይጠብቁን፡፡