ኦሊጋርኪዎቹ ከባድ ናቸው

ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው በሚገባ እየተናበቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠበቅ ያለ ሲሆን፤ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብትና የሥራ ዕድል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈሉም ሌላኛው እና ለሃገራችን ሰላም ቅድመ ሁኔታ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ከሕዝብና ከአገር ጥቅም  ይልቅ የግልና የቡድን ጥቅም  ሲቀድም የሆነውን አይተናል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ሲጠፋም የተከሰተውን ቀምሰናል፡፡ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በተግባር ማረጋገጥ ባለመቻላችን ለአንድ ሰሞን ቆስለን፣ ታመንና ሞተን ታይተናል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ራሱን ለማደስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ሚናችንን ለይተን በሚገባ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ፡፡

የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ በህዝቡ ይሁንታ የጸደቁትን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በጥቅሉ የህግ የበላይነት የነገሰባት አዲስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የፍትህ አካላቱን ጨምሮ ህዝቡም ስለህግ የበላይነት ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚጠበቅበት መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም። አሁን እየሆነ ያለውና የጥልቅ ተሃድሶን የተመለከተው አረዳድ ከዚህ በተቃራኒ እና መንግስት ላይ ብቻ ሃሳቡን የጣለ መሆኑ የሚያሳስበውም ስለዚህ ነው።  

በእርግጥ መንግስት ጥያቄ አለኝ ብሎ ለተነሳው ህጋዊና ሰላማዊ ሕዝብ ሁሉ በአግባቡ እና በፍጥነት ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሰላማዊ እና ህጋዊ  ለሆነው ህዝብ መብት ሲሆን ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ለሆነ መንግስት ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን ጥልቅ ተሃድሶው ህዝቡንም እንደሚመለከት በመዘንጋት እና ግና ወደህዝቡ ሳይወርድ በማግስቱ እሪ ማለት ቅንነት የሚጎድለው እይታ ይሆናል። ይህ ማለት ግን የሕዝብ ጥያቄ እየተደራረበና የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ዘገምተኛ ሲሆን ለተጨማሪና ሌላ ችግር የሚዳርግ መሆኑን መዘንጋት አይደለም። ይልቁንም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ከሚቀያየምባቸውና ጥላቻ ውስጥ የሚከቱትን ዋነኛ ምክንያቶች ለይተን እንድንዋጋና ሚናችንን እንድንለይ የሚያስችል ነው ።

መንግሥት በውስጡ የተሰገሰጉ መርህ አልባዎችን ማፅዳት ካልቻለ ችግሩ ይቀጥላል እና በማጥራቱ ሂደት ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ሕዝባዊ ዓላማ የሌላቸው ራስ ወዳዶችን ከመንግስት በላይ የሚያውቃቸው ተገልጋይ የሆነው ህዝብ ነው። መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከላይ እስከ ታች ጥልቅ ተሃድሶ እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት እንኳ፣ ከራሳቸውና ከቢጤዎቻቸው ጥቅም በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የማይሰጣቸውን  በየሥፍራው እየተመለከትን ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ወደእነዚህ ነቀዞች ሲወርድ ከኛ በላይ ሊደግፈውና በመረጃ ሊያግዘው የሚችል ከወዴት ይገኛል?  

በመላ አገሪቱ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ በትራንስፖርት፣ በግዥና ጨረታ፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በፍትሕ አካላት፣ ወዘተ ውስጥ ለመልካም አስተዳደር መጥፋትና ለሙስና መስፋፋት አሉታዊ ሚና የሚጫወቱትን ነጣቂዎች ከተነጠቀውና እየተነጠቀ ከሚገኘው ህዝብ በላይ ማንም አያውቃቸውምና ወደታች የሚወርደው ተሃድሶ የህዝብን ከፍተኛ ተሳትፎ ይጠይቃል ማለት ነው።

የሚጠብቃቸውን የሚያውቁትና ቀኗን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ሀቀኛ ሠራተኞችን ከወዲሁ እያሸማቀቁ ነገሮችን ለማክሸፍ በመትጋት ላይ መሆናቸውም እየታየ ነው፡፡ የሐሰት ሪፖርቶችን በመፈብረክ ያልተሠራውን እንደተሠራ ማቅረባቸውንም አሁንም ቀጥለውበታል፡፡ ለመውቀስ፣ ለመተቸት፣ ለማረምና ለማስተካከል የሚፈልጉ ዜጎችን በአሉባልታ እንዲጠፉ ማድረጋቸውንም ቀጥለዋልና ወደታች በሚወርደው ተሃድሶ ውረድ እንውረድ ልንባባል ይገባል፡፡

በዚህ ፅሁፍ ርእስ ላይ እንደተገለፀው ኦሊጋርኪዎቹ (ከገዥው ፓርቲ በተፃራሪ የቆሙቱ) ከባድ ናቸው። የመንግሥትን ሚዲያዎች ሳይቀር  ጠልፈው  ማደናገር እና ተሃድሶው ትርጉም እንዲያጣ በመስራት ላይ ስለመሆናቸው ማየትና መስማት የተለመደ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ሚና ሳይኖራቸው፣ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን የሚያከናውኑ ወገኖችን በእነዚህና በውጭ ጽንፈኛ ሚዲያዎች በኩል ሲያብጠለጥሉም እየሰማንና እያየን ነው፡፡

ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ብቻ ስለሚያስቀድሙ፣ ለእነሱ ሕዝብ ማለት ምንም አይደለም፡፡ ሕዝብን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በዳበረ ዕውቀትና ክሂሎት ለማገልገል አሁንም ብቃቱ ያላቸው በርካታ ዜጎች እያሉ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ የኦሊጋርኪዎች ስብስብ መንግሥትን መፈናፈኛ እያሳጡት መሆኑን ማወቅና ሁሉንም በትእግስት ከመጠበቅ ባሻገር በተጠናከረ ተሳትፎም አጋር መሆን ያስፈልጋል፡፡  

ኦሊጋርኪዎቹ ጥልቅ ተሃድሶው እየተድበሰበሰ ተራ ግምገማ እንዲሆንም ሆነ እንዲመስል የሚደረገውን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ የሕዝብን ቅሬታና ብሶት መነሻ ያላደረገ ግምገማ እንዲሆንም በመትጋት ላይ ናቸውና ልናኮላሻቸው እንጂ የእነርሱ ሰለባ በመሆን መንግስት ላይ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። እነርሱ እኮ  የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ሃላፊነታቸው የሆኑ ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ተሰግስገው እየመዘመዙን የሚገኙ የዘመናችን ኦሊጋርኪዎች ናቸው ።  

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነት የሌላቸውና ልፍስፍስ እንዲሆኑ  የተደረጉትም በእነዚሁ ኦሊጋርኪዎች ነው፡፡ የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና ያልተሰራውን ሲያንጎላጅ የሚውል ሚዲያ እንዲገነግን የሚያደርጉትም እነዚሁ አካላት ናቸው፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንዲኮሰምንና ሙስና እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ሕዝብ በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ምሬት እየተፈጠረበት አገሩን እንዲጠላ እየተደረገ የሚገኘው ኦሊጋርኪዎቹ ጠርንፈው በያዟቸው ሚዲያዎች በኩል መሆኑን ተገንዝበን ወደታች ለሚወርደው ተሃድሶ በሚገባ ልንዘጋጅ ይገባናል። በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴውም እነዚህን ችግሮች በሚገባ ማየት የሚችለው እኛ የተመዘመዝነው እና የተበዘበዝነው በሚገባ መሳተፍ ስንችል ነው። (እዚህ ላይ “ኦሊጋርኪ/Oligarchy” ስንል “a form of government in which all power is vested in a few persons or in a dominant class or clique; government by the few.” የሚለውን የመዝገበ ቃላት ብያኔ መሰረት አድርገን ኘሆኑን ለአንባኒያን መግለፅ ይገባል።)