በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የሙያና ብዙሃን ማህበራት እውን የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነውን?

 

ኢፌዴሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በአዋጅ 621/2001 ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሰረት እንዲወጡ ብሎም አሰራራቸው ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን፤ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 31 የተደነገገውን የዜጎች የመደራጀት መብት እውን ለማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን መዝግቦ ፈቃድ በመስጠት ዘርፈ ብዙ የክትትልና ድጋፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም ማህበራት በሀገራቸው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና የልማት ስራዎች ላይ የመሳተፍ እድል አግኝተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያና የብዙሃን ማህበራት ተደራጅተው ፍቃድ በመውሰድ በሀገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ አብዛኞቹ ማህበራት ተመዝግበው መንቀሳቀስ የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቢሆኑም ከተመሰረቱ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ማህበራትም አሉ፡፡ ሆኖም እንደ ቁጥራቸው ብዛትና እንደ እድሜያቸው ልክ የሙያ ማህበራት በሀገሪቷ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የሙያም ሆኑ የብዙሃን ማህበራት የህዝብን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ እያቀረቡ እንዲፈቱ ለማስቻል በመንግስት እና በህብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ አይደሉም፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው ፍቃድ የወሰዱ በጥቅሉ 333 ገደማ የሚሆኑ የሙያና የብዙሃን ማህበራት ቢኖሩም የረባ ስራ ሰርተዋል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ይህን ስንል በጥቅሉ ሁሉም ማህበራት ለተቋቋሙለት ዓላማ በተገቢው መልኩ አስተዋፅኦ አላበረከቱም ማለታችን አይደለም፤ ለዓብነት የሚጠቀሱና ስኬታማ ስራ መስራት የቻሉ ማህበራት መኖራቸው አይካድምና፡፡ ለአብነትም እንደ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ያሉ፣ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ማህበራት መኖራቸውም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ 

አብዛኞቹ የሙያና ብዙሃን ማህበራት የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት የሆነባቸው ሀገሪቱ በዘርፉ የምትከተለው ህግ መሆኑን በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ የ10/90 ህግ ማህበራት የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ ሀገር እንዳያገኙ በማድረጉ ለመዳከማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ህገ-መንግስቱ በደነገገው መሰረት በማህበር የመደራጀት መብት የተሰጠው ለዜጎች ብቻ ነው፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የኢትዮጵያ ማህበራት ፍቃድ ወስደው ለመስራት ሁሉም ዓባላት ኢትዮጵያዊ መሆን ያለባቸው ሲሆን የገቢ ምንጫቸውም ከሀገር ውስጥ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም በህግ ከተፈቀደው ውጪ ከውጭ የገንዘብ ምንጭ መጠቀም አይቻልም፡፡ የሙያና ብዙሃን ማህበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰሩ በመሆናቸው እንደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰፊ የሀብት መጠን ላያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ 90 ከመቶ የሚሆነውን ሀብት ከሀገር ውስጥ በማመንጨት እንዲሁም ከ10 በመቶ የማይበልጠውን ከውጭ ሀገር በማምጣት ከሰሩ የተቋቋሙለትን አላማ ከዳር ማድረስ ይችላሉ፡፡ ማህበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የውጭ እርዳታ ሳያስፈልግ በሀገር ውስጥ ሀብት መስራት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በሀገራችን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ማህበራት የ10/90 ህግ ውጤታማ ላለመሆናቸው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ህግ ሲወጣ ማህበራት ሀብት የማግኘት አቅማቸው እንዳይዳከም ብዙ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለዓብነት ያህል ማህበራት ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ግንኙነት ባላቸው ብሎም ዓላማቸውን ለማስፈፀም ብቻ የሚውል የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ የንግድ ህግ ጠብቀው ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ መሰማራት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ህዝባዊ መዋጮ በማካሄድ ከሀገር ውስጥ ሀብት ማመንጨት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አማራጮችን ተጠቅመው ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት አመለካከት ተላቀው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ስለሚችሉ የ10/90 ህግ አላሰራንም ማለት ምክንያታዊና ከህግ አንፃርም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ማህበራት ቆም ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ህልውናቸው የሚወሰነው እራሳቸውን ለማጠናከር በሚሰሩት ስራ ነው፡፡

ይህ ሲባል የብዙሃንና የሙያ ማህበራት ምንም ተግዳሮቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ስራቸውን የሚሰሩበት ቢሮ የላቸውም፤ ለስራቸው ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችንም የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡ በየዘርፉ ያሉ የመንግስት ተቋማት ለሙያና ብዙሃን ማህበራት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ የሙያ ማህበራትም ለአባላት ስልጠና እና የትምህርት እድልን ከማመቻቸት ባለፈ ያላቸውን እውቀት እና ክሂሎት ተጠቅመው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለፖሊሲና ስትራቴጂዎች ግብዓት የሚሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም መንግስትን በማማከር ለሀገሪቷ አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ማህበራት የጎላ አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት አይቻልም፡፡ በቀጣይ በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሙያ ማህበራት በየዘርፋቸው ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ፈጥረው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እጅና ጓንት ሆነው መፍታት አለባቸው፡፡ የሙያ ማህበራት ውጤታማ የሚሆኑት ያላቸውን እምቅ እውቀት እና ክሂሎት ሳይሰስቱ ለሀገራቸው ማበርከት ሲችሉ ነው፡፡ በሌላ መልኩ 10/90 ለሚተገብሩ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እንዲጠናከሩ መንግስት የማህበራዊ ተጠያቂነት ፈንድ (Social Accountability fund) ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት፡፡  

የሙያና ብዙሃን ማህበራት በራሳቸው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተምሳሌት መሆን መቻል አለባቸው፡፡ የዓባላትን መብትና ጥቅም በማስከበር፣ በጠቅላላ ጉባኤ መሪዎችን መምረጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ያልተከበሩ መብቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለሱ/ከበሩ አባላትን በማለማመድ እንደ ሀገር በሚደረገው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መነሻና ትምህርት ቤት መሆን አለባቸው፡፡ የአንዳንድ ማህበራት የስራ ኃላፊዎች የጊዜ ሰሌዳቸውን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የስራ አፈፃፀማቸውን አያቀርቡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ አመታት ስልጣናቸውን ለሌሎች አባላት ሳይለቁ የሚቆዩበት ሁኔታ አግባብነት የለውም፡፡ የመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው መሰረት በየሁለት ዓመቱ በሚካሄዱ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎችን በማካሄድ ስልጣናቸውን አዲስ ለሚመረጡ ለሌሎች አባላት አሳልፈው መስጠት አለባቸው፡፡ የማህበራት አመራር አባላቱን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያወያዩ ዜጎች የጠራ አመለካከት ይዘው ለልማት እንዲነሳሱ የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ የሙያና ብዙሃን ማህበራት የሀገሪቱ አይን፣ ጆሮና አፍ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ መልኩ ማህበራት በውስጣቸው ሰፊ ቁጥር ያላቸው አባላትን በመያዛቸው ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው የጠራ ግንዛቤ ብሄራዊ መግባባትን ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡

የሙያና ብዙሃን ማህበራት ውስጣዊ አሰራርም ግልፅነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ይህ መሆን ሲችል ነው በአገራችን መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ሊጎለብት የሚችለው፡፡ ማህበራት በሀገሪቷ ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር ላይ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ አቅም ሲፈጥሩም በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው፣ በዚህ ረገድ የሙያም ሆኑ ብዙሃን ማህበራት ይህ ነው የሚባል ነገር አልሰሩም፡፡

በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የብዙሃን ማህበራትን ገዢው ፓርቲ ያቋቋማቸውና ለሱ በመወገን የፖለቲካ ስራ እንደሚሰሩ አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ ነገር ግን የሙያና ብዙሃን ማህበራት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆነው በገለልተኝነት የሚሰሩ ናቸው፡፡ ህጉም ይህንኑ ነው የሚደነግገው፡፡ በሌላ መልኩ የሙያና ብዙሃን ማህበራት በመንግስት መዋቅር ያሉ ክፍተቶችን ነቅሰው በማውጣት እንዲፈቱ ጫና እየፈጠሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ ማህበራት ይህንን እንዲያደርጉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንኳ ገና አልደረሱም፤ ሁሉንም ማህበራት የሚገልፅ ባይሆንም ማህበራት የሙያ ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እየተመሩ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንዳንድ ማህበራት ስልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ሽኩቻ በመጠመዳቸው ትርጉም ባለው መልኩ ሀገራዊ ራዕይ አንግበው ሙያውን ለማሳደግ እየሰሩ አይደለም፡፡ ይህም በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ 

የሙያም ሆኑ ብዙሃን ማህበራት በስነ-ምግባር የታነፁ እና በእውቀት የበለፀጉ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡ የአባላትን አቅም በመገንባት ዙሪያ ብዙም የተሰራ ስራ የለም፡፡ ማህበራት በተጨባጭ አባላትን ማፍራትና አቅም መገንባት መቻል አለባቸው፡፡ ማህበራት ሲጠናከሩ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር ይችላሉ፡፡

የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከር የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ማህበራት እንቅስቃሴያቸው በበጎ ፍቃደኞች እንዲደገፍ ለማስቻል የበጎ ፍቃደኝነት ባህል እንዲዳብር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የህትመት እና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ትኩርት ሰጥተው የሙያና ብዙሃን ማህበራትን የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ያሉባቸው ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሰፊው መስራት አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች በዘርፉ ያሉ ድክመቶችን ለመፍታት የሚያስችል ጥልቅ እይታ መሰረት አቅጣጫ አመላካች የመፍትሄ ሀሳቦችን መስጠት መቻል አለባቸው፡፡

የሙያ ስነ-ምግባር እና ብቃትን ከማሳደግ አንፃር የሙያ ማህበራት ብዙ መስራት ያለባቸው ስራዎች ቢኖሩም አሁንም የሚጠበቅባቸውን ያህል ርቀው መጓዝ አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቆጠረው የሙያ ማህበራት ተዝቆ የማያልቅ ትልቅ አቅም እያላቸው ከስብሰባ የዘለለ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት ያላቸው ቁርጠኝነት ማነስ እንደ ድክመት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም ለማህበራት ተገቢው እገዛ ሳይደረግ በድፍኑ መውቀሱ አግባብ ባይሆንም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለሙያና ብዙሃን ማህበራት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ የብዙሃንና የሙያ ማህበራት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ ቀምሮ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውስጥም ሆነ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮዎችን ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስፋፋት ቅድሚያ የሚሰጠው፣ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል:: እንደ ሀገር የሙያም ሆኑ የብዙሃን ማህበራት በዜጎች መብትና መብት ነክ ጉዳዮችና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸው አሰራር መዘርጋት አለበት እንላለን፡፡