የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዲይዝ መሠረቱን የመጣልና ህዝቡ ከፍተኛ እሮሮና ምሬት የሚያሰማበት መልካም አስተዳደር በመሆኑ መሰሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ የማድረግና ውጤት የማስመዝገብ ጉዳይ ወሣኝ ይሆናል።
ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በየወቅቱ ፈጣን ምላሽ እየሰጡ መሄድ የግድ ይላል፡፡ ለምሣሌ ባለፈው ዓመት አጋጥሞ በነበረውና ኤልኒኖ በሚባለው የአየር መዛባት ክስተት ምክንያት በአገራችን የተፈጠረው የድርቅ ችግር የ2008 ዓ.ም የትኩረት ማዕከላችን አደጋውን የመመከትና ጎን ለጎን ዘላቂ ልማታችንን የማስቀጠል ሥራ ነበር፡፡
በመሆኑም የብሄራዊ አደጋ መከላከል ምክር ቤቱ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ተደራጅቶ የአደጋው ስፋት፣ ጥልቀትና ባህሪን በዝርዝር የማወቅና ከዚያ ላይ ተመሥርቶ የመከላከያ መፍትሄዎቹን እንደየባህሪው በየደረጃው የማስኬድ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት የያዘው አቋም በዚህ የድርቅ አደጋ ምክንያት አንድም የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና እንስሳት ላይም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመመከትና ጎን ለጎን ዘላቂ ልማት ማካሄድ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት መደበኛ የበልግ ፕሮግራም የሳሳ ስለነበር፣ የበልግ ወቅቱ መዛባት አልበቃ ብሎ በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት መደበኛው የመኸር ወቅት እንዲሁ በመዛባቱና ዝናቡ በመዘግየቱ በዘነበባቸው አካባቢዎችም ቢሆን ተመጣጣኝ ሽፋን ያልነበረና ቀላል መሆኑ አደጋውን አባብሶታል፡፡ በዚህ ምክንያት የአደጋ ሚዛኑ እየሰፋ ስለሄደ ተጨማሪ ጥናትና ተጨማሪ ሥራ በማስፈለጉ ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ከአጋር የውጭ ድርጅቶች የተውጣጣ የጋራ ቡድን ጥናት እንዲያካሂድ በማድረግ ነበር እንቅስቃሴ የተጀመረው፡፡
አደጋውን ለመመከት የሚያስችል ዝግጅት የማድረግና የከፋ ሁኔታ የሚከሰት ከሆነም ለመቋቋም በሚያስችል መልክ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ የተጓዝንበት ሁኔታ ነበር፡፡
ሆኖም ድርቁ እየሰፋና የተጎጂ ወገኖች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ሄዶ በዚያን ወቅት የተረጂዎች ቁጥር ወደ 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ደርሶ ነበር። በጥናቱ ላይ በመመሥረት የሚያስፈልግ በጀትና የእርዳታ እህል በአገራዊ አቅም በማቅረብ አደጋውን ለመቋቋም ተችሏል፡፡ የህፃናት አልሚ ምግብ፣ የውኃና የእህል አቅርቦት እንዲሁም የጤናና የትምህርት ፕሮግራሞች ከድርቁ ጋር በተያያዘ እንዳይስተጓጎል መስተካከል ያለበት ሁኔታ በማመቻቸት ራሱን የቻለ የተሟላ እቅድ በማዘጋጀት ወገኖችን የመታደግ ሥራ ተከናውኗል።
መንግሥትም ከስምንት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ልዩ ልዩ የእርዳታ አቅርቦት አሟልቷል። የመድኃኒት፣ የውኃ፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት በማመቻቸት አደጋ የመመከትና የመቋቋም ሥራም አከናውኗል፡፡ የዚህ የኤልኒኖ ክስተት ጉዳይ የሚያመጣውን ጫና ሙሉ ለሙሉ ለመመከት በሚያስችል የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል። የእለት ደራሻ እርዳታ የሚፈልጉ አካባቢዎች የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ የእርዳታ አቅርቦት በመልካም ሁኔታ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የእንስሳት ሃብቱን ለማቆየት በአንድ በኩል ወዳልተጎዱ አካባቢዎች የማንቀሳቀስ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለምሣሌ አፋር ላይ ያለውን ችግር ለመቋቋም በአቅራቢያው ወደሚገኘው የአማራ ክልል የማውጣትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሸንሌ ዞን ያጋጠመን ችግር ለመቋቋም ደግሞ ወደ ሌሎች የሶማሌ ክልል ቦታዎች የመውሰድ አማራጮችን ሥራ ላይ ውለዋል።
ሌላው ፈታኝ ችግር ሆኖ ያለው የውኃ አቅርቦት በመሆኑ የውኃ እሴቶች በእነዚህ አካባቢዎች እየሳሳ የመጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ ቀድሞ ለልማት የተዘጋጁ ጉድጓዶች ነጥፈዋል። ምንጮች እየጎለበቱ መጥተው የነበረ ቢሆንም በተከሰተው ችግር ምክንያት እየራቁ የመጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ ውኃ ለሰው ልጅም ሆነ ለእንስሳት ህይወት ቀዳሚ ቦታ ያለው በመሆኑ ይህንን ለመቋቋም እጅግ የከፋ የውኃ አቅርቦት ያለባቸው አካባቢዎች ቦቴ እየተመደበ ውኃ እንዲቀርብ ተደርጓል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የዝናብ ትንፋሽ ጠብታ ስትኖር ያችን የማቀብ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሰራው ሥራ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ሥራው ምን ያህል እጃችንን ይዞ እያወጣን እንደሆነ የሚያሳዩ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በላይ ብንሰራ ኖሮ ምን ያህል አሁን የማንገዳገድበት ደረጃ ልንደርስ እንደምንችል አሳይቶናል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ካለፈው ዓመት ጀመሮ የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ችግሩን ለመቋቋም እገዛ አድርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ትግራይ ክልል የተሳካ ሥራ ከውኗል፡፡ በተወሰነ ደረጃም በአማራ ክልል እና በምዕራብ ሐረርጌ የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ጠቀሜታ ጎልቶ ታይቷል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን የውኃ ጥያቄ ቁልፍ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል በመገንዘብ ውኃን የማልማትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ላይ ርብርብ ተደርጓል።
ይህንን አደጋ ለመመከት በግብርና በኩል የእንስሳት መኖ አቅርቦት የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ መሥራትና ብዙ ጉዳት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ምርት እንዳይቀንስ የመሥራትና ተለዋጭ ሰብሎችንና እርጥበትን የመጠቀም ሥራ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል። ሌላው ደግሞ ጤና ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት የድርቅ ወቅት የተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ የመስፋፋት እድል ስላላቸው ይህንን ለመከላከል ዝግጁነት ያለው የጤና መዋቅር ተዘርግቷል። ከዚህ ጋር ተይይዞ የሚነሳው ሌላው ነገር የትምህርት ፕሮግራም ነው፡፡
በተለይ አርብቶ አደሩ አካባቢ የተሻለ ግጦሽና አማራጭ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እድል ስለሚሰፋ የትምህርት ሥርዓቱ የመስተጓጎል አደጋ አጋጥሞት ነበር፡፡ የትምህርት ሽፋኑ ወደኋላ እንዳይመለስ ለማድረገ የትምሀርት ቤት የምዝገባ ፕሮግራምንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም አራቱ ፕሮግራሞች ተመጋጋቢነት ባለው ሁኔታ በማስኬድ አደጋውን ለመመከት ተሰርቷል።
ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረውን የድርቅ አዝማሚያና ሁኔታ በመለየት ለውጭ አገር የልማት አጋሮች ጥሪ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን አሁን ያለው ዓለማዊ ሁኔታ በጣም ፈታኝና ብዙ እርዳታ ብዙ የእለት ደራሽ እንቀስቃሴ ጥሪ እያቀረበ በመሆኑና የዓለምን እርዳታ የሚሻማው ብዙ ስለሆነ ከውጭ የሚመጣው አቅም ብዙ መሠረታዊ ለውጥና ብዙ ወንዝ እንደማያሻግር ግንዛቤ ተወስዷል።
በመሆኑም በራስ አቅም ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን በመገንዘብ አቅማችንን አረባርበን እየሰራን እንገኛለን፡፡ አቅምና ገንዘቡ እያለ፣ በአመራር ትኩረትና ክትትል ማነስ ምክንያት ምንም ዓይነት የህይወት መጥፋት ጉዳት መድረስ እንደማይገባው በመገንዘብ በዚህ ጉዳይ የሚከሰት ችግር ካለም ተጠያቂነቱ የከፋ እንደሆነ አቅጣጫ ተይዞ በዚያ ደረጃ መንግሥት ተረባርቧል።
ዋናው ነገር አሁንም ዘላቂ ልማት የማጠናከር ሥራ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ልማት የማጠናከርና አደጋ የመመከት አገራዊ አቅማችንን ማጠናከር ነው። ሌሎቹ ተጨማሪ አቅሞቸ ናቸው፤ ለተጨማሪ አቅሞች በራችን ክፍት ነው፤ ግን ደግሞ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ቢቆሙ የሚጨልምብን ሊሆን አይገባም፡፡
ይህንን ሊሸከም የሚችል አገራዊ አቅም አጠናክሮ መረባረብ የግድ ይላል፡፡ በሌላ መልኩ በአንዳንድ አካባቢ የኅብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ እጅግ የሚገርም ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በአንድ በኩል ድርቁ በከፋበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንስሶቻቸውን ይዘው ሲሄዱ ባለው መሬት በጋራ የመጠቀምና ቦታውን አመቻችተው ከራሳቸው እንስሳት ጋር አድርገው ችግሩን በጋራ የመካፈልና እንዲህ ዓይነት ወቅት የማለፍ ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለሃብቶችና ነዋሪው ኅብረተሰብ ከግሉ እያዋጣና እያሰባሰበ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ሃብት ለተጎጂዎች የሚያግዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ በስኬት እየተሰራ ያለውን ተግባር በአብነት ሊወሰድ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ርብርብና እንቅስቃሴ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ድርቅን የመቋቋም መልካም ተሞክሮም አለን- እጅግ የሚያኮራ ባህል ነው ያለን፡፡