ለአረንጓዴው ልማት ስኬታማነት

 

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በተለያየ አገራትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ተቀባይነት እያገኘና ለሌሎች አገራት በአርአያነት እየቀረበ ይገኛል።  ከእነዚህ አገራት መካከልም አሜሪካ አንዷ ናት። በቅርቡ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ልማት ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረሟ ይታወቃል።

በወቅቱ ይፋ የተደረገው ስትራቴጂ እንደሚያትተው፣ ይህንን ገንዘብ ምዕራባውያኑ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ገንዘቡ ለአየር ብክለት ተጋላጭ የሆኑ (ለብክለት አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው በግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት የሚጎዱ) አገሮች በካሣ መልክ የሚያገኙት እንጂ ችሮታ ወይም ዕርዳታ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ 

መንግሥት በ15 ዓመታት ውስጥ ለአረንጓዴ ልማት ያስፈልገኛል ያለውን የ150 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ፣ ደኖችን በማፋፋት በእነሱም የሚታመቀውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመለካትና በመሸጥ የካርቦን ፋይናንስ እየተባለ የሚታወቀውን ሥልት ለመከተል ያስባል፡፡

ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ አንድ ሺህ ዶላር ደርሶ  አገሪቱ መካከለኛ ኢኮኖሚ ይኖራታል ብሎ የሚያስበውና ለዚሁ እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ሊያሳካው እንደሚችል አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ፖሊሲውን ለማስፈፀም ይረዳሉ የተባሉ የመተግበሪያ ረቂቅ ማኑዋሎች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት አዲስ የተቋቋመው የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ሥልታዊ የሆኑ የቴክኒክ ዝርዝር ማኑዋሎችን አዘጋጅቷል፡፡ መንግሥት  ከውጭ መንግሥታት ገንዘብ መገኘቱን ተከትሎ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የሚሰራውን ሥራ በተመለከተ ዕቅዱን ሲያቀርብ፣ የሥራ ክንዋኔው የሚገመገምበት አሠራር ለውይይት ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በተፈቀደለት የሥራ መስክ ላይ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እንዴት መሥራት እንደሚገባው ይገመገማል፤ መሥሪያ ቤቶችም ከእንግዲህ ዕቅዳቸውን ለበጀት ሲያቀርቡ በአሠራር ሥልቱ መሠረት እንደሚሆንም በተደጋጋሚ የተነገረ ጉዳይ ነው።

ዓለም የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ውስጥ መግባቷ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን የ150 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም   አንዳንድ አገሮች የተሻለ የገንዘብ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ግን የአገሪቱን የአካባቢ ጥበቃ ሲመራ የነበረው ተቋም ማለትም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የአሠራር ሥልት ሲተች ቆይቷል፡፡

ይኸውም የተቋቋመለትን አካባቢን የመንከባከብ ተግባር በሥራ ጠባያቸው የጥቅም ግጭት ላለባቸው መሥሪያ ቤቶች ሥልጣኑን በውክልና መስጠቱ ነው፡፡ ለምሣሌ የመንገዶች ባለሥልጣን በሥሩ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የሚያካሂድለት የራሱ አካል አለው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ዓላማው ግብርናን ማስፋፋት ሆኖ ሳለ ደንን እንዲንከባከብ ኃላፊነት መውሰዱ የአገሪቱን የአካባቢ ጥበቃ በተቀናጀ ሁኔታ ለመፈጸፀም የራሱ አሉታዊና አወንታዊ ሁኔታዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።

በቀደሙት ሥርዓታት ነባር ደን ያለርህራሄ ሲጨፈጨፍ በመቆየቱ ይህንን ለማስተካከል መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። የአካባቢ ጥበቃ ቁጥጥር ተግባርን ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በውክልና መስጠቱ ሥራን ለማቀላጠፍ ታስቦ እንደሆነ፣ ዋናው ነገር ውክልናው መሰጠቱ ሳይሆን ቁጥጥሩ መሆኑ ይታመናል፡፡ የአገሪቱ የደን ሽፋን ችግር ውስጥ ከገባ ዘመን ተሻግሯል፡፡ ሆኖም ክልሎች አሁን የተሻለ የደን ጥበቃ አላቸው፡፡ 

ኢትዮጵያ በዓለማችን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ 10 አገራት መካከል አንዷ መሆኗን የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት (UNEP) ጥናት ያመለክታል፡፡ በአማካይ ሙቀት መጠን መጨመርና የዝናብ ሥርጭት መዛባት የመሰሉ ቀጥተኛ የሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችም ተጠቂ ናት፡፡

 

የአገሪቱ 80 በመቶ ዜጎች መተዳደሪያ እንዲሁም 40 በመቶ አገራዊ ምርት የተመሠረተበት የግብርናው ዘርፍ፤ የአየር ንብረት ለውጡ ቀጥተኛ ተጠቂ መሆናቸው ተጋለጭነቱን ያባብሰዋል፡፡ የአየር ንብረት በዓለማችን ላይ ከደቀነው ተጨባጭ አደጋ ባሻገር የዘላቂ ልማት አማራጮችን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ ተቋቁሞ እሰከ 2017 መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ለመፍጠር ካለው ብርቱ ፍላጎት የተነሳ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ቀርጿል፡፡ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መሪነት በየካቲት ወር 2003 ዓ.ም የተቀረጸው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የተለጠጠ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችና ዕድሎችን መለየት ዋናው ዓላማው ነበር፡፡

 

ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ዕድገት አማራጭ ምንነት፣ ከልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር ያለው ቁርኝት፣ አዋጭነት፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለአካባቢያዊ ሀአገራት ያለው ፋይዳ እንዲሁም ተግዳሮቱን በተገቢው መንገድ በመዳሰስ የአረንጓዴ ልማት ዕቅድ የአየር ንብረት ለውጥ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው የበለፀጉት አገራት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የታዳጊ አገራት ተሳትፎ ወሣኝ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እየተሰራ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 

ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውኃ የኤሌክትሪክ ሀይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች አገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት በፍጥነት የአረንጓዴ ልማት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ቀርጻለች፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሠረቶች ናቸው፡፡

 

የስትራቴጂው መሠረቶች አተገባበር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው የስትራቴጂው መሠረት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ነው፡፡ ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪ ዘርፍ መሆኑና የአብዛኛው የአገሪቱ ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የሚታረስ መሬትን ማስፋፋትና የቀንድ ከብቶችን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ የመሬትንና የቀንድ ከብቶችን ምርታማነት ማሳደግ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ነው፡፡

 

የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ ሥልት ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለይም በተራቆቱና በተጎዱ አካባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትም በስትራቴጂው የተያዘ ዕቅድ ነው፡፡

 

በተለይም የአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሆኑትን ሙቀት አማቂ ጋዞችን በማምከን ረገድ የደን ዘርፉ የማይተካ ሚና አለው፡፡ የተለመደው የኢኮኖሚ ዕድገት አማራጭ ከቀጠለ እስከ 2022 ዓ.ም ባለው ጊዜ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ደን ይመነጠራል፡፡

 

ለአገሪቱ ጤናማ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው የደኑ ዘርፍ ጉዳት ለመቀነስ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሥልቶችን ቀይሷል፡፡ ዜጎች ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ ከማገዶ ውጭ  በኤሌክትሪክ፣ ባዮ ጋዝና በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ምድጃዎች ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም በማድረግ የደን ምንጠራን ትርጉም ባለው መጠን መከላከል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው ሌላው ሥልት ነው፡፡

 

ከዚህ ጎን ለጎን የተጎዱ መሬቶችን በመከለል እንዲያገግሙ ማድረግና ተጨማሪ መሬትን በደን በመሸፈን የደን ልማቱ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ሥልቶች ናቸው፡፡ ለአገር ውስጥና ለአካባቢያዊ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታን፤ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ማስፋፋት የስትራቴጂው ሦስተኛ መሠረት ነው፡፡ ኤሌክትሪክ ለዘመናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሣኝ የኃይል ምንጭ ነው፡፡

 

የአረንጓዴ ልማት ስትራጂው፤ ከዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱ ጋር ያለው ቁርኝት ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከዓለማችን ድሃ አገራት ተርታ ብትመደብም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዘብ ላይ ትገኛለች፡፡ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ኢትዮጵያ በፈረንጆች አቆጣጠር 2011 ጀምሮ በቀጣይ አምስት ዓመታት ጠቅላላ የአገሪቱ ምርት በአማካይ ከስምንት በመቶ በላይ እንደሚያድግ ግምቱን ሰጥቷል፡፡ ካለፉት የልማት ዕቅዶች በመነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዘመን ዕድገቱ በአማካይ 11 በመቶ እንደሚሆን ትንበያውን አስቀምጧል፡፡

 

የኃይል አቅርቦቱን ለማሟላት አንደኛው አማራጭ የበለፀጉት አገራት በኢንዱስትሪው አብዮት ወቅት ይከተሉት የነበረው፤ በአሁን ወቅት ለዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛው መንስዔ የሆኑት የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝና የመሳሉትን የኃይል አማራጮችን መጠቀም ነው፡፡ አማራጩ ለአየር ንብረት ለውጥን ለማባባስ ካለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ባሻገር፣ የኃይል ምንጮቹ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው ኢትዮጵያን በመሰሉ ታዳጊ አገራት የሚያደርሰው የውጭ ምንዛሪ ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

 

ሌላው አማራጭ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ነው፡፡ አማራጩ ነዳጅና የድንጋይ ከሰልን የመሰሉ የኃይል አማራጮች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ቀላል አይደለም፡፡ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ዕቅድን አውጥቶ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ጎን ለጎን ያቀደችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ካላት ዕምቅ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ጋር ተዳምሮ አገሪቱ አሁንና ወደ ፊት የሚያስፈልጋትን የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው ዋስትና ሆኗል፡፡

 

የአረንጓዴው ዕድገት አማራጭና አዋጭነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት አማቂ ጋዞች መቀነስ የሚችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መፈብረክ የተለመደ ሆኗል፡፡ የቴክኖሎጂዎቹ ውጤታማነት ከሚያሳድጉት ምርታማነት ባሻገር መቀነስ በሚችሉት የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን ይወሰናል፡፡ በተለይም የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች እንዲለቁት የሚፈቀድላቸው የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን ውስን በመሆኑ ምርታቸውን ላለመቀነስ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡

 

የመጀመሪያው አማራጭ ሙቀት አማቂ ጋዞች መቀነስ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የቀነሱትን ጋዝ ያህል ምርት መጨመር ይችላሉ፡፡ ሌለኛው አማራጭ የአየር ንብረት ፈንድ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ አማራጩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሙቀት አማቂ ጋዞችን ከሚቀንሱ አካላት በቀነሱት መጠን ክፍያ በመፈፀም ተጨማሪ ምርት ማምረት የሚያስችል አማራጭ ነው። 

 

መንግሥት እየደከመ ላለው ድህነትን የመቀነስና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ተግባር አረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሃብት ልማት የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎችን በማጠናከር በቀጣይ የበለጠ ውጤት ማስገኘት በሚችል መልክ ሥራውን እየመራ ይገኛል የሚል እምነት አለ፡፡