ሀገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ባለቤት የነበረች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን የግብርና ስራም ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲካሄድ የኖረባት ሀገር ነች፡፡ ሰፊ የስነ-ምህዳር ተለያይነት ያላት ሀገር በመሆኗም በኢትዮጵያውያን የተላመዱና የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑትን ጤፍ፣ ገብስ፣ እንሰት፣ ጫት እና ሌሎችም ሀገር በቀል ሰብሎች መኖራቸው ሲታይ ከዚህ የበለጠ መልማት የሚችል እምቅ ሀብት እንዳለን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ የግብርና ሥራው ኋላ-ቀር በመሆኑ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ለዘመናት ሳይረጋገጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋና ጉዳይ የነበረው የህዝቡ የመሬት ባለቤትነት መብት በተሟላ መልኩ ምላሽ ቢያገኝም ከዝናብ ጥገኝነት አለመውጣትና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለመላመድ የነበረው ውጣ ውረድ ለበርካታ አመታት ሰቅዞ ይዞን የነበረ መሆኑም ነው። አሁን ከነዚህ ችግሮች በመላቀቅ ሂደት ላይ ስለመሆናችን አመላካች የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት ወቅቱ የመኸር ነውና ዘመቻውን ማፋፋም የዚህ ፅሁፍ ግብ ነው ።
የግብርና ልማትን በማፋጥን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ እየተደረገ ከመሆኑም በላይ መንግስት ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ፖሊሲ ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬትና ውሃ እንዲሁም ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል፤ በሂደትም ግብርናው የኢንዱስትሪ ግብዓት፣ የካፒታል ክምችት፣ የገበያ ዕድልና የጉልበት አቅርቦትን በማረጋገጥ ለከተማውና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ተደርጎ የተሰናዳና በተግባርም በርካታ ውጤቶችን ያስገኘ ነው፡፡
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገትም ሆነ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ብሎም የመላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሻጋገር መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተቀመጡ ግቦች አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ በመነሻው ዓመት የነበረውን 191ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 267 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 27ዐ ሚሊዮን ኩንታል በማምረት የዕቅዱን 101 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ አርሶአደሩ ማሳ ላይ መሆኑ ሲታይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመተግበር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከተልነው አቅጣጫ ትክክለኛነት በተግባር የተረጋገጠበት ነው፡፡ ሆኖም በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ቢያንስ በሄክታር ከ50-60 ኩንታል ለማምረት ካለው ዕድል አኳያ ሲታይ ግን አሁንም በሚፈለገው የምርታማነት ደረጃ ላይ ያልደረስን በመሆኑ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለብን የሚያመላክት ሆኖ መገኘቱን ታሳቢ ያደረጉት ስራዎች ለወትሮው ያለውጭ እርዳታ መቋቋም የማንችለውን ድርቅ እስከመቋቋም ባደረሰ ውጤት ተረጋግጧል፡፡
ሰሞኑን የፌዴራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተለያዩ የልማት ስራዎችንና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በጎበኘበት ወቅት በአርብቶ አደር አካባቢዎች የድርቅ ስጋትን ለመቀነስ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጡ አንደኛው ማሳያ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በመስኖ የበቆሎና የሰሊጥ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ የጉብኝት ልኡካኑ ማረጋገጣቸውም በተመሳሳይ።
የልኡኩ መሪ የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች ሲናገሩ እንደተሰሙትም በቦረና፣ ጉጂና ሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋለውን የድርቅ ስጋት ለማስወገድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ስራ እንደሚከናወንና፤ ለእንስሳት በቂ መኖ ማቅረብ እንዲቻል በቂ መኖ ከማይገኝባቸው አካባቢዎች መኖ ወዳለው ቦታ በማንቀሳቀስ ያለውን የድርቅ አደጋ ከእጃችን ሳይወጣ ያለንን ልምድ ተጠቅመን በቁጥጥር ስር ማዋል የሚቻል መሆኑን የተመለከተ እና ሁሉ አቀፍ በሆነ መልክ አቅም መገንባታችንን የሚያጠይቅ ነው። እየፈረጠመ በሚገኘው አቅማችን እና ፖሊሲያችን ታዳጊ ክልሎች በልዩ ድጋፍ አማካኝነት ልማታቸውን የማመጣጠን ስራ ተግባራዊ ውጤት እያሳየ መምጣቱም ሌላኛው ማሳያ ነው።
በሀገራዊ የልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ ተመርኩዘው የሚካሄዱትን የምርምር ስራዎች አቅጣጫ የሚያሲዝ የምርምር ምክር ቤት ተቋቁሞ፣ ምርምሩን የሚደግፍ እና የሚያስተሳስር ስራ መሰራቱ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና ተመዝግቧል ለተባለው ውጤት ምክንያት መሆኑንም ማጤን ያስፈልጋል።
ዛሬ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት ላይ የሚገኘውና መስኖን መሰረት ባደረገው የግብርና ስራ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ተወዳዳሪ ሆና በዓለም የግብርና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራት በማስቻል ውጤታማ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ከምክር ቤቱ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ ።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለዓለም ገበያ በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ ሆና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን የምታሳድግበት አቅጣጫም እንደሚዘረጋ የሚገልጹት መረጃዎች፤ ምክር ቤቱ አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን የምርምር ስራዎች ማጠናከር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ የግብርና ምርምር ስራዎች የሚያከናውን እንደሆነ፤ ይልቁንም የግብርናው ዘርፍ እያደገ ሲሄድ በመጠኑ ግዙፍ ሊሆን የሚችለው ባዮማስ በአስተማማኝ ሁኔታ ለባዮ ኢንደስትሪው ግብዓት እንዲሆን የማስቻል ስራ የሚያከናውን እንደሆነ መገለጹ የፖሊሲውን ትክክለኛነት እና መሬት መርገጥ የሚያመላክት ለእድገታችንም እንደዋና አስረጂነት ሊጠቀስ የሚገባው ነጥብ ነው።
የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ዋነኛ ሞተር በመሆኑ ምክር ቤቱ የግብርና ልማቱን ለማገዝ ወቅታዊ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም እውቀቶችን ያቀርባል። ምክር ቤቱ ለጋራ ሀገራዊ የልማት ግብ ስኬትም የምርምር አቅምና ብቃትን ማሳደግ እና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች የማቅረብም ሃላፊነት የተሰጠው መሆኑ የሁለተኛውን ዙር ጉዞ ፈጣንና ውጤታማ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም ።
ግብርናችን ከኋላቀር አሰራርም ሆነ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደኢንዱስትሪ ለሚደረገውን ሽግግር አስተማማኝ መሰረት እየጣለ ስለመሆኑ ሌሎች አስረጂዎችንም መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ተጨማሪ አስረጂዎች መካከልም በየክልሎችና በፌደራል ደረጃ የሚገኙት የምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴ ነው። ለዚህ ፅሁፍ ደግሞ የሁሉንም ክልሎች መጥቀስ ሳይጠበቅብን በቅርቡ አሊያንስ ፎር ግሪን ሪቮሉሽን አፍሪካ (AGRA) በተባለ በ10 የአፍሪካ አገራት የተቋቋመና ከ100 በላይ ኩባንያዎች አባል በሆኑበት አፍሪካዊ ተቋም የ2016 የአፍሪካ ምርጥ ኩባንያ ተብሎ የተሸለመውን የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በአስረጂነት ብናነሳ ወቅታዊ፣ ተገቢና ምክንያታዊ ያደርገናል።
የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራዝ ለሽልማት የበቃው ባለፍው ዓመት 33ሺህ ቶን ምርጥ ዘር በማምረት ለተጠቃሚዎች በማከፋፈሉና ዘንድሮም 60 ሺህ ቶን ምርጥ ዘር ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ እየሰራ በመሆኑ ነው። ኢንተርፕራይዙ ብዛትን በቻ ሳይሆን ጥራትን የጠበቀ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በስፋት በማዳረስ ላይ በመሆኑ በአግራ ተሸላሚ መሆኑን ሸላሚው ማስታወቁም በዘርፉ የደረስንበትን ከፍታ በሚገባ የሚያረጋግጥ ነው።
የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ባሉት 10 ማዕከላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአርሶ አደሩን የዘር ፍላጎት ለሟሟላት እየሰራ ሲሆን፤ በ24 ሺህ ሄክታር መሬት በተለይ የስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ቦቆሎና ሌሎች ምርጥ ዘሮችን አምርቶ በማከፋፈል አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ይፋ ባደረገው መረጃ አመልክቷል። ይህ ኢንተርፕራይዝ ካከፋፈለው ምርጥ የስንዴ ዘር በአንድ ሄክታር መሬት በአማካይ 41 ኩንታል ስንዴ መገኘት መቻሉ ምርታማነታችን በምን ያህል ጥራትና ስፋት በመወንጨፍ ሂደት ላይ መገኘቱን ይጠቁማል።
ዝናብ አጠርና እርጥበታማ በሆኑ አካባቢዎችም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን መከላከል የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱ ሌላውና ስለደረስንበት አቅም ለማስላት አስረጅ ሆኖ ሊጠቀስ የሚገባው ነጥብ ነው ። ይህ ስርአት ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ነው። ባሳለፍነው አመት የተከሰተውን እና ያለብዙ የውጭ እርዳታ የተቋቋምነውን የድርቅ አደጋ ብናስታውስ እንኳ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ባፈሩት ጥሪት የተፈጠረውን ችግር መቋቋም መቻላቸውን ነው።ይህም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ይፈጠር የነበረን ችግር መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባታችንን ያሳያል ።
የሁለተኛው እቅድ ዘመን አካል ሆኖ መተግበር በጀመረው የ4ኛው የልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የመጀመሪያ አመት፥ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ቀጥተኛ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን የእርሻና ግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ቀሪዎቹ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ የመንገድ ግንባታ፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ የትምህርት ቤት እና ጤና ኬላዎች ግንባታን በመሳሰሉት የማህበረሰብ ስራ ላይ መሰማራታቸው ባለመንታ ጥቅሞችን የሚያስገኝልን ፕሮግራም እንደሆነ ይጠቁማል።
ይህ ብቻ አይደለም ለወትሮው ዝናብ አጠር ባልሆኑ አካባቢዎችም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ለማካካስ አርሶአደሩ በአነስተኛ መስኖ ፈጥነው የሚደርሱ ሠብሎችን እንዲያለማ እየተደረገ መሆኑንም ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደሚንስቴሩ መረጃ ከሆነ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋርና ሐረሪ ክልሎች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ስራ በመከናወን ላይ ነው። እስካሁን ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ አርሶአደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል ።
ቀደም ብለው ወደ መስኖ ልማቱ የገቡት የአማራ፣ የደቡብ ፣ የትግራይና የአፋር ክልሎች 184 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ፣ 80 ሺህ ቶን ብስባሽና ከ168 ሺህ በላይ ምርጥ ዘር በመጠቀም 485 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻላቸውን የሚገልጸው ይህ መረጃ፤ ከዚህ ውስጥ 362 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በአዝርዕት፣ በስራስርና በሌሎች ሲሸፈን ቀሪው የእርሻ መሬት በዝግጅት ላይ መሆኑን በመጠቆም የደረስንበትን ከፍታ ያሳየናል።
በአንደኛና በሁለተኛው የመስኖ ልማት ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ወደ መስኖ ልማቱ ቀድመው ከገቡ ክልሎች በተለይ የደቡብና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። እኒህን እና መሰል በርካታ አስረጂዎች በመጥቀስ የፖሊሲውን ትክክለኛነት እና የደረስንበትን ከፍታ ማየት የሚቻል ቢሆንም ስለአጀንዳችን ከላይ የተመለከቱት በቂ ይሆናሉ እና የስኬቱ መነሻ ከሆነው ፖሊሲ በስተጀርባ ያሉትን ነገሮች ጠቃቅሰን እናብቃ።
ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር የህብረተሰቡ ሰፊና የተደረጃ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራው በእንስሳት ማድለብ፣ በግና ፍየል በማሞከት፣ ንብ በማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚሊዮን ለሚቀጠሩ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ሥራ በስፋቱም ሆነ ህብረተሰቡን በማሳተፍና ተጠቃሚነተቻውን በማረጋገጥ ረገድ በአህጉራችንም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በምርጥ ተሞክሮነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡
በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በዕቅድ ዘመኑ ከተወሰዱ መፍትሄዎች አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክሂሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋትን ሥራ አሁንም ሙጥኝ ማለት ለበለጠ ውጤት የሚያበቃን መሆኑን መዘንጋት አይገባም።
ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየተገነባ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችን እያደገ መጥቷል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡
እንደዚህ አይነት ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የጀመርነውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራችንን ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስረን በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል ወደ ኢንዱትራላይዜሽን የምናደርገውን ሽግግር በሚያቀላጥፍና አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን የህዳሴ ጉዞ በሚያሳካ መንገድ ሊፈጸም የሚገባው መሆኑ ላይ ሁሉም ተመሳሳይና ግልጽ አቋም ሊኖረው ይገባል።