የእነ መድረክ የህግ የበላይነትን የመፃረር አባዜ

                                                     

ሰሞኑን የኦፌኮ ሊቀመንበርና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የዶክተር መረራ ጉዲናን በህግ ጥላ ስር መዋል ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው—ከሀገር ውስጥና ከውጭ። ከሀገር ውስጥ መድረክ የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ የዶክተሩ መታሰር አስመልክቶ “…የታሰሩበትን ምክንያት ሰንካላ ሰበብ ነው። እስሩ በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ የተደረሰውን መግባባትን የጣሰም ነው።” ብሏል። የውጭ አጋሩ የሆነውና ራሱን “አምኒስቲ ኢንተርናሽናል” እያለ የሚጠራው አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ተቋምም፤ “እስሩ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር መብት ላይ የተቃጣ እርምጃ ነው” የሚል መግለጫ በማውጣት ዶክተሩ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል። ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ በበኩሉ ዶክተር መረራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀፅ 1 ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ክልከላ ጥሰው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በማድረጋቸው ምክንያት መሆኑን ገልጿል። ይህ የኮማንድ ፖስቱ ምክንያትም በቀጥታ የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ግልፅ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት የዶክተሩ በህግ ጥላ ስር የዋሉበት ምክንያት በህገ መንግስቱ አማካኝነት የወጣውን ህግ በመተላለፋቸው ብቻ ነው። እንደሚታወቀው በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው የህግ የበላይነትን ማክበር አለበት። አንድ ሰው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም አመራር በመሆኑ እንዳሻው ከህግ በላይ ይሆናል ማለት አይቻልም። ግለሰቡ የታቀፈው በፖለቲካ ፓርቲ፣ በጋዜጠኝነት፣ በዳኝነት አሊያም በሌላ ማህበራዊም ይሁን ሙያዊ መዋቅር ውስጥ ቢሆንም፤ ህግን ተላልፎና በማን አለብኝነት የህግ የበላይነትን የሚፃረር ድርጊት እስከፈፀመ ድረስ ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም። ያኔም ከሳሹም ሆነ ፈራጁ ህግ እንጂ ሌላ አካል ሊሆን አይችልም።

በመሆኑም ዶክተር መረራ ጉዲና በእነ አና ጎሜዝ አማካኝነት በተጠራው የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት የፈፀሙት ድርጊት  አግባብነት የለውም—የተፃረሩት ህግንና የህግ የበላይነትን ነውና። እናም ዶክተር መረራ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶችና ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ ክልክል መሆኑን የሚገልፀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንቀፅ የተላለፉ በመሆናቸው በህግ ጥላ ስር እንዲውሉና ጉዳያቸውም እንዲጣራ መደረጉ የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ብቻ መታየት ያለበት ይመስለኛል። እናም መድረክ “የታሰሩበት ምክንያት ሰንካላ ሰበብ ነው።…” ማለቱ አግባብነት ያለው ፍረጃ አይመስለኝም።

እርግጥ መድረክ “ሰንካላ” ያለው ምክንያት ለራሱም ቢሆን ግልፅ አይመስለኝም። በአንድ ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ የተቋቋመ ድርጅት የህግ የበላይነትን ተፃርሮ ይቆማል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም የህግ የበላይነት እስካልተተገበረ ድረስ ፓርቲው ራሱ የሚፈልገውን አቋም ማራመድ የማይችል በመሆኑ ነው። እናም የህግ የበላይነትን ማስከበር ለእነ መድረክ “ሰንካላ ምክንያት” ከሆነ ሰንካላ ያልሆነው አመክንዩ ህግና ስርዓትን እንዳሻ በመደፍጠጥ ከህግ በላይ ሆኖ መንቀሳቀስ ነውን?—እኔ በበኩሌ አይመስለኝም። “ለምን?” ከተባለ መድረክ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ራሱም መንግስት ቢሆን ሊፈፅመው ስለማይችል ነው።

ያም ሆኖ ከመድረክ ያለፈ ታሪክ በመነሳት ለህግ የበላይነት የሚሰጠው ቦታ እጅግ አናሳ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት አቋም ቢይዝ የሚገርም አይሆንም። መድረክ ወትሮም ቢሆን ህግንና ስርዓትን ከውጭ ሃይሎች ለመሸመትና በእነርሱው ሳንባ የመተንፈስ አባዜ የተጠናወታቸው ተቃዋሚዎች ስብስብ እንደሆነ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ምርጫ 2002 ያቧደናቸው የመድረክ ስብስቦች በተለያዩ ወቅቶች በየኤምባሲዎቹ በመዞር እንዲሁም ድብቅ የፖለቲካ አጅንዳቸውን በሀገራችን ላይ በኃይል ለመጫን ለሚሹ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዓይነት ፅንፈኛ ኒዮ- ሊበራል ኃይሎች ተላላኪና እማኝ ሆነው በማሸርገድ፤ የህልም የስልጣን ወንበራቸውን በፍጥነት ለመያዝ ሲቋምጡ ተመልከተናቸዋል።

እስከዛሬ ድረስ ይህን ሁኔታ ያጤኑ ወገኖች “ያልዘሩትን አጨዳ” የምሬት እንጉርጉሯቸው በመነሳት “ብሶተኞቹ” ይሏቸዋል። አባባሉ የእነ መድረክን ብሶትን የማራገብ ፖለቲካ የሚያመላክት በመሆኑ ተገቢ ነው ባይ ነኝ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ ለትንሹም ይሁን ለትልቅ በየኤምባሲው ይዘውት የሚዞሩትን ብዛት ያላቸው ረብ- የለሽ ማመልከቻዎችን እየተመለከቱ “በዶሰኝነት” ይፈርጇቸዋል። ይህ ፍረጃም የተቃዋሚዎቹን ህገ- ወጥና ህጋዊ አሰራርን አደባልቆ የመሄድና በውጤቱም ሰሞተኝነትን ብቻ የሚያስገኝ በመሆኑ ከእነርሱ ውጪ በስያሜው ላይ የማይስማማ ወገን ይኖራል ብዬ አላስብም። ለእኔ ግን እነ መድረክ ብሶተኞችም ይሁኑ ሶሰኛ ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም። ምክንያቱም የእስከ ዛሬው ማንነታቸው የሚያሳየው ነገር ቢኖር የመድረክ ስብስቦች የዚህን ሀገር የህግ የበላይነት በውጭ ኃይሎች ችሮታና ወሳኝነት ለማስፈፀም የሚሹ በመሆናቸው ነው።

እርግጥ ይህ የተሳሳተ መንገዳቸው ምንም ዓይነት እርምጃ ሊወስዳቸው አልቻለም—እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን ህዝብ የሚያከብርና የእርሱን ውሳኔ “አሜን” ብሎ የሚቀበል አይደለምና። ዶክተር መረራ አውሮፓ የተገኙበት ምክንያትም ይህ የመድረክ ዛሬም ድረስ የዘለቀ የውጭ ኃይሎች አምላኪነት ሁነኛ መገለጫ ነው። ያም ሆኖ ግን እዚህ ሀገር ውስጥ በውጭ ኃይሎች አማካኝነት ተፈፃሚ የሚሆን የህግ የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ማወቅና መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ እጅግ ያስገረመኝ ሌላው ጉዳይ መድረክ ኮማንድ ፖስቱ ዶክተሩን በህግ ጥላ ስር ማዋሉ “ከመንግስት ጋር የተስማማነውን የሚጥስ ነው” በማለት ያቀረበው ስሞታ ነው። እርግጥ መድረክ ከመንግስት ጋር ተስማምቶ ከሆነ (ምናልባት ስምምነት ካለው ማለቴ ነው)፤ የተስማማበት ነጥብ የህግ የበላይነትን የተመለከተ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። መድረክ መቼና የት ከመንገስት ጋር እንደተስማማ ግልፅ ባይሆንም፤ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በመንግስት በኩል ‘የህግ የበላይነትን ብትጥሱም ምንም አናደርጋችሁም’ የተባለ አይመስለኝም። ይህ ካልሆነ ደግሞ ፓርቲው እንዳለው ‘ከመንግስት ጋር የተግባባነው ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ተፈራርሞ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሲያዝ ብቻ ነው’ በሚል ያቀረበው የመግለጫ አቤቱታ ነው።

ሆኖም መድረክ ምናልባትም ቀደም ሲል ከመንግስት ጋር እርሱ ባለው መንገድ ተግባብቶ ከሆነ፤ ያ በመደበኛ ህግ ወቅት የነበረው የመግባባት ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚሰራ አለመሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣው መደበኛ ህጎች ሊሰሩ ባለመቻላቸው ነው። በመሆኑም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተከለከሉ ጉዳዩችን መጣስ የሚቻልበት ምክንያት የለም። ስለሆነም መድረክ ተስማምቼባቸዋለሁ የሚላቸው ስምምነቶች ካሉ አሁን በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቅቡል ሊሆኑ እንደማይችሉ ማወቅ ይኖርበታል ባይ ነኝ። እናም መድረክ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከሚከተለው ህጋዊና ህገ ወጥ አካሄዶችን ከማጣቀስ ተግባሩ መቆጠብ ያለበት ይመስለኛል።

ካለፉት ተሞክሮዎች ማወቅ እንደሚቻለው አንድ አክራሪ ኒዩ-ሊበራል ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተ አንድ ጉዳይ መግለጫ ሲያወጣ፤ እንደ መድረክ ዓይነት የሀገር ውስጥ “ክንፉ” ደግሞ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ትርክት እንዲያስደምጠን ይደረጋል፤ ወይም ግልባጩ አካሄድ እውን እንዲሆን ይደረጋል። ለዚህም ነው ዶክተር መረራ እንደታሰሩ ወዲያውኑ ራሱን “አምንስቲ ኢንተርናሽናል” በማለት የሚጠራው ተቋም “እስሩ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር መብት ላይ የተቃጣ እርምጃ ነው” በማለት ከሁኔታው ጋር የማይገናኝ መግለጫ ያወጣው።

አዎ! ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዶክተር መረራ ጉዳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከመተላለፍ ጋር የተያያዘ ነው። ሃሳብን ከመግለፅም ይሁን ከመናገር መብት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም። ምንም እንኳን ዶክተር መረራ ላለፉት 25 ዓመታት በተቃዋሚነት በተሳተፉበት የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ያሻቸውን ሲናገሩ የነበሩ ቢሆኑም፤ እርሳቸውን ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ አሊያም የመናገር መብታቸው እንዲታገድ የተደረገበት ጊዜ ያለ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ምክንያቱም በእነዚያ ዓመታት ውስጥ ለእርሳቸውም ይሁን ለሌላው ዜጋ እነዚህ መብቶች ያለ መሸራረፍ እውን እንዲሆኑ እየተደረጉ በመምጣታቸው ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ዶክተር መረራ የሚታገዱ ከሆነ ያኔ እንጂ ዛሬ አልነበረም። ዶክተሩ ባለፉት ጊዜያት የህዳሴውን ግድብ አስመልክተው የ“አልተሳክቶም” ልቦለዳዊ ትርክትን በማነብነብ የህዝቡን የተነሳሽነት መንፈስ ሊሰብሩ ሲያሴሩ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ለንፅፅር የማይቀርቡትን የአስመራውን አስተዳደርና የኢፌዴሪ መንግስትን በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ረገድ ‘ሻዕቢያ ይሻላል’ በማለት እንደ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ምስክርነት ሲሰጡ፣ እንዳሻቸው ሲናገሩና ሲያስነግሩ…ወዘተ. ጉዳዩችን ሲፈፅሙ እንኳን ሃሳባቸውንም እንዳይገልፁ አልታገዱም። ምክንያቱም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን የመግለፅም ይሁን በነፃነት የመናገር መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያለውና የማይሸራረፍ በመሆኑ ነው።

እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ጉዳይ ሲከሰት የርዕዩተ-ዓለም ጣጣቸውን ሀገራችን ላይ ለማራገፍ የሚሽቀዳደሙት እንደ “አምንስቲ ኢንተርናሽናል” ዓይነት ፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች የማይገጥምን ነገር ለመስፋት መሞከራቸው የተለመደ ነው። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ያልተፃፈን ነገር ለማንበብ መሞከር ምንም ዓይነት ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከሰት የህግ ጥሰት የሚፈታው በሀገሪቱ ህግ እንጂ በውጭ ሃይሎች ውትወታም ሊሆን አይችልም። በጥቅሉ ዶክተር መረራ በህግ ጥላ ስር የዋሉበት ምክንያት በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተሰየመውና የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ ከሆነው አሸባሪው ግንቦት ሰባት ጋር ባደረጉት ግንኙነትና ግንኙነቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቃረን በመሆኑ እንጂ፤ መድረክ እንደሚለው በቁጥጥር ስር የመዋላቸው ምክንያት “ሰንካላ” ስለሆነ አሊያም “አምንስቲ ኢንተርናሽናል” ተሽቀዳድሞ እንዳለው ጉዳዩ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ ወይም ከመናገር መብት ጋር ስለተያያዘ አይደለም። የሁለቱም ድርጅቶች ፍላጎት የህግ የበላይነትን ከመፃረር አባዜ አኳያ እንጂ፤ በሌላ ሊተረጎም የሚችልም አይመስለኝም። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

መታሰራቸው በእጅጉ ያሳስበኛል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ‹‹እስሩ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር መብት ላይ የተቃጣ እርምጃ ነው” ሲል ኮንኗል፡፡

በኢትዮጵያ ይፈፀማል ስለሚባለው የሰብአዊ መብት በቤልጂየም ብራሰልስ ተገኝተው ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እማኝነታቸውን እንዲሰጡ የፓርላማው አባል በሆኑት እና ጎሜዝ እንደተጋበዙ የተነገረላቸው ዶ/ር መረራ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ አውሮፓ አምርተው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ማብራሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡

 

 

ዶ/ር መረራ በተጋበዙበት በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ  በ“አሸባሪነት” የተፈረጀው የ“ግንቦት 7” መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና  በየሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር አትሌት ፈይሳ ሌሊሳም ተጋብዘው ነበር ተብሏል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀፅ 1 ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ክልከላ ጥሰው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በማድረጋቸው መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትን ጠቅሶ ኢቢሲ ከትላንት በስቲያ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ዶ/ር መረራ፤ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምስክርነታቸው እንደሰጡ ጋብዘዋቸዋል የተባሉት አና ጎሜዝ በበኩላቸው፤ የፖለቲከኛው መታሰር ቢያስደነግጠኝም አላስገረመኝም ብለዋል፡፡ መረራ መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን ከትላንት በስቲያ ለቪኦኤ የተናገሩት ጎሜዝ፤ እስካሁን ህብረቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የመለሳለስ አካሄድ ሲከተል መቆየቱን ጠቅሰው ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለህብረቱ ኮሚሽን መፃፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የህብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን ገልፆ ግንኙነቱ ይሻክራል የሚል ስጋት እንደሌለው ጠቁሟል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤
‹‹ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር የተዳረጉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በመገኘታቸው ህግ ለማስከበር ሲባል ነው›› ብለዋል፡፡