ኢህአዴግን በድል ማግስት የገጠሙትን ችግሮች በሙሉ ከተመለከትን ባለፉት 26 ዓመታት ድርጅቱን ከገጠሙት ችግሮች ሁሉ በስበቱ እንዳሁኑ ኃይል ያለው ችግር ገጥሞታል ለማለት ይቸግረኛል፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ በሽግግር መንግስቱ ዘመን የተጋፈጣቸው ፈተናዎች በፍፁም ቀላል የሚባሉ አልነበሩም፡፡ የሽግግር ዘመን ፈተናዎቹን ቀላል ሊያስመስላቸው የሚችለው፤ እጅግ ከባዱ የትግል ምዕራፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ በንጽጽር ችግሮችን አሳንሶ የማሳየቱ እና እጅግ ከባድ ችግርን ተሻግሮ መምጣት ሌሎች ችግሮችን ሁሉ ቁልቁል ከሚያሳይ የመንፈስ ከፍታ የሚያቆም ከመሆኑ በቀር ፈተናዎቹ ቀላል አልነበሩም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ በነበሩትን ዘመናት የኢህአዴግን የትግል ጉዞ የሚቃኝ አንድ ታዛቢ (የታሪክ ጸሐፊ ወይም የፖለቲካ ተንታኝ) ድርጅቱ የትጥቅ ትግሉን በድል ካጠናቀቀ በኋላ በተጓዘባቸው የትግል ዓመታት የገጠሙት ፈተናዎች፤ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከገጠሙት አደጋዎች የሚተናነሱ አለመሆናቸውን ይገነዘባል፡፡
የትጥቅ ትግሉ ተጠናቅቆ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግሉ ከተጀመረ በኋላ ኢህአዴግን ከገጠሙት ችግሮች መካከል ወሳኝ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ሦስት ፈተናዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፤ በ1993 ዓ.ም የተከሰተውና የአመለካከት እና የድርጊት አንድነት ከማጣት የመጣው ድርጅታዊ ቀውስ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ የመጣው ‹‹የፖለቲካ ሱናሚ›› ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው፤ አሁን ጸንቶ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት የሆነው እና የፖለቲካ አለመረጋጋት የጎተተው ሁከት ወይም ቀውስ ነው፡፡ ይህ በሰፊ የህዝብ አመጽ እየተገፋ እና ወድቆ – እየተነሳ በኃይል ሲንጠን የቆየ ችግር የመጨረሻው ነው፡፡
የቀውሱ ሙሉ አንድምታ እና የአፈጣጠሩ ሂደት፤ ቀውሱ የከፈታቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ፈለጎች በሙሉ በዝርዝር መጠናት ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥ ለቀውሱ ምን ዓይነት ችግሮች ሰበብ ሆኑ የሚለው ይታወቃል፡፡ ችግሮችን ማን ለጥፋት ዓላማ ተጠቀመባቸው የሚለውም የሚታወቅ ነው፡፡ ግን በደንብ መጠናት ይኖርበታል፡፡ ይህ ችግር ሲገጥመን ከተለያየ ወገን የታየው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል የሚለው ነገር በደንብ ተጠንቶ ተመሳሳይ ችግር ሲገጥመን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠትም ሆነ፤ አስቀድሞ ለመጠንቀቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ብቁ በሚያደርገን ደረጃ ችግሩ ቢታወቅ ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ ጥናት መደረግ ይኖርበታል፡፡ አሁን ዓለም የሚቀናበትን የአብሮ መኖር ቅርስ ሳናጠፋ መዝለቅ የምንችለው፤ ችግሩን በዚህ መልክ የተረዳነው ሲሆን ነው፡፡ ይህ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ወዘተ ምሰሶዎቻችንን ሁሉ ያንቀጠጠ ችግር በደንብ መጠናት አለበት፡፡ የተሐድሶ እንቅስቃሴው መጠናከር አለበት፡፡ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥራችንም በጥራት መሰራት ይኖርበታል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን የህዝብ ግንኙነት ሸቀጥ አድርጎ አይመለከታቸውም፡፡ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በህዝብ ግንኙነት ገበያ ለሽያጭ የሚቀርቡ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ዋጋቸው በህዝብ ግንኙነት ትርፍ አይተመንም፡፡ በኢህአዴግ ቤት የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በስልጣን በመቆየት ሒሳብ የሚታይ ትርጉም የላቸውም፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጅግ ውስብስብ ከሆነ እና ስር ከሰደደ ድህነት ለመውጣት የሚያስችል ምቹ የልማት ሁኔታ የሚጥሩልን መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ከዛሬ ነገ ኑሮዬ ይሻሻላል፤ በልቼም የማድርበት ጊዜ ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረጉን ትቶ፤ መጪው ዕድሉ ሁሉ ጨለማ መስሎ ታይቶት በተስፋ መቁረጥ ላይ የተመሠረተ ጎዳና እንዳይከተል እና ፋይዳ ወደ ሌለው ትርምስ እና ደም መፋሰስ እንዳንገባ የሚጠብቁን፤ የግጭት እና የጦርነትን ፖለቲካዊ ምንጮች በማድረቅ ለልማት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉን፤ የልማት፣ የሰላም እና የሀገራዊ ህልውና ዋስትና የሆኑ ክቡር ግቦች ናቸው፡፡
ከ14 ዓመታት በፊት በወጣ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የፖሊሲ ሰነድ የሰፈረውን ቃል መመልከት ይቻላል፡፡ ገዢው ፓርቲ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በምን ደረጃ እንደሚመለከታቸውም በግልጽ ያመለክታል፡፡ ‹‹የዴሞክራሲ እና የመልካም ስርዓት መገንባት ከተሳነንእጅግ ዘግናኝ በሆነ እልቂት ተንጠን ረጅም ባልሆነ ጊዜ ውስጥ እንበታተናለን›› የሚለው ኢህአዴግ፤ ‹‹ህልውናችንን ለማረጋገጥ ከዴሞክራሲ እና ከመልካም አስተዳደር ግንባታ አማራጭ የለንም፡፡ በዚህ ዓላማ ላይ መንሸራተትን፣ ወደኋላ መመለስን፣ ሽንፈትን መቀበል አይቻልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሽንፈት ማለት እንኳንስ ለመሸከም ለማሰብም የሚከብድ ጥፋት የሚያስከትል ነገር ይሆናል››፤ ይላል፡፡ ጉዳዩን በዚህ ደረጃ የሚመለከት ድርጅት በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ አይቀልድም፡፡
መንግስት የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የህልውና ጉዳዮች አድርገው ይመለከተዋል፡፡ ስለዚህ የሐገራችን የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ስርዓት የማሽቆልቆል ጎዳና መከተል ቀርቶ መንቀራፈፍ እንኳን አይገባውም፡፡ የችግራችን የምንጭ በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የሚገኝ ነው፡፡ በሐገራችን ካለው ፈጣን የፖለቲካ (በንቃተ ህሊና ረገድ)፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የማህበራዊ ጉዳዮች የለውጥ ሂደት ጋር የሚመጣጠን የመልካም አስተዳደር መሻሻል ማሳየት ይኖርብናል፡፡
ኢህአዴግ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ምን ትርጉም እንዳለው በደንብ ያውቃል፡፡ ትርጉሙን ከፓርቲ ህልውና የላቀ መሆኑን ያውቃል፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር በራሳቸው ክቡር ግቦች ናቸው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሁኔታ ያላቸው ትርጉም በሐገር ህልውና እና ሰላም የሚመነዘር ነው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥረታችን አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ባህርይ ያለው ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ ‹‹ይህ ስርዓት ወደኋላ መመለስ ሳይሆን ከተንቀራፈፈም አደጋ ያመጣል›› ብሎ የሚያስብ ድርጅት ነው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥረታችን መንቀራፈፍን የሚሸከም አይደለም ይላል፡፡
በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የሚታየው ችግር፤ ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር የሚያደርግ ችግር ያስከትላል፡፡ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ስርዓታችንን በሚፈለገው ፍጥነት፤ በተሳካ ሁኔታ መገንባት አለመቻላችን አደጋን እንደሚጎትት አይተናል፡፡ አሁን የታየው ችግርም የዴሞክራሲ ስርዓቱ ወደ ኋላ ከመመለሱ የመነጨ ሳይሆን፤ በፈጣንና በተሳካ ሁኔታ ግስጋሴ ለማሳየት ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የሐገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዓላማ፤ የሐገር ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማ እንዲሆን ያደረገውም ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት ነው፡፡ የፍላጎት ማነስ ባይኖርበትም፤ በባህርይው ዴሞክራሲያዊ እና የላቀ የህዝብ ወገንተኛነት ያለው ድርጅት ቢሆንም፤ የጉዳዩን አጣዳፊነትም የተረዳ ቢሆንም፤ በተለያዩ አክሎች ጉዳዩ በሚጠይቀው ፍጥነት መራመድ አለመቻሉ ክፍተት መፍጠሩ ሊካድ የማይችል ሐቅ ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ ዴሞክራሲ በሌለበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ሥራ ሊኖር አይችልም፡፡ መልካም አስተዳዳር ሊኖር የሚችለው በዴሞክራሲ ስርዓት ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲ ባለበት ሐገር ሁሉ የመልካም አስተዳደር ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን የተፈጠረው ችግር ከዴሞክራሲ አለመኖር ጋር የተያያዘ ሳይሆን፤ የህዝቡን ያደገ የመልካም አስተዳደር ፍላጎት የሚመጥን ስኬታማ የመልካም አስተዳደር ሥራ ካለመኖሩ ጋር የተቆራኘ ችግር ነው፡፡
ታዲያ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር የግድ አብረው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ዴሞክራሲ ሐገራችን ከጥፋት የመታደግ ሚና ያለው የሐገራዊ ህልውና ጥያቄ እንደሆነ፤ መልካም አስተዳደርን በፍጥነት የማስፈን ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚያመለክት ችግር እያየን ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር፤ ህዝቡ በዴሞክራሲ ስርዓቱ ላይ ያለውን እምነት እንደሚያጠፋው ይታወቃል፡፡ ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ያለው እምነት ሲሸረሸርም፤ በሰላማዊ እና ህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ መፍትሔ ከመፈለግ ሊወጣ ይችላል፡፡
አሁን የገጠሙን ችግሮች በውስብስብነታቸው እና በአደናጋሪው ባህርያቸው፤ ድርጅቱን በትጥቅ ትግል ዘመን ከገጠሙት ፈተናዎች ከብደው የሚታዩ ናቸው፡፡ የህይወት መስዋዕትነት የማይጠይቁ ፈተናዎች በመሆናቸው ቀላል ተደርጎ የመታየት ዕድል ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም የህይወት መስዋዕትነት የማይጠይቁ መስለው ይታያሉ እንጂ፤ ከዛሬው የተሻለ ምዕራፍ ለመድረስ የተከፈለውን የህይወት መስዋዕትነት ሁሉ ከንቱ የማድረግ ችሎታ ያላቸው፤ የሞት ወይም ሽረት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ችግር በፍጥነት በመውጣት የታጋይ ሰማዕታትን መስዋዕትነት ማክበር ይኖርብናል፡፡ ላሉታ ኮንቲንዋ!!