የወጣቶች ተጠቃሚነት ከቢዝነስ ፕላን ፕሮጀክቶቻቸው አኳያ

 

በሃገራችን በሚገኙ ከተሞች በተለይ ባሳለፍናቸው 15 አመታት ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ልማት እንዲስፋፋ በመደረጉ በተለይ ደግሞ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ልማት ዘርፍ  በማደጉ የተነሳ የህዝብ ተጠቃሚነት መጨመሩ የማይተባበል ነው፡፡ በከተማም በገጠርም ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢው ያለማቋረጥ ሲያድግ ቆይቷል፡፡ በቀጥተኛ የገንዘብ ገቢ መልክ የማይገለፁ ጥቅሞችም በተለይ የትምህርት፣ የጤና፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ተጠቃሚነት እድል ወዘተ . . . ሰፍቷል፡፡ በጦርነት ከመታመስ ተገላግሎ የሰላም አየር የሚተነፍስ  ህብረተሰብ ተገንብቷል፡፡ ይህ የአገራችን እድገት በትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመመራቱና መንግስትም ይህን የመሪነት ሚና ከመጫወቱ ጋር ተያይዞ የተመዘገበ ውጤት ነው፡፡ 

ወጣት ማለት ጉልበት እና እውቀት ያለው ሰርቶ ሀብት ሊያፈራ የሚችል የህብረተሰብ ክፍል ማለት ነው፡፡ ይህ ክፍል በዋነኛነት በመንግስት አመራር እና የፋይናንስ ድጋፍ እየታገዘ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ልማት ላይ በመሳተፍ ሀብት ማፍራቱና በበርካታ ውጤቶች ሊገለጹ በሚችሉ ደረጃ ላይ መድረሱም እሙን ነው፡፡ ከእንጨት እስከ ብረታ ብረት፣ ከኤሌክትሪክ እስከ ሞተር ስራዎች ወዘተ . . .  የተሰማራው ይህ አምራች ሃይል በከተሞችከ ሀብት መፍጠር እንዲስፋፋና የብዙኀኑ ተጠቃሚነት አብሮ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተሰማራው ጀምሮ በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስኮች  ላይ የተሰማራው ባለሃብትም ባደረገው ጥረት በየደረጃው እሴት የመጨመር ተግባራት እየተከናወኑ ከተሞቻችን በፈጣንና ህዝብ በሚጠቀምበት የልማት አቅጣጫ ተጉዘዋል፡፡ ይህም በአገራችን ገጠሮችና ከተሞች እጅግ ተስፋ ሰጪ የሆነ ልማታዊ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋና ውጤትም እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ የዓለማችን አገሮች ቀዳሚዋ ልትሆን ቻለችባቸው ምክንያቶች አንዱም ይህ ነው፡፡ 
ያም ሆኖ ግን አብዛኛው የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የሌለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዛሬ ከተሞቻችን ተጨናንቀዋል። እነዚህን በወጣቶች  የተጨናነቁ ከተሞች ታሳቢ ያደረገ የተጠቃሚነት ስርአት መዘርጋትንየና አፈጻጸሙንም የተመለከተው ጉዳይ ወቅታዊና የዚህ ተረክ ልዩ ትኩረት ነው።   
ጉዳዩን ወቅታዊና ልዩ ትኩረት እንድንሰጠው ግድ እንዲለን ምክንያት ከሚሆኑን መካከል ወጣቱ በአገራችን በተስፋፋው የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆኖ ከቆየ በኋላ የወላጆቹን ልማዳዊ የግብርና ስራ ሊቀጥልበት የማይፈልግ እየሆነ በመምጣቱ የገጠሩ ወጣት ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች በተለይ ደግሞ ወደገጠር ከተሞች እየጐረፈ መከማቸት የጀመረ መሆኑ የመጀመሪያው ነው፡፡
በየአካባቢያችን እንደሚስተዋለው ወጣቱ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው እና በዚህም ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ መሆኑም ሌላኛውና መሰረታዊ ምክንያት ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት ከመቸውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር በተደጋጋሚ መጋለጧ እንደማይቀር በመገንዘብ አዲስ አይነት አሰራር ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡
ይህን ስንል ከላይ በተመለከተው አግባብ መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን ባለመዘንጋት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ይታወቃልና፡፡ 
ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚህ ላይ በመመሰረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን ታሳቢ ያደረገ ፈጣንና ተመጣጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ ችግሩን ያባባሰው መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወቅ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና የተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአድልአዊ እና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት መደነቃቀፉ የፈጠረው የተስፋ ቢስነት ስሜት ባሳለፍነው አመት እንድትየው ሃገርን ስጋት ላይ ለሚጥሉ የግጭትና የትርምስ አደጋዎች የሚያጋልጥ መሆኑ አያጠያይቅምና በመንግስት በኩል የተዘጋጀውን ውጥንና በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋለውን ተቃራኒ ስሜትና መንሰፍሰፍ በሚገባ ልንመክርበት ይገባል ፡፡  
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ስነ ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር  የወጣቶች የማነቀሳቀሻ ፈንድ 10 ቢሊዮን ብር መንግስት መመደቡን መግለጻቸው ይታወሳል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከላይ የተመለከቱ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የ2009 ዓ.ም የመንግስት ትኩረት የአገሪቱን ወጣቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑም በንግግራቸው ተመልክቷል፡፡ ይህ የወጣቶች የማንቀሳቃሻ ፈንድን ተግባራዊ ለማድረግ የተያዘው እቅድ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የስራ እድል ፈጠራና የመልካም አስተዳደር ችግሮችኘ ለማስወገድ የሚያግዝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢነገርም ይህቺንም ለቀራመት ያሰፈሰፈው ሃይል እየበዛ የመጣ ይመስላል። በየአካባቢው ስራ ያለውና የተሻለ ኑሮ አለው የሚባለው ሳይቀር መደራጀትን እየሰበከና ማህበር በማቋቋም ሊቀራመት እያሰላ መሆኑም በስፋት እየታየ  እና ይህ ጸሃፊም ባለስራ ሆኖ ከባለስራ ጓዶቹ የቀረበለት የእንደራጅ ጥያቄ ነው።
መንግስት ስራ አጥነትን ለመቀነስና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተመደበውን በጀት ፍትሃዊ ተደራሽነትና ለታቀደው ዓላማ መዋሉን ሊከታተል የሚገባው መሆኑን የተመለከቱ ዜናዎችም ከሰሞኑ መብዛታቸው የሚጠቁሙት ይህንኑ እና የተንሰፈሰፈው ሃይል መብዛቱን ነው።
ከነዚህና ሰሞንኛ ከነበሩት ዘገባዎች መካከል የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ወጣቱ በተመደበለት በጀት ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠር ሚናውን ለመወጣት እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑን መግለጹና፤ የማኅበሩ አባላትም ማኅበሩ ወጣቱን የሚወክል ተቋም በመሆኑ አፈጻፀሙን መከታተል እንደሚኖርበት ጨምሮ መንግስት ገንዘቡን ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ አሰራሮችን መከተል እንዳለበት ማሳሰባቸው እግረመንገዱን በየአካባቢው ተንሰፍሳፊው መብዛቱን የሚያረጋግጥ አስረጅ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረትም በፕሬዘዳንቱ በኩል መንግስት እስከታች ድረስ ወርዶ ገንዘቡ ለተደራጀው ወጣት በትክክል እየደረሰ መሆኑን ክትትል ማድረግ እንዳለበት መግለጹም በተመሳሳይ የሚያጠይቀው የተንሰፍሳፊውን ሃይል መበራከት ነው።
በእርግጥ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ለወጣቶች የተመደበውን ፈንድ አፈጻፀም የሚከታተልበት መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን በቅርቡ መግለጹ አንድ ነገር ቢሆንም በአመለካከት ደረጃ ይህን ማስተካከልና በህብረተሰቡ ይልቁንም በወጣቶች ዘንዳ ጥልቅ ተሃድሶ በተለየ ሁኔታ መደረግ ያለበት መሆኑን የሚያመላክቱ አስረጂዎች ናቸው።
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘገባ መሰረት ከወደአማራ ክልል  አካባቢ እየተደረገ የሚገኘው ዝግጅት ለሁሉም የክልል ከተሞች በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባውና ተንሰፍሳፊ የሆነውን ሃይል ቅስም የሚሰብር እንደሚሆን መገመት አይከብድም። ይህ ተሞክሮ በክልሉ ስራ ፈላጊ የሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ የተነገረለት አዲስ መመሪያ ነው።
የክልሉ ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ለኤፍ ቢ ሲ እንደተናገረው መመሪያው ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የስራ መስኮችን የለየና የማደራጀት ሃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ሃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቢቀሩ ተጠያቂነትንም ያስቀመጠ ነው።
የስራ ፈጠራ ፓኬጆችን በቅርበት የሚከታተለው የስፖርት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ደግሞ በቅርቡ የተመደበው 10 ቢሊየን ብር አዋጭነት ያለው የቢዝነስ ፕላንና ፕሮጀክት ለሚያቀርቡ ወጣቶች ውጤታማነትን መሰረት በማድረግ በብድር መልክ ይሰጣል ማለቱ እና የሚሰጠውን ብድር ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማና ወጣት ለማድረስ የሚያስችል ወጣቶችን ያሳተፈ የህግ ማእቀፍም እየተዘጋጀ ነዉ ማለቱን እያሰላን፤ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ  በዚህ አመት ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የያዘውን እና አሁን ላይ በራሱ አቅም ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድርግ አዲስ መመሪያ በማውጣትና የራሱን በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአማራ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተያዘው 10 ቢሊየን ብር በሚደርሰው ድርሻ የክልሉን ወጣቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አለማጠራጠሩ ነው “ሊወሰድ የሚገባው ተሞክሮ” እንድንለው ያስገደደን ።
መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመደበው 10 ቢሊየን ብር የማንቀሳቀሻ መበጀት ለስራ ፈላጊ ወጣቶች በብድር መልክ የሚሰጥ እና ከወጣቶች ጋር በሚደረግ ውይይት በተመረጡ የስራ መስኮችና ፕሮጄክቶች ላይ እንዲውል የሚደረግ እንጂ እንዲያው አማረኝ ያለ ሁሉ የመንሰፍሰፍ አምሮቱን የሚያስታግስበት አይደለም።
ይህንና ከላይ የተመለከተውን የአማራ ክልል ተሞክሮ  መነሻ በማድረግ በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ  ይልቁንም ስራ አጥ ወጣቶችን የመለየት እና የስራ እድል ፈጠራ ፓኬጅ የማሻሻል ስራቸውን  ከወዲሁ በመጀመር የኪራይ ሰብሳቢ ሃይሉን ቅስም መስበር ይጠበቅባቸዋል።
በብቤሄራዊ ፕላን ኮሚሽን በኩል በዋናነት በበርካታ መስሪያ ቤቶች በርካታ የስራ እድል መኖራቸው የተለየ መሆኑ ጨምሮ፤ በተሻሻለው የስራ እድል ፈጠራ ፓኬጅ በእርሻ መካናይዜሽን ወጣቶች ተደራጅተው የእርሻ መሬት እንዲሰጣቸው እና መሳሪያ በግዢ እንዲያገኙ በማድርግ በመስኩ ማሰማራት በቀዳሚነት የተመረጠ ዘርፍ እንደሆነ ይፋ መደረጉን የተመለከተውንም ዜና ተንሰፍሳፊዎቹ ተረድተው የአቅጣጫ ለውጥ ቢያደርጉ የሚያዋጣቸው ይሆናል። የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባልተዳረሰባቸው ገጠራማ የሀገሪቱ ክፍሎችም ወጣቶች ተደራጅተው አግልገሎቱን እንዲያቀርቡ ማስቻል እና የኮንስትራክሽን ዘርፍም በስራ አማራጭነት ከተያዙት መካከል ይጠቀሳሉ።
የወጣቶች የማንቀሳቀሻ ፈንድ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆን መንግስት የገባው ቃል እና ከላይ በተመለከተው መልኩ የጀመረው ስራ አጥ ወጣቶችን የመለየት እና የአሰራር ስርአት የመዘርጋት ስራ በብልሹ አሰራሮች እና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ተጠልፎ ወደባሰ ቀውስ እንዳይወስደን ደግሞ ወጣቱና ልማታዊው ሁሉ በአይነ ቁራኛ ተሳትፎ ማድረግና ሃብትና ንብረቱን መጠበቅ ያለበት ሲሆን፤ መንግስትም ከላይ በተመለከቱት እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይወሰን ወጣቱ ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችለውን ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እና የስልጠና እድሎችን ማመቻቸት  ያለበት መሆኑ ከቶም ሊዘነጋው የማይገባ ወግማረጉ ይሆናል።