ድርቅን ለመመከት መስኖም ማልማት

 

                                                                          

የአለም ባንክ ባለፈው አመት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በሀገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የተፈራውን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ አለማሳደሩን ገልጾአል፤ ሀገራችን ባለፈው ዓመት ያስመዘገበችው የምጣኔ ሀብት እድገት 8 በመቶ መሆኑንም አስምሮበታል፡፡ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ወቅታዊ የኢኮኖሚ እድገትና የቀጣዩን አመት ምጣኔ ሀብት የፈተሸው 5ኛው የባንኩ ሪፖርት ባለፈው አመት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ድርቅ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት እንደነበር ገልጾአል፡፡ ባንኩ ከራሱ ስጋት በመነሳት ይሄን ቢገልጽም ድርቁን ለመመከትና ለመቋቋም መንግስት የወሰደው ፈጣን እርምጃ ነው ሊያስከትል ይችል የነበረውን ግዙፍ አደጋ እንዲቀንስ ያደረገው፡፡ ለዚህም በርካታ ምእራባውያን መንግስታትና ለጋሾች ጭምር በወቅቱ አድናቆታቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

የአለም ባንክ በ2015/16 እ.ኤ.አ በሀገራዊ የግብርና ዘርፍ ሪፖርቱ የመኸር ምርት እድገት በ1 ነጥብ 3 በመቶ መቀነሱን፣ በበልግ ወቅት በ113 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን በዚህም የነበረውን ስጋት መቅረፉን በምጣኔ ሃብቱ ላይ የተፈራው ተጽእኖ እንዳይደርስ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ የባንኩ የኢኮኖሚ ባለሙያና የጥናት ቡድኑ ሃላፊ ሚካኤል ቶቤጋስ ኢትዮጵያ ከ50 አመታት ወዲህ አስከፊ የተባለ ድርቅን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻልዋ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የእድገት ስጋት የሆኑ ሁኔታዎችን የመቋቋም አቅሟን የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቦአል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው አመት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤት ቢያስመዘግብም በወጪና ገቢ ንግድ ዘርፎች ላይ የሚታየው አለመመጣጠን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ጫና ማሳደሩ በባንኩ ሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በኢትዮጵያ ባለፈው አመት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን ቢጨምርም የወጪ ንግድ መጠን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አንፃር ሲታይ እንዳለፉት አራት አመታት ሁሉ ባለፈው አመትም መቀነሱን ችግሩን ለመቅረፍ የውጪ ንግድ ላይ የሚታየውን መቀዛቀዝ ወደ እድገት መቀየር የሚቻለው የግሉን ባለሃብት ተሳትፎ በማሳደግና የማምረት አቅምን ከፍ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአለም ባንክ ትንበያ መሰረት በመጪው አመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተለመደው የመኸር ዝናብ ስርጭት መኖር፤ የአዲስ አበባ – ጅቡቲ የባቡር መስመር ፕሮጀክት መጠናቀቅ፤ የአዳዲስ የኢንዱስትሪ ዞኖች ወደስራ መግባትን ተከትሎ አገሪቷ መልካም ጅማሮዎች እየታዩባት መሆኑን አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አፈፃፀም የዳሰሰው ይህ ሪፖርት የሀገር ውስጥ የስራ አጥ መጠንንም ያካተተ ሲሆን ባለፉት 10 አመታት የሀገር ውስጥ የስራ አጥነት መጠን ከ27 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማለቱን፤ ዛሬም 9 በመቶ የስራ አጥነት መጠን ካላቸው እንደ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አንፃር በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጾአል፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ስራዎችን በመስራት በሰፊው እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የአለም ባንክ ሪፖርት ከገለጻቸው ክፍተቶች በተጨማሪ በቀጣይ ቢሰሩ ውጤት ያመጣሉ  ያላቸውን አምስት ሃሳቦችን አካቶአል። ዶክተር አብርሃም የስራ አጥነት ችግርን አስመልክቶ  የተቀመጡትን መፍትሄዎች ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም አሁን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሪፖርቱ ከመንግስት ጥናትና ግኝት ጋር የተጣጣመና በቀጣይ ቢስተካከሉ ተብለው የተቀመጡ ነጥቦችም የሚወሰዱ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

አምና ተከስቶ የነበረውን ድርቅ አስፈሪነት የአለም ባንክ መግለጹ ትክክል ነው፡፡ ማንም አካል ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ትመክተዋለች ወይንም ትቋቋማለች የአደጋውን መጠንና አስፈሪነት ትቀንሰዋለች ብሎ የገመተም ሆነ ያሰበ አልነበረም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ አስከፊ በሆነው ኤልኒኞ ድርቅ ምክንያት ምስራቅ ኦሮሚያ፣ የአማራ ምስራቃዊ አካባቢ፣ በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች፣ የአፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የድሬዳዋ አካባቢዎች በድርቁ ቀጥተኛ ተጠቂነት ስር ወድቀው ነበር፡፡ እርዳታ የማዳረስ ስራን ድርቁ ከሸፈነው ሀገራዊ የቆዳ ስፋት አንጻር አስቸጋሪ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ቀድሞ የተዘረጉትን የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ፕሮግራም መንግስታዊ መዋቅሮችን በመጠቀም እርዳታዎችን ለተጎጂ ወገኖች በፍጥነት በማዳረስ የዜጎችን ህይወት መታደግ ተችሎአል፡፡

ባለፈውም ሆነ በአሁኑ የእድገትና ትራንስፖርቴሽን እቅድ ዘመን መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የድርቅ ስጋትን ለመቀነስ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፤ ከነዚህም አንዱ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚስተዋለውን የድርቅ ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል የመስኖ ልማት ስራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የመስኖ ልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመስኖ የበቆሎና የሰሊጥ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ሊበረታታና ሊታገዝ የሚገባው ጅምር ነው፡፡ በቦረና፣ ጉጂና ሌሎች አካባቢዎች የሚታየውን የድርቅ ስጋት ለማስወገድ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ በርካታ ሰራዎች እንደሚሰሩ ይጠበቃል፡፡

ለእንስሳት በቂ መኖ ማቅረብ እንዲቻል በቂ መኖ ከማይገኝባቸው አካባቢዎች መኖ ወዳለው ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አንዱ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ በትኩረት እየሠራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት አሁን እየተስተዋለ ያለው ድርቅ ከእጃችን ሳይወጣ ያለንን ልምድ ተጠቅመን በቁጥጥር ስር እናውለዋለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የገለጹ ሲሆን የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃንም በክልሉ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ታዳጊ ክልሎች በልዩ ድጋፍ አማካኝነት ልማታቸውን ለማመጣጠን እየተሰራ ያለው ስራ ተግባራዊ ውጤት እያሳየ መሆኑንና በክልሉ በራስ አቅም እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች አማካይነት ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ይህም የህብረተሰቡን ለልማት የመነሳሳት መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ከድርቅ፣ ከአለም ባንክ ሪፖርትና ከመስኖ ልማት ጋር በተያያዘ ሌላው ተስፋ ሰጪ ዜና የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ዘንድሮ ከሚገኘው የመኸር ሰብል በአጠቃላይ 320 ሚሊዮን ኩንታል ያህል ምርት ይሰበሳባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ማስታወቁ ነው፡፡

የታረሰው መሬት 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሆኑን በመኸር ወቅት በሀገሪቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ለግብርና ተስማሚ የሆነ የዝናብ ሥርጭት መኖሩ ለአርሶ አደሩ ከተሰጠው ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና ጋር ተቀናጅቶ ለውጤቱ መገኘት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልከቷል፡፡ የዘንድሮ የመኸር ምርት ከነበሩት የቀድሞ አመታት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ የሃገራችን ግብርና አመቱን ጠብቆ ከሚመጣ ዝናብ ጥገኝነት ቢሆንም በያዝነው አመት ብቻ 320 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቦአል፡፡ ለቀጣዩ አመትም የበለጠ ዝግጅት በማድረግ ከተሰራ ከዚህም በላይ ማምረት እንደሚቻል ይታመናል፡፡

የተፈጥሮ የአየር ንብረት ሊፈጥረው የሚችለው ሁኔታ የማይታወቅና በእጅ ያለ ባለመሆኑ ተመልሶ የድርቅ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ብቸኛው መፍትሄ የመስኖ ተጠቃሚነትን ማስፋፋት፣ አርሶ አደሩ በሚገባ ጥቅሙን አውቆ ስራ ላይ እንዲያውለው ማድረግና  በሙያተኞች የታገዘ ተከታታይ ስልጠናና ትምህርት ያለማሰለስ መስጠት በተለይም ተተኪውን ወጣት ማሳተፍ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

እንደአጠቃላይ ስናየው የመስኖ ልማት ተጠቃሚ በመሆን አርሶ አደሩ እንዲሰራ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፣ ተግባሩ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሎአል፡፡ በቀደሙት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 116 አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተዋል፡፡ በዚህም 12 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ64 ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ ለመሆን እንደቻሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል። ሁለተኛው የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ይፋ የተደረገ ሲሆን 108 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በመጪዎቹ 7 ዓመታት ስራ ላይ የሚውለው ቀጣዩ ደረጃ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 145 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚደረግበት ሲሆን 150 የአነስተኛ መስኖ ልማቶችን የመገንባት እቅድ መያዙንና እቅዱ በተለያዩ ክልሎች ባሉ 110 ወረዳዎች እንደሚሰራበትም ሚኒስቴሩ ገልጦአል፡፡

ሀገራችን ተፈጥሮ የጋረጠባትን ችግሮችና መሰናክሎች እየተጋፈጠች በራስዋ አቅምም እየመከተች በሂደቱም ይበልጥ እየተማረች ጉዞዋን ወደፊት ቀጥላለች፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ከማዘመኑ ስራ ባሻገር ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት በመስኖ ልማት ላይ ማተኮር ድርቅንም ሆነ ረሀብን ለመቋቋም፣ ቤተሰብንም በምግብ ራስ ለማስቻል እጅግ ተመራጭና አዋጪ መንገድ በመሆኑ አጠንክረን ልንይዘው ይገባናል፡፡