የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ ለማጨናገፍ . . .

 

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑ የታወቃል። ይህ ስርአት የዘመናት የብሄራዊና የመደብ ድርብ ጭቆናዎችን የተመለከቱ የህዝብ ጥያቄዎችን ከመሰረቱ ለመለወጥ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብቶችን ማረጋገጥ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ ነው። በዚህም ሃገራችን በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት ሃገር እንድትሆን  ሁል ጊዜም ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን እያነሱ መወያየትና ለተግባራዊነቱ መረባረብ ያስፈልጋል። ይህ ትርክትም ከርብርቦቹ እንደ አንዱ የሚወሰድ ነው።

ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም በነፃ ፍላጎት፣ በሕግ የበላይነትና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ስምምነት ላይ ከተደረሰ 22 ዓመታት የመቆጠሩን ያህል በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ደካማ የሚባል መሆኑም ነው ሁሌም ጉዳዩን ማንሳትና መጣል ግድ እንዲለን እና ለዚህ ተረክ እንደ አንድ ምክንያት የሆነው ፡፡

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተግባራዊ ካደረገች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ መቆጠሩን ስናሰላ፤ በአገሪቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ይበልጥ ተግባራዊ የሆነው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቃል ኪዳን ያደረጉበት ሕገመንግሥት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ መሆኑን በመዘንጋት እንዳልሆነም ልብ ይሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ  የጋራ ጥቅሙና መብቱ በሕግ የበላይነት ሥር እንዲከበርለት ያስቻለው ህገ መንግስት ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም ሰፊና ጥልቅ እንዲሆን ማድረጉ የመጀመሪያውና የጋራ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ቁልፍ ነጥብ ነው፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ጎልቶ ሊታይና ሊደመጥ የሚገባው ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ ህዝቡ ያላንዳች ልዩነት ቋንቋዎቹ፣ ባህሎቹ፣ ሃይማኖቶቹ፣ አመለካከቶቹና የመሳሰሉት መብቶቹና ነፃነቶቹ የተከበሩለት መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡ የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ በህገመንግስቱ በተወሳው አግባብ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያላንዳች ልዩነት እንዲራመዱ ፅኑ እምነት መያዙም በተመሳሳይ።

ይህች ሃገር ሰብእዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩባት፣ የዴሞከራሲ ባህልና ተቋሞች የሚያብቡባት፣ ህዝቡ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ህይወት የነቃ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥበት ሃገር በመሆን ላይ ስለመገኘቷ መነሻና መድረሻው ህገ-መንግስታዊ ስርአቱ ነው። በህዝቦች መብት መከበር፣ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ አንድነት የሚጎለብትበት፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ስርአት ለመፍጠር የሚያስችል ስርአት ተገንብቷል።

ይህ በሆነበት አግባብ ከዚህ ቀደም በነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት የተፈጠሩ ቅሬታዎችን እያቀነቀኑ ልዩነቶችን መለጠጥ ኪሳራው የበዛ መሆኑን አሁን በቅርብ አይተናል፡፡ ከህገመንግስታዊ ስርአቱ ትሩፋቶች ባሻገር ህዝቡ በዘወትራዊ ግንኙነቱ እርስ በርሱ እየተከባበረና ዕውቅና እየተሰጣጣ መኖር የቻለና ከዚያ አልፎ ተርፎ በጋብቻ ተሳስሮ በመዋለድ ተምሳሌትነትን ማሳየት የቻለ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የተዛቡ ግንኙነቶች እየታረሙ ለጠንካራ አንድነት ከመሥራት ይልቅ ልዩነትን ማቀንቀን የጸረ-ሰላም ሃይሎች ባህሪ ነው። ህገመንግስታዊ ስርአቱን በአግባቡ የተረዳ እና የተገነዘበ ህብረተሰብ ደግሞ እነዚህ ጸረ ሰላም የጥፋት ኃይሎች በየወቅቱ የሚይዟቸውን ድብቅ አጀንዳዎች በቀላሉ ተረድቶ ስርአቱን ሊከላከል እና ከገዛ ጥቅሙ ጋር እንዳይጋጭ ያስችለዋል።

በህገመንግሥቱ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም ሀብት የማፍራት መብት ያለው መሆኑን ጠንቅቆ መገንዘብ የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ አስቀድሞ ለማጨንገፍ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ በህገ-መንግሥቱ ዋስትና ያገኘ መብት በፍፁም ሊጣስ እንደማይችል፤ የማይችልበትም ምክንያት ህገመንግሥቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በመሆኑ መሆኑንም ጭምር በተመሳሳይ፡፡

የግለሰብ ወይም የቡድን መብቶችም በእኩልነት እንዲከበሩ ህገመንግሥቱ ዋስትና መስጠቱን፤ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖርና መብቶችም በዝርዝርና በጥልቀት ዋስትና ያገኙት በህገመንግሥቱ መሆኑን፤ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ሊኖር የሚችለውም የፌዴራል ሥርዓቱ የጀርባ አጥንት የሆነው ህገመንግሥት ሲከበርና ከስጋት በጸዳ አግባብ ሲጠበቅ መሆኑን፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሞላ ጎደል በጋራ ጥቅሞቹና ዕድሎቹ ላይ በሕግ የበላይነትና በራሱ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ የሚደርሰውና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥረው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን በጥልቀት መረዳት የጥፋት ሃይሎችን ማናቸውንም አይነት ከስርአቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ አጀንዳዎች አስቀድሞ ለማጨንገፍ ያስችላል፡፡

የኢትዮጵ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር በመሆንዋ፣ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው ማመናቸው አያስደንቅም። ዋናው እና ቀሪው ነገር መጪው የጋራ ዕድላቸው የሚወሰነው ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ አለመዘናጋት ነው የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ አስቀድሞ ለማጨንገፍ የሚያስችለው፡፡  

በፌዴራል ሥርዓቱም ሆነ በሕገመንግሥቱ ላይ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ቢኖሩ እንኳ፣ በህጋዊ አግባብ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ስርአት መገንባቱን መረዳትም ሌላኛውና የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ የሚያሳጣ ነጥብ ነው ፡፡

የማንነት ጥያቄዎችም ሆኑ የመብት ጥያቄዎች ሲነሱ  በዴሞክራሲያዊ  ሂደት የሚፈቱባቸው ህገመንግስታዊ አካሄዶችን መዘርጋቱን፤ በማንነት ስም የሚቀነቀን ጠባብነትንም ሆነ ትምክህትን አለማስተናግዱ፤ በመፈቃቀርና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት መገንባቱ፤ ይልቁንም ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ልዩ ጥበቃ የሚያደርግ፤ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን የሚያስችል፤ ኢፍትሐዊና ሕገወጥ ድርጊቶችን ማስወገድ የሚችል፤ ምግባረ ብልሹዎችና አምባገነኖች ቦታ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ወዘተ ህገመንግስታዊ ስርአት መዘርጋቱን  እና ይህንኑም በጥልቀት መገንዘብ ከብዙ በጥቂቱ የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ አስቀድሞ ለማጨንገፍ የሚያስችልና ምናልባትም አጀንዳ የሚያሳጣቸው ይሆናል፡፡