በገለልተኝነት መርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን የምትከተል ሀገር

                                                         
ከመሰንበቻው አንዳንድ ፅንፈኛ ኃይሎች    የደቡብ ሱዳን መንግስት ተቃዋሚ የሆኑት ዶክተር ሪክ ማቻር በኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ እንደነበራቸው በማስመሰል አሉባልታዎችን ሲያናፍሱ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የኢፌዴሪ መንግስት ከአንድ ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር በተናጠል የሚያደርገው ምንም ዓይነት አሰራር የለውም። የሚከተለው የገለልተኝነት መርህም ይህን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም። 
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲካሂደው የነበረው ግንኙነት ከሀገርና ከህዝቦቿ ተጠቃሚነት እንዲሁም እነርሱን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንጂ ከግለሰቦች ጋር አይደለም። ከዚህ የመንግስት አሰራር አኳያ የዶክተር ማቻርን “ኢትዮፕያ ውስጥ የነበራቸው ቢሮ ተዘጋ” ትረካ ከልቦለዳዊ ድርሰት ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም።  ምክንያቱም ሀገራችን ከጎረቤቶቿ ጋር ስታካሂድ የነበረችው ግንኙነት በፅንፈኛ ሃይሎች አማካኝነት የቀረበውን ሰንካለ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ስላልሆነ ነው። 
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት ከጎረቤቶቹ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ግለሰቦችን ማዕከል ያደረገ አይደለም—ጎረቤት ሀገርንና የዚያን ሀገር ህዝቦች ባማካለ መንገድ በመደጋገፍና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥን እንጂ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ላለፉት 25 ዓመታት በከባቢው ያከናወነቻቸው የዲፕሎማሲ ተግባራት ለየትኛውም ወገን ያልወገነና በገለልተኝነት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህም በምሳሌነት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው ረጅም ውጊያ እንዲያበቃ ሀገራችን በተዓማኒነት ያከናወነቻቸውን ተግባራት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።
ሁላችንም እንደምንገነዘበው በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናው ያንዣበበው ከባድ የጦርነት አደጋ የሁለቱንም ሱዳን ህዝቦች የሰላም ተስፋ ያሟጠጠ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን በሱዳን ጉዳይ ያን ያህል እምነት እንዳያሳድር ምክንያት ሆኖት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ይመስለኛል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሁለቱን ሱዳኖች ሰቆቃ ያጠላበት ረጅም ጦርነት እንዲቆም ብርቱ ጥረት ማድረጉ የሚዘነጋ አይደለም—ለየትኛውም ወገን ሳይወግን። ይህ የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራትንና ህዝቦችን ማዕከል ያደረገ መርህ ለግለሰቦች ፈቃድ ሲባል መቼም ቢሆን ሊንጋደድ የሚችልበት ምክንያት የለም።
እርግጥ መንግስት ይህን የሚያደርገው የጎረቤቶቹን ሉዓላዊነት ከማክበርና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ መሆኑ ከማንም የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። አዎ! የደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሚናው የጎላ ሀገራችን በፅኑ ታምናለች። እርግጥ የደቡብ ሱዳን ሰላም ለሀገራችን ሰላምና ልማት የሚኖረው አስተዋጽኦ በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ቢያንስ በጎረቤት ሀገራት አካባቢ ያለው የሰላም እጦት ቢያንስ የድንበሮቻችን አካባቢዎችን የስጋት ቀጣና ሊያደርጋቸው ስለሚችል ነው። 
ይህ ደግሞ ፍልሰት እንዲኖርና ስደተኞች እንዲበራከቱ ማድረጉ አይቀሬ ነው። እናም ደቡብ ሱዳን ሰላም ሆነች ማለት እነዚህ አካባቢዎች ከስጋት ነፃ የሚሆኑበት ዕድል ይፈጠራል እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታም የልማት ስራዎችን ያለ አንዳች እክል እንድንፈፅም ዕድል ይሰጠናል። ከዚህ ጎን ለጎንም የህዝብ ለህዝብ ግንኘኩነቱም ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ያግዛል። በተለይም ከሀገሪቱ ጋር በሰላም ጉዳይ በጋራ ለመስራት የሚያስችለን አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ የምትከተለው ጎረቤት ሀገርን የሚያከብርና በሉዓላዊነታቸው ጣልቃ ባለመግባት የጋራ ጥቅምን መርህ የመከተል አካሄድ የሚመነጨውም ከዚህ ዕውነታ መነሻ ይመስለኛል። 
እንደ እውነቱ ከሆነ የማንኛውም ጎረቤት ሀገር ሰላም የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት ይጥላል። ከዚህ አኳያ ደቡብ ሱዳን ከእኛ ጋር በንግድና በኢንቨስትመንት ብሎም በህዝብ ለህዘብ ግንኙነት ልትተሳሰራቸው የሚያስችሉ ሰፊ አማራጮች ያሉ መሆናቸው እውነት ነው። ከዚህ አኳያ የደቡብ ሱዳን የሰላም እጦት ጠንካራ የሆነ የልማት ትስስር እንዳይፈጠር የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት ሊሆን አይችልም። ለአብነት ያህልም ያቺ ሀገር መረጋጋት ባለመቻሏ ምክንያት ዜጎቿ የሆኑት የሙርሌ ጎሳ አባላት የሀገራችንን ድንበር ተሻግረው ህፃናትንና ከብቶችን መውሰዳቸውን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሁኔታም በአንድ ጎረቤት ሀገር ውስጥ የሚከሰተው የሰላም እጦት ምን ያህል ጎረቤቱን ሊጎዳ እንደሚችል ሁነኛ ማሳያ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ዶክተር ሪክ ማቻር “ቢሮ አላቸው” ተብሎ በፅንፈኛ ሃይሎች አማካኝነት ከተነገረው ትረካ ጋር በተያያዘ፤ ገና ከጥንስሱ ሀገራችን የደቡብ ሱዳን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲወሰን በገለልተኝነት ብርቱ ጥረት መድረጓ ግለሰቦችን በማሰብ አለመሆኑ ግልፅ ይመስለኛል። ደቡብ ሱዳን በህዝብ ውሳኔ ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን የበቃችበትን ዕድል እንድታገኝ የአንባሳውን ድርሻ የተጫወተችው ኢትዮጵያ፤ ግለሰቦችን ባማከለ አሊያም ተቃዋሚና ገዥ ፓርቲዎችን ከመደገፍና ከመጥላት አኳያ ተሰልቶ የሚደረግ አይመስለኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳንና ለህዝቦቿ መፃዒ ብሩህ ህይወት ብሎም ለጋራ ተጠቃሚነት በማሰብ የምታከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት ከግለሰቦችና ከፓርቲዎች ፍላጎት የነፃ ስለሆነ ነው። 
ያም ሆኖ ግን ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገርነቷን ካወጀች ካለፈው በጣት የሚቆጠር ዓመት ወዲህም ቢሆንም በቀጣናው የተጠበቀው ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር አልቻለም። በአዲሲቷ ሀገር ውስጥ አዲስ የጦርነት አደጋ ሊያንዣንብብና የቀጣናው ሰላምም ለዳግመኛ ችግር ሊጋለጥ ችሏል። ይህን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውታለች። በቀድሞው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን የተመራው አደራዳሪ ቡድንም ለየትኛውም የደቡብ ሱዳን ሃይል ባልወገነ መልኩ በገለልተኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም የማድረግ ስራዎችን በብቃት አከናውኗል።
በኢጋድ አማካኝነትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጁባ ድረስ በመመላለስ ሁለቱ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ችግራቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም ኋላ ላይ “ኢጋድ ፕላስ” በተሰኘው ቡድን አማካኝነት በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና በዶክተር ሪክ ማቻር አማካኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ምክንያት ሆኗል። ይህም ቀየውን ለቆ ለተሰደደው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ታላቅ እፎይታን ከማስገኘት ባሻገር፤ ያቺ ሀገር እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናዋ እንዲያንሰራራ አድርጓል።
ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከጦርነት እንዲላቀቅና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ብሎም በአዲስ ሀገርነት በመንግስታቱ ድርጅት ባህር መዝገብ ላይ ስሟ የሰፈረው ጎረቤታችን ከሰላም የሚገኘውን ማናቸውንም ሀገራዊና ቀጣናዊ ትስስሮችን በሚፈለገው መጠን አሟጣ እንድትጠቀም ኢትዮጵያ ብዙ ደክማለች። ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ሰላም አስከባሪ ኃይሏን በዚያች ሀገር እንድታሰማራ ለቀረበላት ጥያቄም በጎ ምላሽ በመስጠት የጎረቤቷን ሰላም ለመታደግ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች። ይህ የዲፕሎማሲ ሂደቷም በምንም ዓይነት መንገድ ግለሰቦችን ከማገዝ ጋር ሊገናኝ አይችልም። እናም በየትኛውም መስፈርት “ኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸው ቢሮ ተዘጋ” በሚል በፅንፈኛ ሃይሎች የተናፈሰው አሉባልታ መሰረት ያለው ሊሆን አይችልም።
ይህን ዕውነታ ሀገራችን ከምትከተለው የገለልተኝነት መርህ አኳያ በማስረጃ አስደግፎ ለመመልከትም የሚቻል ይመስለኛል። እንደሚታወቀው በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል እስካሁን ድረስ ቁርጡ ያልለየለት የአብዬ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ አለ። የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያስታውሰው የደቡብ ሱዳንን ህዝብ ውሳኔን ተከትሎ የሱዳንና የደቡቡ ሱዳን መንግስታት የነዳጅ ሃብት ባለቤት የሆነችውን አብዬ  ግዛትን አስመልክቶ መግባባት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። በዚህም ሳቢያ በግዛቲቱ ውስጥ ግጭት በመቀስቀሱ የሰው ህይወት  ሊጠፋ ችሏል። የአካባቢው ነዋሪም ቀዬውን ጥሎ ተሰድዷል። ንብረትም ወድሟል።  
ታዲያ ይህን ሁኔታ የተገነዘበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአካባቢው ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት 15ቱ አባል ሀገራትም በመጀመሪያው ዙር 4200 የኢትዮጵያ ሠራዊት በአብዬ ተሰማርቶ የህዝቦችን ሰላም በብቸኝነት እንዲጠብቅ ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ  ውሳኔ አሳልፈዋል። 
ታዲያ እዚህ ላይ አስገራሚው ጉዳይ ሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ያለ አንዳች ልዩነት ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሁንታ መስጠታቸው ብቻ አይመስለኝም። የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ሱዳኖችም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአብዬ ግዛት ብቸኛው የሰላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ እንዲሰማራ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መግለጻቸውን ሁኔታውን የተለየ የሚያደርገው ይመስለኛል። 
እርግጥ እዚህ ላይ አንድ ማንም የማይክደው ዕውነታ አለ። እርሱም ሁሉም አካላት በኢትዮጵያ ላይ እምነታቸውን የጣሉት የመንግሥታችን ሰላም ወዳድነት፣ የሚመራባቸው የሰላም ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የሚያከናውናቸው ተግባራት ለማንም ያልወገኑና በገለልተኝነት መርህ የሚመራ መሆናቸውን በማወቃቸው ነው። እንዲህ ዓይነት ዓመኔታ ያተረፈን ገለልተኛ መንግስት ሆን ብሎ ጥላሸት ለመቀባት ሲባል “ለዶክተር ሪክ ማቻር የተሰጠው ቢሮ ተዘጋ” ብሎ ልቦለዳዊ ትረካ ማቅረብ ተራኪውን ወገን ኢ-ተዐማኒ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። 
በዚህ ዓይነት መንገድ ዲፕሎማሲውን የሚመራ መንግስት ደግሞ ለሀገራት የሚያደርገው ማናቸውም ድጋፍ በግለሰቦች ላይ ተንጠልጥሎ ከመርህ ውጪ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው። እናም በፅንፈኛ ሃይሎች የቀረበውና “ዶክተር ሪክ ማቻር ኢትዮጵያ የነበራቸው ቢሮ ተዘጋ” የሚለው አሉባልታ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉት መሆኑ ሊዘነጋ የሚገባው አይመስለኝም—የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገርና ለህዝቦች የጋራ ጥቅም እንጂ፤ ከገለልተኝነት መርሁ ወጥቶ ለጎረቤት ሀገር ተቃዋሚ ሲል የሚያከናውነው ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ መስመርን ሊከተል አይችልምና።    

 

ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ባካሄደቻቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች ሀገራችን ለሱዳን ህዝቦች እውነተኛ አጋር እንደሆነች የሁለቱም ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች ህያው ምስክሮች ይመስሉኛል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም በሃቀኝነት የቆመችና ከየትኛውም ወገን ያልወገነች ገለልተኛ ሀገር እንደሆነች በተግባር ከማረጋገጡም ባሻገር፤ ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት የግጭት ቀጣና በሆነችው አብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪ ሰራዊቷን እንድታሰማራ እስከመወትወት ደርሷል፡፡