የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መነሳት የጀመረባቸውን ዓመታት ወደኋላ ትተን ስለጥልቁ ተሃድሶ ግምገማችን የሁለተኛውን ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መነሻ ብናደርግ መነሻው ላይ ከነበረን የቅርብ ጊዜ መረጃ አኳያ ተመራጭ ይሆናል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ ላይ በተካሄዱ ውይይቶች ወቅት ከሞላ ጐደል በአብዛኛዎቹ መድረኮች የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በጣም ያወያየ፣ ችግሩ ለዕቅዱ መሳካት እንቅፋት ይሆናል ተብሎ በስጋት መልክም የቀረበ፣ ለመንግስትም እውነት ትፈታዋለህ ወይ? የተባለው እና በብዙ መልኩ በሚገለጽ አግባብ ጐልቶ የወጣው ጥያቄ መሆኑ የሚታወቅና ይልቁንም የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ የመሆን ደረጃ ላይ በመድረሱ ዘመቻም ያስፈልገዋል ሲል ከፍተኛ አመራሩ ሲትከነከን መመልከታችን የሚታወቅና የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው ፡፡
ስለሆነም፤ በችግሩ መኖር ላይ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም፡፡ አመራሩ የችግሩን መኖር ያውቀዋል ወይ? ከተባለም ይህም የሚያጠያይቅ አያጠያይቅም፡፡ አመራሩ የችግሩን ስፋት፣ ጥልቀት፣ አንገብጋቢነት፣ አደጋውን በደንብ ተገንዝቧል ወይ? ከተባለ ግን ይኸን በዝርዝር ማየት የሚጠይቅ የመሆኑ እውነታ የጥልቅ ተሃድሶው መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
በከተሞች አካባቢ ከመሬት ጋር ተያይዞ አመራሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን አውቆ፣ በሱፐርቪዥንም አረጋግጦ ሲያበቃ፣ ህዝቡም በየመድረኩ ነግሮት ሲያበቃ ከወር ወር፣ ከዓመት ዓመት ችግሮቹ በተሟላ መልኩ የማይፈታበት ምክንያትና መንስኤም ከቀርፋፋው የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተደምሮ ለተሃድሶው መነሻ ከሚሆኑ ምክንያቶች መካከልም እንደሚገኝበት ለመገመት የፖለቲካ ሰው መሆንንም አይጠይቅም፡፡
ይህን ለመገመት ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያደረገውን ጥናትና ለህዝብ ይፋ ያደረገውን መረጃን ማስታወስ በቂ ነው። እነዚህ ተቋማት በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አበባ ባደረጉት ጥናት መሬት ነክ የሆነው ኪራይ ሰባሳቢነት አንዱና ግንባር ቀደሙ መሆኑ ተመልክቷል።
ከላይ በተመለከተው አግባብ ከሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ጋር ተያይዞ በሁሉም መድረኮች በተደረጉ ውይይቶች ሙስና ስለመንሰራፋቱ፤ ጉቦ መስጠትና መቀበልም የቀልድ ያህልና የማያሸማቅቅ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ፤ ያለጉቦ የሚሰራ ስራ እንደሌለ፤ እንዲያውም ጉቦ መብላት ስራ ሆኗል በሚል መገለጹ ይታወሳል፡፡ የፖሊሲ ጥናት ማእከል ያዋቀረው የጥናት ቡድንም በተመለከታቸው የተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች (በተለይም በገቢዎችና ጉሙሩክ፣ በመሬት አስተዳደርና የፍትህ ተቋማት) የዳሰሳ ሪፖርት ኪራይ ሰብሳቢነት በስፋት እንዳለ ማመላከታቸው ይታወቃል፡፡
ማእከሉ አጠናሁ ሲል በቱባ ባለስልጣናቱ ፊት ይፋ ካደረገው እና ህዝቡ ከተመለከተው እንደማሳያነት የመሬት አስተዳደር ዘርፍን ስናይ፦ በእያንዳንዱ የሊዝ ጨረታ አስቀድሞ ለጨረታ የሚወጡ ቁራሽ መሬቶች በችካል ተለይተው ወደ ጨረታ እንደማይቀርቡ፤ ለድርድር በሚመች መንገድ በጅምላ ለጨረታ ይቀርቡና ገንዘብ ለሚሰጡ አካላት የተመቹና የሚመርጧቸው ቦዎታች እንደሚሰጡ፣ በግዥ የተገኘ ቤት ነባር ይዞታ እንደነበረ አስመስሎ ሰነድ አመቻችቶ መስጠት፣ የአያት ስም ያልተጻፈበት በዝርዝሩ ሲገኝ ተመሳሳይ ስም ፈልጎ መሙላት፣ ነባር ይዞታ በማጥራት ላይ ቤት ያልነበረውን ባዶ መሬት ህንፃ ወይም ግንባታ ያለበት አስመስሎ ካርታ መስጠት፣ በመመሪያ የታገደን በመጣስ ትርፍ መሬት ማካተት፤ ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር የሚጋጭ ፕላን ይዘው ለመጡ ማጽደቅ፣ ህንፃ ያላረፈበት ባዶ መሬት ህንፃ እንዳለው አስመስሎ እንዲሸጥ ማድረግ፣ ከሻጭና ከገዥ ጋር በመመሳጠር በዝቅተኛ ዋጋ እንደተሸጠ አድርጎ ውል ማጽደቅ፣ ፋይሎችን ሆን ብሎ መደበቅ እና ሳይት ፕላን አዘጋጅቶ ለፕላን ማሰሪያ እና መደራደሪያ ማቅረብ፣ የጨረታው መመሪያ በሚያዘው መሰረት ሁሉንም መረጃዎች ሳያካትቱ ጨረታ ማውጣት፣ ወደ ጨረታ የሚወጣ መሬት ከይገባኛል ጥያቄ ነፃ ሳይሆን በችኮላ ማውጣት፣ ከጨረታ በኋላ ከህግና አሰራር ውጭ ተመሳሳይ ስም በማለት ተለዋጭ መሬት መስጠት፤ በዚህም የተነሳ ድሃው እየተጉላላ ስለመሆኑና ተስፋ ወደመቁረጥ መሄዱን የተመለከቱ እና ለነዚህም ችግሮች ግንባር ቀደም ተዋናዩ አመራሩ መሆኑን የተመለከተው የጥናት ውጤት ስለጥልቅ ተሃድሶው ግምገማችን ሁነኛ ማጠየቂያ የሚሆነን መረጃና ማስረጃ ይሆናል።
አዲስ አበባ ላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ የፖሊሲ ማእከሉ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው አመራሩ የቁርጠኝነት ችግር እንዳለበት ነው። ከዚያም በላይ፤ በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የተዘፈቀ እንደሆነ፤ ይልቁንም የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ ግንባታን እንዳላወቀ ማለፍ፤ በጥቅም ትስስር ምክንያት በህዝቡ የሚነሱ እሮሮዎችን ቸል ማለት፤ ሕዝብን ማስለቀስ፤ ማመናጨቅ፤ ማሸማቀቅ፤ ከሰራተኞች ጋር ተግባብቶ አለመስራት፤ አድሎአዊነት (የአንዱን የህገ-ወጥ ግንባታ አፍርሶ የሌላውን መተው) በሰፊው እንደሚስተዋል የጥናት ውይይት ተሳታፊዎች በምሬት መናገራቸውን ጠቅሶ ይፋ የተደረገልን መረጃ ያመለክታል፡፡
እነዚህን የገዘፉ ችግሮች የተሸከመችው አገራችን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በልማት ጎዳና መወንጨፏ የሚያሳስባቸው እና የፖለቲካ ጥማታቸው ከአናታቸው ላይ ወጥቶ የሚያሰቃያቸው ጸረ ሰላም ሃይሎች ከላይ በተመለከቱት ችግሮች መነሾ ኢፍትሃዊ በሆነ የሃብት ክፍፍልና በስራ አጥነት የሚንገላታውን ዜጋ ስሜት አጡዘው ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስካበቃን ጥፋት ያደረሱን መሆኑም ከላይ ከተመለከቱት ጋራ ተደምሮ ከገዢው ፓርቲ ጀምሮ መንግስትና ህዝቡ ድረስ ለዘለቀ ጥልቅ ተሃድሶ ቢያበቃን ተገቢና ትክክል ይሆናል።
የዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ጅምርና በእርግጥም የመንግስትንና የገዢውን ፓርቲ ህዝባዊ ውግንና አመላክቶ ያለፈውን ሂደት እዚህ ላይ ማስታወስ ከሞላ ጎደል እየተጠቃለለ የሚመስለውን ጥልቅ ተሃድሶ ለማሄስ ጠቃሚና አስፈላጊ ይሆናል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 10-15/2008 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በመገምገም በአንድ በኩል በእስካሁኑ ትግል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የተመለከተ መግለጫ ማውጣቱ የጥልቅ ተሃድሶው መንደርደሪያ ነበር፡፡
በዚህ ግምገማ ስለተገለጸ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭም መላው ህዝብ አገራችን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች በመሆኑ ላይ ልዩነት ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚህ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው ተከብረዋል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት ተነጣጥለዋል፡፡ የዜጎችና የመላ ህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው ግምገማ መሰረት በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስትን ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ስለማረጋገጡ ማውሳቱም ይታወሳል።
የዚህ ግምገማ መቋጫም የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴና እንደገና የመታደስ ጥረት ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ መላ የአገራችን ህዝቦች ሰላማዊና ህጋዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በቀረበ ጥሪ የነበረ መሆኑም ይታወሳል ፡፡
በዚህ ጥሪ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ ወስኖ የነበረው ህዝብ ዛሬም አለመሳተፉን እየተናገረ ባለበት ሁኔታ ጥልቁ ተሃድሶ በማጠቃለያው ዋዜማ ላይ የደረሰ ይመስላል። እናም ይህ ጥድፊያና የሽፍንፍን ጉዞ ጥልቁ ተሃድሶ በራሱ ተሃድሶ የሚያሻው መሆኑን አመላካች ነው። ምክንያቱም፤ ከላይ በተመለከተው አግባብ የችግሮቹ ሁሉ ቁንጮ አመራሩ ነው ተብሎ ሲያበቃ ጥቂት የታችኛውን አመራር እና ፈጻሚ ሰለባ ባደረገ እርምጃ ብቻ ዝም ጭጭ መባሉም ሌላኛው ጥልቁ ተሃድሶ እራሱ ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ጠቋሚ ነው። በየትኛውም መመዘኛ ለየመዋቅሩ በልምድ ብቃትና በዲሲፒሊን የታነጸ አመራር መመደብ ተገቢ መሆኑ ባያጠያይቅም፤ በግምገማ የወረደው አካል የመውረዱ ምክንያት አለመገለጹም፤ የህዝቡን ስለወደፊቱ ተሳትፎው የሚያሸፍተው የመሆኑ እውነታም ሌላኛው የጥልቁ ተሃድሶ ተሃድሶ ምክንያት ይሆናል። ስለዚህ፤ መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ ከላይ የተመለከቱ የጥናትና የግምገማ ውጤቶችን ይፋ ሲያደርጉ ስላጠኑት እና ስለገመገሙ ብቻ ሳይሆን፤ የህዝብ አካል እንደመሆናቸው በህዝብ ውስጥ ያለውን መብሰክሰክ ስለሚያውቁትም ጭምር ሆኖ ሳለ፤ በዚህ መልኩ ወደመቋጫው ላይ መድረሳቸው አነሰም በዛ፤ አረረም መረረ በጥልቅ ተሃድሶው አግባብ እርምጃ በተወሰደባቸው አመራሮችና ፈጻሚዎች ተነቃቅቶ የነበረውን ህዝብ ተስፋ ቆራጭ የሚያደርግ የመሆኑን እውነታ ታሳቢ ያደረገ የጥልቅ ተሃድሶ ተሃድሶ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። ከላይ በተመለከተው የግምገማ ውጤትና ጥናት መሰረት በውሸት ሪፖርቶች ጉድ በመሰራቱ የተቆጨ መንግስት፤ በህዝብ ስም ካድሬዎች የሞሉበትን የጥልቅ ተሃድሶ የመድረክ ውጤቶች ተቀብሎ ለመጓዝ መሞከርም የሚያስከፍለው ዋጋ በሌላ ዙር ተሃድሶም የማያሽር መሆኑ ታውቆ ጥልቁን ተሃድሶ ማደስ ተገቢና ወቅታዊ ሊሆን ይገባዋል። ከላይ የተመለከቱት እና ለመሸከም የሚከብዱ መሰል አገራዊ ውድመቶች ያለከፍተኛው አመራር የረዘሙ እጆች እንደማይፈጸሙ መንግስት ይፋ ካደረገው በላይ፤ ይልቁንም መንግስት እራሱ በፈጠረው ጠያቂ ህዝብ ዘንድ መታወቃቸው በሚታወቅበት አውድ ውስጥ ተሁኖ በጥቂት የታችኛው አመራሮችና ፈጻሚዎች (ለያውም ስማቸው እንኳ ይፋ ባልተደረጉ ግለሰቦች ) በተወሰደ እርምጃ ጥልቁን ተሃድሶ ለመቋጨት ማኮብኮብ ቀልድና “አለባብሰው ቢያርሱ…” አይነት ይሆናል። ውጤቱም በአረሙ ለመመለስ የማያስችል መሆኑ ታውቆ ጥልቁን ተሃድሶ ከወዲሁ ማደስ ተገቢ ይሆናል። ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር በሚገኙ በርካታ ትሩፋቶች ህዝባዊነቱ ከተረጋገጠለት መንግስትም የሚጠበቅ ነው።