ፓርኮች፤ ከመዝናኛ ወደ ኢንዱስትሪ!

 

 

የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት  ስትራቴጂው መነሻ እንደ አገራችን ባሉ ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮች ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በመናድ በምትኩ የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ነው። የተቀየሰው ስትራቴጂ በአገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችልና ህዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆን እንዳለበት ታምኖ ተግባራዊ ተደርጓል። ከዚህም ባለፈ በከተሞች ለዴሞክራሲ ማበብ የሚበጅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ የሚፈጥር መሆን ያለበት መሆኑን በማመን ባለፉት 25 ዓመታት ርብርብ ተደርጓል። ይህ ርብርብ ደግሞ ለዘመናት ፓርክ ሲባል ከመዝናኛ ቦታዎች የዘለለ እውቀት ያልነበረንን ዜጎችና አገር ወደአዲስ አይነትና ኪስን ከማራገፍ ኪስን ወደሚሞሉ ፓርኮች ለመውሰድ አስችሏል። ይህ ተረክም የኢንዱስትራላይዜሽን ደረጃችን የት ላይ እንዳለ የሚፈትሽና ለከተሞቻችን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚኖረውንም ፋይዳ የሚመለከት ነው።

በበርካታ የምጣኔ ሃብት ምሁራን አስተያየት መሰረት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ውድድር ላይ የመግዛት እንጂ የመሸጥ ተሳትፎዋ እጅግ አነስተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የማኑፈክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ሚና አነስተኛ  ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ልሂቃኑ ይጠቅሳሉ ። ዘርፉ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ፤ የቴክኖሎጂ አቅም ስለሚሻ እና ጠንካራ የማኔጅመንት ክህሎትንም ስለሚያስፈልገው አልሚ ባለሃብቶች እንዳይሳተፉ ካደረጓቸው ምክንያቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱቱ ናቸው። ስለሆነም የባለሃብቶቻችን ትኩረት ትንሽ ጉልበትና ወጪ በሚጠይቁት ላይ፤ይልቁንም ኢምንት ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል በሚፈጥሩ የመዝናኛ እና የሆቴል አገልግሎት ስራ ላይ ተንጠልጥሎ ለዘመናት ዘልቋል።

ኢንቨስተሮች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል ዋናዎቹ የመሬት እና የባንክ ብድር ሲሆኑ፤ ሌላው እና ግዙፉ ፈተና ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደነበር ይታወቃል ። በተለይ መሬት ለማግኘት ስለኪራይ ሰብሳቢነት ያለው ውጣ ውረድ አሰልቺ መሆኑም የአደባባይ ሃቅ ሆኖ ዓመታትን ማስቆጠሩም ይታወቃል ።

ከዚህ ዓይነቱ ውስብስብና ድካም በኋላ መሬቱ ሲገኝም ህንጻውን ለመገንባት ደግሞ ሌላና ከፋይናንስ ጋር ተያያዥ የሆነው ፈተናም የአልሚውን ወኔ የሚሰልብ መሆኑም እዚያው ውጣ ውረዱ አነስተኛ በሆነው እና ፋይዳውም ከባለሃብቱ በማያልፈው የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ ተንጠልጥሎ አመታት ቢገፋ የሚገርም አይሆንም። እኒህን በመሰሉ በርካታ ችግሮች የተተበተበው ይህ ዘርፍ የቢሮክራሲው ሂደት ሲታከልበት በእርግጥም አልሚውን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑ አያጠያይቅም። አሁን ግን፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ምንጭ በሆነው ፖሊሲ የተመራው መንግስት ይህን ቁስል የሚያሽር መፍትሄ አበጅቷል፤ ይልቁንም የደረስንበትን እና የምንደርስበትን አመላካች በሆኑ ፓርኮቹ ጉዳዩን ወደሌላ ምእራፍ እየቀየረው ነው ። ከእነዚህና አዲሱን ምእራፍ አመላካች ከሆኑት ማረጋገጫዎች የመጀመሪያን መለኪያ ሰሞነኛ ከመሆኑ አንጻር ከወደድሬዳዋ ሄደን እንመልከት፤

 በድሬዳዋ አስተዳደር ስትራቴጂውን መነሻ ያደረገ የኢንዱስትሪ መንደር እየተገነባ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከዚህ መንደር ታዲያ በ47 ሚሊዮን ብር የተገነባው የፋብሪካ እቃዎች መለዋወጫ ማምረቻ ተቋም ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በአስተዳደሩና በመከላከያ ብረታ ብረትና  ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ትብብር የተገነባው ይህ ተቋም በ2007 ዓ.ም የተጀመረና በቅርቡ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ተቋሙ ከእህል ወፍጮ እስከከፍተኛ ፋብሪካ መለዋወጫዎችን በማምረት ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረትና የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለማፋጠን አስተዋጽኦው የላቀ እንደሆነ በባለሙያዎች የተመሰከረለት ነው ።

ስራውን ለማስጀመር 50 ማሽኖችና ሌሎች ቁሳቁሶች የተዘጋጁለት ይህ ተቋም ፤ በምርት ስራው ለሚሳተፉ 60 ወጣቶች ስልጠና ሰጥቶ አጠናቅቋል፡፡ ከከተማ ልማትና ዴሞክራታይዜሽን ግንባታ ጋር ተያያዥ የሚሆነው ተሞክሮ የሚመጣውም እዚህ ላይ ነው።

የማምረት ስራውን በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ  በሚጀምረው ይህ ተቋም ወደ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶች በአክሲዮን ተደራጅተው ለማሽን ግዥ የወጣውን ወጭ ሲመልሱ ማምረቻው ወደማህበሩ  የሚዘዋወር ሲሆን፤ ለዚህም ወጣቶቹን አደራጅቶ ከባንክ ጋር የማስተሳሰሩ ስራ ተጀምሯል። ወጣቶቹ ደግሞ እስካሁን አክሲዮን ለመመስረት የሚያስችላቸውን 50 ሺህ ብር ቆጥበዋል፡፡ የሃዋሳውን ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃና ሥራ መጀመር እዚህ ላይ ያስታውሷል።

 

የሃዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ሃያ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት አምራች ፋብሪካዎችን የያዘ ሲሆን፤ 1.3 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ እና በውስጡ ያሉት ፋብሪካዎች መጠለያዎች ብቻ በ300 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡና ግዙፍ ፓርክ መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ይህ መንደር በጠቅላላ 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶች ሲኖሩት፣ 21.5 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር፣ 16 ኪሎ ሜትር የስልክ መስመሮችና 23 ኪሎ ሜትር የንፁህ ውኃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ተዘርግተውለታል፡፡ በተጨማሪም፤ ፓርኩ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ሱቆችና የተለያዩ አገልግሎቶች ለሚሰጡ ተቋማት የሚውሉ ቢሮዎችም አሉት፡፡

 

የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአምራቾች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡ የአንድ መስኮት አገልግሎቶች የተሟሉለት ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የስልክ፣ የሎጂስቲክስ፣ የጉምሩክ፣ እንዲሁም የቪዛ አገልግሎትን ያካተተ በጥቅሉ ውጣ ውረድ ያልበዛበትና የኪራይ ሰብሳቢዎችን ቀዳዳዎች ሁሉ የሚደፍን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡

 

በዚህ መንደር በዘርፉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው 14 የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች  ለማምረት ቅድመ ዝግጅቶቻቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የ130 ዓመታት ልምድ እንዳለው የሚነገርለት የአሜሪካው ፒቪኤች ይገኝበታልና የሚገነባውን ትልቅ አገራዊ አቅም መገመት አይከብድም፡፡ መቶ ከሩብ ዓመታት ከዘለሉት ልምዶቹ  ባሻገር ፒቪኤች ካልቪን ክሌይ፣ ቶሚ ሂል ፊገርና በመሳሰሉት አልባሳት መለያዎች (ብራንዶች) መታወቁን ስለምንና እንዴትነት ማስያዎቻችን ልብ ይሏል፡፡ እንዲሁም፤ የቻይናው ውሺ ጂንማኦ፣ የህንዱ አርቪንድ የመሳሰሉትን ጨምሮ የሆንግ ኮንግ፣ የቤልጂየም፣ የሲሪላንካና የአሜሪካ ኩባንያዎች ስንቅና ትጥቃቸውን አሟልተው በመንደሩ መገኘታቸውን ከላይ ስለተመለከቱት ማሳያዎቻችን ማስታወስ ግድ ይላል ፡፡

 

በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ስድስት ሲሆኑ፣ አቅማቸውንና ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ከመንግሥት ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑም ስለአቅም ግንባታና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ፖሊሲው የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለሚሳተፉ ባለሀብቶች መንግሥት እስከ 85 በመቶ የሚደርስ የባንክ ብድር ያመቻቸ መሆኑም የደረስንበትን ደረጃና የምንሄድበትን አቅጣጫ ጨምሮ የምንደርስበትንም ከወዲሁ ለመገመት የሚያስችለን ነው። ይህ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመቀሌ እና በኮምቦልቻ ለተጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በሰአቱ መጠናቀቅ የላቀ ልምድ የተቀመረበት እንደሚሆን መገመትም አይከብድም፡፡ በተጨማሪም በ300 ሚሊዮን ዶላር ለተጀመረው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም የተሞክሮነት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡  

ፓርኮቻችን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ብቻ የታጠሩ አይደሉም ። በተለይ በስትራቴጂው ላይ ልዩ ትኩረት በተሰጠው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍም ፓርኮቻችን መዝለቃቸው የደረስንበትን ደረጃና የምንሄድበትን መንገድ አመላካች ሆነውናል።

በአግሮ ፕሮሰሲንግ  ዘርፍ በነጠላ ከሚደረግ መፍጨርጨር እየተወጣና በፓርኮች ደረጃ መፈጸም ወደሚያስችሉ አግባቦች እያመራን ለመሆኑ በርከት ያሉ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል ። ከአስረጂዎቹ ሁሉ የሚልቀውና ሚዛን የሚደፋው ደግሞ በመጪው ጥር ግንባታቸው የሚጀመረውና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር እንደሚያፋጥኑ የሚጠበቁት የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው። ፓርኮቹ የግብርና ምርት የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች ማዕከል የሚሆኑ ሲሆን፤ የፓርኮቹ ግንባታ በአማራ­-ቡሬ፣ በትግራይ-ሁመራ፣ በኦሮሚያ­-ቡሌቡላ አካባቢና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች­- በሃዋሳ አካባቢ ይካሄዳል።

የፓርኮቹ መገንባት የግብርናውን ምርት የእሴት ሰንስለት በማጠናክር በዘርፉ የተሰማሩ ባለኃብቶችንና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያፋጥን እንደሚሆን አያከራክርም። በአገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ዙሪያ ተወስኖ የነበረውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ወደ ክልሎች በማስፋትም በከተሞች ለሚከናወነው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አይከብድም ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ለመገንባት በሁሉም ክልሎች 17 የግብርና ቀጣናዎች የተለዩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ፓርኮች በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፓርኮቹ መገንባት አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ እና ኢንዱስትሪው አሁን ካለበት 15 በመቶ ወደ 28 በመቶ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው መሆኑም ነው የደረስንበትን እና የምንሄድበትን ያመላክተናል ያስባለው፤

ከዚህ ቀደም በዘርፉ የታዩ ክፍተቶች አሁን እንዳይደገሙ እና ኢንቨስትመንቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ ፓርኮቹን ወደ ልማት ለማስገባት የሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውም ነው የደረስንበትን እና የምንሄድበትን አመላካች ፓርኮች ማለታችን፤ እነዚህ ፓርኮች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሜሃንድሪ ከተባለ የህንድ አማካሪ ድርጅት ጋር በመተባበር የጥናት አዋጪነት የመለየት ሥራው ተከናውኖላቸዋል።

የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ደረጃችን በዚህ አስረጅ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሌሎች ሌሎች በርካታ ማሳያዎችንም ማንሳት ይቻላል። የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዝዋይ ከተማ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ሞጆና ዱከም የሚገኙ ስድስት የበግ፣ የፍየልና የዳልጋ ከብት ማደለቢያና ቄራዎች፤ እንዲሁም የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያዎችን ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቶ ነበር፡፡ ከተጎበኙት መካከል በህንዳውያን ባለሀብቶች የተገነባውና የአላና ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነው ዘመናዊ ቄራና የተረፈ ምርቶች ማቀነባበሪያ አንዱ ነው፡፡

አላና ፍሪጎሪፊኮ የቦራን ፉድስ ኩባንያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለ ኤክስፖርት ቄራው በቦታው ተገኝተው ለነበሩት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ይህ ኤክስፖርት ቄራ መሠረቱን ህንድ ያደረገና በዓለም ከ80 በሚበልጡ አገሮች ኤክስፖርት በማድረግ 2.2 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ኤክስፖርት ቄራ በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ግንባታውን አጠናቆ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፤›› ብለዋል፡፡

የአላና ግሩፕ በኢትዮጵያ የገነባው ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ በህንድ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግንባታውን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2015 ጥር ወር ነበር፡፡ በ75 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ኢንቨስትመንቱን የጀመረው ይኸው ኩባንያ፣ በዝዋይ አዳሚ ቱሉ አካባቢ 75 ሔክታር መሬት በመረከብ ፋብሪካውን ገንብቷል፡፡ ኤክስፖርት ቄራው በቀን 3000 ሺህ ዳልጋ ከብቶችን፣ ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ የሚደርሱ በግና ፍየሎችን ለእርድ ያውላል፡፡ ፋብሪካው ከራሱ ባሻገር የሌሎች ፋብሪካዎችን ምርቶች በመቀበል በተከላቸው የደምና የአጥንት ተረፈ ምርት ማቀነባበሪያዎች አማካይነት 80 ኩንታል አጥንት እንዲሁም 40 ኩንታል የደም ተረፈ ምርት የሚያቀነባብር ሲሆን፣ የተቀነባበሩት ተረፈ ምርቶችም ለዶሮ መኖነትና ለዓሣ ምግብነት ይውላሉ፡፡

በፋብሪካው ከተተከሉት መሣሪያዎች አንዱ ከእንስሳቱ የሚወጣውን ፈርስ በማድረቅ ለኢነርጂ ምንጭነት እንዲውል የሚያስችል ምርት የሚያስገኘው ነው፡፡ ይህም ተረፈ ምርት ለኤክስፖርት ገበያ የሚውል ነው፡፡ በአንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተሠራው ፍሳሽ ማስወገጃ በፋብሪካው ጥቅም ላይ የዋለውን ውኃ አጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባሻገር፣ ምንም ዓይነት የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠር ለመከለከል የሚያስችል  ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኢንዱስትሪውን በሚመለከት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 11 ቄራዎች ሥጋ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ቄራዎቹ ባለፈው ዓመት ኤክስፖርት ካደረጉት ምርት 102 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከዘርፉ እንዲገኝ ከታቀደው ውስጥ 70 በመቶ የተከናወነበት ነው፡፡ ዘንድሮ 157 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት የታቀደ ሲሆን፣ ባለፉት በአምስት ወራት 39.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ቀሪውን አላናን ጨምሮ ሦስት የኤክስፖርት ቄራዎች በቅርቡ ወደ ሥራ ስለሚገቡና ወደ ሳዑዲም መላክ ስለምንጀምር ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ የሚሳካ መሆኑንም ያትታል። መረጃው አያይዞም አላናን ብቻውን  ለግንባታ የሚውለውን 75 ሚሊዮን ዶላር ከራሱ ምንጮች ነው ያመጣው፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ከዶላሩ በላይ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ የሚለው አገላለጽ በሥጋ ምርት ኤክፖርት አንደኛ በሚለው የሚቀይር እንደሆነም ያረጋግጣል።ይህ ደግሞ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የደረስንበን እና የምንሄድበትን አቅጣጫ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና የፖሊሲያችንን በልካችን የመሰፋት ሚስጥራት የሚገልጥ ነው።

መንግሥት በፖሊሲው አግባብ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መሬት በሊዝ  ከማቅረብ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉም ከላይ ለተመለከቱት እና መሰል ትሩፋቶች ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ለመገመት አይከብድም፡፡

ከላይ የተመለከተው ኩባንያ 90 በመቶ የተቀነባበረና አሥር በመቶ ጥሬ ሥጋ ለ80 አገሮች እያቀረበ ነው። የግብዐት አቅርቦቱ ከአፋርና ከሶማሌ ክልል፤ እንዲሁም ከቦረና አካባቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፖሊሲው አርብቶአደሩን በምን አግባብ ከኢንቨስትመንቱ ጋር እያስተሳሰረ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው። የአገሪቱ ወቅታዊና ቁልፍ ጉዳይ ከሆነው የስራ እድል ፈጠራም ጋር ተያይዞ ኩባንያው ሁነኛ ማሳያ ይሆናል። ፋብሪካው በጊዜያዊነት 1500 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር 300 ሺሕ ሠራተኞች ይኖሩታልና፤