የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። የኢትዮጵያውያን የሁሉ ችግራቸውና ስጋታቸው ምንጭ ድህነት ነው። ድህነት የህይወትን መሰረታዊ ላጎቶች ማሟላት አለመቻል ቢሆንም፣ መዘዙ ግን ብዙ ነው። ድህነት ሰዎች ህይወታቸው ተስፋ እንዲያጡ ስለሚያደርግ የወንጀል፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የሽብርተኝነት፣ የጽንፈኝነት፣ . . . አነሳሽ ምክንያት ነው። አጠቃላይ ህዝቡ ደሃ የሆነ አገር ለውጭ ጥቃት ተጋላጭ መሆኑንም ተጨባጭ እውነት ነው። እናም ድህነትን መዋጋት በርካታ የሰውና የማህበረሰብ ጠላቶችን መዋጋት ነው። የኢፌዴሪ መንግስት ዋነኛ የአገሪቱና የህዝቡ ጠላት ድህነት መሆኑን አሳውቆ ድህነትን ለማስወገድ ዘመቻ ያወጀው ለዚህ ነው።
የኢፌዴሪ መንግስት ያወጀው የጸረ ድህነት ትግል ሂደትና ውጤቱን በአንድ የጋዜጣ ጽሁፍ ሊነሳ የሚችለውን ያህል እንመልከተው። ከዚያ ቀደም ግን ድህነት ምንድነው? የሚለውን እንመልከት። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ የዓለም ባንክ ለድህነት የሰጠውን ትርጉም እጠቅሳለሁ።
ድህነት ረሃብ ነው። ድህነት መጠለያ ማጣት ነው። ድህነት ሃኪም ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ መታመም ነው። ድህነት የትምህርት እድል ማጣትና ማንበብ መጻፍ አለመቻል ነው። ድህነት ስራ ማጣት፣ መጻኢን ግዜ መፍራት፣ ነገ አልቦ ሆኖ ዛሬን ብቻ መኖር ነው።
ድህነት ከስፍራ ስፍራ፣ ከጊዜ ወደጊዜ የሚለዋወጥና የተለያየ መገለጫ ያለው ገጸ ብዙ ነው። በአብዛኛው ድህነት በውስጡ ባሉ ሰዎች ማምለጫ የሚፈለግበት ሁኔታ ነው። እናም ድህነት ለደሃም ሆነ ለሃብታም በተመሳሳይ ሁኔታ ለድርጊት የሚቀሰቅስ ሁኔታ ነው። ዓለምን በመለወጥ ብዙዎች በቂ ምግብ፣ የተሟላ መጠለያ፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚያገኙበት፣ ከሃይል ጥቃት ነጻ የሚሆኑበት፣ በሚኖሩበት ማህበረሰብ የሆነውን የሚገልጹበት ሁኔታን ለመፍጠር ድርጊት የሚቀሰቅስ፤
የኢፌዴሪ መንግስት የድህነት መገለጫ የሆኑ ገጽታዎችን ለማቃለል የሚያስችል ድርጊት ለማከናወን ነው ጸረ ድህነት ጦርነት ያወጀው። ከድህነት ጋር ተስማምቶ መኖርን ያልመረጠውን ህዝቡን አነሳስቶ ድህነትን ለማስወገድ የቆረጠ መንግስት ነው። ይህ መንግስት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ያወጀው ስትራቴጂና ማስፈጸሚያ እቅድ አውጥቶ ለተግባራዊነቱ ሲፍጨረጨር የቆየበት ጸረ ድህነት ትግል ተጨባጭ ውጤት አሳይቷል።
85 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠር በእርሻና በከብት እርባታ ስራ የሚተዳደር ነው። ይህ አብዛኛውን የአገሪቱን ህዝብ የሚወክል ገጠሬ አርሶና አርብቶ አደር ህዝብ የግብርናን ያህል ባረጀ ኋላ ቀር ቴክኖሎጂ የሚያመርት በመሆኑ ራሱን እንኳን በወጉ መመገብ አይችልም ነበር። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ዓመቱን ሙሉ ጠግቦ መመገብ የማይችል፣ መጠለያ ለማለት በሚያስቸግር ደሳሳ የሳርና የአገዳ ጎጆ ውስጥ የሚኖር፣ የሌትና የቀን ልብስ የሌለው ነበር። ትምህርትና ህክምና ለጥቂት ከተሜዎች እድል የሰጣቸው ተድርጎ ነበር የሚወሰደው። የኢትዮጵያ አርሶ አደር አልተማረም፣ ልጆቹንም አያስተምርም፤ ሲታመም አይታከምም ቤተሰቦቹንም ማሳከም አይችልም።
የጸረ ድህነት ዘመቻው እነዚህን የድህነት መገለጫዎች ከመዋጋት ነው የተጀመረው። ጸረ ድህነት ትግሉ ገጠርንና ግብርናን መሰረት ያደረገ ግብርና መር የእድገትና ልማት ፖሊሲ በመቅረጽ ‘ሀ’ ብሎ ተጀመረ። እስከመንደሩ ድረስ በሚዘልቁ የግብርና ልማት ሰራተኞች ፈፃሚነት አርሶ አደሩ የተሻለ ዘር፣ ማዳበሪያና ተያያዥ የግብርና ቴክኖጂ እንዲጠቀም የሞያ ድጋፍ ይደረግለት ያዘ። ስራውን እንዳያሰፋ ቀይዶ የያዘውን የድህነት ኡደት እንዲሰብር የፋይናንስ አቅሙን የሚያጠናክር ስርአት ተዘረጋ። የምርት ግብአቶቹን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል፣ ምርቱንም በተገቢው ዋጋ ለገበያ እንዲያቀርብ በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጀ። አሁን በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ካፒታል ያላቸው በርካታ የህብረት ስራ ማህበራትን ያቀፉ ዩኒየኖች ተመስርተዋል።
በዚህ ሁኔታ በርካታ አርሶ አደሮች ዓመቱን ሙሉ ራሳቸውን መመገብ የሚያስችል ምርት ማምረት ጀመሩ። እየከራረመ ደግሞ ትርፍ ማምረት የሚችሉ አርሶ አደሮች ተፈጠሩ። ትርፍ የሚያመረቱት አርሶ አደሮች በየመንደራቸው ሞዴል በመሆን ሌሎች አርሶ አደሮችም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ አነሳሱ። መንግስት ትርፍ ላመረቱና ሌሎችንም ላበረታቱ ለሞዴል አርሶ አደሮች በ “ልማት አርበኝነት” እውቅና ይሰጥ ጀመረ። ይህ ሁኔታ አጠቃላይ አርሶ አደሩን አነሳሳው።
አሁን በርካታ አርሶ አደሮች ገቢያቸው በማደጉ ኑሯቸው ተሻሽሏል። በቀን ሶስቴ በወጉ ከመመገብ አልፈው የተሻለ የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤት ገንብተዋል። የአዘቦትና የክት፣ የሌሊት ልብሳቸውን አሟልተዋል። መኖሪያ ቤታቸውን ከከብት በረትና ከጪስ ቤት ለይተዋል። ድሮ ለከተሜዎች ብቻ የተተዉ ይመስሉ የነበሩትን ጫማ መጫማት፣ እንዲሁም ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ሳሙና፣ . . . የመሳሰሉ የፋብሪካ ምርት የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን መጠቀም ጀምረዋል። ሬዲዮ፣ ቴፕ ሪከርደር፣ አልጋና ፍራሽ፣ እና መሰል የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችንም መጠቀም ጀምረዋል። አሁን ደግሞ አብዛኛው አርሶ አደር የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ነው። የጸሃይ ኃይል በመጠቀም ቴሌቪዥንና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የጀመሩትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ከዚህ ያለፉም አርሶ አደሮች አሉ። በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት ያፈሩ፣ በከተሞች የሚከራዩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን የገነቡ፣ ወፍጮ ያቆሙ፣ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ካሚዮን ባለቤት የሆኑ፣ በርካቶች ናቸው። ከአርሶ አደርነት ወደኢንቨስተር ባለሃብትነት የተሻሸገሩም አሉ። ይህ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጸረ ድህነት ትግል የተገኘ ውጤት ነው። ምርታማነታቸውን አሳድገው ራሳቸውን በምግብ ያልቻሉ አርሶ አደሮች ደግሞ በልማት ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ታቅፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው ራሳቸውን ወደመቻል እየተሸጋገሩ ነው።
የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁን ልጆቹን ያስተምራል። የጤና አገልግሎት ያገኛል። ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት በአርሶ አደሩ በአቅራቢያው ተገንብተዋል። በተጨማሪም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ወደአርሶ አደሩ መንደር እየዘለቁ የጤና አጠባበቅ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በአገሪቱ የተመዘገበውን ውጤት ጠቅለል አድርገን እንመልከት። ከ1983 ዓ.ም በፊት በአገሪቱ የነበሩትን ትምህርት ቤቶችና የተማሪዎች ቁጥር ስንመለከት፤ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 4 ሺህ፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 278 ነበሩ። አጠቃላይ የተማሪዎች ቁጥርም 2 ሚሊዮን ገደማ ነበር። አሁን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 39 ሺህ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 3 ሺህ 3 መቶ ደርሷል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩት ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 27 ሚሊዮን ገደማ ነው። አሁን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ ከ96 በመቶ በላይ ሆኗል። ከ1983 ዓ.ም በፊት 16 ብቻ የነበሩት የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማት አሁን 1 ሺህ 3 መቶ ሃምሳ ደርሰዋል። ከ1983 ዓ.ም በፊት 2 ብቻ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች የፖሊስ፣ የመከላከያና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ 36 ደርሰዋል። በቅርቡ ከ10 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጤና አገልግሎት ልማት ዘርፍ ወዳለው ሁኔታ ስንመለስ፤ ከ1983 ዓ.ም በፊት 153 ብቻ የነበሩት የጤና ጣቢያዎች አሁን ከ3 ሺህ 5 መቶ በላይ ደርሰዋል። ለ25 ሺህ ህዝብ 1 የጤና ጣቢያ ለማዳረስ ተይዞ የነበረው እቅድ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል። በመላ አገሪቱ ከ16 ሺህ 2 መቶ በላይ የጤና ኬላዎች ይገኛሉ። ከ39 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች በመላው አገሪቱ ተሰማርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። በሆስፒታል ረገድ በግልና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚተዳደሩትን ሳይጨምር በ1983 ዓ.ም 72 ብቻ የነበሩት ሆስፒታሎች አሁን ቁጥራቸው ከአራት እጥፍ በላይ አድጎ 310 ደርሷል።
አጠቃላይ የአገሪቱን የድህነት ምጣኔ ስንመለከት በ1983 ዓ.ም ከ50 በመቶ በላይ የነበረውን የድህነት ወለል በታች የነበሩ ዜጎች ምጣኔ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ማብቂያ ዘመን፤ (በ2007 ዓ.ም) ወደ 22 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ ተችሏል።
አሁን ኢትዮጵያ ህዝቧን ከድህነት በማውጣት ወደብልጽግና በማሸጋጋር በ2017 ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን አልማ እየሰራች ትገኛለች። ይህ የብልጽግና ሽግግር በግብርና ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚ ወደኢንዱስትሪ መር ማሸጋጋር ይሻል። ለዚህም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ከ2008 ዓ.ም የጀመረውና አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረው 2ኛው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመተግበር ላይ ይገኛል።
ከአንድ ዓመት በፊት የተጠናቀቀው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከሞላ ጎደል ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል። አፈጻጸሙ ምን ይመስል እንደነበረ በአጭሩ እናስታውስ።
ድህነትን ከኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋትና መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ለማድረስ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በተያዘው ጎዳና ታላላቅ የልማት ግቦችን በመያዝ የተዘጋጀው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ምዕራፍ በ2007 በጀት ዓመት መጠናቀቁ ይታወቃል። በአጠቃላይ፤ ተግባራዊ ለማድረግ የተያዙ ዋና ዋና የኢኮኖሚና የልማት ግቦች አብዛኞቹን ማሳካት የተቻለበትና በአገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ታላላቅ የልማት ውጤቶች የተገኙበት እንደሆነ የዕቅዱ ትግበራ ግምገማ አመልክቷል። ሆኖም በአንዳንድ ዘርፎች በእቅዱ የተያዘው ግብ እንዳልተሳካም ይታወቃል።
በዚህም መሠረት፤ ፈጣን፣ ዘላቂና መሠረተ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ከማሳካት አንፃር በመንግስት፣ በኅብረተሰቡና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ፤ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግባራዊ በሆነባቸው ዓመታት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ 6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። በኢንዱስትሪ የ20 በመቶ፣ በአገልግሎት ዘርፍ የ10 ነጥብ 7 በመቶ አማካይ ዕድገት ተመዝግቧል። ይህ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አኳያ፤ ከአውሮፓውያኑ 2000 እሰከ 2015 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገውን የተባበሩት መንግስታት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ለማሳካት ከሚያስፈልገው የዕድገት መጠን፤ እንዲሁም በሌሎች ፈጣን ዕድገት ከተመዘገበባቸው አገራት ኢኮኖሚ አንፃር የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል።
በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በሌሎች ከተመዘገቡ የኢኮኖሚ ዕድገቶች የተለየ የሚያደርገው ልዩ መገለጫው በዕቅድ እንደተቀመጠው ፈጣን፣ ዘላቂ፣ መሠረተ-ሰፊ ያረጋገጠ ዕድገት መሆኑ ነው። በአጠቃላይ የተመዘገበው ዕድገት በዕቅዱ በመሠረታዊ አማራጭ የተያዘውን የኢኮኖሚ ግብ ያሳካ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በእርግጥ የተመዘገበው ዕድገት በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር በዕቅዱ ከሚጠበቀው ግብ አኳያ በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ አልቻለም። ይሁን እንጂ፤ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለው ድርሻ በ2003 ከነበረበት 10 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 3 በመቶ በማደጉ መጠነኛ መሻሻል አምጥቷል። በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪው ዘርፍ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ነበር። ሆኖም በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት የተለየ ትኩረት መደረግ እንዳለበት የእቅዱ አፈጻጸም ግምገማ አሳይቷል።
በዕቅዱ የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረተ ሰፊና በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት የዜጎች የገቢ አቅም እንዲሻሻልና ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግ አስችሏል። በተመዘገበው ፈጣን ዕድገት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ጨምሯል። የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 396 የአሜሪካን ዶላር ወደ 632 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል። ይህም መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን የተያዘውን ራዕይ ማሳካት እንደሚቻል ያመለክታል። በዕቅዱ የትግበራ ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለኅብረተሰቡ በርካታ የሥራ ዕድሎች ፈጥረዋል። የኅብረተሰቡንም የገቢ አቅም ማሳደግ አስችለዋል። በዚህም መሠረት፤ በ1997 ዓ.ም የድህነት ምጣኔው 38 ነጥብ 7 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በ2003 ወደ 29 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማለቱን የተደረገው በቤተሰብ ገቢና የፍጆታ ወጪ መረጃ ላይ ተመሥርቶ የተካሄደው የድህነት ዳሰሳ ጥናት አመላክቷል። ከ2004 ዓ.ም ወዲህም በተከታታይ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የድህነት ምጣኔው እንዲቀንስ ማድረግ አስችሏል። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ በተጠናቀቀበት በ2007 ዓ.ም ከድህነት ወለል በላይ ያሉ ዜጎች ምጣኔ 22 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት በተመዘገበው ዕድገት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተቸሏል። በተለይም በከተሞች ውስጥ የነበረው የሥራ አጥነት ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል። ሆኖም አሁንም ድህነቱና ሥራ አጥነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማፋጠን የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻልና በሥራ ሥምሪት ያላቸው ተሳትፎ የማጠናከሩ ጉዳይ አሁንም ቅድሚያ ትኩረት የሚያሻው ነው።
በወጪ ንግድ አፈጻጸም ረገድ፣ ከወጪ ምርቶች የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የሚያስፈልጋትን ወጪ በውጭ ምንዛሬ የመሸፈን አቅም ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። የወጪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል። በዚህም ምክንያት የኤክስፖርት ገቢ በዕቅዱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትግበራ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየት ችሎ ነበር። ሆኖም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የዕቃዎች ኤክስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም በዚህ ደረጃ መቀጠል ባለመቻሉ፣ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ሳያሳይ እስከ 2007 በጀት ዓመት ድረስ በመዝለቁ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጠው ከፍተኛ የኤክስፖርት ግብ ላይ መድረስ አልተቻለም።
በዚህ ዘርፍ ለታየው ደካማ አፈፃፀም አንዱ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ መቀነስ ነበር። ዋነኛው ምክንያት ግን አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በዓይነት፣ በብዛት እና በጥራት የማቅረብ አቅም በሚፈለገው ደረጃ አለመዳበሩ ነበር። የግብርና ምርታማነት እያደገ ቢመጣም እስከ እቅዱ የትግበራ ጊዜ ማብቂያ ድረስ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሠማራት ያለው ፍላጎት መሻሻል ያሳየ ቢሆንም፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማጠናከር የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን ወይም አዳዲስ ምርቶችን በዓይነትና በብዛት በማምረት በስፋት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ሳይቻል ቀርቷል።
በዕቅዱ ለተቀመጠው የኢኮኖሚ ዕድገት ግብ መሳካት አንዱና ወሳኝ ጉዳይ የኢንቨስትመንት መስፋፋት ነው። ዕቅዱ ሰፋፊ ግቦችን ዕውን ለማድረግ የታለመ ከመሆኑ አንፃር የሚያስፈልገው የኢንቨስትመንት ፍላጎትና የፋይናንስ መጠን ከፍተኛ ነበር። ከዚህ አንፃር የአገር ውስጥ ፋይናንስ አቅም እንዲጠናከር ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል። የውጭ ፋይናንስ ዕድልንም አቅም በፈቀደ ሁሉ ለመጠቀም ተሞክሯል። በተለይም ዜጎች መቆጠብ እንዲችሉ የፋይናንስ ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረግና የተለያዩ የቁጠባ መሳሪያዎች ሥራ ላይ እንዲውሉና ዜጎችም በቁጠባ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት አገራዊ ቁጠባ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ረድቷል። በዚህም ምክንያት ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ፍጥነት ተስፋፍቷል። በ2006 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንትና የአገር ውስጥ ቁጠባ ምጣኔዎች በቅደም ተከተል 40 ነጥብ 3 በመቶ እና 22 ነጥብ 5 በመቶ በመድረስ በዕቅዱ ከተያዘው ግብ በላይ አፈፃፀም እንዲያሳዩ ማድረግ ተችሏል።
በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ የመጀመሪያ ሁለት ዓመታት የዋጋ ንረት የዕቅዱ ፈታኝ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ሆኖም መንግስት ጥብቅ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የዋጋ ዕድገት በአንድ አሃዝ እንዲወሰን ማድረግ ተችሏል። ለዘለቄታው የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ለማድረግ፤ በተለይም የምግብ ዋጋ ተረጋግቶ እንዲቀጥል የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ኢንቨሰትመንትን ማስፋፋትና የአገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ተሰምሮበታል።
አሁን 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በትግበራ ላይ ይገኛል። ባለፈው ዓመት በድርቅ ምክንያት የታሰበው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ባይቻልም፣ ፈጣን ሊባል የሚችል የ8 በመቶ እድገት ተመዝግቧል። የ2008 ዓ.ም መኸር ዝናብ በመስተካከሉና አርሶ አደሩ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀሙ የዘንድሮ የግብርና ምርት 12 በመቶ ገደማ ያድጋል ተብሎ ተገምቷል። ከዚህ አንጻር እድገቱ ወደባለሁለት አሃዝ ደረጃው ሊመለስ ይችላል።
በአጠቃላይ፤ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የታየውን ድክመት በመገመገም ለማስተካከል፣ እንዲሁም አዳዲስ እቅዶችን ይዞ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት ህዝቡን ከድህነት አረንቋ መንጭቆ አውጥቶ ወደብልጽግና ለማሸጋጋር በመተግበር ላይ ያለው እቅድ ይሳካል የሚል ግምት አለ። በእቅዱ ስኬት ልክ ድህነት ወደኋላ ይቀራል። ድህነት ወደኋላ በቀረው ልክ የብልጽግና መሰላል ላይ መረማመድ ይጀመራል። እናም ድህነትን በመጣል ወደብልጽግና የሚደረገው ጉዞ በተጨባጭ ተስፋ ሰጪ ነው።