የዓምናውን የሚፋጅ የህዝብ ቁጣ ማስታወስ ብልህነት ነው

ባለፈው ዓመት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች፣ በኋላም በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች አፈትልኮ ወጥቶ ሲንጠን የከረመው፣ ሃገሪቱን ለከፋ አደጋ ያጋልጣል የሚል ስጋት በብዙዎቻችን ዘንድ አሳድሮ የነበረው ሁከት ዘንድሮ ወደሰገባው ገብቷል። ታዲያ ይህ ሁከት ወደሰገባው የገባው እንደዋዛ አልነበረም። የበርካታ ዜጎቻችንን ህየወት ቀጥፏል፤ አካል አጉድሏል፤ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ንብረት አውድሟል፤ የኢኖሚያና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል። ከሁሉም በላይ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሳቸውን በጥልቀት እንዲፈትሹ አስገድዷል። መንግስትና ገዢው ፓርቲ የመልካም አስተዳደር መጓደልና በኪራይ ሰብሳቢነት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛነፍ የስርአቱ አደጋዎች ናቸው እያሉ ሲናገሩ፣ ነገሩ ወደልባቸው ሳይገባ እንደበቀቀን የደግሙት የነበሩ የድርጅቱ አባላት እነዚህ ችግሮች ምን ያህል የስርአቱ አደጋ እንደሆኑ እንዲገነዘቡም አድርጓል፤ አስደንግጧቸዋል። 
እናም መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ለሁከቱ መፈጠር ምክንያት የሆነው የህዝብ ቅሬታ መንስኤ በራሳቸው ውስጥ ያለ ችግር መሆኑን ተገንዝበው ራሳቸውን በጥልቀት ለመፈተሽና በጥልቀት ለማደስ ወስነው ተፍ ተፍ ማለት ከጀመሩ መንፈቅ ሊሞላ ነው። ይህን ተከትሎ በጥልቀት መታደስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ህዝብን የማገልገል ስሜት ማጣት፣ ስልጣንን ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ለራስ ኑሮ ማደላደያነት ማዋል ወዘተ የሚሉት ጉዳዮች እዚያም እዚህም የምንሰማቸው፣ ያሀገር ውስጥ ሚዲያዎች አዝማች ለመሆን በቅተዋል። የፌደራልና ኢህአዴግ የሚያስተዳድራቸው የአራቱ ክለሎች መንግስታት በጥልቀት የመታደሱን ንቅናቄ ተግባራዊ ለማድረግ ከከፍተኛ እሰከ ወረዳ ያሉ አመራሮቻቸውን ገምግመው ግምገማውን ያለፉ ጥቂቶችን ባሉበት ሲያጸኑ የተቀሩትን አሰናብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ በጥለት መታደስንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአመራሮቸ ላይ የተወሰደውን እርምጃ አስመልክተው የመከተለውን በለው ነበር።
በአሁኑ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ያጋጠሙንን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ለይተናል። ከእነዚህም መሃከል ዋናውና በውልም ለይተን የያዝነው የመንግሥትን ሥልጣን የምናይበትን መንገድ ነው። ይህንን በምንፈትሽበት ጊዜ በሌብነትና በሙስና የሚገለጽ የመጨረሻው ደረጃ ብልሹነት አለ። ከዚህም ባሻገር የያዘውን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት መጠቀም ሲገባ ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ ሕይወቱን በመምራት ዙሪያና ምቹ ኑሮ ለመኖር የመሞከር ነገር ተስተውሏል። ባይሰርቅ እንኳ ስርቆት ድረስ የመሄድ አመለካከት ተለይቷል። ከዚህ በመነሳት እጅግ አብዛኛውን አመራር እያጠቃ ያለው ለሥራ ከመትጋትና መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ፣ ባለጉዳይን ያለማስተናገድ፣ ቢሮ ያለመገኘት ወይም ዝግ መሆን፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ ያለመሥራት፣ እንደ ማንኛውም ሲቪል ሠራተኛ 11፡30 ሰዓት ሲሆን ከቢሮ ወጥቶ መሄድ፣ የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛትና የመሳሰሉት ውጤታማ የማያደርጉ ዝንባሌዎች ይታያሉ። ይህ ደግሞ ሥልጣንን ለኅብረተሰብ ጥቅም ብሎ ለወሰነ ፓርቲ የማይገባ ሥነ ምግባር ነው። ስለዚህ በቅርቡ ባደረግነው የአመራር ለውጥና ሽግሽግ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉት ከታች እስከ ላይ በዚህ ችግር ውስጥ ያልገቡትን ነው። አመራሮች የሕዝብ አገልግሎት ውስጥ ሊሳተፉ ይገባል በሚል መርህ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ከአቅም ማነስ ማለትም ከዕውቀት ወይም ከክህሎት ማነስ ጋር ተያይዞ ነው የተቀነሰው። አንድ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ነገር በስርቆት፣ በሌብነት፣ በሙስና ተሳትፎ ማስረጃ የተገኘበት በምንም መልኩ ተጠያቂ ሳይሆን ሊቀር አይችልም። 
የእነዚህ እርምጃዎች ዓላማ ህዝብ ላይ ስር የሰደደ ቅሬታ ፈጥሮ ድንገት እንዲገነፍል፣ ሃገሪቱን ለማፍረስ የሚፈልጉ የውጭ ጠላቶችና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎቻቻው ደግሞ ሃገሪቱን ለማፈረስ የሚያስችል አመቺ አጋጣሚ የፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ተያያዥ ችግሮችን በማስወገድ ቢያንስ በማቃለል የህዝብ እርካታ መፍጠር ነው። በጥልቀት የመታደሱ ግብም ይሄና ይሄ ብቻ ነው። በጥልቀት የመታደስ ጉዳይ ሲነሳ ሁሉም ዜጋ በተለይ መታደሱ የሚመለከታቸው ግለሰቦችና ተቋማት ይህን ማስታወስ አለባቸው። በጥልቀት መታደሱ በራሱ መድረሻ አይደለም። ህዝብን በትክክል በማገልገል ተጠቃሚ ማድረግና ማርካት ወደሚቻልበት ሁኔታ የሚወስድ መነገድ እንጂ።
እንግዲህ በጥልቀት የመታደስ ጉዳይ በዋናነት የአመለካካት ለውጥ ማምጣትን የሚመለከት በመሆኑ ረዘም ያለ ግዜ የሚጠይቅ መሆኑ ባይካድም፣ በአጭር ግዜ በተጨባጭ ሊታዩ የሚችሉና የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸው ግን አይካድም። ይህም በቀዳሚነት አገልግሎት ፍለጋ ወደመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሄዱ ዜጎችን  በአግባቡ ማስተናገድ መቻል ነው። ቢያንስ ሳይንግላቱ ፈጣን አገልገሎት እንዲያገኙ ማድረግ። 
እጅ መንሻ የመጠየቁ ነገር ጸያፍ አመል በቀላሉ ይለቃል ታብሎ አይታሰብም፤ “ሌባ ላመሉ . . .” እንዲሉ። ይህ የአመለካከት ለውጥ የሚጠይቅ በመሆኑ እጅ እጅ የሚያይ በር ላይ ካለ የጥበቃ ሰራተኛና መዝገብ ቤት ሰራተኛ አንስቶ እስከባለሞያና ባለስልጣን ያለን የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ከዚህ አመሉ በቀላሉ ማስጣል ይቻላል የሚል ግምት የለኝም። ከዚህ ጸያፍ አመላቸው ማስጣል ግን ግዴታ ነው። አሁን፤ ዛሬ የህዝብ ማመላለሻ ስምሪት ላይ በተለይ የአዲሰ አበባ የታክሲ ስምሪት ሰራተኞች፣ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ፣ ወዘተ የመሳሳሉ የአገልግሎት የሚሰጥባቸው አካባቢዎች ብትሄዱ እጅ እጃችሁን የሚያዩ ሰራተኞችንና አቀባባይ ደላሎችን ታገኛላችሁ። ይህ ሁኔታ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት አሰጣጡን ማደናቀፉ አይቀሬ ነው። ቢያንስ መንግስት የሾማቸውና በጥልቀት የመታደስ ምንነት የገባቸው ሃላፊዎች ለዚህ አይነት ጸያፍ ድርጊት የተጋለጡ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ማስተካካያ እርምጃ ሊወስዱ የገባል። አዲስ አበባ ውስጥ በየአስር ደቂቃ ልዩነት አንድ ታክሲ ሊደርስ በሚችልበት አኳኋን የስምሪት ምደባ የተካሄደባቸው አካባቢዎች፣ አንድ ታክሲ በአርባ አምስት ደቂቃ ሲደርስ ዝም ብሎ መመልከት ተገቢ አይደለም። ይህን ማስተካከል ይሄ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ግዴታ እንጂ። የስርአቱን ህልውና መጠበቅ መሆኑንም አትዘንጉ። ከመንግስት የተሟላ አገልግሎት ማግኘት ተስኖት ተሰፋ የቆረጠ ህዝብ ሲቆጣ፣ ቁጣው እንደሚፋጅ ባለፈው ዓመት አይታችሁ የለ? ይህን ያስታወሰ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ እግሮችን ችላ አይልም፣ እናም ችላ አትበሉ።
እንግዲህ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማትን ወይም የመንግስት መስሪያ ቤትና ሰራተኞችን የሚመለከት ነው። ሰሞኑን በጥልቀት የመታደሱ ጉዳይ ወደ ፐብሊክ ሰርቪሱ መውረዱን ሰምተናል። ፐብሊክ ሰርቫንቱ ወይም የመንግስተ ሰራተኛው ሰሞኑን በጥልቀት ለመታደስ ውይይት እያካሄደ ይገኛል። ተሃድሶው በስልጠና መልክ ነው የሚሰጠው። 
የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በመንግስት ሰራተኛው ዙሪያ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የመንግስት ሰራተኛው የሚጠበቀውን ያህል የህዝብ አገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል ብለዋል። ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት፣ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስን አለመላበስ እንዲሁም ኃላፊነትን ለግል ጥቅም ማዋል በመንግሥት ሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ በሀገሪቱ በሁሉም የአስተዳደር እርከን ያለው የመንግሥት መዋቅር በአገልጋይነት መንፈስ ማገልገል ቢችል 70 ከመቶ የሚሆነውን ችግር መፍታት ይቻላል ብለዋል።
በሀገሪቱ ብቁ እና ውጤታማ መንግስት ሰራተኛ ለመፍጠር እና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሚረዳ የተሃድሶ ስልጠና ለመስጠት ሰነድ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የሰነዱ የመጀመሪያ ክፍል ባለፉት 25 አመታት መንግስት በሀገሪቱ ለውጥ ለማምጣት የተከተላቸው መስመሮች ባህሪያትና ተልዕኮዎች ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን፣ ሁለተኛው የሰነዱ ክፍል ደግሞ ባለፉት 15 አመታት የተመዘገቡ ለውጦችንና በመንግስት ሰራተኞች በኩል የሚታዩ ጉድለቶችን የሚመለከት መሆኑንም አመልክተዋል። ሰነዱ እያንዳንዱ መንግስት ሰራተኛና ተቋማት ራሳቸውን እንደሚለከቱ የሚያስችሉ ነጥቦች መያዙንና በሚካሄዱ የተሃድሶ ስልጠና መድረኮች በየተቋማቱ የሚታዩ ጉድለቶች በጥልቀት እንደሚነሱ፣ እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛም የራሱን ተጨባጭ ክፍተቶች እንዲያይ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት ሰሞኑን ለመንግስት ሰራተኞች የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ተገልጋዩ ህዝብ በተሃድሶው ማግስት ህግና ደንብን የተከተለ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ይጠብቃል። ይህ እንዲሳካ ደመወዝ የሚከፈላቸው ህዝብን ለማገልገል መሆኑን የዘነጉ ወይም ሃይ የሚላቸው ያጡ የመንግስት ሰራተኞና ሃላፊዎች ባለጉዳዩን እንደአስቸጋሪ እዳ ተመልክተው ከማመናጨቅ ዓመላቸው ጸድተው ምን ልታዘዝ? ብለው ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። አይናቸው የባለጉዳይን እጅ ከመመልከት ማደብ አለበት። ሃላፊዎችም ባለጉዳይ ከፊታቸው ዞር እንዲል ያህለ ብቻ በቀጠሮ ማሰናበቱን፣ በተቀጠረበት ቀን ሲመጣም ፣ ባለጉዳዩን እንደአዲስ ተመክተው “ያንተ ጉዳይ ደግሞ ምንድነው?” በለው በሌላ ቀጠሮ እያሰናበቱ የትየለሌ ቀጠሮ መስጠቱን ይተዉ። ጫን ያለ ጉዳይ ያለውን ተገልጋይ በደላላ አማካኝነት በጅ እንዲል ማድረጉም ጸያፍ መሆኑን ያስታውሱ። ይህ ካልሆነ የተሃድሶው ስልጠና ትርጉም አልባ የአዳራሽ ጫጫታ ከመሆን አይለይም። የዓምናውን የሚፋጅ የህዝብ ቁጣም ማስታወስ ብልህነት ነው፤ በተለይ ተሿሚዎች።