ድርቅን የተመለከተ ዜና ላለመስማት•••

 

 

 

ባለፈው አመት ሁለንተናዊ በነበረው የልማት እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው ካለፉት ጉዳዮች መካከል ድርቅ ዋነኛው የነበረ መሆኑ ይታወቃል።ይህ አደጋም ቀድሞ ከነበሩት ቢያንስ በየ10 ዓመታቱ ከገጠሙን ሁሉ የከፋ የነበረ ቢሆንም በአንጻሩ ከቀደሙት በተለየ በራሳችን አቅም ልንቋቋመው ችለናል። ያም ሆኖ ግን፤ የአለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ዛሬም ጫናውን እንዳሳረፈብን ነው። የተሻለ የመኸር ምርት እንደሚሰበሰብ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅትም በርከት ያሉ እርዳታን ተስፋ ያደረጉ ነፍሶች  እንዳሉ ከመንግስት እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የመኸር ሰብል ጉብኝት አዘጋጅቶ ነበር። የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች፤ በትግራይ ክልል ምስራቃዊ እና ደቡባዊ ዞኖች የተመረጡ ቀበሌዎች የጉብኝቱ አካሎች ነበሩ። በዚህ ጉብኝት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች ዛሬም ምጽዋትን የሚሹ ስለመሆናቸው ለጉብኝት አካላቱ የገለጹ ሲሆን፤ የመሬት ጥበትና የመሬቱ ምርታማነት አነስተኛ መሆን ዋና ከተባሉት ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል።

የመሬት ጥበት ሊፈታ የሚችለው በምርታማነት ብቻ ነው። ምርታማነት ደግሞ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና በትጋት፤ ለጎርፍ እና ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ስለምርታማነት እና ትጋት ምሳሌ የሚሆነንን አንዱን እናንሳና ነገሩን እንፈትሽ፤

የድሬዳዋ አስተዳደር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት ለጎርፍ አደጋ የምትጠቃና ዙሪያዋም ለድርቅ ተጋላጭ እንደነበረች ይታወቃል። አሁን በድርቅ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የውኃ እጥረት ለማቃለል በአስተዳደሩ 110 የውኃ ማጠራቀሚያ ኩሬዎች ተቆፍረዋል። ይህም ብቻ አይደለም በመንግሥትና በሕዝብ ተሳትፎ በተከናወነው የተፋሰስ ሥራ ድሬዳዋና አካባቢዋ ከጎርፍ ሥጋት ነፃ ሆነዋል።

በመስተዳድሩና በኅብረተሰቡ በተሰራው የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የጎርፍ አደጋ ሥጋቱን መቀነስ መቻሉ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የነበረውን ዝናብ አጠርና ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢ ምርታማነት ለማሳደግ አስችሏል ።

በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በሰራው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሬታቸው ከመሸርሸርና ከጎርፍ አደጋ ሥጋት ነፃ ወጥቶ የልማት መሰረት መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ እና ከህብረተሰቡ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

የኡርሶ ተራራ በፊት የተራቆተና ባዶ መሬት ነበር። አሁን ግን አርሶ አደሩ እርከን በመስራትና ችግኞችን በመትከል አካባቢውን አረንጓዴ ማልበስ በመቻሉ የመሬቱ ምርታማነት ጨምሯል። በድሬዳዋ አስተዳደር የእርሻና የተፈጥሮ ኃብት ቢሮ  እንደገለጸውም፤ የተፋሰስ ሥራዎች ከመሰራታቸው በፊት ዝቅተኛ ቦታ ላይ የነበሩ የእርሻ ማሳዎች በጎርፍ ይጠፉ ነበር። በጎፍር የሚጠቁ አከባቢዎችን ሥጋት በመቀነስ እንዲለሙ ለማድረግ የእርጥበት ዕቀባ ሥራ ተሰርቷል። የጎርፍ ዋና መነሻ በሆነው የኡርሶ መንደር አካባቢ ብቻ ከ700 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል። ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ የሚዘራው ሰብል እንዳይጎዳ እስከ 1 ሺህ 600 ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ መያዝ የሚችሉ ኩሬዎች በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ድጋፍ ተሰርተዋል።

በትግራይ ደቡባዊ እና ምስራቃዊ ዞኖችም ሆነ በአማራ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የሚጠበቀውም ተመሳሳይ አይነት የተፋሰስ ልማት ስራ እንጂ፤ የመሬት ጥበትን አስታኮ መተኛት ሊሆን አይገባም። ባለችውም ቢሆን ያአንዳች መቆራረጥ በዓመት ሁለቴና ሶስቴ ማምረት ከተቻለ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ምርጥ ዘሮች ሲታከሉበት ዛሬ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ማምረት በሚቻልበት አግባብ የመሬት ጥበትን የጥቃት ሽፋን ማድረግ ተገቢ አይሆንም።

ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ዛሬም ዋናው ችግር የግብርና ሥራው ኋላ-ቀር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ። ይህ ደግሞ  በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ መልኩ ለመቋቋም አያስችልም፡፡

ህዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ በሂደትም የበለፀገ አገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ቢሆንምና መንግስትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ቢገኝም፤ በመንግስት እቅድና ፍላጎት ልክ ዛሬም እየተሰራ አይመስልም። የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂው ያለንን የልማት አቅም ማለትም፤ ሰፊ ጉልበት፣ መሬትና ውሃ እና ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን መዘንጋት የመሬት ጥበትን በምክንያትነት ለማንሳት ይዳርጋል።   

በትግራይ ደቡባዊ እና ምስራቃዊ ዞኖች፤ እንዲሁም በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና ሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ከላይ በተመለከተው አግባብ የመሬት ጥበትን በምክንያትነት ቢያነሱም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተቀመጡ ግቦች አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ መሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመተግበር የግብርንና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚቻል ከመረጋገጡ እውነታ ጋር ይጣረሳል።  

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድም፤ በዕቅድ ዘመኑ መነሻ የነበረውን 3.7 ሚሊዮን ሄክታር በተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሸፈነ ማሳ ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማድረስ ስለመቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ፤ ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር ትጋትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ብቻ ነው። ይኸውም የህብረተሰቡ ሰፊና የተደራጀ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራው በእንስሳት ማድለብ፣ በግና ፍየል በመሞከት፣ ንብ በማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚሊዮን ለሚቀጠሩ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  

በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት ምርታማነቱን የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን ዘላቂነት ያለው የድርቅ መፍትሄ ነው፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡

ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንን የመቀነስና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ አገር እየተገነባ የመጣበት እውነታ ከላይ በተመለከተው አግባብ ቢኖርም፤ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ፤ ይልቁንም ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችንን የሚጨምር ዝግጅትም ከወዲሁ ያስፈልጋል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን በጉልህ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኤሊኖ አየር መዛባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ፤ እንደዚህ አይነቱን ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮች መቋቋም የምንችለው ለአየር ንብረት ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስሮ በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም፤ ብሎም  የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል ድርቅ ዜና የማይሆንበትን እድል ልንፈጥር ይገባል።