በየጊዜው በዓለም ላይ በሚከሰተው የአየር ንብረት መዛባት የተነሳ በተለያዩ አገራት ላይ የሚከሰተው ድርቅ፣ ከፍተኛ የዝናብ መጠን፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የወንዞችና የውቅያኖሶች ከመጠን በላይ ሞልቶ መፍሰስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት ናዳና ከፍተኛ አውሎ ንፋስ የመሳሰሉት በሰው ልጆች ላይ ይህ ቀረው የማይባል አደጋ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ የእኛን አገር በተደጋጋሚ የሚያጠቀው አደጋ ድርቅ ነው፤ ዘንድሮም በተለያዩ አንዳንድ ቦታዎች ተከስቷል፡፡
አምና በድርቅ ከተጎዱት አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች የክረምቱን መዝነብ አጋጣሚና የባለሙያዎችን ምክር በመጠቀም ወደ መልካም ልማት ለውጠውት ለከብቶቻቸው መኖ ማግኘት ችለዋል። ውኃን በጉድጓድ በማጠራቀም የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
በሌሎች ቦታዎች ዘንድሮ ድርቁ ቢከሰትም በኢትዮጵያ ለድርቅ ተጋላጭ ዜጎች እርዳታ የሚውል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትርክ ቶን የእህል ክምችት መኖሩን የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ የድርቅ አደጋው ቢከሰትም ለድርቅ ተጋላጭ ዜጎች የሚቀርበው ድጋፍ እና እርዳታ ያለምንም መቆራረጥ መቀጠሉን፤ ባለፉት ወራት የተወሰኑ አርሶ አደሮች ወደ መደበኛ የማምረት ሥራቸው በመመለሳቸው አሁን ላይ የተረጂዎች ቁጥር ከነበረበት በግማሽ ያህል ዝቅ ማለቱን ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለድርቅ ተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ሳይስተጓጎል እየደረሰ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ለተረጂዎች የሚውል የእህል ክምችት ችግር እንደሌለና እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የሚያገለግል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የእህል ክምችት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የድርቅ ተጎጂዎች ራሳቸውን ችለው ለምምረት ብቁ እስኪሆኑ ድረስ ለእርዳታ ከመደበው 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ በእስካሁን እንቅስቃሴው ሰባት ቢሊዮን ብር ለተረጂዎች እገዛ መዋሉን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
መንግሥት በባለቤትነት የራሱ ጉዳይ ስለሆነ ለድርቅ ተጎጂዎች የሚያደርገው ድጋፍ የላቀውን ሥፋራ ቢይዝም የልማት አጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ በተደረገው ጥናት መሠረት ከተረጂዎች መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ወደ መደበኛ ማምረት ሥራቸው በመመለሳቸው ራሳቸውን ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመኸሩን የምርት ውጤቶች መሠረት በማድረግ ከእርዳታ የሚላቀቁ ተረጂዎችን ለመለየት በብሔራዊ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ቡድን ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
የጥናቱ ውጤቱ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የሚገለጽ ይሆናል። የተረጂዎች ቁጥር እንደሚቀንስም ይጠበቃል፡፡ በቀጣይም ለተረጂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ የእህል ክምችት ችግር እንደማይገጥም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን የነበረው የእለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ በግማሽ ያህል እንደሚቀንስ በዚህም የተረጂዎች ቁጥር ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን መውረዱን የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ በጥናት መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ የ2008 በጀት አፈጻፀሙን የሥራና የ2009 የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ሪፖርትን ለብሄራዊና ለክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት የጋራ ኮሚቴ አቅርቧል። በዚህም ለድርቁ ተጎጂዎች 1 ነጥብ 2 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን እህል መከፋፈሉን፣ ለሥራውው 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ምንም አደጋ አለማድረሱን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መግለጻቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
መንግሥት በቂ ሀብት ገንዘብና የሰው ኃይል መድቦ በመንቀሳቀሱ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ ሌሎችንም መሰል መሠረተ ልማቶችን እንደ አስፈላጊነታቸው ሥራ ላይ በማዋል እርዳታዎችን አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ በድርቁ ለተጎዳውና በፍጥነት እርዳታ ለሚጠብቀው ሕዝብ ለማድረስ በመረባረቡ ድርቁን መቋቋም የተቻለ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ እርዳታውን በማድረስ በኩል የመጋዘኖች እጥረት እንዲሁም የገጠር መንገዶች ከባድ ጭነቶችን ለማስገባት ፈታኝ እንደነበሩም ታውቋል፡፡
128 ባለሙያዎች በተሳተፉበትና በተደረገው ጥናት የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ነው፤ ለምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ወጪዎች 921 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተረጋግጧል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንስሳት ሞተዋል፡፡ የመጠጥ ውኃና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተከሰተባቸው አካባቢዎችም አሉ፡፡ ድርቁ በተከሰተበት አካባቢ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለመራቅ ተገደዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የፌዴራሉ መንግሥት ከክልሎች ጋር በመሆን የህፃናት ምገባ፣ የእንስሳት መኖ እና የውኃ አቅርቦት እንዲሁም ለተጎጂዎች የእርዳታ እህል በመከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለህዝቡ የሚደረገውን ድጋፍ መንግሥት አጠናክሮ እንዲቀጥል ነዋሪዎቹ የጠየቁ መሆኑ በዜና አውታሮች ተዘግቧል፡፡ በዋርዴር ዞን የቡዳ ዴሬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አሚና አውአደም የድርቁን መከሰት ተከትሎ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፤ በቀበሌያቸው ከእህልና እንስሳት መኖ በተጨማሪ የመጠጥ ውኃ በቦቴ እንደሚቀርብላቸው ተናግረዋል፡፡
የጋሻሞ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሙርሲ መሐመድ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ለድርቁ ተጎጂዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ በመሆኑ የሰው ሕይወትን ለመታደግ መቻሉን፤ በድርቁ የተወሰኑ እንስሳት ከመሞታቸው በስተቀር በሰው ህይወት ላይ ያስከተለው የሞት አደጋ እንደሌለ፤ በጋሻሞ ወረዳ በየሣምንቱ 12 ቦቴ ውኃ እንደሚከፋፈልና የእንስሳት መኖ ከሌላ ሥፍራ በማምጣት እየተሰራጨ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለአንድ አባወራ በሣምንት ስምንት እሥር የእንስሳት መኖ ይከፋፈላል። በመጋዘንም የመጠባባቂያ መኖ ተቀምጧል፡፡ በጋሻሞ ወረዳ የለገመገዳ ቀበሌ ነዋሪዎች የሆኑት አቶ አህመድ ፋራህ እና ወይዘሮ ዛራ ሼህ አህመድ በሚያዝያ ወር የሚጠበቀው ዝናብ እስኪመጣ ድርቁ በክልሉ ህዝብ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል መንግሥት እየሰጠ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ በመከላከል የሰውና እንስሳት ሕይወትን ለመታደግ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል። ባለፉት 15 ቀናት ብቻ ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ ሩዝና 50 ሺህ እሥር ሣር ለድርቅ ተጎጂዎች መከፋፈሉን፣ ውኃ ፣ ምግብ፣ የእንስሳት መኖ፣ መድኃኒት በፍጥነት የማቅረብ ተግባሩን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሷል። 40 የህክምና አባላት ያሉት የህክምና ቡድንም በድርቅ በተጠቁ የክልሉ አካባቢዎች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡