በሕዝብ የሚታገዘው ወሣኙ ትግል 

             
                                                     
አገርና ሕዝብን ያናወጠውን ሙስና በመንግሥትና በህዝብ ጠንካራ ትብብር ከሥሩ መንግሎ ለመጣል ወሣኙ ትግል ተጀምሯል፡፡ የእስካሁኑ በአብዛኛው ይነሳ የነበረው አከራካሪ ጉዳይ ማን ማንን ይነካል በሚል የተንሸዋረረ እይታ ሥር ስለነበር ነው የሚለው አስተያየት ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ሰፊና ውስብስብ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ቢዘገይም አሁን የተጀመረው ወሣኝ እርምጃ በጥንቃቄ መራመድ ከቻለ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግባል፡፡ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ ሊሆን አይችልም፡፡

ይታሰሩ ከተባለ አገር ሙሉ ሰው ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ይታሰራል የሚሉ ወገኖች በስላቃቸው መጠቆም የፈለጉት በአብዛኛው በሙስና ውስጥ የተነከረ የተዘፈቀ በአንዱም ሆነ በሌላው ጎኑ የተነካካ የበዛበት ሁኔታ እንዳለ ለማሳየት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡
ጉዳዩ በውል ከታወቀ ዘንዳ ሥራው ያውጣው እያሉ መተው ሳይሆን መታሰርና በህግ መጠየቅ ካለበት በህግ እንዲጠየቅ መሆን አለበት፡፡ 

የሙስና ትንሽና ትልቅ እንዳለው ቢታወቅም ደረጃው ቢለያይም ሌባ…ሌባ ነው፡፡ እንደመጠኑ እንደ ዓይነቱ በህግ መጠየቅ ዳኝነት ማግኘት የተዘረፈውም የህዝብና የመንግሥት ሀብት ለባለቤቶቹ መመለስ አለበት፡፡ ህግ ነጻ ያውጣው፡፡ ህግም ጥፋተኛ ነህ ብሎ ማስረጃውን መርምሮ ይቅጣው፡፡

አዎን ኢሕአዴግ ለተፈጠረው ስህተት ሁሉ የራሴ ችግር ነው ብሎ አምኖ በመቀበል ጥልቅ ተሀድሶ ውስጥ ገብቷል፡፡ በወቅቱ እነዚህን በስሙ ሲነግዱና ህዝቡን ሲያስለቅሱ የኖሩ ዋልጌዎች ቢያርም፣ ቢቀጣና ከኃላፊነት ቢያነሳ ኖሮ ይህቺ "ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም" አይሆኑም ነበር፡፡ በህዝብ ሀብት የከበሩና የደለቡ ፈሪሀ አምላክ የሌላቸው መንግሥትና ህዝብን በዘረፋ ተግባራቸው ሆድና ጀርባ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ ዘርፈውም ነጥቀውም የማይጠግቡ የቀን ጅቦችን ማየት ለህዝቡም ከማስገረም ያለፈ ነው፡፡ ለመንግሥትም ከባድ ነው፡፡
ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት እንደ ፓርቲ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ በየትኛውም ጊዜ ያልነበሩ፣ ያልታዩና ያልተሰሩ ሥራዎችን ከውኗል፡፡ ዛሬም በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በውስጡ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸው ከብረት የጠነከረ ለህዝቤ ነው ህይወቴ እስከ እለተ ሞቴ ብለው የቆሙ ብርቱዎች የመኖራቸውን ያህል ድህነቴን መንግሥትና ኢሕአዴግ የሰጠኝን ወንበር ተጠቅሜ አሸንፈዋለሁ ብለው የተነሱ ማፈሪያዎች ድርጅቱም ሆነ መንግሥት ለአገር የሰሩትን ታላላቅ የተተከሉ የልማትና የእድገት ሥራዎችን ጥላሸት የሚቀባ ድርጊት በመፈፀም ህዝብና መንግሥትን አናክሰዋል፡፡ ለማባላትም ሞክረዋል፡፡

ትልቁ ነጥብ ኢሕአዴግ ቢዘገይም እነዚህን ጉድፎች አሁን በጀመረው መልኩ አበጥሮና አንጠርጥሮ በማውጣት በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ምንም አያጠራጥርም፡፡ የወንጀል ተጠያቂነታቸው በመንግሥትና ህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለግል ጥቅም አሳልፎ በማዋልና በዘረፋ በመክበር ህዝብን በመበደል ነው የሚሆነው፡፡

ኢሕአዴግ የተጀመረውን አገራዊ ጥልቀታዊ ተሀድሶ ያለምንም ጥርጥር የማሳካት አቅሙም ብቃቱም አለው፡፡ ግለሰቦች ዘርፈው ከጣሪያ በላይ ስለከበሩ አይነኬ ናቸውና እነሱ ከተነኩ አገር ይፈርሳል የሚለው ኢ አመክኖአዊ አስተሳሰብ በህዝብም በመንግሥትም ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡

ኢትዮጵያን የመሰለች ታላቅ አገር ሕዝቡ በብዙ ሺህና ሚሊዮኖች ድር የተሳሰረ፣ የተዋለደ፣ የተጋባ፣ አብሮነቱን አጥብቆ አክብሮ የኖረና የሚኖር በመሆኑ ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል በዘራፊዎችና በሙሰኞች አልጠግብ ባይነት በተፈፀመ የህዝብና የመንግሥት ሀብት ዝርፊያ አገር አትፈርስም፡፡ አትበተንም፡፡ ጥንትም ዛሬም የአገሩ ዋና ጠባቂ ዘብ ህዝብና ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ሠራዊቱም፣ ደህንነቱም፣ ፖሊሱም የኢትዮጵያ ልጅ ነው፡፡ የህዝብ ልጅ ነው፡፡ አገሩን ከህዝቡ ጎን ቆሞ ይጠብቃል፡፡

ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች በሥርዓቱ በህግ ጥላ ሥር ውለው ተጠያቂ ይሆናሉ እንጂ በእነሱ ምክንያት የምትፈርስ በአንድ ጀምበር የተገነባች ኮሽ ሲል የምትናድ አገር አይደለችም – ኢትዮጵያ፡፡ መሠረቷ በፀና ድንገተኛ አውሎ ንፋስም ሆነ የውቅያኖስ ማዕበል የማያናውጣት በደደረ አለት ላይ ታንጻ የቆመች አገር ናት – ኢትዮጵያ፡፡ አገርና ህዝብ የበደሉና የዘረፉ ለህግና ፍትህ ማቅረብ ዓይነቱ ቢለያይም ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ መንግሥት ዘግይተሀል የሚል ወቀሳ ሲሰማበት የከረመ ቢሆንም አሁን እርምጃው ተጀምሯል፡፡ ይልቁንም እውነተኛ ዜጎች ሁሉ ከኢሕአዴግ ጎን ቆመው ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ፀንተው በመዋጋት፣ ጥቆማ በመስጠትና ማንኛውንም ዓይነት ትብብር በማድረግ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው ጊዜ  ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡ ሌብነት ጎሣና ብሄርን አይወክልም፡፡

ከሁሉም ብሄርና ብሄረሰብ ውስጥ ግለሰብ ሌቦች፣ ዘራፊዎች፣ ቀጣፊዎችና አታላዮች ታምነው ኃላፊነት ሲሰጣቸው በዝርፊያ ተሰማርተው የመንግሥትንና የህዝብን አደራ የሚበሉ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ግለሰቦችን በሥራቸው ተጠያቂ ማድረግ፣ ህግ ፊት ማቅረብና የህግን ዳኝነት መጠበቁ ነው ዋናው፡፡ በምንም መሥፈርት ቢሽሞነሞን ሌባ… ሌባ ነው፡፡

ፎቅ ቢሰራ፣ ሕንጻ ቢገነባ፣ ዘመናዊ መኪና ቢያዝና ኢንቨስተር ቢሆን በሥርቆትና በማጭበርበር የህዝብና የመንግሥት ሀብት በመዝረፍ ከብሮ የተገኘ ከሆነ ሌባ…ሌባ ነው፡፡ ያውም ሞላጫ ሌባ፡፡ ለዚህ ነው መንግሥትን ከመኮነን ይልቅ መንግሥት ሙሰኛውንና ዘራፊውን ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው ትግል ከጎኑ መቆም፣ መሰለፍና ማጋለጥም እጅግ ወሣኝ የሚሆነው፡፡

አሁን ለመወቃቀስ፣ ለመወነጃጀልና ትናንት ይኼ ለምን ቀድሞ አልተደረገም ወዘተ… በሚል የሚባክነው ጊዜ አላስፈላጊ ነው፡፡ በአንድ ጀምበር አገራዊ ለውጥ አይመጣም፡፡ ለውጥ ራሱን ችሎ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ አብሮ ካልተንቀሳቀሰና ካልሰራ ከሰማየ ሰማያት አይወርድም፡፡ ለውጥ በሣምንት በወር የሚጠበቅም አይደለም፡፡ ጊዜን ትዕግሥትን ይጠይቃል፡፡ ቀስ በቀስ ከትናንቱ የተሻሉ ለውጦችን ማየት ይቻላል፡፡ የተሀድሶው ለውጥ የሚጎለብተው በሂደት ነው፡፡ የአሁኑ የጥልቀታዊው ተሀድሶ ጅምር በእጅጉ የሚበረታታ ሲሆን በህዝቡም ሆነ በመንግሥት በኩል የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ማምጣትን የግድ ይጠይቃል፡፡
ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው በየቦታው ከላይ እስከ ታች በህዝቡም ውስጥ ከከተማ እስከ ክልል የዘረጋው የገነባው የተሳሰረ መረብ መዋቅር አለው፡፡ ይኖረዋልም፡፡ ይህንን አጥርቶ ለመለየትና መረቡን ለመበጣጠስ ከዚያም አልፎ የተመዘበረውን የአገርና የህዝብ ሀብት ለማስመለስ እጅግ ሰፊ ጊዜና ገንዘብ የሰው ኃይልም ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ ብቻ ኢሕአዴግ ዘገየ፣ ተኛ፣ እርምጃ ሊወስድ አልቻለም ማለቱ አይጠቅምም፡፡ የትም አያደርስም፡፡

ለምን ዘገየ ጉዳዩ ምን ያህል ውስብስብ ነው እንዴትስ ነው መኬድ ያለበት የሚለውም ጥያቄ ተገቢ መልስ ይጠይቃል፡፡ በችኮላ፣ በፍጥነት፣ በግርግርና በስሜት የሚሰራ ሥራ አይደለም፡፡ ማስረጃዎች ሊኖሩ ቢችሉም መረጃን በአግባቡ ማጠናከር ይጠይቃል፡፡ እንደ መንግሥት ሲታሰብ ግለሰቦቹ በወንጀል ተጠርጥረው ቢያዙም ወንጀል ነው ብሎ የሚያፀናው ወይም የሚሽረው በተጨባጭ የቀረበለትን ማስረጃ፣ መረጃ፣ ሰነዶችንና የሰው ምስክሮችን መርምሮ ውሣኔ የሚሰጠው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ የህግ የበላይነትም አንዱ የሚረጋገጠው በዚህ ነው፡፡

ያለአግባብ በበቀል ስሜት በመነሳት ንጹኃን እንዳይወነጀሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እንዳይነካም መንግሥት ጥበቃም ጥንቃቄም ያደርጋል፡፡ በስሜት መነዳትና ህግና ሥርዓትን ተከትሎ በመረጃ ተደግፎ መሄድ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰፊ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው የሚታመነው፡፡ መጠየቅ ያለባቸው ይጠየቃሉ፡፡ ለህግና ለፍትህም ይቀርባሉ፡፡ ከአገርና ከህዝብ በላይ የሚሆን ምንም ነገር የለም፡፡ ግለሰቦች ከአገርና ከህግ በላይ አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ በህግ ሥር መጠየቅ ካለባቸው ይጠየቃሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሥራው ላይ ለተሰማሩ ኃላፊዎች ጉዳዩ ብቻውን ተይዞ ከሌላ ሥራ ጋር ሳይቀላቀል የሚሰራ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቶቹ የሙስና ወንጀሎች ብቻ ተሰይመው የሚሰሩ፣ የሚያጣሩ፣ የሚከታተሉ ዓመታትን ብቻ የሚያስቆጥሩ ሳይሆን በቀረበላቸው ተጨባጭ ማስረጃ ተመርኩዘው አጣርተው ፍርድ የሚሰጡ የተለያዩ ልዩ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋምንም ይጠይቃል፡፡ የጠቅላይ ዐቃቤ ህጉን ሥራን ለማቀላጠፍም ይረዳል፡፡
ልዩ ችሎቶቹ በሙስና በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በመልካም አስተዳደርና በፍትህ በደል በደላላውና በአቀባባዩ አማካይነት በአገር፣ በመንግሥትና በህዝብ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ብቻ የሚከታተሉና ውሣኔ የሚሰጡ ሲሆኑ እነዚህን የመሰሉ ልዩ ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በክልል፣ በክፍለ ከተማ፣ በዞን ድረስ አዋቅሮ በየደረጃው ያሉ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎችን እንደ ጥፋታቸው መጠንና ደረጃ ለህግና ለፍትህ በህዝቡ ፊት ማቅረብ ወሣኝ ነው፡፡ ሕዝቡ በየደረጃው የሚሰጠው ተጨባጭ ማስረጃም ቅሬታን ባስነሱበት መጠን ራሱ በሚገኝበት በሚያይበት በሚከታተልበት ግልጽ ችሎት የዳኝነት ውሣኔ ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡

ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጄኔራል ልዩ አማካሪ ኮማንደር ደስታ አስመላሽ በሰጡት መግለጫ የሙስና ወንጀሎችን መመርመር ከተጀመረ በኋላ ከህዝብ፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት 260 የሚሆኑ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል፤ በሙስና ወንጀል ከተጠረጠሩ 260 ግለሰቦች መካከልም 130ዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኮማንደሩ ከታሰሩት ውስጥ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ የሀብት ንብረት እገዳ መጣሉን በስምንት ትላልቅ አክሲዮኖች፣ በአራት ህንጻዎች፣ በ49 ተሽከርካሪዎች፣ በ22 መኖሪያ ቤቶችና በሁለት ፋብሪካዎች ላይ እገዳ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ የተቀሩት  የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የመንግሥት አመራር አካላትና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ ሣምንት መግቢያ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉም ተዘግቧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በደቡብ ክልል በሙስና ወንጀል የተሳተፉ 198 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
በደቡብ ክልል በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት በሙስና ወንጀል በመሳተፋቸው የተጠረጠሩ 198 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር አባይነህ አዴቶ ገልፀዋል። ባለፉት አምስት ወራት ለኮሚሽኑ ከአንድ ሺህ በላይ ጥቆማዎች ከኅብረተሰቡ መቅረባቸውና 198 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል መሳተፋቸው የተረጋገጠባቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በዓይነትና በገንዘብ የተመዘበረ ሦስት ሚሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማስመለስ መቻሉን፤ በክልሉ 11 ሚሊዬን ብር የሚገመት የተመዘበረ ሀብት ለማስመለስ ጥረት መደረጉን ጠቁመው 67 ሺህ 982 ካሬ ሜትር መሬት ወደ መሬት ባንክ መግባቱን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ በሙስና ወንጀል ላይ ለኮሚሽኑ የሚያቀርበው ጥቆማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ 
ይህም ሰሞኑን በመንግሥት በኩል በተጠናከረ ሁኔታ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች በመላው አገሪቱ በመወሰድ ላይ ያለው እርምጃ ከፍተኛ የሕዝብ መነቃቃትን በተጨባጭ የፈጠረ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡