ስለሠላም – የኃይማኖት አባቶች ድርሻ …

 

በኢትዮጵያ ዛሬ ዜጎች የአምልኮ ሥርዓቶቻቸውንና አስተምህሮዎቻቸውን ያለምንም ተጽዕኖ በነጻነት ማከናወን የቻሉበት ወቅት ነው። የኃይማኖት ነጻነት በዚህ መልክ ተረጋግጦ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የሉም ማለት አይቻልም። ኃይማኖትን በሽፋን ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው።  

እነዚህ ቡድኖች የኃይማኖት ለምድ ለብሰው ድብቅ አጀንዳቸውን ለመፈፀም የሚጥሩ ናቸው። በክርስትና ሆነ በእስልምና ኃይማኖት ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዳሉና የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ማጠንጠኛው ደግሞ ፀረ ሠላም አስተሳሰብና ግለኝነት እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ይህ እንቅስቃሴ ከኃይማኖት አክራሪነትና ከሽብርተኝነት ተግባራት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። አክራሪነት ሲባል የሚደናገሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። 

አክራሪነት ማለት አጥባቂነት ማለት አይደለም። አጥባቂነት ለአንድ ኃይማኖት ተከታይ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው የያዘውን እምነት ማጥበቅ ይችላል። ይህ ማለት ኃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚያዘውን ነገር በሙሉ ያለምንም ማመንታት መፈፀም ማለት ነው። አንድ የእስልምና ወይም የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ ኃይማኖቱን አጥብቆ ሊይዝ ይችላል። ኃይማኖቱን አጥብቆ በመያዙ የሚቃወመው ማንም ሰው አይኖርም። መንግሥትም ቢሆን ኃይማኖትህን ለምን አጥብቀህ ያዝክ የሚል ነገር አያመጣበትም። ይህ ሕገ መንግሥቱ የሰጠው መብት ነው። 
ስለዚህ አጥባቂነት ማለት ድንጋጌን ሳያዛንፉና በሌላ ጥቅም ሳይታወሩ አሳምሮ መያዝና መፈፀም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት የሚጎዳ ሌላ አካል አይኖርም። አጥባቂነት የሌላን ወገን እምነትም ሆነ ሌላ ተግባር የሚነካ አይደለም። የሌላውን መብት የሚተላለፍና እኔ ያልኩት ብቻ የሚል አይደለም። ስለዚህ አጥባቂነት በመሠረቱ የማንም ሥጋት አይደለም። የሠላም ፀርም አይደለም። አክራሪነት ማለት ግን ከላይ ከተዘረዘረው የተለየ ነው። አክራሪነት እኔ ከያዝኩት እምነት ሌላ እምነት የለም የሚል ነው። እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ስለሆነ ሁሉም ሰው እኔ የያዝኩትን ይያዝ የሚል አካሄድ አለው። በዚህ ምክንያትም የሌሎች ወገኖች ፍላጎትንና መብትን የሚተላለፍ ይሆናል። ይህ ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። 
የሌሎች መብት ይታፈን የእኔ ብቻ ይከበር የሚል እይታ ለሠላምም የሚበጅ አለመሆኑ አያጠራጥርም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ኃይማኖት አማኞች ባሉባቸው አገራት አክራሪነት ተቀባይነት ስለማይኖረው ወደ አሸባሪነት ይቀየራል። አሸባሪነት ደግሞ እያደፈጡ በሠላማዊ ዜጎችና በህዝብ ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀም ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ኃይል ነው። ይህ ኃይል በመሠረቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ነው። ፀረ ፀላምና መረጋጋት ኃይልም ነው። ዜጎች በሠላም ውለው እንዳይገቡ የሚያደርግ የሁከትና የሥጋት ኃይል ነው።  
በዓለማችን በተለያዩ አገራት እየታየ ያለው የአሸባሪዎች ድርጊትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ በመሠረቱ ፀረ ሕዝብ የሆነ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ተግባር ከኃይማኖት ጋር አስተሳስሮ በኃይማኖት ሽፋን ለመፈፀም የሚደረገው ጥረት ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ገጽታው ነው። አክራሪነትን በጽንሰ ሃሳብ ብቻ ለመረዳት መሞከር ትንሽ ያስቸግር ይሆናል። በተለይ ከአጥባቂነት ጋር ያለውን ልዩነት ለመገንዘብም ሳያስቸግር ይቀራል የሚል እምነት የለኝም። የአክራሪነትና የአጥባቂነት ተግባራትን ማየቱ ግን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ያሳየናል። 
አጥባቂነት ሠላማዊ ተግባር ሲሆን አክራሪነት ግን ፀረ ሠላም ተግባር ነው ማለት ይቻላል። አጥባቂነት በራስ ዙሪያ የታጠረ ሲሆን አክራሪነት ግን የሌሎች ህይወትና መብት የሚነካ እንቅስቃሴ ነው።
አክራሪነትን ይበልጥ ለመገንዘብ ደግሞ በተለያዩ አገራት የተፈፀሙና የበርካታ ንጹኃንን ህይወት የቀጩ ድርጊቶችን ማየት ጠቃሚ ይሆናል። በኬንያ፣ በኡጋንዳ በሶማሊያና በናይጀሪያ የተፈፀሙ የአሸባሪዎች እኩይ ተግባራትን በመመርመር አክራሪነትና ሽብርተኝነት ምን ያህል አስከፊ ገጽታ እንዳላቸው ለመገንዘብ አያዳግትም። እነዚህን ተግባራት የሚያራምዱ ቡድኖች ደግሞ ፀረ ሠላም ፀረ ህዝብ ኃይሎች መሆናቸውን ለመረዳት አያጠራጥርም። 
አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነት ከአንድ ኃይማኖት ወይም ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር የሚያያዝ እሴት እንዳልሆነ በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች የሚያካሂዱ ምሁራን ይገልጻሉ። የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ምንጩ የተለያየ የተዛባ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ባህሪ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ብዝሃነትንና ልዩነትን የማይቀብል ስብዕና ባለቸው ሰዎች ዘንድ የሚከወን እንደሆንም መረጃዎች ያሳያሉ። ሌሎችን በማንነታቸው ለመቀበል ያልተዘጋጁና ማንነታቸውን ጥለው እነሱን እንዲመስሉ የሚሹ ሰዎች ናቸው አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉት። መቻቻል የሚባል ነገር የማይዋጥላቸውና በእነሱ  አስተሳሰብ የበላይነት መረጋገጥ ብቻ የሚያመልኩ ሌላውንም በዚህ ደረጃ የሚለኩ ሰዎችና እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያዘለና ከእኔ ሌላ ላሳር የሚል እምነት የያዙ ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚራምዱት ተግባር ነው አክራሪነት የሚባለው። 

ይህ ደግሞ ሠላምን ለማረጋገጥና የህዝቦችን እኩልነት ለማስፈን የማያስችል ጉዳይ ነው። ወደ አገራችን ተመልሰን ያለውን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን ስንፈትሽ ከላይ ከተተነተነው የተለየ ነገር አይኖረውም። የኢትዮጵያን ሠላም የማይመኙና የያዘችውን የልማት ጎዳና ማደናቀፍ  ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ለሚተጉ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነት የተደፈቀው አስከፊ ሥርዓት  ናፋቂና፣ የከሰረ ፖለቲካቸውን ለማራመድ ሲሉ ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በኃይማኖት ሽፋን በአክራሪነትና በፅንፈኝነት ጎዳና ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴያቸውም በማናቸውም መሥፈርት ቢለካ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንደሆነ ለማየት አያስቸግርም። 

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 11 መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ኃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በማለት በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል፡፡  አክራሪዎች ግን ይህንን መብት ለመሸርሸር የማያደርጉት ነገር የለም። መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለት መንግሥት የህዝቦችን ሠላም አይጠብቅም፣ ሕግንና ደንብን አያስከብርም ማለት አይደለም። የኃይማኖት ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ግን ይህንን ይጠቀማሉ። 
ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ እያደረጉና ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጩ መንግሥት በዝምታ እንዲመለከታቸው ይፈልጋሉ። የአገሪቱን ሠላም ሲያደፈርሱ መንግሥት በታዛቢነት እንዲያይ መፈለጋቸው የመንግሥት ተግባርና ኃላፊነት ጠፍቷቸው ሳይሆን ኅብተሰቡን ለማደናገር ነው። ስለሆነም በየትኛውም መንገድ መንግሥታዊ ኃይማኖት ለመመሥረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ህገ መንግሥታችንን ለመናድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ማናችንም ብንሆን ብዥታ የለንም፡፡ መንግሥታዊ ኃይማኖት በመደንገግ ወይም ኃይማኖታዊ መንግሥት በመፍጠር ሌሎች ኃይማኖቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመደፍጠጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለውና የእኩልነታችን ጠንቅ ከመሆኑም በላይ ኢ ህገ መንግሥታዊ የሆነ አፍራሽ አስተሳሰብ /ተግባር ነው። 

አክራሪው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግሥቱ ካስቀመጠው አኳኋን ውጭ በድርድርም ይሁን ህገ መንግሥቱን በመጣስ መንግሥታዊ ሥልጣን መያዝ እንደማይችል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ኃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የጎዳና ላይ ነውጥ እና ትርምስ መፍጠር በህጋዊ መንገድ ያጡትን ሥልጣን በአቋራጭ በግርግር ለመቆናጠጥ የመቧዘኑ ምስጢር   ኃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነው፡፡ የአክራሪው ኃይል አማኞችም ሆነ ቅዠት የተለያዩ የማደናገሪያ የፈጠራ ወሬዎችን በማዘጋጀት የምዕመኑን አስተሳሰብ በመስለብና በማታለል የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያስችለው አፍራሽ ድርጊት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰንበትበት ብሏል። 

ይህ አክራሪው ኃይል በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎች የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም። ማንኛውን ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም የሚለው ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚተላለፍ ድርጊት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፤ ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም በግል ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተግበር ወይም የመግለፅ መብትንም የማያከብር በመሆኑ በሕዝቦች ዘንድም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።  

የአክራሪነትና የፅንፈኝነት ጫፍ ንፁኃን ዜጎችን አስተሳሰባቸውና አመለካከተቻውን በጫና የመቀየር አካሄዱ ካልተሳካ ወደ ጅምላ ግድያ የሚሸጋገር ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ በማንኛውም መሥፈርት ኃይማኖታዊ ተልዕኮ የሌለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ዜጎችን በመረጡትና በያዙት ኃይማኖት ምክንያት ለማሸማቀቅ መሞከር በኃይል ኃይማኖታቸውንና እምነታቻውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ በአገሪቱ ህግ መሠረት ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ የሚሸከም ኅብረተሰብም በአገሪቱ እንደሌለ መገንዘብ የግድ ይላል። የእኔን ኃይማኖት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም፤ አሊያም ከሐዲ ነህ በማለት ማሸበርም ሆነ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈፀም የእምነት ተቋማትን ማፍረስና መካነ መቃብሮችን ማውደም በእውነት በፀረ ሠላም ኃይሎች የተጠነሰሰ ሴራ በመሆኑና የሌሎችን ነጻነት በማፈን ድብቅ ዓላማን ለማሳከት የተያዘ እንቅስቃሴ እንደሆነ ከማንም የሚደበቅ አይደለም።   

እነዚህ ድርጊቶች የአክራሪነትና ፅንፈኝነት መገለጫዎች ናቸው። በአገራችን እየተፈሠመ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንደዚህ ዓይነቱ ሽብርተኝነት ፀረ ልማት በመሆኑ ይህንን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንጂ ለመንግሥት ብቻ ወይም ለሌላ ወገን የሚተው አይደለም፡፡ የኃይማኖት አክራሪነት በጥቅሉ የዜጎችን የኃይማኖትና እምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ እንደሆነ ለማየት ይቻላል። የኃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስም ሌላው ተግባራቸው ነው። መንግሥታዊ ኃይማኖትን ለመመሥረት የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ በመሆኑ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥርዓቱን ለመቀልበስና ህገ መንግሥቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚጠነጠን ድርጊት እንደሆነ እሙን ነው፡፡

አክራሪው ኃይል እኩይ ተልዕኮውን ለማከናወን ወጣቶችን የዓላማው ማስፈፀሚያ አድርጎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ፈታኝና አስከፊ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ፅንፈኛው ኃይል የተለያዩ በሬ ወለደ ዓይነት የማደናገሪያ አጀንዳዎችንና አማላይ ዘዴዎችን በመጠቀም ወጣቶችን በዓላማ ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም ያለ የሌለ አቅሙ በመጠቀም እየተፍጨረጨረ ነው። 
ለዚህም ሲባል ነው የተለያዩ ኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሰሞኑን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ ሠላምና ዕድገት ለማስመዝገብ የተቻለውን አስተዋፅኦ እንዲያበረከት ጥሪ ያቀረቡት። 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሣት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሥ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ አባቶች ኢትዮጵያን ያስረከቡት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሰሩ እንደሆነና አሁንም አንድነትን፣ ሠላምንና ዕድገትና አስጠብቆ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል ሲሉ ያሳሰቡት። 
ብጹዕነታቸው “ችግሮች ሁሉ ከሠላም በታች ናቸው” የሚለውን ጠንካራ አስተሳሰብ መርህ በማድረግ ሁሉም በአንድነት በኃላፊነት፣ በቅንነትና በተቆርቋሪነት አገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ አስገንዝበዋል። 
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሣት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው መላው ዜጋ ለሕዝቦች ኑሮ መሻሻልና የበለጠ ዕድገትና ብልጽግና ሲባል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል። 
የሰው ልጆች ሁሉ ጥልቅ የሆነ ፍቅር፣ የመግባባትና የመቻቻል ብሎም የመቀራረብ መንፈስ በየዕለታዊ ኑሮ መግለጽና ማሳየት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየዕለቱ ተግባር በታማኝነት ማከናወንና በእውነት መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል። 
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቅሥዩም ኢዶሣ በበኩላቸው እርቅን፣ ሠላምንና በረከትን ለባልንጀሮች፣ አሳደጊ ላጡ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያን፣ ሕሙማንን በመጠየቅ፣ በመርዳትና ለእነርሱ በመፀለይ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ታዲያም የሁሉም ኃይማኖቶች አባቶች ስለሠላም ሲባል ድምፆቻቸውን ከፍ አድርገው ሊያስተምሩ፣ ሊዘምሩና ሊመክሩ ይገባል።