ግብጻዊያን ትብብሩ እንጂ ውዝግቡ አይበጃችሁም!

ጽሁፌን በዳንኤል ካሊናኪ  ዘገባ ጀመርኩ። ዳነኤል ካሊንካ ማነው ለምትሉኝ፤ በኬንያ የሚኖር ለዴይሊ ሚኒተር የሚዘግብ  ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ ነው። የባለፈው ፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ ይህ ጋዜጠኛ  ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብን በተመከከተ “How wily Ethiopia outflanked Egypt and Sudan on the dam” በሚል ርዕስ  ሃሙስ  ታህሳስ 15 ቀን  2016  እንዲህ ስል አስፍሯል፡፡  ካሊናኪ ስለታላቁ የህዳሴ ግድብና የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን ለመገንባት የተከተለውን ብለሃት  አስቀምጧል። እኔ ካሊናኪ ያነሳቸውን ነጥቦች  እንዳለ ላቀርበው አልፈለግኩም። ይሁንና አንዳንድ ነጥቦችን ብቻ ለማንሳት ወደድኩ።

ካሊናኪ ዘገባውን ሲጀምር እንዲህ ይላል ለረጅም ጊዜ በተለይ  በ1980ዎቹ ኢትዮጵያን የምናውቃት  በአንድ በረሃብና  ድህነት  የተጎሳቆለ  የህፃን ልጅ ፖስተር ነበር። ይሁንና መንግስት  ይህን ለመቀየር በግብርናው ላይ ጠንክሮ መስራት በመቻሉ  ሁኔታዎች አሁን ላይ ተለውጠዋል። በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይሯል።
አሁን ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር  እንዲቻል  ርካሽ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ለማስፋፋት በትጋት እየሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት ትላልቅ የሃይል ማመንጫ ግድቦችን በመገንባት ላይ ይገኛል።   ኢትዮጵያ ለዚህ  ግዙፍ ግድብ ግንባታ  ገነዘብ ማሰባሰብ የመረጠችው ከአገር ውስጥ መሆኑ ሁኔታውን ለየት ያደርገዋል።  ሌላው ኢትዮጵያ ግንባታውን ለመጀመር የመረጠችበት ወቅት በአረቦች ጸደይ ወቅት ነው። አረቦች በጎዳና ሰልፍ ተጠምደው ሳሉ  ኢትዮጵያ 6 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግድብ ለመገንባት ይፋ አደረገች። ይህን ግዙፍ ግድብ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በርካታ ኢንጂነሮችና ሌሎች የግንባታ ሰራተኞች አሰማርታ ቁፋሮ አስጀመረች። እነዚህ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን ውጤታማ አድርጓታል። 

በመጨረሻም ግብፅና ሱዳን ተቃውሞአቸውን ቀጠሉ፤ አዲስ የሚገነባው ግድብ በነሱ ላይ ስለሚያመጣባቸው ተፅዕኖ መረጃ ይሰጠን ሲሉ ጠየቁ፤ አልፎ ተርፎም በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የሚያስከትለው ጉዳት እስከሚጠና ድረስ ግንባታው እንዲቆም አበዳሪ ተቋማትም ለፕሮጀክቱ ብድር እንዳይፈቅዱ ወተወቱ። ይሁንና ኢትዮጵያን ማንም ሊያስቆማት የሚችል አልነበረም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው በራሷ አቅም  በመሆኑ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያና የታችኞቹ  የተፋሰሱ አገራት የሚያጨቃጭቃቸው የግድቡ መገንባትና አለመገንባት ሳይሆን የግድቡ የውሃ አሞላል ላይ  ተፅዕኖ መቀነስ ወደሚቻልበት  ሁኔታ ወደሚለው መቀየሩን አስቀምጧል። 

ዳንኤል ካሊናኪ  እንዳለው  ኢትዮዽያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የራሷን የሃይል ፍላጎት አሟልታ ለአካባቢው አገሮች  የምትተርፍ ትሆናለች። ይህ ደግሞ አገሪቱን የቀጠናው የሃይል መዕከል ያደርጋታል።   ሁሉም የአካባቢው አገሮች ይህን   በርካሽ  የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለመሆን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። አሁን ላይ የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት  ግብፅና ሱዳንስ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግባቸውን በማቆም ከኢትዮዽያ የተመቻቸላቸውን ርካሽ የኤሌክትሪከ ሃይል ለመጠቀም ውሳኔ ላይ ደርሰዋል። በመሆኑም ይላል ዘጋቢው ካሊናኪ  የአገሩን  የዩጋንዳ ፖሊሲ አውጪዎችና ፈፃሚዎች በርካታ የልማት ስራዎችን መተግበር እንዴት እንደሚቻል ኢትዮዽያውያኑን ልትጠይቋቸው ይገባል ሲል ምክሩን ለግሷል።

ከዳንኤል ካሊናኪ መልዕክት የምንረዳው ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነችው መንግስት በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲ ሳቢያ ነው።  ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ  በተመለከተ ከመጀመሪያ ጀምሮ  ስታራምድ የቆየችው  “ፍተሃዊ የውሃ ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል” የሚለውን መርህ ነው። አሁንም እየተከተለችው ያለው አቋም ይህ ነው። ኢትዮጵያ አቋሟን  በሁሉም የተፋሰሱ አገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራዋን ሰርታለች። በዚህም ተጨባጭ ድል አገኝታለች።

ኢትዮጵያ የምታራምደው አቋም  በተፋሰሱ በአገራት መካከል አንድነትና መተባበር እንዲዳብር የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር  የወንዙን ዘላቂ ህይወትም አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት  ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ  የአባይ ውሃ ፍሰት ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።  ይህን  የወንዙን የውሃ ፍሰት መዋዠቅ ለመቅረፍና  የወንዙን ዘላቂነት ለማረጋገጥ   በላይኛው የአባይ ተፋሰስ አገራት በተለይ በኢትየጵያ ደጋማ አካባቢዎች በቂ  የአካባቢ ጥበቃ ስራ መከናወን ይኖርበታል። የላይኞቹ የተፋሰስ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲያከናውኑ በወንዙ መጠቀም መቻል ይኖርባቸዋል።

ዳንኤል ካሊናኪ በዘገባው እንዳመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮጀክቱን ይፋ እንዳደረገ፣ ህብረተሰቡ  ለግድቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ከፍተኛ  የማነሳሳት ስራዎችን አካሂዷል።  ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለግድቡ ግንባታ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው። መንግስት የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የሰራው ጠንካራና ትክክለኛ የህዝብ ግንኙነት ስራ  ህብረተሰቡ  ግድቡን  የእኔነት ስሜት እንዲፈጥርበት አድርጓል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። ብዙውን ጊዜ ታዳጊ አገሮች እንዲህ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት በብድርና እርዳታ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ የባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት  እየገነባች ያለችው በውስጥ ገቢዋ በቻ መሆኑ በራሱ ፕሮጀክቱን ልዩ ያደርገዋል።  ግብታታው አሁን ላይ ከ58 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህ ፕሮጀክት ለአካባቢው አገሮች ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ፖለቲካዊ እንድምታውም የጎላ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ የምትገነባው ይህ ግድብ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስተሳስር በመሆኑ ለቀጠናው ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫ እንዲሁም ለአገሪቱም የልማት ብራንድ የሚሆን ነው።  ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን እንዲጎለብት  ያደረገ፣ ህዝቦች በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል የለውጥን መንገድ ያመላከተ ታላቅ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም ይህን ግድብ ለማጠናቀቅ ብድርም ሆነ እርዳታ አገራችን እንደማታገኝ ፕሮጀክቱ ሲጀመር ጀምሮ ይታወቃል። በመሆኑም  ሁላችንም እስካሁን ለፕሮጀክቱ  የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል።  

ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት በማንም አካል ይሁንታ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከውሃው 85 በመቶ የሚሆነውን የምታመነጭ አገር ሆና ሳለ የአባይ ተጠቃሚነቷ ማንም በችሮታ የሚሰጣት አይደለም።  ኢትዮጵያ የወንዙን አብዛኛውን ውሃ ብታመነጭም እንኳን አብዛኛውን ውሃ እኩል ልጠቀም እንኳን አላለችም። ይልቁንም “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” በሁሉም የተፋሰስ አገር ይንገስ የሚል መርህን ተከተለች። ኢትዮጵያ በአካባቢው አገሮች የምትታወቀው በሰላም ማስከበር፣ የቀጠናው አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጥሩ በመስራት፣ በዲፕሎማሲያዊ ስራዋ ነው። የግብጽ መንግስታት በአፍሪካ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ የበላይነት የሚቀበሉት ጉዳይ አይደለም።  

የቀድሞ የግብጽ መንግስታት የአባይን ጉዳይ በተሳሳተ መልኩ በህዝባቸው ውስጥ እንዲሰርጽ በማድረጋቸውና እንዲሁም እስካሁን የግብጽ ሚዲያዎች በሚያራግቡት የተሳሳተ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያራምደውን ፍተሃዊ አቋም ለመቀበል ቸግሯቸዋል። እያንዳንዷን የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ ግብጻዊያን በጥርጣሬ ይመለከቷታል።  ይሁንና ከመጀመሪያው እስካሁን የኢትዮጵያ አቋም አንድና አንድ ነው።  በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ እዚህ ግገባ የሚባል ጫና ሳይፈጠር ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ፕሮጀክት ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ ነች።

የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ቁጠባንም አስተምሯል። ምክንያቱም የመንግስት ሰራተኛው፣ ነጋዴው፣ ተማሪው፣ ህጻን አዛውንቱ በአጠቃላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ቦንድ ያልገዛ ሰው የለም። ይህ ቦንድ ወለድ የሚታሰብለት ነው። በመሆኑም የህዝቦችን የቁጠባ ባህላችንንም እንዲጎለብት አድርጓል፣ በዚህም ከፍተኛ  ገንዘብ መቆጠብ ተችሏል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ ከተሰበሰበው 8 ቢሊዮን ብር ውስጥ  4 ነጥብ 27 ቢሊዮኑ ከተቀጣሪ ሰራተኞች የተገኘ ነው። ይህ ትልቅ አስተዋጽዖ ነው። የመንግስት ሰራተኛውም ይህን ያህል ቁጠባ ባለፉት ስድስት ዓመታት በቦንድ ግዥ ብቻ ማጠራቀም እንደቻለም ያመላክታል።

ታላቁ የህዳሴ ግድባችን  ከሃይል ማመንጫ ባሻገር በህዝቦች መካከል “የእንችላለን ስሜት”  እንዲፈጠር አድርጓል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለታዳጊ አገራት ትልቅ ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ፕሮጀክት ነው።  በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመንን ያጎለብታል፣ የወንዙም ዘላቂ ህይወትም ይረጋገጣል። እንግዲህ ይህን በርካታ ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክት ከዳር ማድረስ የጀመርነው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው አገራችንም  አቅም ፈጥራ የዘመናት ቁጭቷን ጠቀም እንደምትችል ማሳያቷ ለሁላችንም በራስ የመተማመን ስሜት ፈጥሯል።