ስለሰላማችን ስንል አዙረን እንመልከት

 

 

በአንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ተነስቶ በነበረው ሁከት በውስጥና በውጭ የሚገኙ ጽንፈኛ ሃይሎች ሴራ ታክሎበት በርካታ ጥፋቶች ካስከተለ በኋላ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅና ከህዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች አደብ ገዝቷል። ኦሮሚያን በተመለከተ ስለሁከቱ ከፊት ይውለበለብ የነበረው ባንዲራ ፊንፊኔን የተመለከተ ሲሆን የአማራው ደግሞ ወልቃይት ነው። የዚህ ተረክ አብይ ጉዳይም ለግጭቱ መነሻ ተብለው የተውለበለቡ ከላይ የተመለከቱ ጉዳዮችን ወደኋላ ተመልሶ በማስታወስ አሁን የደረሰበትን ደረጃና ዘላቂ የሆነውን መፍትሄ የሚዳስስ ነው። ይልቁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጊዜ ገደብ በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአመክንዮ የሚሞግት ነው።

በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች የተካሄዱት የተቃውሞ ሠልፎች  ስናስታውሳቸው ሕዝቡ እንዲወጣ ጥሪ የተደረገው በማኅበራዊ ድረ ገጾች ነው፡፡ እነዚህ  በየማህበራዊ ድረገጾች ቀርበው በርከት ያሉ ዋጋዎችን ያስከፈሉን ጥሪዎችም ሆኑ ቅስቀሳዎች ስሜታዊ እና ዘረኛ  በሆኑ ንግግሮች የታጨቁ እንጂ ክርክር ተደርጐ በነጠረ ሀቅ ላይ የተመሠረቱ  ያልነበሩ መሆኑም ይታወሳል፡፡ የማኅበረሰቦችና የመንግሥት ህልውና በክልል የተወሰነ ቢሆንም፣ ክስተቶችን ድንበር ዘለል ሆኖ ከመጋራት ባለፈ ለውጥንም ለማምጣት ጽንፈኞቹ በዚሁ መስመር ተንቀሳቅሰው የነበረ መሆኑ ደግሞ ሌላኛው እና የአደጋውን ክብደት የሚያጠይቅ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡

የተደራጀ መሪ የሌለው ተቃውሞ መሪ እስኪያገኝ ሊቀጥል የመቻሉ እውነታና በዚያው ልክ የሚያስከፍለው ዋጋ የተወሰደውን የአስቸኳይ ጊዜ የአዋጅ እርምጃ ተገቢ ከማድረጉም በላይ የአዋጁ ይነሳልን ጥያቄም መመዘን ያለበት ከዚሁ አንጻር ነው። ተቃውሞው የታቀደ መጨረሻ እንደሌለው በመገንዘብና የህዝቡን ስጋት ከግምት በመክተት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባሻገር መንግስት በተቃውሞው ግለት ልክ መልስ ሊሰጥ ሞክሮ የነበረ ቢሆን  ከላይ በተመለከተው አግባብ ይዋል ይደር እንጂ አስቀድሞም መልስ የተሰጣቸውን ጥያቄዎች ያነገበ ሃይል የበለጠ ድፍረትና ጉልበት እንዲያገኝ ያስችለው የነበረ መሆኑንም ስለአዋጁ ቀነ ገደብ የይነሳ ጥያቄ ማስታወስ ተገቢ እና ምክንያታዊ ነው ።

ከላይ በተመለከተው አግባብ እና በሌሎችም መመዘኛዎች ከሁከቱ በስተጀርባ የነበሩት አጀንዳዎችና ግለሰቦች የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያላደረጉ መሆናቸው ሲታሰብ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ የሰጠውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በችኮላ የይነሳ ጥያቄ ትርጉም አልባ ከማድረጉም በላይ ከጥያቄው በስተጀርባ ሌላ ሴራ እንዳይኖር የሚያስጠረጥር ነው ።

ሁላችንም የችግሩ አካል መሆናችን አያጠያይቅምና መፍትሔውም የሚገኘው ከሁላችንም መሆኑ ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም፡፡ አንዱ አካል ችግር ፈጣሪ፣ ሌላው አካል ደግሞ መፍትሔ ፈላጊ መሆን የለበትም፡፡ ተቃውሞ ከተባለም ያየናቸው እንቅስቃሴዎች በተደራጀና ኃላፊነት መውሰድ በሚችሉ ኃይሎች የተመሩ ያልነበሩ መሆኑን መዘንጋት አይገባም ፡፡ በአመፅ የሚገለጽ እንቅስቃሴ ደግሞ የሚያመጣውን  መፍትሔ ከግብጽና ሊቢያ ተምረናል፡፡ልክ እንደነሊቢያ ይህኛውም በአብዛኛው ተመርቶ የነበረው በፌስቡክ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነት የሕዝብ እንቅስቃሴ ግቡና መድረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ኅብረተሰቡ በሚገባ አጢኖታልና ብዙም ባያሳስብ ከጥያቄዎቹ ጀርባ ማሽተት ስለሰላማችን ተገቢና የሁሉም ሃላፊነት ይሆናል፡፡ 

ውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መስማማት፣ መፈራረምና አብረው መሥራትን የተመለከቱ ዜናዎች በመፈብረክ ህዝቡን ማወናበዳቸው የተለመደ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አብረው መስራታቸው መብት እና ለሃገራችንም ጠቃሚ መሆኑ አያጠያይቅም። ነገር ግን በኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚጎለብተው እና የሚጠናከረው  ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ፓርቲዎች ብቻ መሆኑንም ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ካሳለፈው ታሪክ አስታውሶ ቆም ብሎ እራሱን ሊፈትሽ ይገባል፡፡በየትኛውም ሃገር እንደሆነውና እየሆነ እንደሚገኘውም በሃገራችንም ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ   እየተደረገ ያለው ትጋት ለውጤት  የሚበቃው  ትግሉን የሚመሩት ፓርቲዎች እዚሁ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ ብቻ  እንደሆነ ማንኛውም የሃገሩን ሰላም የሚሻ ዜጋ ሁሉ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ አሁን እየተደረገ የሚገኘውንም የፓርቲዎች የድርድር ቅድመ ውይይቶች መመዘንም የሚገባን ከዚሁ አንጻር እና የየአጀንዳውን ጀርባ ስለሃገራችን ሰላም በማሽተት ነው።

 

በተለይ በትጥቅ ትግል የሚያምኑና ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተባብረው ለኢትዮጵያ መፍትሔ እናመጣለን የሚሉ ኃይሎች አዳዲስ ችግር ይወልዱ እንደሆነ እንጂ፣ ምንም ዓይነት የተሻለ ለውጥ ሊያመጡ የማይችሉ መሆኑንም ሌላና ፖለቲካዊ አመክንዮ ሳንሻ ለራሱ መሆን ካቃተው እና ስለኛ ከሚዘላብደው የኤርትራ መንግስት መሰረታዊ ባህሪ በመነሳት አጢኖ መንቀሳቀስ  ስለሃገራችን ሰላም ጠቃሚ ይሆናል፡፡   

በሃገር ውስጥ የሚኖሩትንም (የተቃዋሚ እና የገዥው ፓርቲዎችን የድርድር እንቅስቃሴዎችን) ተከትሎ ተቃዋሚዎችን መመዘን የሚገባን ገዥው ፓርቲ ያሳድርብናል የሚሉትን  ተፅዕኖ በብቃት መቋቋም ከመቻላቸው ላይ በመነሳት እንጂ በገዢው ፓርቲ ላይ ነጋ ጠባ ከሚደፈድፉት የገዛ ድክመቶቻቸው ሊሆን  አይገባም፡፡ ያም ሆኖ ግን ስለሃገራችን ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወሳኝ ናቸውና ሕዝቡ  ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መከተል ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቃዋሚ እንዲፈጠር በዚህ የድርድር ጊዜ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ያለበት መሆኑንም ለአፍታ መዘንጋት አይገባም፡፡ ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጣዊ ዴሞክራሲ ኖሯቸው፣ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ሥራ ሠርተው ማደራጀትና ሕዝቡን በዙሪያቸው ማሰባሰብ እንጂ በውሃ ቀጠነ  የቀረበላቸውን የድርድር  መድረክ በቅድመ ሁኔታ አጣቦ ድክመትን ለመሸፈን መጣር የተበላ እቁም መሆኑን ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ከጀርባቸው ለነበረው ሴራ ከፊት የተውለበለቡት እና የህይወትን ጨምሮ የበርካታ ንብረቶችን ዋጋ አስከፍለው ለነበሩት ፊንፊኔና ወልቃይትም ሃገር ወደነበረበት ሲመለስ መላቸው እየተበጃጀ መሆኑን የተመለከቱ መረጃዎች ይፋ ተደርገዋልና መረጋጋት ይበጃል፤ይልቁንም ከየአጀንዳዎቹ በስተጀርባ ማሽተት።

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ልዩ ጥቅሙን በተመለከተም መንግስት ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ  ሕግ በማውጣት ሂደት ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንቱ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በመክፈቻ ንግግራቸው ሲከፍቱ በዚህ ዓመት ሕግ ይወጣለታል ማለታቸውን ተከትሎ “እስከህዳር ይወጣል” ተብሎ ነበረ በሚል ለመንግስት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች ጥያቄዎች በስተጀርባ ስለሰላማችን ነገር ማሽተት ተገቢ ነው። ይህ ሕግ የሚወጣው በሩጫ አይደለም፡፡ የሕጉ የመጀመሪያ ረቂቅቅን መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ ረቂቁን ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትና ባለድርሻዎች ጋር መምከርም ሂደቱና ሳይንሱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው። ስለዚህ የተቀረፀው ረቂቅ ሕግ በአመራር ደረጃ ከታየ በኋላ ባለድርሻዎች እንዲወያዩበት ተደርጎ በመጨረሻም የሕግ አወጣጥ ሒደትን ተከትሎ መፅደቅ ያለበት የመሆኑን ህጋዊነት እና ምክንያታዊነት ሰላም ወዳድ የሆነው ዜጋ ሁሉ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ መሆኑና ማንም ሊከራከረው የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑ ነው፡፡  

በአማራ ክልል ተውለብልቦ የነበረውንም በተመሳሳይ ማጤንና የአጀንዳዎቹን ጀርባ ማሽተት ያስፈልጋል። ከማንነት ጋር ተያይዞ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለይ የማንነት ጉዳይ ከወሰን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለውም፡፡ የማንነት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ማንኛውም የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል አካል መጠየቅ ያለበት ራሱ መሆኑን መጀመሪያ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ወክዬህ እጠይቅልሃለሁ የሚል አካል ከመጣ አጀንዳው ሌላ ነው፡፡ መጠየቅ ያለበት ራሱ ሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት የተቀመጡ መሥፈርቶች አሉ፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አካባቢ የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ በዚያው አካባቢ ላለው መስተዳድር አካል ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ በዚያ መሥፈርት ይካሄዳል፡፡ ይህንን የሚገድብ ምንም አይነት ህጋዊ ነገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በመንግስት በኩል ይህንን መብት ለማስፈጸም ግን ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ነው፡፡  

ሽፋን ሆነው ዋጋ ካስከፈሉን የወሰን ጉዳዮች መካከል በትግራይ ወልቃይት ፀገዴና በአማራ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ያሉት ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ይህ የወሰን ጥያቄ ያልተፈታው ውስብስብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ያልተፈታው በአመራሮች ውስጥ ባለ የአመለካከት ችግር  እንደሆነ መንግስት አረጋግጧል፡፡ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት በቅርቡ ባደረጉት  ግምገማ መሠረት ይህ የአመለካከት መዛነፍ ተስተካክሎ ከላይ እስከ ታች እስከ ቀበሌ ድረስ ይህንን የወሰን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስለመፍጠራቸው ይፋ አድርገዋል። በነገራችን ላይ በዚያ አካባቢ ያሉ ሕዝቦች ከማናችንም በላይ የሚተዋወቁ ናቸው፡፡ ወሰናችሁን ራሳችሁ ወስኑ ተብለው በተዉ እንኳ  መወሰን ይችሉ የነበረ መሆኑ አያጠራጥርም ፡፡ ውስብስብ ያደረገው  እና  ሽፋን ሆኖ ዋጋ እንድንከፍል ያደረገን የመንግስት አመራር እጅ በረጅሙ ስለገባበት መሆኑን ስለሰላማችን ማስታወስ  እና ከዚያ ውጭ ያለውን በሚገባ ማሽተት ያስፈልጋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳትን በተመለከተ ሊታይ የሚገባው አንደኛውና የመጀመሪያው ጉዳይ ያገኘነው ሰላምና መረጋጋት መሠረታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሕዝቡን አስተያየት ማግኘት አስፈላጊ መሆኑንም በተመሳሳይ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት ሕዝቡ አስተማማኝ ሰላም ማግኘቱን ማረጋገጥና በስተጀርባ የሚሸት አጀንዳ የሌለ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።የመንግስት ውሳኔም   ይህንኑ መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባዋል ።በእርግጥ  እስካሁን ባለው አፈጻጸም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጠበቀውን ግብ አሳክቷል ብሎ ለመናገር ይቻላል፡፡አዋጁን ለማንሳት ግን ይህ ስኬት ዘላቂ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ስናረጋግጥ በማንኛውም ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ይህ ካልተረጋገጠ ደግሞ እንዲራዘም ማስገደድም የኛው መብት ይሆናል፡፡ በኢኮኖሚያችን ላይ ያመጣው ተፅዕኖ የለም ፤ በዲፕሎማሲያችን ላይም ያመጣው ተፅዕኖ የለም፡፡ ይህ በሆነበት አግባብ መጣደፉ ከጀርባ አሽትተን ላላረጋገጥናቸው አጀንዳዎች መጋለጥ ነው።

ዴሞክራሲን የማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው የማድረግ ጉዳይ ተወስኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንደኛው ከተቃዋሚዎች ጋር የመገናኘት ጉዳይ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል የዴሞክራሲ ግንባታን የሚከታተል ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ማዕከል ዕቅዱን አውጥቷል፡፡ አንደኛው የዕቅዱ አካል ከተቃዋሚዎች ጋር የመደራደርና የመነጋገር ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን እድል ስለሃገር ሰላምና እድገት መጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ የህዝቡ ግዴታ ይሆናል።